የሀትሪክ ስፖርት የሳምንቱ ምርጥ 11

ይህ የሀትሪክ ስፖርት የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ የሚደረገው ጨዋታውን ከሚከታተሉ ሪፖርተሮች በምትሰበስበው የተናጠል ነጥብ አሰጣጥ ሲሆን፣ ተጫዋቾችን የሳምንቱ ምርጥ ለማካተት የተጫዋቾች የጨዋታ ብቃት፣ ለግብ የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ማቀበል፣ ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ማድረግ እና በጨዋታው ተፅእኖ መፍጠር ብሎም ተጋጣሚን ማስጨነቅ ለሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ ለመካተት የሚያስፈልጉ ናቸው።

አሰላለፍ  – 3-4-3


ግብ ጠባቂ

ዳንኤል አጃየ (ሰበታ ከተማ)

ይህ ግብ ጠባቂ ምንም እንኳን አንድ ግብ ቢቆጠርበትም በግሉ ያደረገው እንቅስቃሴ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ያካተተው ሲሆን፣ ሁለት ያለቀላቸው ኳሶችንም በማዳን ሰበታ ከተማ ተጨማሪ ግቦች ሳያስተናግድ ከሜዳ እንዲወጣ አስችሎታል።

ተከላካዮች

አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና)

ከመከላከሉ ባሻገር ወደ ፊት ነቅሎ በመውጣት የአማካይ ስፍራ ከማገዙ ባሻገር ወደ ሳጥን ሲያሻግራቸው የነበሩ ኳሶች የወላይታ ድቻን ተከላካዮች ያስጨነቀች ነበረች። ውብሸት አለማየሁ የራሱ ግብ ላይ ያስቆጠራት ግብ አህመድ ረሺድ አመቻችቶ ለመመከት አስቸጋሪ የነበረች ኳስም ትጠቀሳለች።

እዮብ በቃታ (ሀድያ ሆሳዕና)

ሀድያዎች ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ በ15ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ሲያሸንፍ፣ የተገኘችውን ብቸኛዋን የቅጣት ምት አጋጣሚ በሚገባ ተጠቅሞ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ሀድያን የመጀመሪያው ዙር በድል እንዲያጠናቅቅ ከማስቻሉም በላይ የመከላከል መስመሩን በሚገባ ሲመራ ነበር።

መሳይ ጳውሎስ (ሀዋሳ ከተማ)

ተከላካዩ አዝናኝ እና ፈጣን በነበረው እና በርካታ ግቦች በተቆጠሩበት የዚህ ሳምንት ጨዋታ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ሙጂብ ቃሲምን ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን የተቆጣጠረበት መንገድ አስደናቂ ከመሆኑም ባሻር አንድ ለአንድ ሲገናኙ ብሎም ታክል በመውረድ ሲያስጥላቸው የነበሩ ኳሶች የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።


አማካዮች

ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና)

ከአጣማሪው ጋር ድንቅ ብቃቱን በማድረግ በተለይ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የቡድኑን ማጥቃት በይበልጥ ሲያግዝ የነበረ ሲሆን ሀብታሙ ታደሰ እና አቡበከር ናስር ያስቆጠሯቸውን ሁለት ግቦች አመቻችቶ ማቀበልም ችሏል።

ሱራፌል ዳኛቸው(ፋሲል ከተማ)

በተለይ ፋሲል በመጀመሪያው ግማሽ ጫና በመፍጠር ቡድኑ ተጭኖ በመጫወት የግብ እድሎችም እንዲፈጥር ከማድረጉ በተጨማሪ የግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር ጥሩ አለመሆን በንቃት ተመልክቶ ከርቀት አክርሮ አስደናቂ ግብ ሲያስቆጥር በአብዛኛውን ጊዜ ኢላማቸውን የጠበቁ ወደ ግብ በቀጥታ ሲመታቸው የነበሩ ኳሶች ለሀብቴ ከድር አስጨናቂዎች ነበሩ።

ኤልያስ ማሞ(ድሬዳዋ ከተማ)

ከትናንት በስትያ (እሁድ) መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ከተከታታይ ውጤት ቀውስ በኋላ የመጀመሪያውን ዙር በድል ሲዘጉ ምንም እንኳን በጨዋታ ወጣ ያለ ባህርይ ቢታይበትም ድሬዳዋ በማጥቃት ሂደት ላይ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን የግብ አጋጣሚዎች እንዲፈጠር የተመቻቹ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል በመላክ ጫና ከመፍጠራቸው በተጨማሪ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል።

ታፈሰ ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)

ተጫዋቹ ኳስን በመቆጣጠር ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመጣመር ሲያደርጋቸው የነበሩ አስደናቂ እንቅስቃሴዎች እና የወላይታ ድቻን የመሀል ክፍል ሲያስጨንቅ የነበረበት ብቃቱ በዚህ ሳምንት የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።


አጥቂዎች

ራምኬ ሎክ (ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ)

ተጫዋቹ በጨዋታው በተለይም ወልዋሎ በግራ መስመር አጥቅቶ በሚጫወትበት ስአት የተጋጣሚ ቡድን እንዲረበሽ ከማድረጉም በላይ አንድ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያደረገው ሙከራ አግዳሚው መለሰበት እንጂ ቢጫ ለባሾቹ አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበረች። እኒህ ነገሮች ተዳምረው የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።

ጫላ ተሺታ (ወልቂጤ ከተማ)

ወጣቱ የመስመር አጥቂ ከትናንት በስትያ (እሁድ) ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ከሜዳው ውጭ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ከፍተኛ ደርሻ አድርጓል። በጨዋታው ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አህመድ ሁሴን ላስቆጠረው ግብም አመቻችቶ አቀብሏል። ከነዚህ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ወደኋላ ተመልሶ የመከላከል መስመሩን ሲያግዝ የነበረበት መንገድም የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።

መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)

በጨዋታው ወቅት ጎል ከማስቆጠር በላይ የሀዋሳ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚናን መጫወት ችሏል። በተለይም በግራ መስመር በኩል ባመዘነው የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በአንድ ለአንድ የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ፍጥነቱን በመጠቀም ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችል ወደ ኋላ በመመለሰም የአማካይ ክፍሉን ሲያግዝ ታይቷል።


ተጠባባቂዎች

ፓትሪክ ማታሲ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ሳሙኤል ታየ (ሰበታ ከተማ)
ይገዙ ቦጋለ (ሲዳማ ቡና)
አህመድ ሁሴን(ወልቂጤ ከተማ )
ፈርሀን ሰይድ(ድሬዳዋ ከተማ)
ሳምሶን ጥላሁን (ባህርዳር ከተማ)
ተስፋየ አለባቸው (ወላይታ ድቻ)

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team