“ውሳኔውና አላማው ባይገባኝም ከዋሊያዎቹ ውጪ መደረጌን የግድ ተቀብዬዋለው” ሙጂብ ቃሲም /ፋሲል ከነማ/

“ውሳኔውና አላማው ባይገባኝም ከዋሊያዎቹ ውጪ መደረጌን የግድ ተቀብዬዋለው”

 

“መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዋሊያዎቹ አለመመረጤን ሳይቀበለውቀርቶ ቅሬታውን መግለፁ አኩርቶኛል…”

 

“በኮሮና ቫይረስ ለተያዙ በሙሉ ባዝንም ህፃናት ተያዙ ሲባልግን ይበልጥ ልቤ ይደማል”

 

 

 

ፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ኮከብ ግብ አግቢ ቢሆንም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስራክተር አብርሃም መብራቱን ልብ ማሸነፍ አልቻለምና ሀገሩን እንዳያገለግል በምርጫው ተዘሏል እሱ ግን ጨዋነት
በተሞላበት መልኩ “አሰልጣኙ የወሰነውን ውሣኔ በፀጋ እቀበላለሁ” ሲል ይናገራል….. ለሲዳማ ቡና፣ ለሀዋሳ ከተማና ለአዳማ ከተማ ከተጫወተ በኋላ አሁን በፋሲል ከነማ ማሊያ 2ኛ አመቱን ይዟል
ከተከላካይ ወደ ሚፈልገው አጥቂነት የመለሰውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን አመሰግኖ አይጨርስም፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እግር ኳሱ ከቆመ በኋላ ሀዋሳ ከባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር ጊዜውን እያሳለፈ
ይገኛል፡፡ ኮከብ አግቢነቱን እየመራ ያለው የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም፡፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለኮሮና ቫይረስ ጉዳት፣ ስለ አባይ ግድብ፣ ከዋሊያዎቹ ስለመዘለሉ፣ እምነቱን
ጥሎብኝ አላሣፈርኩትም ስለሚለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ቤቱ በመቆየቱ ከባለቤቱ ጋር ተጋጭቶ ይሆን፣ ዋሊያዎቹ ላይ የምጨምረው አቅም አለኝ ስለማለቱ፣ የፋሲል ከነማ ውጤት ለዋጭ ማነው
ስለሚለው፣ አብሮት ቢጫወት ስለሚወደው ተጨዋችና ሌሎች ጉዳዮች ሰፋ ያለ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- አመሰግናለሁ.. ለቃለ ምልልሱ.. እግር ኳስ አልናፈቀህም?
ሙጂብ፡- (ሳቅ) በጣም ነው የናፈቀኝ… በታሪክ አጋጣሚ ይህን መሰል ችግር ያየሁት በኔ እድሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከባድ ጊዜ እያሳለፍን ያለንበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አለም ላይ ብዙ ነገር ቆሟል…
በርካታ ነገሮች ተበላሽተዋል…. ከነዚህ አንዱ እግር ኳስ እንደመሆኑ እኛም ተጎጂ ሆነናል፡፡ እንደ ተጨዋች ረጅም ጊዜ ነው ሣንጫወት የቀረውና ኳስ በጣም እንዲናፍቀን አድርጓል፡፡ ለሳምንት ያህል ከኳስ
መራቅ ደግሞ ይከብዳል፡፡ እንኳን እንደዚህ ሰፊ ጊዜና መቼ ይጀመር በማይታወቅበት ሁኔታ በጣም ደብሮኛል ኳሱ ደግሞ በጣም ናፍቆኛል፡፡
ሀትሪክ፡-የኮሮና ቫይረሱ ፍርሃት ፈጥሮብሃል ወይስ በእውቀት እየተጠነቀክ ነው?
ሙጂብ፡- ኮሮና አለም ላይ ከባድ ችግር እየፈጠረ የሰው ህይወት እየቀሰፈ ይገኛል እንደበሽታ ሃኪሞቹ የሚሉንን ነገር በመስማትና በመጠንቀቅ በእውቀት እየተጠነቀኩ እንጂ ፍርሃት የለብኝም፡፡ አሁን
ያለሁት ሀዋሳ ከቤተሰቤ ጋር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከቤት የመውጣት ልምድም የለኝምና አልተቸገርኩም፡፡ ቤተሰቤን ለመጠበቅ ግዴታም ቤቴ እገኛለሁ፡፡ ከባለቤቴና ልጆቼ ጋር በመሆኔ የተሻለ ስሜት እንዲሰማኝ
አድርጓል፡፡ ከቤት ሳልወጣ እነርሱ ጋር በመሆኔ ብዙም ሳልከፋ እንድቆይ አድርጎኛል ወጣ ሲባል ነው የበሽታው ሙድ የሚጋባውና ከቤተሰቤ ጋር በቤት እያሳለፍኩ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ብዙ ጊዜ ባሏ ቤት አይቀመ ጥም በኮሮናው የተነሣ ቤት በመዋሉ ደጋግማ አየችውና ለካ ባሌ ቀይና ቆንጆ ነው አለች አሉ… አንተስ ይሄ አጋጣሚ አልደረሰብህም?
ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ጨዋታ ላይ እያለን ልምምድ ሰርተን ተጫውተን ስንጨርስ ፊታችን መጠጥ የማለት ባህሪ ነበረው አሁን ግን ቀላ አለና ኪሎዬ ጨምሮ ወፈር አልኩ፡፡ ሚስቴ ታዲያ ስትወፍር ጥሩ
አይደለም የመጀመሪያው መልክና አቋምህ ይሻላል ብላኛለች /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- ድብድብስ አልገጠማችሁም…. ?
ሙጂብ፡-አይ አልገጠመንም አይገጥመንምም፡፡ ገና ወጣት ስለሆን ፍቅራችን የሚጨምርበት በቅርበት የምንተያይበት እድል አግኝተናል፡፡ ርቀቱ የጠፋበት በመሆኑ ደስ የሚል ጊዜ ላይ እንገኛለን በዚህ
ጊዜ ድብድብ እንዴት ይታሰባል?
ሀትሪክ፡-በኮሮና ተያዙ ሲባል ልብህን የነካው የነማን ነው?
ሙጂብ፡-በኮሮና የተያዙት በየትኛውም የእድሜ ክልል ይገኙ ሁሉም የተያዘ ያሳዝናል ተያዙ ሲባል ያገግሙ ወይም ይሙቱ የሚታወቅ ነገር ስለሌለ ያሳዝናል በጣምም ያስደነግጣል..… በግሌ ግን በኮሮና
ቫይረስ ለተያዙ በሙሉ ባዝንም ህፃናት ተያዙ ሲባል ግን ይበልጥ ልቤ ይደማል ምንም አያውቁምኮ… እንዴት ልብ እንደሚያደማ… ለተያዙት በአጠቃላይ ግን አላህ ይርዳቸው ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ፋሲል ከነማና መቐለ 7ዐ እንደርታ ወደ አፍሪካ ተሳትፎ እንዳይጓዙ መታገዳቸውን እንዴት አገኘኸው?

ሙጂብ፡- በጣም ቅር ብሎኛል.. ተከፍቻለሁ…. ውድድሩ ቀጥሎ ዋንጫ በልተን ቢሆን ኖሮ የበለጠ እደሰት ነበር አልሆነም… ጨዋታዎች ተቋርጠውም ቢሆን በአፍሪካ መድረክ ተወካይ መላክ
ነበረበት፡፡ ብዙ ሀገራት ሊጎቻቸውን ቢሰርዙም የሻምፒየንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ ክለቦቻቸውን ግን አሳውቀዋል፡፡ የእነሱን ልምድ ወስደን ተግባራዊ ማድረግ ነበረብን ቀጣዩ አመት ኢትዮጵያን
የሚወክል ክለብ አለመኖሩ ልክ አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ራሱ ትልቅ ኪሳራ ይመስለኛል፡፡ እኛ ደግሞ እየመራን መሆናችን የበለጠ ያናድዳል፡፡
ሀትሪክ፡-የሊጉ መሪ ሆናችሁ ነው የተቋረጠው… ባይቋረጥ ኖሮ ድሉ የኛ ይሆን ነበር የሚል በራስ መተማመን ነበራችሁ?
ሙጂብ፡- አዎ….ጥርጥር አልነበረኝም በጥንከሬ እየተጓዝን ነበር በመጀመሪያው ዙር መርተን ጨርሰን ሁለተኛው ዙርም ላይ እየመራን ቀጠልን በርግጥ ከተከታይ ክለቦች ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት ጠባብ
ቢሆንም ከአምና የተሻለ ልምድ ስለያዝን ጥሩ ውጤት ይመዘገባል ብዬ አምናለሁ… ግብ እያስቆጠርን እያሸነፍን በመጓዛችን ለምን ዋንጫ አንወስድም?
ሀትሪክ፡- ሄደውም ምን ላያመጡ ይሄ ጩኸት ምንድነው የሚሉ ወገኖች አሉ.. የሙጅብ ምላሽስ ምን ይሆን?
ሙጂብ፡- ይሄ እግር ኳስ ነው ነገ ምን እንደሚፈጠር ርግጠኛ መሆን አይቻልም ከዚህ በፊት ወድቃችኋልና አሁንም ትወድቃላችሁ ማለት ስህተት ነው ከነውድቀትም ከትላንት የተሻለ ልምድ አግኝተን
ስለሚሆን አንከስርም የልምድ ማግኘቱ ደሞ አይከፋም ተወደቀም ታለፈም ሀገሪቱ ተወካይ ማግኘቷ የግድ ይመስለኛል አሁን ግን የተወሰነው ልክ አይደለም እንደገና ቢያስቡት ደስ ይለኛል… አምና የነበረን
ተሞክሮ ደስ ይላል በትንሽ ስህተት ነው ከመጀመሪያው ዙር የወደቅነው ማለፍ የምንችለውን ነው ያጣነው….. ዘንድሮ ደግሞ ከትላንት መማር እንችል ነበር ነገር ግን አልሆነም፡፡
ሀትሪክ፡- ሙጅብ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ እየመራ ነው… ከብሔራዊ ቡድኑ ምርጫ ግን ተዘለለ.. ምን ይመስላል ስሜቱ? ውሳኔውንስ ተቀበልከው?
ሙጂብ፡- እኔ ባልቀበለውም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ አለመመረጤን ተቀብሎታል /ሳቅ በሳቅ/ ምን ላመጣ እችላለሁ…? በሰዓቱ ባዝንም ብከፋም እንደ አሰልጣኝ ውሳኔውን ከመቀበል ውጪ
አማራጭ የለኝም ዝም ብያለሁ…. ውሳኔውና አላማው ባይገባኝም ከዋሊያዎቹ ውጪ መደረጌን የግድ ተቀብዬዋለው እርሱ አሰልጣኝ እኔ ተጨዋች ነኝ ለአጨዋወቴ አትሆንም ካለኝ ምን ማድረግ እችላለሁ
ሊያሳምነኝ ግን አይችልም… በዚህ አጋጣሚ የገረመኝ በኔ አለመመረጥ የተነሣው ክርክር እንዲህ የሰፋ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም.. ምናልባት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ይቆጡ ቅር ይላቸው ይሆናል ብዬ
ገምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ አልፎ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዋሊያዎቹ አለመመረጤን ሳይቀበለው ቀርቶ ቅሬታውን መግለፁ አኩርቶኛል…ለኔ ክብር ነው ሕዝቡም ለእግር ኳሱ ያለው ስሜት ትልቅ
መሆኑን ነው የተረዳሁት… ያን በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡


ሀትሪክ፡- ብመረጥ ኖሮ ለዋሊያዎቹ የምጨምረው ነገር ይኖር ነበር ብለህ ታምናለህ?
ሙጂብ፡- በሚገባ ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩኮ… ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ ጠርቶኝም በቂ የመሰለፍ እድል አላገኘሁም….ተከላካይ ሆኜ ተመርጬ እንኳን የተወሰነ ጨዋታ ነው የተጫወትኩት አጥቂ
ከሆንኩኝ በኋላ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ነው የተጫወትኩት.. በአንድ ጨዋታ ደግሞ ተጨዋችን መገምገም ከባድ ይመስለኛል ከዚያ አንፃር የተሻለ ነገር አበርክት ነበር የሚል እምነት ነበረኝ አምናና ዘንድሮ
አንድ አይደለሁም አምና ከተከላካይ ወደ አጥቂ እየመጣሁ ከመሆኔ አንፃር ዘንድሮ ደሞ ቦታውን በደንብ ለምጄ ግብ አስቆጣሪ እንደመሆኔ አምናና ዘንድሮ የተለያየ አቋም ነበረኝ ዘንድሮ ጥሩ አቋም
እንደነበረኝ ግቦቼ ይመሰክራሉ… ብመረጥ የተሻለ ነገር አበርክት ነበር በሚለው ጠንካራ አቋም አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በሙጂብ ህይወት ውስጥ እነማን.. አሰልጥነውት አልፈዋል?
ሙጂብ፡- መንግሥቱ ሳሳሞ/የሲዳማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት/ ከወረዳ ውድድር ላይ አይቶ አመጣኝ በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለው.. ከዚያም ሀዋሳ ከነማ ላይ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ፣ አዳማ
ከተማ ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ ፋሲል ከነማ ላይ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አሰልጥነውኛል፡፡
ሀትሪክ፡-በኔ ህይወት ላይ ትልቅ ሚና ተጫውቷል የምትለው አሰልጣኝ ማነው?
ሙጂብ፡- ከሁሉም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይበልጥብኛል ማንም አሰልጣኝ የውበቱን ያህል ኃላፊነት አይወስድም በርግጥ የምወደው ቦታ አጥቂ ቢሆንም ከተከላካይነት ወደ አጥቂ ማምጣት ከባድ ነው
ውበቱ ግን አልፈራም ስላመነኝም ደስ ብሎኛል ስላላሳፈርኩትም ኮርቻለሁ፡፡ ተከላካይ ሳለሁ ጠርቶ አጥቂ አድርጎኝ አቅጣጫዬን የለወጠ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ወደ ኋላ ከወሰደኝ ቦታ ወደ ፊት አምጥቶ
አጥቂ ያደረገኝ አሰልጣኝ ውበቱ የቅድሚያ ምስጋናዬ ይገባዋል፡፡ በእርግጥ ያሰለጠኑኝን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ውበቱ አቅምህን አይቶ በድፍረት ከተከላካይነት ምርጥ አጥቂ ሲያደርግህ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም ግን ከኔ አጨዋወት ጋር አይሄድም ሲል አንተን አልመረጠህም… በሁለቱ
አሰልጣኞች መሀል አንተን የማንበብ ልዩነት መፈጠሩን እንዴት አየኸው?
ሙጂብ፡- በጣም ልዩነት አላቸው ግልፅ ነው እኔን የተረዳኝ ውበቱ ነው ደጋግሜ አመሰግነዋለው… ውበቱኮ ተማምኖብኝ በአጥቂነት ያጫወተኝ በኔ ጠንካራ እምነት ስላለው ነው እምነቱን ሳልበላ
ስለተወጣው ደስ ብሎኛል እኔን ከአሰልጣኝ አብርሃም በላይ አሰልጣኝ ውበቱ ተረድቶኛል በዚህም ደግሜ አመሰግናለሁ በጊዜ ሂደት ተከላካይ ሆንኩ እንጂ ተፈጥሯዊ አጥቂ ነኝ የምወደውን ስፍራ ስላገኘሁ
ተደስቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-አሰልጣኝ ታረቀኝ ተከላካይ ሲያደርግህ በፀጋ ተቀበልከው?
ሙጂብ፡- የግድኮ ነው የምትቀበለው.. .አሰልጣኜ የሚለኝን መስማት ነው የምፈልገው… አሠልጣኝ ታረቀኝ ባዘዘኝ ቦታ መጫወቴና ለአሠልጣኙ ተገዢ መሆኔ ይገባኛል…ሙያዊ ስነምግባር በመሆኑ
አልቃወምም፡፡


ሀትሪክ፡- አንተና ዳዊት እስጢፋኖስ ላይ በቦታችሁ ያመነባችሁ ውበቱ አባተ ነው ለብሔራዊ ቡድን እንዲመረጥ እየፀለይክ ነው ማለት ነው?
ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ቢሆን ደስ ይለኛል ቦታውም ይመጥነዋል
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ውጤት ለዋጭ ወይም ልዩነት ፈጣሪ ማነው?
ሙጂብ፡- /ሳቅ/ … ቆየ.. /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆነ ትወደዋለህ?
ሙጂብ፡- በፍፁም አልወደውም.. አይመቸኝም
ሀትሪክ፡- በራስ መተማመኑና እውነታውን በማስቀመጡስ?
ሙጂብ፡- በድፍረቱና የፊት ለፊት ሰው በመሆኑማ ደስ ይለኛል
ሀትሪክ፡- ታዲያ የወደድከው ድፍረቱን ከሆነ አንተስ ለምን ፈራህ?
ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/…
ሀትሪክ፡- እሺ ሁለት ወይም ሶስት ተጨዋቾች ጥራልኝ ጥያቄውን ላቅልልህ?
ሙጂብ፡-ከተከላካይ ያሬድ ባዬ ከአማካይ መስመር ሱራፌል… ከአጥቂ እኔ… (ሳቅ በሳቅ) ቡድናችን ለዋንጫ እንደመጫወቱ አንደኛውን ዙር አልፎ ሁለተኛው በተጀመረበት ሰዓት ሁሉ መሪ ነበር እንደ
ቡድን ጠንካራ ከአምናው የተሻለ ልምድ ይዞ ወደፊት እየተንደረደረ እንዳለ የሚያሳይ ምርጥ አቋሙን አሳይተናል ሊጉ ባይቋረጥ ደግሞ ቀጣይነቱን እናስመሰክር ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ሙጅብ ከማን ጋር ቢጫወት ደስ ይለዋል?
ሙጂብ፡- ለባህርዳር ከነማ እየተጫወተ ያለው ኤፍሬም አለሙ… በይበልጥ ደግሞ ለድሬደዋ ከተማ እየተጫወት ካለው ኤሊያስ ማሞ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል… ከኤፍሬም አለሙ ጋር ተጫውቻለው
ተመችቶኛል ከኤሊያስ ማሞ ጋር ለብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሆኜ ተጫውተናል አጥቂ ሆኜ ባገኘው ግን ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ አመራሮች ግዙልኝ እያልክ ነው?
ሙጂብ፡-/ሳቅ በሳቅ/ ደስ ይለኛል ቢገዛ.. (ሣቅ)
ሀትሪክ፡- አባይ ይገደባል ብለህ ታምናለህ…ግብፅኮ እየጮኸች ነው?
ሙጂብ፡- (ሳቅ) ፖለቲካዊ ልዩነቶች በሠላማዊ መንገድ ቢፈቱ ደስ ይለኛል… ፖለቲካዊ መስመሩን ለፖለትከኞቹ ሰጥቻለሁ… እንደ ሀገር ግን የግድ ይገደባል በዚህ ሙሉ እምነት አለኝ አባይ ይገደባል
እያልኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አባይ ይገደባል.. ቡና ዋንጫ ይበላል.. የሚል ዜማ ይታወቃል.. ሙጂብስ ይቀበለዋል?
ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/ አባይ ይገደባል.. ፋሲል ዋንጫ ይበላል.. (ሳቅ በሳቅ)
ሀትሪክ፡- ፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን እድል አልተገኘም? ወደፊትስ ይታሰባል?
ሙጂብ፡- ብዙ እድሎች አሉኝ ከአላህ ጋር ይሣካል ብዬ አስባለሁ ከዚህ በፊትም እድሉ መጥቶልኝ ለክለቤ ቅድሚያ በመስጠቴ ሳልጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ከክለብ ክለብ ስትዘዋወር ገንዘብ በጉቦ መልክ ተጠይቀህ አታውቅም?
ሙጂብ፡- ማንም ጠይቆኝ አያውቅም… በፍፁም እጠየቃለሁ ብዬም አላምንም እስከአሁንም በችሎታዬ ያመኑብኝ ብቻ ናቸው ያሰፈረሙኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር አባል ነህ?
ሙጂብ፡- አይደለሁም…
ሀትሪክ፡- ለምን?
ሙጂብ፡- አላውቅም…. ምክንያቱ በኔም ይሁን በማህበሩ አባል አልሆንኩም ያናገጋረኝም ሰው የለም፡፡ ማህበር መኖሩ ያዋጣናል… ማህበሩ ቢጠናከርልን እወዳለው በቀጣይ አባል እሆናለሁ ብዬ
አስባለሁ፡፡ ማህበራችን ቢጠናከርልን ክለቦች መብታችን ነው ብለው የሚያደርጉት ነገር ባልተከሰተ ነበር… ማህበሩ ጠንካራ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በርካታ ክለቦችን የጎበኘው የደመወዝ አልከፍልም በሽታ ፋሲል ከነማንስ አልጎበኘውም..?
ሙጂብ፡- በፍፁም የለም… ክለባችን ጋር ይሄ ችግር ተከስቶም አያውቅም… የተወሰኑ ክለቦች 5 ወር 4 ወር ደመወዝ አልከፈሉም የሚሉ ዜናዎችን እየሰማን ነው፤ እኛ ጋር ግን ክፍያውን በስርዓት
እየከፈለን እንገኛለን በዚህም ደስተኛ ነን፡፡ ለርዳታ ተብሎ ከኛ ደመወዝ ተቆርጦ ወገኖች በመረዳታቸውም የቡድኑ አባላት ደስተኛ ናቸው፡፡


ሀትሪክ፡- የውጪ ኳስ ታያለህ?
ሙጂብ፡- አዎ
ሀትሪክ፡- የማን ደጋፊ ነህ?
ሙጂብ፡- ከእንግሊዝ ማን.ዩናይትድ ከስፔን ባርሴሎና
ሀትሪክ፡- ማን.ዩናይትድ ሪያል ማድሪድ አርሴ ባርሴ የሚሉ ብዙ ናቸው አንተጋ ደግሞ የተለየ ሆነ ምንድነው ምክንያቱ?

ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/ የተቀመጠ ህግኮ የለም ሁለቱም አጨዋወትና ውጤታማነታቸው ማርኮኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ከተጨዋቾች ውስጥህን የማረከው ማነው?
ሙጂብ፡- ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነዋ… ለኔ ምርጡ እሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጠንክሮ በመስራት ሙጂብም ጎበዝ ነው አሉ… ለዚህ ነው ሮልዶን የወደድከው?
ሙጂብ፡- /ሳቅ/ ለማመሳሰል ሳይሆን ጠንክሮ ሰርቶ አሸናፊነቱን ማሳየቱ በምሳሌነቱ እንድማረክ አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ያለህበት ደረጃ እደርስበታለሁ ብለህ ያሰብከው ቦታ ነው?
ሙጂብ፡- አዎ የምፈልገውን ህልሜን እየኖርኩ ነው ማለት እችላለሁ /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- ብጫወትለት ደስ ይለኛል የምትለው ክለብ የትኛው ነው?
ሙጂብ፡- ከውጪ ነው?
ሀትሪክ፡- ሀገር ውስጥ ልጫወትለት ይገባል ብለ የምታልመው ክለብ አለ እንዴ? ምነው ከውጪ ነው አልከኝ…?
ሙጂብ፡- /ሳቅ በሳቅ/ እንደገና ረጅም ሳቅ… ኧረ የለም /ሳቅ/ ክለብ እየመረጥኩ አይደለም ውጪ ወጥቶ መጫወት በጣም እፈልጋለሁ፡፡ ዝግጁነትም አለኝ… አሁን ደግሞ ውስጤ የበለጠ ተዘጋጅቷል
ፕሮፌሽናል ሆኖ የመጫወት አቅሙም አለኝ ብዬ አምናለሁ.. እንደሚሳካልኝ ርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ… የምታስተላል ፈው ቃል ካለ?
ሙጂብ፡- ፈጣሪዬን አላህን ማመ ስገን እፈልጋለሁ… ባለቤቴን ኢማንን በጣም አመሰግናለሁ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን እንዲሁም ሌሎች ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ ጓደኞቼን፣ የፋሲል ከነማ አመ
ራሮችና ደጋፊዎችን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

📸 KZG

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport