ወልዋሎ አዲግራት አፍሪካዊያንና ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾችን ይለያያል መባሉን አስተባበለ

“ከየካቲት ጀምሮ ለማንም ተጨዋች ደመወዝ አልከፈልንም“
ኮማንደር ኪዳነ ኃብቴ/የክለቡ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በተጨዋ ቾች መሀል ምንም አይነት ልዩነት እንደማያደርግ በአፍሪካና በኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች መሀል ምንም አይነት የልዩነት አጀንዳ እንደሌለው አስታወቀ፡፡ የክለቡ ጊዜያዊ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ኪዳነ ኃብቴ በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት ከሰሞኑ ለአፍሪካውያን ተጨዋቾች ሙሉ ደመወዝ ከፍሎ ለኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ደመወዝ ከከፈለ አራት ወራት አስቆጠረ ተብሎ የተናፈሰውን መረጃ መሠረተ ቢስና ክለቡን ፈፅሞ የማይመጥን ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
እንደ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር መረጃ ከፕሪሚየር ሊጉ 16 ክለቦች መሀል አስሩ ሙሉ ደመወዝ ሲከፍሉ 6ቱ ከ1-5 ወራት የተጨዋቾች ያልተከፈለ የደመወዝ እዳ እንዳለባቸው ይፋ ሆኗል፡፡ 16ቱ ሙሉ ደመወዝ ያልከፈሉ 6 ክለቦች ደግሞ አዳማ ከተማ፣ ስሁል ሽረ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ አባጅፋር፣ ሀድያ ሆሳዕናና ወላይት ድቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከትላንት በስቲያ በኛ ይፋ በተደረገ መረጃ ከ6ቱ ያልከፈሉ ክለቦች መሀል የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጨዋቾች ደመወዝ አልተከፈለንም መረጃ ጀርባ ሌላ ምስጢርም አፈትልኮ ወጥቷል በሚል ሲናፈስ ቆይቷል፡፡ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በቡድኑ ውስጥ ላሉ አፍሪካዊያ ተጨዋቾች ሰኔ 30/2012 ሙሉ ደመወዝ ከፍለው ወደ ሀገራቸው ሸኝተዋቸዋል፡፡ ለሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ሙሉ የ3፣የ4 እና የ6 ወር ደመወዝ ያላገኙ ተጨዋቾች መኖራቸውን ይህው መረጃ ገልጿል፡፡ የውጪ ሀገር ተጨዋቾች ሙሉ መብት ሲከበር ኢትዮጵያኑ ግን መገፊታቸው ምንም አታመጡም ከሚል የመነጨ ይመስላል በሚል መረጃዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል፡፡
የክለቡ አመራሮች በተለይ የውጭ ተጨዋቾችን የሚይዙበት መንገድ ያስቀናል ተጨዋቾቹ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቋረጠው ሊግ ሲቀጥል ዳግም ማሊያውን እንዲለብሱላቸው በማሰብ ተንከባክበዋል፡፡ በተለይ አንድ የቡድን ወሳኝ ተጨዋች ከታህሳስ ጀምሮ አልተከፈለውም፡፡ ነገር ግን ለቡድኑ መንፈስ ሲል ምንም አይነት ተቃውሞ ፊት ለፊት አላቀረበም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስም ከፊርማ ክፍያ ውጪ ያለፉትን 3 ወራት ያለ ደመወዝ ሰርተዋል፡፡ ይሄ ክለብ ወዴት እየሄደ ነው የሚል ስጋት ፈጥሮብናል ሲል ከክለቡ የውስጥ አዋቂ የተገኘ መረጃ ይገልፃል፡፡ ጊዜያዊው ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ኪዳነ ለሀትሪክ በሰጡት በዚሁ መላሻቸው “የተባለው ነገር ከሀቅ የራቀ ነው፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደተገለፀው ሙሉ ደመወዝ ካልከፈሉ ስድስት ክለቦች መሀል እንደገኛለን፡፡ በተፈጠረብን የበጀት ችግር ከአለቆቻችንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን ቀርፈን ለተጨዋቾቻችን ደመወዛቸውን ለመክፈል እየጣርን ነው” ሲሉ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡ “የአፍሪካና የኢትዮጵያ ተጨዋቾች እያልን ማንም ማግለል አንፈልግም አላደረግነውም አናደርገውምም የክለቡም አቋም አይደለም ክለባችን ከሚባለው በላይ በእኩልነት ያምናል፡፡ አንድ በእርግጠኝነት የምናገረው ጉዳይ ቢሆን ከየካቲት ወር ጀምሮ ለማንኛውም ተጨዋች በምንም ምክንያት ምንም ደመወዝ አልከፈልንም” በማለት ከሀትሪክ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport