የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ጥቅምት 17 2011 ዓ.ም ጅማሬውን ሲያደርግ በዛሬው ውሎ ክልል ላይ 9:00 ላይ 3 ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን 3ቱም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል።
አዳማ ከተማ ከጅማ አባጅፋር
አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በእንግዳው ጅማ አባጅፋር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለጅማ አባጅፋር ግቦቹን አስቻለው ግርማ 45ኛው ደቂቃ እንዲሁም ከ5 ደቂቃዎች በኋላ 50ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሐመድ አስቆጥረው ጅማ አባጅፋርን ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ 3ነጥቦች እንዲያስመዘግብ አስችለውታል። ይህንንም ተከትሎ ጅማ አባጅፋር በግብ ክፍያ ተበልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሐዋሳ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ
በሌላ የ9:00 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሐዋሳ ላይ ሐዋሳ ከተማ ወልዋሎ አ.ዩ.ን ያስተናገደበት ጨዋታ የሚጠቀስ ነው። በጨዋታውም ባለሜዳው ሐዋሳ ከተማ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1ደቂቃ ሲቀረው 44ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር ክለቡን ቀዳሚ በማድረግ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል። ከመልበሻ ቤት ሲመለሱ 46ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ከፍ አድርጓል። ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ 94ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ድንቅ ግብ በማስቆጠር ክለቡን የ3-0 ድል እንዲያስመዘግብ አስችሎታል።
መቐለ 70 እንደርታ ከደደቢት
መቐለ ላይ ስሙን ከ መቐለ ከተማ ወደ መቐለ 70 እንደርታ የቀየረው እና ተቀማጭነቱን ከአ.አ ወደ ትግራይ ያዞረውን ደደቢትን ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው መቐለ 70 እንደርታ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ደደቢት አምና ከነበሩት ተጫዋቾች ሙሉ ለሙሉ ሊያስብል በሚያስደፍር ሁኔታ የለቀቀ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታም ወደ 15 ተጫዋቾች ለቆ 11 ተጫዋቾችን አስፈርመው ለዚህ የውድድር አመት መቅረብ ችለዋል። በጨዋታው ላይም 3ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ ማድረግ የቻለ ሲሆን 74ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳሙኤል ሳሊሶ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር የመቐለ 70 እንደርታን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።

የመቐለ 70 እንደርታ የጨዋታ ሪፖርት ሊንኩን ይጫኑ
ውጤቶቹን ተከትሎ በመጀመሪያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሐዋሳ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ጅማ አባጅፋር በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ አዳማ ከተማ፣ ደደቢት እና ወልዋሎ.አ.ዩ. ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አስተያየት ይስጡ