የሊግ ካምፓኒ ኃላፊዎችና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከDSTV ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው ቅሬታን ፈጥሯል

👉የሊግ ካምፓኒ ኃላፊዎችና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከDSTV ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው ቅሬታን ፈጥሯል

👉ጨረታው የሚወጣበት ማርች 3ዐ መተላለፍ አለበት

ኢትዮጵያ የሊግ ካምፓኒ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በኢሊሊ ሆቴል በተገኙበት መመሰረቱ ይታወሳል፤የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፌዴሬሽኑ ሞግዚትነት ወጥቶ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም፣ራሱን በተለያዩ ገቢዎች እንዲያጠናክር፣እግር ኳሱንም ያሳድጋል የሚል እምነትን በውስጡ ይዞ የተቋቋመው የሊግ ካምፓኒው በይፋ ከተመሰረተ በኋላ ካምፓኒውን የሚያስተዳድር ስራ አስኪያጅና የራሱ ሂሣብ ሹም ቅጥር ተፈፅሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡
የሊግ ካምፓኒው በይፋ ከተቋቋመ በኋላ የተለያዩ ጨረታዎችን በማውጣት እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንደኛው 16ቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት ውድድር ዋንጫ ተዘዋዋሪ እንዲሆን በማሰብ ዋንጫውና በሊጉ ከ1-3 ደረጃን ይዘው ለሚጨርሱ ቡድኖች የሜዳልያ ሽልማት በተለየ መልኩ ለማዘጋጀት ያወጣው ጨረታ የሚጠቅስ ነው።
ከዚህ ውጪ ደግሞ ከሣምንት በፊት የሊግ ካምፓኒው 16ቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በሜዳና ከሜዳ ውጭ የሚያደርጉትን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የማስተላለፍ መብት (Broadcast) እና የፕሪሚየር ሊጉ ስያሜ ባለቤትነትን (Title Sponsor) የመሆን ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች እንዲሳተፉ የሚጋብዝ የጨረታ ማስታወቂያ በእንግሊዘኛ በጋዜጣ አውጥቷል፡
ፌዴሬሽኑ ያወጣው ይሄንን ጨረታ ተከትሎ ጨዋታን በባለቤትነት የማስተላለፍና የሚሰራጩት(Broadcast) መብትና ከፍተኛ ልምድ አቅም ያላቸው በርካታ ተጫራቾች በጨረታው ለመሣተፍ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ ባለበት ሰዓት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒን በበላይነት የሚመሩት መቶ አለቃ ፍቃድ ማሞና ዶ/ር ከሳቴ ለገሰ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳን አቶ ኢሳያስ ጅራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ከ DSTV ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ መባሉ ከወዲሁ ለከፍተኛ ቅሬታ እየጋበዘ ነው፡፡
በጨረታው ላይ ለመሣተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ካሳዩትና እየተዘጋጁ ያሉ ታላ ላቅ ኩባንያዎች በተለይ ለዝግጅት ክፍላ ችን እንደገለፁት “ፌዴሬሽኑ ጨረታ አው ጥቶ በጨረታው ተሳትፈን ጨረታው የሚከፈትበትን March 30 በጉጉት እየጠበቅን ሳለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ ኃላፊዎች በጨረታው ጠንካራው ተፎካካሪ ይሆናል ብለን ከምንገምተው ተቋም ጋር መወያየቱ ስጋትና ጥርጣሬ በውስጣችን እንዲፈጠር አድርጓል፤የሁለቱ ወገኖች ውይይት አጀንዳው ምን እንደሆነ ባናውቅም ጨረታው ከወጣ በኋላና ጨረታው ከሚከፍትበት ቀን በፊት መገናኘታቸው ሁኔታውን በጥርጣሬ እንድንመለከተው ብቻ ሣይሆን ምን ያህል ነፃ ጨረታ ይሆናል? ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ እያስገደደን ነው” ብለዋል፡፡
“በአሁን ወቅት አለም በኮሮና ቫይረስ ጭንቀት ውስጥ ወድቃ የዓለም ብቻ ሣይሆን የሀገራችን ሊግም ተቋርጦ ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚጀመር በግልፅ ባልታወቀበት ሁኔታ ገና በ2013 ዓ.ም ለሚጀመር ውድድር ከስምንት ወራት የበለጡ ጊዜያት እየቀሩት በዚህ ወቅት መገናኘት ለምን አስፈለገ ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል” ካሉ በሃላ “ውይይቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቢሆን እንኳን ወቅቱ ባለመሆኑ ለጥርጣሬና ለሀሜት የሚዳርግ ሁኔታ እንዲፈጠር ይጋብዛል” በማለት ቅሬታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
ይሄንን ዘገባ ሚዛናዊ ለማድረግና የሊግ ካምፓኒውስ በጉዳዩ ዙሪያ ምን ይላል? የሚለውን ለማውቅ የሊግ ካምፓኒ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ በስልክ ጠይቀናቸው” እስከ አሁን በጉዞአቸው ዙሪያ የቀረበ ሪፖርት የለም፤ከሪፖርቱ ውጪ ጉዞአቸውን በተመለከተ እኔ በግሌ እንደማውቀው የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፊቃደ ማሞና ምክትል ሰብሳቢው ዶ/ር ከሳቴ ለገሰ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዙት የብሮድካስት መብት ሽያጭ ወይም በጨረታው ዙሪያ ውይይት ለማካሄድ ሳይሆን የሊግ ካምፓኒው አዲስ በመሆኑ ሊግ እንዴት ይመራል? ስለ ስትራክቸር፣ ስለ ስልጠናና…ካምፓኒው እንዴት የገንዘብ አቅም መፍጠር ይችላል? በሚለው ዙሪያ የተሻለ የሊግ አደረጃጀት ስላለቸው ከዚያ ልምምድና ተሞክሮ ለመውሰድ ነው እንጂ በጨረታው ዙሪያ ለመነጋገር አልሄዱም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ያወጣው የሊጉን ጨዋታዎች የማስተላለፍ (Broadcast) ና የስያሜ ስፖንሰር(Title Sponsor) ጨረታ የሚከፈተው የፊታችን ማርች 3ዐ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ላይ ከሀገር ውስጥ ይልቅ በርካታ የውጭ ታላላቅ ኩባንያዎች የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትና የጤና ሚኒስቴር ማንኛውም ከውጭ የሚመጣ ሰው ለ14 ቀናት በስካይ ላይትና በግዮን ሆቴሎች በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የሚገደድ በመሆኑ ከውጪ የመጡ ተሳታፊዎች እንዴት በተባለው ቀን በጨረታው ሊሣተፉ ይችላሉ? የሚል ስጋት ያላት ሀትሪክ ካምፓኒው ጨረታው የሚከፈትበት ማርች 3ዐ ከመድረሱ በፊት ከወዲሁ እንዲያስቡበት ትጠቁማለች፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.