“ወደ ሳውዲ አረቢያ በውሰት ያመራሁት ከአሰልጣኜ ጋር ስላልተስማማው ነው፤ ሌሎች ክለቦች ጋር ተዘዋውሬ የመጫወት ዕድሉ ይኖረኛል”ጋቶች ፓኖም

በሰሜናዊቷ ግብፅ የተለያዩ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ እና ተጫውተውም ያሳለፉ የሀገራችን ፕሮፌ ሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች በቆይታቸው አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን ያሳዩ ሲሆን እነዚህም ጥቂት
ተጨዋቾች ለሀገራቸው ብሔራዊ ቡድንም የመጫወት ዕድልን ባገኙበት ሰዓት ስኬታማ የሚባል እንቅስቃሴንም እስከማሳየት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ አንድአንዶቹ ደግሞ አሁንም በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ በመጫወት ላይ
ይገኛሉ፤ ከስኳዱ ውጪ ከሆኑት መካከልም እንደ እነ ዑመድ ኡኩሪ አይነት ተጨዋቾች አሁንም ለሀገር መጫወት ስሜቱ በጣም ጣፋጭ እና ልዩ ደስታንም የሚሰጥም ነው በሚል በድጋሚ የብሄራዊ ቡድኑን ስኳድ
ዳግም ለመቀላቀል ጠንክረው እንደሚሰሩ እየተናገሩ ሲሆን እሱን ጨምሮ ሌሎቹም በግብፅ ሊግ ላይ ሲጫወቱ የነበሩት ሌሎች ተጨዋቾች ኢትዮጵያውያኖች ወደ ግብፅ ሀገር መጥቶ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ለመጫወት
ምክራቸውን እየሰጡም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች እንደሚሉት ማንኛውም የእግር ኳስ ተጨዋች ሁሌም ጠንክሮና ተግቶ ከሰራ በኳስ መድረስ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ሲሉም ሀሳባቸውን በተለያዩ
አጋጣሚዎች የገለፁበት አጋጣሚ ሲኖር የግብፅ ሊግ ላይ በአሁን ሰዓት እየተጫወቱ ካሉ ተጨዋቾች መካከልም ለአል-ኢትሀድ አሌክሳንደርያ፣ ለኢ. ኤን. ፒ. ፒ. አይ፣ ለኢል- ኢንታግ ኢል-አርባይ፣ ለስሞሀ
በመጫወት ያሳለፈው እና የአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ በሰባተኛው ሳምንት ተካሂዶ በነበረው የሀገሪቷ የሊግ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ለክለቡ አስዋን ሲጫወት ጉዳትን ያስተናገደው ዑመድ ኡኩሪም ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች
ወደ ግብፅ ሊግ መጥተው ለመጫወት ስለ ፕሮፌሽኑ ዓላማና ጥሩ የራስ መተማመንም ሊኖራቸው ይገባል፤ ልበ ሙሉም ሊሆኑ እና ያን ዕድል ለማግኘትም ጠንክሮ መስራትም ያስፈልጋል የሚል አስተያየትን ዘ ቢግ
ኢንተርቪው በሚለው አምድ ላይ እንደሰጠን ሁሉ ሌላው በእዚሁ ሊግ ይጫወት የነበረው የአራስ ኤል-ሁዳድ ተጨዋቹ እና አሁን ላይ በውሰት ለሳውዲ አረቢያው ክለብ አል አንዋር ክለብ ሲጫወት የነበረው ጋቶች ፓኖምም
የዑመድን ሀሳብ በመጋራት ዑመድ ያለው ትክክል ነው በማለትም ሀሳቡን ደግፎታል፡፡

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ለኢትዮጵያ ቡና እና ለመቐለ 70 እንደርታ ክለቦች ለመጫወት የቻለው እና ወደ ግብፅ ሊግ ካመራም በኋላ የኢል-ጎኡና የአራስ ኤል ሁዳድ ቡድኖች ውስጥ
ቆይቶ አድርጎ ኮቪድ 19 ከመግባቱ በፊት ከ አራስ ኤል ሁዳዱ አሰልጣኝ ጋር ባለመስማማት ለሳውዲ አረቢያው ቡድን በውሰት ተሰጥቶ እየተጫወተ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ጋቶች ፓኖምን
በቅርቡ ዘ ቢግ ኢንተርቪው በሚለው አምዳችን ከጋምቤላ ክልል አንስቶ ስለ ነበረው የኳስ ህይወቱና በአጠቃላይ ከእሱ ጋር በሚገናኙ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ይዘንላችሁ የምንቀርብ ሲሆን ለዛሬ ግን ከእዚህ ተጨዋች
ጋር በግብፅ በነበረው ቆይታ በምን ምክንያት ከአሰልጣኙ ጋር ሳይስማማ ቀርቶ በውሰት ወደ ሳውዲ አረቢያው ክለብ እንዳመራ፤ በክለቡ ውስጥ ስለነበረው ቆይታና ሌላ አጠር ያሉ ተጨማሪ ጥያቄዎችን አቅርበንለት
ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
በግብፅ ሊግ በነበረበት ሰዓት ስላሳለፋቸው የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ቆይታው
“በግብፅ ሊግ ስጫወት የመጀመሪያ ዓመት ላይ የነበረኝ ቆይታዬ በጣም አሪፍ ነበር፤ ከክለቤ ጉኡና ጋርም በቋሚ ተሰላፊነት የመጫወት እድልንም አግኝቼያለው እና ያ በጣም ደስ ይላል፤ ሁለተኛው ዓመት ላይ ግን
ከአዲሱ ክለቤ አሰልጣኝ ጋር ለመስማማት ስላልቻልን በውሰት ወደ ሳውዲ አረቢያው ክለብ ላመራ ችያለው፤ በውሰት ለሰጠኝ አራስ ኤል ሁዳድ ክለብም ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት አለኝ”፡፡
ከግብፅ ሊግ ወደ ሳውዲ አረቢያ ስላደረገው የውሰት ጉዞው እና በሳውዲ ስለነበረው ቆይታ
“ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጉዤ በውሰት የተጫወትኩት በግብፅ ክለብ ቆይታዬ ከአሰልጣኜ ጋር ስላልተስማማው ነው፤ ከአሰልጣኜም ጋር ልስማማ ያልቻልኩት በአጨዋወት ታክቲክ ሳንግባባ በመቅረታችን ነው፤ በሳውዲ
ሊግም የነበረኝ የውሰት ዘመን ቆይታዬ ለአራት ወራት ያህል ነበር፤ ለክለቤም አል-አንዋር ነበር የተጫወትኩት፤ በእዛም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ”፡፡
ከኮቪድ 19 በኋላ በረራ ሳይኖር ከሳውዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣበት ሁኔታ
“ኮቪድ 19 ለዓለም ስጋት ሆኖ ወደ ሁሉም ሀገራት እየገባ በመጣበት ሰዓት እኔ ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገሬ ለመምጣት የቻልኩት የበረራ ጉዞ ሳይኖር በመከራ በኢምባሲ አማካኝነት ተደዋውለን በመነጋገር ነው
፤ የበረራ ፍላይት ስላልነበርም በካርጎም አማካኝነት ነው ልመጣ የቻልኩት”፡፡


ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ስለሊጋቸው መጀመርና አለመጀመር
“በሳውዲ የሊግ ውድድሩ ከመጀመሩ ጋር እስካሁን ምንም ነገር የለም፤ የሚመጣውን ነገርም እየጠበቅን ነው የምንገኘው”፡፡
ከሳውዲ በኋላ ወደ ሌላ ክለብ የሚያመራበት እድል ይኖረው እንደሆነ
“በኮቪድ 19 የሊጉ ጨዋታዎች በመቋረጣቸው ምክንያት ውድድሩ ይቀጥል አይቀጥል ስላልታወቀ እና ሁሉም ነገሮች ስለተዘጉና ስለቆሙ እንጂ ከኤጀንቴ ጋር በመነጋገር ወደ ሌላ ክለብ ተዘዋውሬ ወይንም ደግሞ
ወደቀድሞ ክለቤ ተመልሼ የምጫወትባቸው እድሎች አሉ”፡፡
ከወራቶች በፊት ስለፈፀመው የጋብቻ ስነ-ስርዓት እና ስለባለቤቱ
“ከባለቤቴ ጋር የጋብቻዬን ስነ-ስርዓት ያኔ ፈፀምኩ እንጂ ቢያንስ ለ9 ዓመታት ያህል ከእሷ ጋር አብረን መኖር ጀምረናል፤ ስለዚህም በጊዜው ሰርጉን አደረግን እንጂ በተዘዋዋሪ ትዳር ላይ ነበርን ማለት ይቻላል፤
በእዚህም ጊዜ ቆይታ ጥሩንም መጥፎንም ነገሮች ማየት የምትችልበት እና የምትረዳበትም ነገር ስላለ ለእኔ እሷን ካገኘሁበት ጊዜ ጀምሮ እንዳየዋት ጥሩ እና ትክክለኛ ምርጫዬ ናት፤ የህይወት አጋሬም ጭምር፡፡
በጋብቻው ወቅት ሚዜዎቹ እነማን እንደነበሩ


“የጋምቤላ ክልል ልጆች ናቸው፤ ከእነዛም መካከል ከሚታወቁት ውስጥ የእግር ኳስ ተጨዋቹ ራምኬል ሎክ ይገኝበታል”፡፡
የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ ትዳርን ስለመመስረት እና በእዛ ህይወት ውስጥ ስለመኖር
“ትዳር ሲጀመር ጥቅሙ ለራስ ነው፤ ህይወትህንም እንድታሻሽል ያደርግሃል፤ ትዳር ሲኖርህ ልጅ ይመጣል፤ ያኔ የምትኖረውም ለእሱም ጭምር ነው፤ ልጅ ሲመጣ ደግሞ ሁሉም ነገርም ይቀየራል፤ ያኔ ለልጅህም
ብቻ ነው የምታስበው እና ያ ጥሩ ነገር ነው፤ ስለዚህም በእዛ ውስጥ መኖር በጣም ይመቻል”፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team