የሀድያ ሆሳዕና ተጨዋቾች ቅሬታ ቀጥሏል

የሀድያ ሆሳዕና ተጨዋቾችና አመራሮች ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የፈጠሩት አለመግባባት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የክለቡ ተጨዋቾች የመጋቢት፣ የሚያዚያና የግንቦት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም በማለት ተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ይህ በቀጣይ የክለቡ ጉዞ ላይ አደጋ እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ለሀትሪክ እንደገለፁት “ክለቡ ደመወዝ ሳይከፍል መቆየቱና ቅሬታ መፍጠሩ እውነት ነው ከሰሞኑ ግን ሁሉንም ክፍያ ከፍሎ የቀረው አሁን ያለንበት የሰኔ ወር ብቻ በመሆኑና በጊዜው ስለሚከፈል ልዩነቱ ተፈቷል” ቢሉም ከቡድኑ ተጨዋቾች በተገኘ መረጃ ግን “የመጋቢትና የሚያዚያ ወር ደመወዝ ከፍለውናል የግንቦት ወር ደመወዝ ግን ይቀረናል የክለቡ አመራሮችም የግንቦትና የሰኔ ወር ደመወዝን በዚህ ወር እንደሚከፍሉን ነግረውናል” በማለት ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ በደረጃ ሰንጠረዡ 16ኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም የአዲሱ የሊግ ኮሚቴ ውድድሮችን በመሰረዙ ተጠቃሚ ሆኖ ከመውረድ ስጋት መትረፉ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችንና ባለሙያዎች ማህበር ይፋ ባደረገው የቅርብ ጊዜ መረጃ የተጨዋቾቻቸውን ደመወዝ ሙሉ ከፍለዋል በሚል ካመሰገናቸው አስር ክለቦች መሀል ስድስቱ ክለቦች ማለትም ሀድያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባጅፋር፣ ስሁል ሽረ፣ ወልዋሎ አዲግራት አዳማ ከተማ የሌሉበት መሆኑ ታውቋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport