“ወልቂጤ ከተማን የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪና የራሱ አጨዋወትም ያለው ቡድን ለማድረግ እዘጋጃለው” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው /ወልቂጤ ከተማ/

 

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው እያሰለጠነ የሚገኘው ደግአረገ ይግዛው የመጪው ዓመት ቡድኑን ጠንካራ የሊጉ ተፎካካሪ ለማድረግ እና በሜዳ ላይ የጨዋታ እንቅስቃሴውም የራሱ የሆነ ቅርፅ ያለው ቡድን ለመስራት እንደሚዘጋጅ አስተያየቱን ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡
የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በሙያው ቆይታ የተለያዩ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን በመውሰድ እየሰራ ያለ ሲሆን ከዛም በተጨማሪ በሰውነት ማጎልመሻ እና ስፖርት ዲፕሎማም አለው፤ አሰልጣኝ ደግአረገ ወልቂጤ ከተማ የፕሪምየር ሊጉን በተቀላቀለበት የዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ ቡድኑን በሀላፊነት መርቶ አበረታች የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴን ቡድኑ እንዲያሳይ ያደረገ ሲሆን የሊጉ ውጤታማ እና ጠንካራ የሚባሉትን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማን የመሳሰሉት ክለቦችንም እስከማሸነፍ የደረሰበት ውጤቱም ተደናቂነትን አትርፎለታል፤ ወልቂጤ ከተማ የሊጉን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀላቀለበት ለአሰልጣኙም ቢሆን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ አንድ ቡድንን በኃላፊነት ሲመራ የመጀመሪያው ጊዜ በሆነበት የውድድር ዓመት ያስመዘገቡት ውጤት ለቀጣዩ ጊዜ ለሚገነቡት ቡድናቸው ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርላቸውም እየተገለፀ ይገኛል፡፡
የወልቂጤ ከተማ ክለብ አሰልጣኝን ከእሱ ጋር ተያያዥ በሆኑ የስፖርት ህይወት ቆይታው እና ስለ አሰልጣኝነቱ እንደዚሁም ደግሞ አሁን እያሰለጠነ ስላለው የወልቂጤ ከተማ ቡድን የተለያዩ ጥያቄዎችን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አቅርቦለት አሰልጣኙ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- በቅድሚያ እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሰህ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ስፖርት ህይወቱ እንዴት ዘልቀህ ገባህ? የትስ ተወልደህ አደግክ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- ተወልጄ ያደግኩት በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 01 በተለምዶ አጠራር ጎጃም ዳቦ ቤት አካባቢ ነው፤ ወደ ስፖርቱ ዓለም የገባሁትም ከልጅነቴ ዕድሜ አንስቶ በአካባቢዬ ይገኙ ለነበሩ የታዳጊ እና የዋናው ቡድኖች እንደዚሁም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ይገኙ ለነበሩት ትላልቅና ታዋቂ ቡድኖችም ውስጥ ገብቼ በመጫወት ነው፤ የእግር ኳሱን በጉዳት የተነሳ ካቆምኩ በኋላ ደግሞ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ በመሰማራት አሁን ላይ በዛ ስራ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ ለማን ለማን ቡድኖች በመጫወት አሳለፍክ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የእግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ በክለብ ደረጃ ገብቼ የተጫወትኩት ለባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ክለብ ነው፤ ያኔ የወጣት ቡድኑ ተጨዋችም ነበርኩ፤ በዋናው ቡድን ደግሞ እነ ገብረመድህን ሀይሌ፣ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም እና ፀጋዬ ሀይሉ /ነፍሱን ፈጣሪ ይማር/ ይገኙም ነበርና እነሱ ልክ ወደ አዲስ አበባዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና እርሻ ሰብል ቡድኖች ሲያመሩ እኔ ደግሞ ወደዋናው ቡድን የማደግ እድሉን በማግኘት ለክለቡ ልጫወት ቻልኩ፤ ከባህር ዳር ቆይታዬ በኋላ ደግሞ እግር ኳስን የተጫወትኩባቸው ቡድኖች የአዲስ አበባዎቹ ባህር ሀይል እና ጉምሩክ ክለቦች ናቸው፤ ተመልሼ ከእነዚህ ቡድኖች በኋላም ለባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ለጥቁር አባይ እና ለባህር ዳር ዩንቨርስቲ ቡድኖች ተጫውቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብም ገብቶ ለመጫወት እድሉን አግኝተህ ነበር፤ በኋላ ላይ ሳይሳካ ቀረና ከክለቡ ወጣህ፤ ያኔ ምንድን ነበር የሆነው?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታቶች ላይ በወንጂ ከተማ ተደርጎ ከነበረው የመኢሰማ ውድድር ላይ ጎጃምን ወክዬ ስጫወት በኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ አማካኝነት ነበር ተመልምዬ የገባሁት፤ ለቡድኑ ከመመልመልም ባሻገር የቡድኑ መኖሪያ ካምፕ የሆነውንም ገነት ሆቴል ገብቼበት ስኖርና በዊንጌት ትምህርት ቤት ሜዳ ላይም ልምምዴን እስከመስራትም ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር፤ ከዛ ውጪ ክለቡ ያን ዓመት ላይ ባሰራውና የውድድር ዓመቱ ተጨዋቾች እነማን እንደሆኑም በሚገልፀው ፖስተር /ካሌንደር/ ላይም ከቡድኑ ተጨዋቾች ጋር ፎቶዬ ወጥቶም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በጊዜው በስኳዱ የያዛቸው ተጨዋቾች በጣም ታዋቂ፣ ዝነኛ፣ ምርጥና የተካበተ የጨዋታ ልምድ የነበራቸው ተጨዋቾች ስለነበሩ ከቡድኑ ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ቢተው አብሬ በአንድ ዶርም ውስጥ አብረን ነበርንና አንተ በእዚህ ክለብ ውስጥ ተሰልፈህ የመጫወት እድልህ በጣም ጠባብ ነው፤ ገና ወጣት ተጨዋችም ነህ፤ ስለዚህም ልትጫወት ወደምትችልበት ቡድን ብትሄድ ይሻልሃል ብሎኝ ወደ ሕንፃ ኮንስትራክሽን ቡድን እንድሄድ ሀሳብ ቢያቀርብልኝም እኔ ግን ወደ ሕንፃ ሳልሄድ ቀርቼ ወደ ባህር ሀይል ቡድን አመራሁና የባህር ሀይል ቡድን ውስጥ ገብቼ ለመጫወት ቻልኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንተን ለቡድናቸው እንድትጫወት አምጥተውክ እና በካምፓቸውም ውስጥ አስቀምጠውክ እያለ ለባህር ሀይል ተጫወትክ፤ ይሄን ስታደርግ ዝም አሉህ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- ያኔ የሆነው የባህር ሀይል እግር ኳስ ክለብ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ እኔን የቡድናቸው ተጨዋች ለማድረግ ይፈልጉ ነበር፤ ከዛም የባህር ሀይል መልማዮች እና አሰልጣኙ ዶክተር ተስፋዬ ሲያናግሩኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካምፕ ወደ እነሱ ጋር ሄድኩ፤ ከእነሱ ጋር ልምምድም ሰራው፤ በጊዜው ወደ እነሱ ስሄድ የአዲስ አበባ ውድድር ሊጀመር አንድ ሳምንት ብቻ ነበር የቀረውና ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁን አገኘሁት፤ ለእሱም ቤተሰብ ናፍቆኛል፤ ወደ ባህር ዳር ልሂድ ስለው ፈቅዶልኝ ለቡድናችን ወጌሻ ለነበረው አቲሞ ትኬት ይቆረጥለት ብሎት ነግሮት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ግን ተመለስ ብሎኝ ሲፈቅድልኝ፤ እኔ ግን ወደዛ ሳልሄድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የባህር ሀይል ተጨዋች ሆኜ ተሰለፍኩ፤ ያኔ ከጀማል ሀሰን ጋር ነበር የአጥቂ መስመሩንም ስንመራ የነበረው፤ መንግስቱም ጨዋታው ላይ አየኝና ተናደደ፤ እኔም ስሜታዊነት ይታይብኝ ነበር፤ ከዛም በእረፍት ሰዓት ላይ ኮሪደሩ ላይ ጠራኝና ነገ ጠዋት 4 ሰዓት ላይ ገነት ሆቴል እፈልግሃለው አለኝ፤ ከዛም በሰዓቱ እሱ ከሰለሞን መኮንን ሉቾ ጋር አብረው ነበሩና ማነው ወደ ባህር ሀይል ሂድ ብሎ የገፋፋ ሲለኝ በወቅቱ ቢተው ወደ ሕንፃ ብትሄድ ለአንተ ጥሩ ነው፤ እዛ ሄደ መጫወትም ትችላለህ ብሎኝ ነበርና የእሱን ስም ሳልጠቅስ በወቅቱ የመብራት ሀይል ተጨዋች የነበረውንና ወደ ኖርዌይ የሄደውን ዳዊት ተስፋሚካኤል የሚባል ተጨዋች ነበርና እሱ ነው አልኩት በኋላ ላይ አንድአንድ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ነግሮኝና መክሮኝም ለባህር ሀይል እንድጫወት ፈቀደልኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ በመጣህባቸው መንገዶች የማትረሳቸው ውድድሮችስ አሉ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- አዎን፤ በተለይ ደግሞ ለእግር ኳስ ጨዋታው በነበረኝ ጥልቅ ፍቅር በ1980 ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ላይ የባህር ዳር ከተማ ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው ሀገር አቀፍ የስፓርታኪያድ ውድድር ላይ ለጎጃም ምርጥ ቡድን በመጫወት ያሳለፍነውን ነው፤ በጊዜው በዞን አራት ውስጥ እኛን ጨምሮ የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን፣ የአስመራ ምርጥ ቡድንና የጎንደር ምርጥ ቡድን በአንድ ምድብ ውስጥ ተካፋይ ነበርን፡፡ ያ ውድድርም ታዋቂ ተጨዋቾችም የተሳተፉበትም ነበር፤ ለምሳሌ ለአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ጋሽ ታዴ /ነፍሳቸውን ይማረው/ እሳቸው ያፈሯቸው ተጨዋቾች ማለትም እንደ እነ ተክሌ ብርሃኔና ወንድማገኝ ማሞን /ፔሌ/ የመሳሰሉ ነፍሱን ይማረው ለመድን የተጫወቱ እንደዚሁም ደግሞ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወት የነበረው አሳምነው ገ/ወልድ ለአስመራ ምርጥ ቡድን ደግሞ ለጉምሩክ ይጫወት የነበረው ኪሮስን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ተሳትፈውበት ነበርና ያ ምርጥ እና ጥሩ ውድድር ፈፅሞ አይረሳኝም፤ በአጠቃላይ ውድድሩ እኛም ነበርን ሻምፒዮና ልንሆን የቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- የምድር ጦሩ ቴክኒሽያን ተጨዋች ማቲያስ ሀብተማሪያም ቀዳሚው ምርጫዬ ነው፤ ከእሱ በኋላ ደግሞ ገብረመድህን ሀይሌ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ኤልያስ ጁሀር፣ ካሳዬ አራጌ፣ ኤፍሬም /ችቦ/፣ አብዲ ሰይድ እና አብርሃም ብስራትን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ምርጦች ነበሩ፡፡
ሀትሪክ፡- የአሁን ሰዓት ላይ ወልቂጤ ከተማን እያሰለጠንክ ነው፤ ከዛ በፊት ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ስትገባ የትኞቹን ክለቦች በኃላፊነት መራህ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሰልጣኝነቱ ሳመራ በክለብ ደረጃ ያሰለጠንኩት ቡድን ደብረማርቆስ ዩንቨርስቲን ነው፤ ያኔ ቡድኑን ከማሰልጠን ባሻገር በቴክኒክ ስታፍ ደረጃም ክለቡን ላገለግልም ችያለው፤ ያኔ ይሄን ቡድን ሳሰለጠንም በብሔራዊ ሊግ ላይ ፋሲል ከነማ፣ ወልዲያ ከተማ እና አውስኮድ በነበሩበት ምድብ ውስጥ ሶስተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅም አድርጌያለው፤ ከዚህ ቡድን ቆይታዬ በኋላ ያመራሁት ደግሞ ወደ አማራ ውሃ ስራ ቡድን ነው፤ ይሄን ቡድን ሳሰለጥን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ሱፐር ሊግ እንዲገባ አድርጌያለው፤ ይሄን ቡድን ድሬዳዋ ላይ ተደርጎ በነበረው ውድድርም ዳግም ከሱፐር ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማስገባት በነበረው ተሳትፎም ለጥቂት ባይሳካልኝም ጠንካራ ቡድንን ለመስራት ችያለው፤ እንደ እነ ያሬድ ባየህ እና ሰይድ ሁሴንን የመሳሰሉ ተጨዋቾችንም ለማፍራት ችያለው፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጣው በኋላ ደግሞ ያሰለጠንኳቸው ቡድኖች ውሃ ስራንና ኢካፍኮን ነው፤ ጠንካራ ቡድንን ለመገንባት ችያለው፡፡ ከእነዚህ ውጪ ስለ አሰልጣኝነት ህይወቴ ልጠቅስ የምፈልገው ነገር ቢኖር የታዳጊ ወጣቶችን ያሰለጠንኩበትን የመጀመሪያ የስልጠና ጊዜዎቼን ነው፤ ያኔ በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ አማካኝነት ነው የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ኮርሶችን
በመውሰድ ወደ ሙያው ዘልቄ የገባሁት፤ በዛን ጊዜም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ መንግስት በዘረጋው የፕሮጀክት ስልጠናዎችም ላይ ተሰማርቼ በመስራትና ሙያዬንም እያሻሻልኩ በመምጣት ነው ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ልበቃ የቻልኩት፤ በፕሮጀክት አሰልጣኝነቴ ብዙ ነገሮችን ልማር ችያለው፤ ከዛ ውጪም ስኬታማ ስራዎችን ለመስራት በቅቻለው፤ ጥሩ ተጨዋቾች ለኢትዮጵያ ታዳጊ እና ኦሎምፒክ ቡድኖች ውስጥ ገብተው እንዲጫወቱም ጥረትንም አድርጌያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ ከተማን በሀላፊነት የመራክበትን የዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በፕሪምየር ሊግ የአሰልጣኝነት ዘመን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀላፊነት የመራሁበት ቡድን ነው፤ ለክለቡም የመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ነው፤ ይህን ቡድን ዘንድሮ ስመራው ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት ውድድሩ በኮቪድ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ የተመዘገበው ውጤት ጥሩ እና የሚያበረታታ ነው፤ ምክንያቱም ቡድናችን የተገነባው በአብዛኛው ከሱፐር ሊግ በመጡና በወጣት ተጨዋቾችም ነበርና ልምድ የነበራቸው ተጨዋቾች በጣም ጥቂቶች ነበሩና ይሄ ለእኛ ዘንድሮ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረልን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ ከተማ ትላልቅ የሚባሉ ክለቦችን እስከማሸነፍ ደረጃም ደርሶ ነበር፤ ስለ እነዛ ድል ምን የምትለው ነገር አለ…..?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- አዎን፤ በውድድር ዓመቱ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ፋሲል ከነማንም ለማሸነፍ ችለን ነበር፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስም በአጠቃላይ የመጀመሪያ ዙርን ጨምሮ አራት ነጥቦችንም ልንወስድበት ችለን ነበርና ያን ማግኘት መቻላችን ለእኛ ትልቅ ደስታን ነው የፈጠረልን፤ ጥሩ ጉልበትም ነው የሆነልን፤ ከእነዚህ ቡድኖች ባሻገር ከቡና ጋር ነጥብ መጋራት መቻላችንና እነ ወላይታ ድቻ የመሳሰሉ ክለቦችንም ለማሸነፍ መቻላችን ብዙዎቹን ጨዋታም ያሸነፍነው ከሜዳችን ውጪ በነበሩት ጨዋታዎች መሆናቸውም እኛን እንድንነቃቃም ሊያደርገን ችሏል፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ ከተማን በአዲሱ የውድድር ዘመን እንዴት እና በምን መልኩ እንጠብቀው?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የዓምናው የውድድር ተሳትፎአችን ለእኛ የሰጠን ጥሩ ግብዐት አለ፤ ይሄ በመሆኑም በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ለክለባችን ጥሩ ሲጫወቱ የነበሩ ተጨዋቾችን ውል በማራዘምና ቡድናችንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ልጆችንም በመቀላቀል በእዚህ ዓመት ጠንካራ ቡድንን እንገነባለን፤ ከዛ ውጪም ወልቂጤ ከተማ የራሱ የሆነ የአጨዋወት ቅርፅ ያለው ቡድንን ይዞ እንዲመጣም እናደርጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- በአሰልጣኝነትህ አሁን የምትገ ኝበትን ደረጃ ምን ላይ ታስቀም ጠዋለህ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- አሰልጣኝነትን ገና ጀመርኩት እንጂ አልተራመድኩበትም፤ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ነገሮችንም መማር አለብኝ፤ ምክንያቱም አሰልጣኝነት ጥልቅ እውቀትን ይፈልጋል፡፡
ሀትሪክ፡- የአሰልጣኝነት ህይወትህ የመጨረሻ ግብ የት መድረስ ነው?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- ሰው ይመኛል፤ ፈጣሪ ደግሞ ይፈፅማል አይደል የሚባለው፤ የእኔ እልሜና ግቤ በውጪ ሀገር ሄዶ ማሰልጠን ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ የብሔራዊ ቡድናችንንም በኃላፊነት መምራት እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኞች ከተጨዋቾች ገንዘብ እየተቀበሉ ሙያቸውን እያበላሹ ነው ተብሎ እየተነገረ ይገኛል፤ በእዚህ ላይ የምትለው ነገር ካለ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- ስለ እውነት ለመናገር ይሄ ጉዳይ በየጊዜው እየተወራ ይገኛል፤ እኔም ሰምቻለው፤ ይህ ድርጊት ኳሱን የሚፃረርም ሆኗል፤ አሰልጣኞች ከተጨዋቾች ገንዘብ መቀበሉን በተመለከተ ሆኗልም አልሆነም ለማለት የማስረጃ ጉዳይ ነው፤ ይህን በተመለከተ ደግሞ ገንዘብ የሚሰጡ ተጨዋቾች ትልቅ ሀላፊነቱን መውሰድ አለባቸው፤ ይሄን ለኳሱ እንቅፋት የሆነውን ነገር እነዚህ ተጨዋቾች ማጋለጥ አለባቸው፤ ተጨዋቾች ለአሰልጣኝ ገንዘብ እየሰጡ መጫወት ማለት ድርጊቱ የቆሸሸ ተግባር ነው፤ ሙያንና አንደበትንም ማሰር ማለትም ነው፤ የሚቀበለው አሰልጣኝም ምንም ሊናገር የሚችልበት አንደበትም ሊኖረው አይችልምና፤ ለዚህ ሰፊ ትግልም ያስፈልገዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ትዳር ህይወትህ እና ስለባለቤትህ ምን ትላለህ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- የትዳር ህይወቴ በጣም ጥሩ ነው፤ ባለቤቴ ናርዶስ ፅጌም በብዙ ነገሮች እኔን እያገዘችኝ ነው፤ ሁለት ልጆችም አለኝ፤ የመጀመሪያዋ ዳሪክ ደግአረገ ስትባል በድሬዳዋ የአንደኛ ዓመት የዩንቨርስቲ ተማሪ ነች፤ ሌላዋ ደግሞ የአንድ ዓመት ከ9 ወር የሆነችው ሀብሳላት ነች፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ከተጨዋችነት አንስቶ አሁን እስካለሁበት የአሰልጣኝነት ሙያዬ እንድመጣ በማድረግ ላለኝ ለውጥ አስተዋፅኦ ላደረጉልኝ የሙያ አባቶቼ ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናዬን ላቅርብላቸው እፈልጋለው፤ በኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ፣ በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ እንደዚሁም ደግሞ በአሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ሰልጥኜ ማለፌ በአሰልጣኝነት ሙያው ራሴን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሻሽዬ እንድጋዝ ያደረገኝ ሁኔታ ስላለ ለእነዚህ የቀድሞ አሰልጣኞች ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፤ ሌላው ልጠቅስ የምፈልገው ደግሞ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለባህር ዳር ከተማ እና ለባህር ዳር ጨርቃጨርቅ በአጠቃላይ ለክልሉ እግር ኳስ ትልቅ መሰረትን ለጣለው የአሁኑ የባህር ዳር ከተማ ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አሻግሬ አድማሱ /ቦንዳ/ ምስጋና አለኝ፤ ከእሱ ውጪም የወልቂጤ ከተማ ክለብ የሱፐር ሊግ አሰልጣኝ ሆኜ በእኔ ላይ እምነት በማሳደር ክለቡን እንድረከብ ስላደረገኝና በዚህ ዓመትም አበረታች ውጤት እንዲመጣም ስላደረጉኝ የክለቡን የቦርድ አመራር አባላቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቱን አቶ አበባው ሰለሞንን ለማመስገን እፈልጋለውኝ፤ ከእነሱ ውጪም ባለቤቴን ናርዶስ ፅጌንም ለማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website