“ወደ ውጪ ወጥቶ ማሰልጠንና የብሔራዊ ቡድናችንን በሀላፊነት መምራት የወደፊቱ እቅዶቼ ናቸው”አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ /ሲዳማ ቡና/

“ወደ ውጪ ወጥቶ ማሰልጠንና የብሔራዊ ቡድናችንን በሀላፊነት መምራት የወደፊቱ እቅዶቼ ናቸው”

“አዲስ ግደይ ፕሮፌሽናል አዕምሮ ያለው ተጨዋች ነው”
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ /ሲዳማ ቡና/

 

በመሸሻ ወልዴ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠን ካራ ከሆኑት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነውን ሲዳማ ቡናን በአሰ ልጣኝነት የሚመራው ዘርዓይ ሙሉ የእግር ኳስ ውድድራችን በኮቪድ 19 ከተቋረጠ በኋላ የውድድሩ መቋረጥ ስለፈጠረበት ስሜት፤ ስለ አሰልጣኝነቱ፤ የሲዳማ ቡና ወሳኝ ወሳኝ ተጨዋቾች ዘንድሮ የውል ጊዜያቸውን ስለሚጨርሱ እነሱን በክለቡ ለማቆየት እየተሰራ ስላለው ነገርና ሌሎችን ተጨማሪ ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አቅርቦለት ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 የእግር ኳስ ጨዋታዎች በበርካታ ሀገራት ተቋርጠው አሁን ላይ ደግሞ ከእኛ እና ከአንድ አንድ ሀገራት በስተቀር ውድድሮቹ መልሰው መካሄድ ጀምረዋል፤ የሊግ ውድድራችን በመቋረጡ ምን አይነት ስሜት ነው በውስጥህ የተፈጠረብህ? እግር ኳሱ ዳግም እንዲመለስስ ምን የምትለው ነገር አለ?

ዘርዓይ፡- እንደ አንድ አሰልጣኝ ከምትወደው ሙያም ሆነ ከፍተኛ ደስታን ከሚሰጥህ የእግር ኳስ ጨዋታ በእዚህ መልኩ ለወራቶች ከሜዳ መራቅ በጣም ከባድ የሆነ ስሜት ነው የሚፈጠርብህ፤ ምክንያቱም አሁን ላይ ኳሱ ቆሞ እረፍት ካደረግን ወደ አራት ወር ሊሞላን ነው፤ አሁን ደግሞ ሁለት ወሩን ስትጨምረው ወደ ስድስት ወር ይጠጋል፤ እነዚህን ወራቶች ሁሉ አንድ ተጨዋች በቤት ውስጥ ተቀምጦና ወደ ውጪም ሳይወጣ በሚፈልገው መልኩ በሜዳም ሆነ በጂም ደረጃ ልምምዱን መስራት በማይችልበት ሁኔታ በቤቱ ውስጥ ሲቀመጥ በስነ-ልቦናም ሆነ በአካል ደረጃ የሚጎዳበት ሁኔታ አለና የተጨዋቹ በዛ ደረጃ ላይ መገኘት መቻል ለእኛ አሰልጣኞች ነገሮች ሁሉ በጣም ከባድ እና አስቸጋሪም ነው የሚሆንብን፤ እንደ አሰልጣኝ የምታስበው እና ፕላን የምታደርገው ሁሌም ተጨዋችን መሰረት አድርገህ ነው፤ ተጨዋች ከሌለ ደግሞ እግር ኳስ የለም፤ ስለዚህም አሁን ላይ ተጨዋቾችህ ከአጠገብህ ስለሌሉ እና የሰውነት አቋማቸውም ምን እንደሚመስል የምታውቅበት ሁኔታ ስለሌለ ይሄን ስራ፤ ይሄን ስራም እያልክ ፕላን አውጥተህም የምትሰራውም ነገር ስለማይኖር ይሄ መሆን መቻሉ ብዙ ነገሮችንም ስለሚያስተጓጉል በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፤ ወደ ኳሱ አሁን ብንመለስ ራሱ ተጨዋቹን ወደነበረበት እና ወደሚታወቅበት ብቃት ለማምጣት ራሱ ትልቅ ፈተና ነው፤ ስለዚህም ያ ራሱ ጊዜ የሚወስድም ነውና ሌላው ዓለም የሚጠቀመውን ነገር እያደረግን እግር ኳሱን ወደነበረበት መመለስና ስፖርቱን እንደማንኛውም ስራ ማስቀጠል የሚሻል ይመስለኛል፤ እግር ኳሱን ዳግም በመመለሱ ዙሪያም ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋርና ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር በቪዲዬ ኮንፈረንስ እኛ አሰልጣኞች እየተነጋገርን ነው፤ በሌላው ዓለም ላይ እግር ኳሱ ከቆመበት አሁን ተጀምሮ ያለው ጥቅሙ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው እኛም ወደ እግር ኳሱ ከእነሱ ብዙ ነገርን በመማር ዳግም ልንመለስ ይገባል፤ ያለበለዚያ እግር ኳሱ ገና ወደ መስመር እየገባ የነበረም ነውና ያ ለመሆን ካልቻለ ጭራሽ ሊሞትም ይችላል፤ ስለዚህም እኛ አሰልጣኞች እንደዚሁም ተጨዋቾች የእግር ኳሱ ምንም እንኳን አሁን በከባድ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም ጥሩ ጥሩ ሀሳቦችን ሰጥተን እግር ኳሱን እንደሌሎቹ ሀገራት ልንጀምረው ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር በቪዲዬ ኮንፈረንስ አሁን ላይ የምትነጋገሯቸው ዋና ዋና ጉዳዬች ምንድን ናቸው?

ዘርዓይ፡- የመጀመሪያው እና አንደኛው ኳሱን እንዴት አድርገን ወደ ነበረበት ውድድር እንመልሰው በሚለው ጉዳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በቴክኖሎጂ ታግዘን እና ተጠቅመን ስፖርቱን ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳን በመጠኑ ማቆየት ስለምንችል ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዳለብን ነው፤ በእዚህ ኢንስትራክተር አብርሃም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገር ሰዎች ጋር እያገናኘንም እነሱ አሁን ላይ ምን እየሰሩ እንደሆነ እንደዚሁም ደግሞ ምን ለመስራትም እያሰቡ እንደሆነም በመነጋገር የእግር ኳሱን እንዴት መመለስ እንችላለን በሚለው ዙሪያ ነው በመወያየት ላይ ያለነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ያለህ የአዋዋል ሁኔታ ምን ይመስላል? ምንስ እየሰራ ነው?

ዘርዓይ፡- በአሁን ሰዓት ያለኝ የአዋዋል ሁኔታ ጊዜ አጥቼ በፊት ሳልሰራቸው ያለፍካቸውን ስራዎች በመስራት እና መፅሀፎችንም በማንበብ ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ በግቢያችን ውስጥ ጠዋት ጠዋት ልምምድን እሰራለው፤ አብዛኛውን ጊዜዬንም በቤት ውስጥ ስለማሳልፍ የቡድኔን ተጨዋቾችም ባለፉት ሁለት ዓመታት ልምምድ ሳሰራቸው የሚያሳዩ ቪዲዮች ስላሉኝ እነሱን በመመልከትም ስራዎቼን እገመግማለው፤ በቀጣይ ጊዜም ምን መስራት እንዳለብኝም አስባለው፤ በሽታው በእዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ስለሚቀይርብህ የልምምድ ዲዛይን ለውጥ ማድረግ አለብህና ራስህን ከወዲሁ በማዘጋጀት ለተጨዋቾችህ ተራርቀው የሚሰሩበትን የልምምድ ስራዎችንም ታዘጋጃለህ፤ ኢንስትራክተር አብርሃምን ጨምሮ ከአሰልጣኞችም ጋር በመደዋወል ያለህን እውቀትም ሼር ትደራረጋለህ እና በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ራሴንም ለጥሩ አሰልጣኝነት ለማብቃት ጭምር በመስራት ላይ ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 በኋላ ከክለብህ ተጨዋቾች ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድን ነው የሚመስለው?

ዘርዓይ፡- የሊጉ ውድድር ከተቋረጠ በኋላ ከእነሱ ጋር የነበረኝ ግንኙነት አሁን ላይ ወራት አለፈው እንጂ ልምምድን በቴሌግራም አማካኝነት እስከማሰራት እና ከዛም አልፎ ደግሞ የእዚህ ዓመት ውድድር መሰረዙን ባወቅን ሰዓት መጪው ወቅት እረፍት በመሆኑ ያለኝ አማራጭ በግላቸው ምን ምን አይነት ልምምዶችን በቴሌግራም አማካኝነት መስራት እንዳለባቸው በመንገር ነው፤ ሌላው ደግሞ ብዙዎቹ የክለባችን ተጨዋቾችም አሁን ላይ ውላቸውን ስለሚጨርሱም ከእ ነሱ ጋር በክለቡ ሊቆዩ የሚችሉበትንም ነገር በስልክ እየተነጋገርንበትም ነውና እስካ ሁን ያለን ግንኙነት ይሄንን ያህል ነው የሚ መስለው፡፡

ሀትሪክ፡- በሲዳማ ቡና ዘንድሮ ውላ ቸውን የሚጨርሱት ተጨዋቾች ከእናንተ ጋር የሚቀጥሉ ይመስልሃል?

ዘርዓይ፡- አዎን፤ ይቀጥላሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ አለኝ፤ ለዛም ነው ተጨዋቾቹን ከእዚህ ሳምንት በኋላ አሁን ወደሌላ ክለብ እንዳያመሩ በመንገር ጭምር ከክለቡ ጋር በሚቀጥሉበት ጉዳይ ዙሪያ ልናነጋግራቸውም የወሰንነው፤ ይህን ካደረግን በኋላ ደግሞ የሊጉ ውድድር መቼም ይጀመር መች በክለቡ ውስጥ ያሉትን ተጨዋቾች ይዘንና አስፈርመን ፌዴሬሽኑ በእዚህ ጊዜ ውድድሩ ይጀመራል ሲል ከሁለት ወር አስቀድመን እኛ በቴሌግራም አማካኝነት ተጨዋቾቹ ልምምዳቸውን ሰርተው እንዲመጡም የምናደርግበት ሁኔታም አለ፡፡

ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡና ከያዛቸው የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ዘንድሮ ወሳኝ የሚባሉት ተጨዋቾች ናቸው ውላቸውን የሚጨርሱት?

ዘርዓይ፡- አዎን፤ ለዛም ነው የእነዚህ ተጨዋቾች በክለቡ ውስጥ ዳግም መኖር በጣም አስፈላጊ እና የተሰራም ቡድን ስለሆነ እንደዚሁም ዓምናም በአንድ ነጥብ ብልጫም ዋንጫን ያጣና ዘንድሮም በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ያለም ስለሆነ ውላቸውን መጨረሳቸውን ተከትለን ልናስፈርማቸው እየተዘጋጀን የምንገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- በሲዳማ ቡና ውላቸውን ከሚ ጨርሱት ወሳኝ ተጨዋቾች መሀል ምንአልባት አንድአንዶቹ በክለቡ ላይቀጥሉ ቢችሉ ቡድ ናችሁ ይጎዳል?

ዘርዓይ፡- በጣም እንጂ፤ እንደምንጎዳ ምንም ጥርጥር አያስፈልገውም፤ ምክንያቱም የእኛ ቡድን በደንብ ተደርጎ የተሰራ ስለሆነና ከዛ ውጪም የዘንድሮ ውድድር ተሰረዘ እንጂ ካሉን ጨዋታዎች መካከል ወሳኞቹንና ጠንካራዎቹን ግጥሚያዎች በሜዳችን ስለም ናደርግ ዋንጫውን የማንሳት እድሉም ይኖረን ነበርና ለቡድናችን ወሳኝ የሆኑ ተጨዋቾችን ማጣት ይጎዳል፤ እነሱን አጣህ ማለት ደግሞ ቡድንህን እንደ አዲስ መስራትም ነውና አይደለም ሶስትና አራት ተጨዋቾችን አንድ ተጨዋች ማጣት በራሱ ይጎድሃል፤ ለምሳሌ ቡድናችን ዘንድሮ ፈቱዲንን በማጣቱ ትንሽ ዋጋ ከፍለናል፤ ስለዚህም ቡድናችን በእዚህ የዝውውር መስኮት አሉ የሚባሉትን ተጨዋቾች ላለማጣት አስፈላጊ የሚባሉትን ጥቅማጥቅሞችም ተጨዋቹ በሚፈልገው መልኩም ለመስጠት ተዘጋጅቷል፤ በእዚህ ዙሪያም ተጨዋቾቹን አናግረናቸው ቡድኑን እንደማይለቁና በመተማመኑም ላይ ጥሩ ምላሽ እየሰጡም ስለሆነ ምንም አይነት ስጋትም የለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት አሳለፍክ፤ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት ስለ ልዩነቱ ምን ትላለህ?

ዘርዓይ፡- በሁለቱ ውስጥ ስታሳልፍ በጣም ነው ልዩነት ያለው፤ ተጨዋች ሆነህ ስታሳልፍ ከአንተ የሚጠበቁብህን ሁሉ ነገርን ታደርጋለህ፤ ራስህንም በመጠበቅ ሰውነትህ በቃ እስኪልህ ድረስ ለረጅም ዓመታትም ስለመጫወት ታስባለህ፤ በተለይ ደግሞ እኔ ለቡድኔ ሲዳማ ቡና ስጫወት ካፒቴን ሆኜ ያሳለፍኩበት እና የተጫወትኩበት ጊዜም ስለነበር የአምበልነት ስራም ደግሞ የቡድንህ ተጨዋቾችን ማስተባበር ጭምርም ስለሆነ ይሄን ተጨዋች ሆነህ የምታሳልፈው ነው፤ ወደ አሰልጣኝነት ስትመጣ ደግሞ አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው፤ ትልቅ ሀላፊነትንም ነው የምትሸከመው፤ የእኛ ቡድን ደግሞ ብዙ ደጋፊ ያለውና የህዝብም ክለብ ስለሆነ ውጤትን በሜዳም ከሜዳ ውጪም ወጥተህ ስትጫወት ከአንተ ይፈልጋልና በእዛ ውስጥ ሆነህ ሁሉ የምትሰራው ስራ ነው፤ ሌላው 30 የሚደርሱ የተጨዋቾችህን ባህሪህ እና አመጋገባቸውንም አውቀህም ለብቻህ የምትሰራውም ስራ ነውና ይሄ ከበድ ይላል፤ በውጪም ዓለም የአንድ ቡድን አሰልጣኞች ብዙ ናቸው፤ በጋራ በሚሰሩት ስራም ነው ወደውጤታማነትም የሚሄዱት እኛ ሀገር ላይ ግን አንድ ቡድን ምንአልባት ከረዳቱ ጋርና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ጋር የምትሰራበት ሁኔታ ቢኖርም ለሚመጣው ነገር ሁሉ ግን ጫናው የሚያርፈው በዋና ኮቹ ላይ ስለሆነ የአሰልጣኝነት ህይወት ሲፈተሽ ከተጨዋችነት አንፃር በጣም ከባድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ስለ ቤተሰቦችህ ምን ትላለህ?

ዘርዓይ፡- በእነሱ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ትዳር መስርቼም የሁለት ሴት ልጆች አባት ለመሆን ችያለው፤ ባለቤቴ እየሩሳሌም በለጠ ስትባል፤ የልጆቼ ስም ደግሞ ፊርቶና ዘርዓይ /አራት ዓመት/ እና ላሊ ዘርዓይ /ሁለት ዓመት/ ይባላሉ፤ ባለቤቴን ጨምሮ እነሱን ከዚህ በፊት ለእዚህን ያህል ጊዜ አግኝቻቸው አላውቅም ነበር፤ አሁን ላይ ግን ከእነሱ ጋር ሆኜ ነው ወቅቱን እያሳለፍኩ የም ገኘው፤ ከዚህ በፊት ግን ተጨዋች እና አሰልጣኝ ስትሆን ለቤተሰቦችህ ሰፊ ጊዜን ሳትሰጥ በስራ ላይ ነበር የምታሳልፈው፤ በበዓል ወቅት እንኳን አታገኛቸውም፤ አሰልጣኝ ስትሆን ራሱ በክረምቱ የእረፍት ወቅት ተጨዋቾችን ለማስፈረም በየቦታው ስለምትዞር ያኔ ጊዜ በማጣት እነሱን ብዙም አታገኝም ነበር፤ ስለዚህም አሁን ነው ከባለቤቴ ጋርም ሆነ ከልጆቼ ጋር ስውል የቤተሰብ ጣህሙን በደንብ እያወቅኩት ያለሁትና በእዚህ መልኩ በሰፊው እነሱን በማግኘቴ በሽታውን ጨምሮ ብዙ ነገሮችን እንድረሳም ስላደረገኝ በእዚህ በጣም ደስተኛም ነኝ፤ በእዚህ አጋጣሚም የአሁን ሰዓት ላይ በቤት በሆንኩበት እና ኮቪድ 19ንም ከእነ ቤተሰቦቼ ጭምር ሆኜ ከፍተኛ ጥንቃቄን በማድረግ እያሳለፍንበት ባለው ሁኔታ ለእኔ በብዙ ነገሮች እና ለሙያዬም ቅርብ ስለሆነች ከፍተኛ እገዛን የምታደርግልኝ ባለቤት አለችኝና ለእሷ እንደዚሁም ደግሞ ለእኔ ቤተሰቦች ከዛ በተጨማሪም ለእሷ ዘመዶች ጭምር ሁሉም ከጎኔ ሆነው ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እያደረጉልኝ ነውና በአጠቃላይ አመሰግናቸዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከሲዳማ ቡና ተጨዋቾች መካከል አሰልጥነኸው ከፍተኛ መሻሻል ያየህበት ተጨዋች ማንን ነው?

ዘርዓይ፡- ብዙ ተጨዋቾች አሉ፤ ከእነዛም መካከል ዳዊት ተፈራ /ኦዚል/፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና አበባ የው ዩሃንስ የሚጠቀሱ ናቸው፤ ከምክትል አሰልጣኝነት ዘመኔ ጀምሮ ደግሞ ተመልክቼው እና በኋላም ላይ አሰ ልጥኜው ሌላ ከፍተኛ ለውጥ ያየሁበት ተጨዋች ቢኖር ደግሞ የእውነት ነው የምልህ አዲስ ግደይ ነው፤ አዲስ ሁሌም አቋሙን እያሳደገ ያለ ተጨዋች ነው፤ ለስራው ታታሪ እና ስራውን የሚወድም ተጨዋች ነው፤ ሁሌም ለመለወጥ ተግቶም ይሰራል፤ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ስለመሆንም ያልማል፤ በዛ ላይ ባህሪው የሚገርም ነው፤ ተመልካቹን፤አሰልጣኙን ሚዲያውን እና ተጨዋቾችን የሚያከብር እና ፕሮፌሽናል የሆነ አህምሮ ያለ ውም አይነት ተጨዋች ነው፤ የእኛ ሀገር ብዙ ተጨዋቾች ከእሱ ጋር ተገና ኝተው ቢያወሩ እንኳን በኳሱ የተሻለ ቦታም ላይ ይደርሳሉ ብዬም ነው የማስ በው፤ አዲስ ሌላው አንድ ጎኑ ስለ ኢትዮጵያ ኳስ የሚያስብበት መንገድም ነው፤ የሀገሩ ኳስ ለውጥና እድገት እንዲ ኖረውም ሁሌ ይመኛል፤ ዓላማው ኳስና ኳስም ብቻ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ለተጨዋቾቼ እሱን ምሳሌ አድርጌም ነው የማወራቸው፤ እሱን ጠቅሼላቸው አብረውት ስለሆኑም እድለኞች ናችሁም ብዬም እነግራቸዋለው፤ አዲስ በቡድናችን ውስጥ ካፒቴን ብቻ አይደ ለም፤ እሱን ቀርበህ ስታየው ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምርም አርሃያ የሆነም ትልቅ ተጨዋች ነውና ወደፊት በኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እመ ኝለታለው፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ አሰልጣኝነትህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሰብከው ትልቁ እልምህ እና ግብህ ምንድን ነው?

ዘርዓይ፡- በአሰልጣኝነት ውጤት ስታመጣ በብዙ ክለቦች ትፈለጋለህ፤ ጥያቄ የሚያቀርቡልህም ቡድኖች አሉ፤ ነገር ግን አንተ ውጤት ሊኖርህ የሚችለው እና እኔም የማምንበት ጉዳይ ባለህበት ቦታ እና ተስፋንም በሰነቅክበት ክለብ ላይ ሆነህ ስራህን ስትሰራ ነውና ዘንድሮ ምንም እንኳን ውሌን በሲዳማ ክለብ ውስጥ የምጨርስ ቢሆንም የተሻለ ነገር አሁን ላይ እየቀረበልኝ በመሆኑ በእዚህ ከተማመንህና ከተስማማን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቡድናችን ያጣውን ዋንጫ በመጪው ዓመት ለማሳካት ነው ትልቁ እቅዴ፤ ምክንያቱም አሁን ላይ ሁሉን ነገር አይተነዋል፤ ምን ብትስራ? እንዴት ብትሰራ? ዋንጫን ማግኘት እንደሚቻል ደርሰንበታልና በእዚህች ሁለት ዓመት ውስጥ የነበረንን ነገር ለማስቀጠል ከቻልን፤ የተሰራው ቡድን የማይፈርስ ከሆነ፤ ለቡድኑ የሚቅርበው ፋሲሊቲ አሁንም እንደበፊቱ የሚሟላ ከሆነ ድሉን አሳከዋለው የሚል እልምና ምኞት አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠን የወደፊት ምኞትህ ነው?

ዘርዓይ፡- አዎን፤ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም አንድ ተጨዋች ኳስ መጫወት ሲጀምር እልሙ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ነው፤ አሰልጣኝ ሲሆን ደግሞ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆንን ይፈልጋልና ይሄ ቀጣዩ እቅዴ ነው ፤ከዛ በፊት ግን በዋናነት የማስበው ምን እሱን ብቻ በፕሮፌሽናል ደረጃ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቼ ማሰልጠንን እፈልጋለው፤ እነዚህን እድሎች ለማግኘት ደግሞ ብዙ ነገር ማወቅን ይጠይቃል፤ መማር አለብህ፣ መጣር ይኖርብሃል፣ በስራ መድከም ያስፈልጋልና ይሄን ልትረዳ ይገባል፤ በእዛ እሳቤና መስመር ውስጥ ስላለው ይሄንን የብሄራዊ ቡድንን የማሰልጠንን እድል ወደፊት የማሳካው ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ፕሮፌሽናል አሰልጣ ኝነትን ስታስብ ነው የብሄራዊ ቡድንን እድል የምታገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…..?

ዘርዓይ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አሁን ላይ ብቻ ሳይሆን ከበፊት አንስቶ ያለውን እውቀት ለሀገሩ የእግር ኳስ ባለሙያዎች የሚያካፍልበት መንገድ በጣም ሊያስመሰግነው ይገባል፤ እሱ ከእኛ ጋር በሚገናኝበት ሰዓትም እንዴት አድርገን ኳሳችንን ማሳደግ እንዳለብንም ሀሳቦችን ከሁሉም በመውሰድ እውቀቶች በሁሉም አሰልጣኝ በኩል ሼር መደረግ እንዳለበትም ስለሚያደርግ ይሄ ስራ ተጠናክሮም ሊቀጥል ይገባል፤ በተረፈ ፈጣሪ ሀገራችንን ከእዚህ ክፉ በሽታ ጠብቋት እና ሰላም አድርጎልን በእግር ኳሱ ዳግም ወጥተን የምንገናኝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብዬ አስባለው፤ ከዛ ውጪም ፈጣሪ ቤተሰቦቻችንን እና እኛን፤ እንደዚሁም ደግሞ ሀገራችንን እንዲጠብቅልን እና በእሱ እገዛ የምንናፍቀውን ኳስም እንድንመለከት ያብቃን ነው የምለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website