መነሻ ገጽ ዋልያዎቹ ክለቦች ተጨዋቾችን ባለመልቀቃቸው ዝግጅት ማድረግ አልቻልኩም”-የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ክለቦች ተጨዋቾችን ያለመልቀቃቸው ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርገው ዝግጅት እንቅፋት መፍጠሩን የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ተናገሩ።
ዋልያዎቹ

ክለቦች ተጨዋቾችን ባለመልቀቃቸው ዝግጅት ማድረግ አልቻልኩም”-የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ክለቦች ተጨዋቾችን ያለመልቀቃቸው ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርገው ዝግጅት እንቅፋት መፍጠሩን የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ተናገሩ።

አጋራ
አጋራ

​የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ክለቦች ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችን እንዲለቁ የሚሰጠው ጊዜ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ህግና ደንብ መሰረት ነው ብሏል።

በ2019 ካሜሮን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ከጋና ጋር ያደርጋሉ።

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለዚሁ ጨዋታ 29 የብሔራዊ ቡድን አባላት መምረጣቸውን ቢያሳውቁም ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ባለመልቀቃቸው ሳቢያ እስካሁን ዝግጅት አልጀመሩም።

ብሔራዊ ቡድኑ ሚያዚያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም ቅድመ ዝግጅት ለመጀመር አቅዶ እንደነበር አሰልጣኙ ገልጸዋል።

ይሁንና ለማቀናጀትና ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን ለማግኘት በቂ ጊዜ እንደሌላቸው ተናግረው የመጀመሪያ የዝግጅት ምዕራፋቸውን ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚጀምሩም ነው ያሳወቁት።  

ከሶስት ተጨዋቾች በላይ ለብሔራዊ ቡድኑ ያስመረጡት የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጆች ከክለብ ይልቅ ለአገር ጉዳይ ቅድሚያ እንደሚሰጡና የመጨረሻ ግባቸውም ተጨዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ ማስመረጥና ማብቃት መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ከሊጉ ውድድሮች እና ከፊፋ ፕሮግራሞች ጋር እንዳይጣረሱ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በሊጉ አናት ላይ የተቀመጠውና በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና እየተካፈለ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብሔራዊ ቡድኑ አራት ተጫዋቾችን አስመርጧል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን በቀለ ክለቡ ላለበት ጨዋታና ከብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ጋር ያለውን ፕሮግራም በተመለከተ ተጠይቀው የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ክለባቸው ቅድሚያ እንደሚሰጠው ገልጸው ፌዴሬሽኑ ዝግጅቱ ከጨዋታ ፕሮግራሞች ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጨዋታ እያካሄደ በተመሳሳይ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ለማድርግ ተጨዋቾች እንደሚደክሙና ክለቡ እንደሚቸገር ተናግረዋል።

ክለቡ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ዲ ቱኒስ ክለብ ጋር ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓም በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገበት ማግስቱ ብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችን ለዝግጅት ጠርቷል ብለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓም በፕሪሚየር ሊጉ ከፋሲል ከነማ ጋር ተስተካካይ ጨዋታውን እንደሚያደርግም ይታወቃል። ፌዴሬሽኑ ይህን ችግር ለመፍታት ፊፋ ባስቀመጠው ህግና ደንብ መሰረት ፕሮግራሞችን ሊመራ ይገባዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ እርቁ በበኩላቸው ክለቡ ሶስት ተጨዋቾች ለብሔራዊ ቡድኑ ማስመረጡን ገለጸው ተጫዋቾችም በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በወቅቱ ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ለተጨዋቾች ጥሪ ሲያቀርብ ከሁሉን ክለቦች የውድድር ፕሮግራሞች ጋር እንዳይጋጭ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።    

የዓለም እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጡ ለውድድሩ ከ21 ቀን በፊት የመልቀቅ ግዴታ እንዳለባቸው በመመሪያው አስቀምጧል።

ለማጣሪያ ጨዋታዎች ደግሞ ከ10 ቀናት በፊት ክለቦች የመልቀቅ ግዴታ እንዳላባቸው የፊፋ ህግ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ክለቦች ለብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾችን እንዲለቁ የሚሰጠው ጊዜ ፊፋ ያስቀመጠውን ህግና ደንብ መሰረት ያደረገ ነው።

ለብሔራዊ ቡድን ሰፊ የዝግጅት ጊዜ ስለተሰጠ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ እንደሚከብድ የተናገሩት ኃላፊው የተሰጠው የዝግጅት ጊዜ ሁሉንም ያማከለ ነው ብለዋል።

ዋልያዎቹ በ2019 ካሜሮን ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ከጋና፣ ሴራሊዮንና ኬኒያ ጋር መደልደላቸው ይታወቃል።

ምንጭ-ኢ.ዜ.አ

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዋልያዎቹዜናዎችየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

አንጋፋው አሰልጣኝ በስማቸው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊገነባላቸው ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት...