ፊቱ ላይ የተዘበራረቀ ስሜት በግልፅ
ይነበባል፡፡ በቁጭት እና በተስፋ መቁረጥ
ውስጥ እንዳለ ከአንደበቱ ይልቅ ራሱ የፊቱ
ገፅታ አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡ በተለይ
በተለይ ከብ/ቡድን ምርጫ በተደጋጋሚ
መዘለሉ “ሀገሬን እንዳላገለግል አሰልጣኞች
ክፉ ፍርድ ፈርደውብኛል” በማለት የመረረ
ቅሬታውን ያቀርባል-የዛሬው እንግዳችን ዳዊት
እስጢፋኖስ፡፡
ስለ ቀድሞ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና
አውርቶ የማይጠግበው ዳዊት “ፍቅራቸውን
ያለስስት የሰጡኝን፤ በአደባባይ ስሜን
ጠርተው የዘመሩልኝን ደጋፊዎችን ከልብ
አመሰግናቸዋለሁ” ይላል፡፡ የአሁኑ ክለቡ
መብራት ሀይልም ላለፉት ሁለትና ሶስት
ዓመታት ላለመውረድ መጫወቱ ዘንድሮም
በስነ-ልቦናው ረገድ እንደጎዳቸው ይናገራል፡
፡ እስጢፋኖስ ያደገው የአቶ እስጢፋኖስ ልጅ
በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋዜጠኛ ይስሀቅ
በላይ ጋር ተከታዩን አነጋጋሪ ቃለ-ምልልስ
አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡- ከአንተ ጋር የማደርገውን
ቆይታ የምጀምረው ድፍረት ባለው ጥያቄ ነው
ትፈቅድልኛልህ?
ዳዊት፡- ምንድነው ጠይቀኝ…?
ሀትሪክ፡- …ለምድነው ሁልጊዜ ስምህ
ከመጠጥና ከመዝናናት ጋር አብሮ ተያይዞ
የሚነሳው…?… እንደሚባለው… ዳዊት ከመጠጥ
ጋር… የተለየ ዝምድና አለው…?
ዳዊት፡- (በጣም ሳቀ)… በጣም
የሚገርምህ… እኔ ከሰው የተየለሁ
አይደለሁም፤ በዚህ የተነሳም ከሰው በተለየ
የማደርገው የተለየ ነገር የለም፡፡ ለእኔ ለራሴም
በዚህ ደረጃ ስሜ ከመዝናናትና ከመጠጣት
ጋር ተያይዞ ለምን እንደሚነሳ አይገባኝም፤
እኔ ስለሌሎች ማውራት አልፈልግም፡፡
ይሄንን የሚያወሩት ሰዎች ወይም አመራሮች
ለምን እንደሰው እንደማያስቡ ግን አይገባኝም።
ሀትሪክ፡-ይሄ ሁሉ ዳር ዳርታ እንኳን ልጠጣ
መጠጥ ባለበት ዝር አልልም ለማት ነው?
ዳዊት፡- አልወጣኝም…!በዚህ ዙርያ
ያለውን አንድ እውነታ ልንገርህ…?
ሀትሪክ፡- ንገረኝ…በጣም …ደስ…ይለኛል…
ዳዊት፡- መዝናናቱን…እዝናናለሁ
አልክድም፤ ስዝናና ግን ከሰው የተለየ
ተዝናንቼ ግን አይደለም፤ እግር ኳስን ራሴን
በሚጎዳ መልኩ የማደርግ ሰውም አይደለሁም፡
፡ የምዝናናበት ጊዜ ወቅት አለኝ፤ በነጋታው
ጨዋታ እያለኝ ቀርቶ ሶስትና አራት ቀን
ለጨዋታ እየቀረኝ የምዝናና ሰው አይደሁም፡
፡ እንደማንኛውም ሰው እንደማንኛውም ኳስ
ተጨዋች ልዝናና እችላለሁ፡፡ ስሜ እየተነሳ
ያለው ግን በየቀኑ የአንድ የመጠጥ ፋብሪካን
ሙሉ መጠጥ እንደሚጠጣና እንደሚዝናና
ሰው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ መልኩ… ስምህ መነሳቱ…
ያበሳጨህ ትመስላለህ…?
ዳዊት፡- ያለ ስምህ ስም ሲሰጡህ ከሰው
ከሌሉች ተጨዋቾች በተለየ እንደሚያደርግ
ሰው ስምህ በዚህ መሃል ተጋኖ ሲነሳ
መበሳጨት ሳይሆን በጣም ቅር ይለኛል፤
ሰዎች እውነታውን ሳይረዱ እኔን በትክክል
የማይገልፅ ነገር ሲናገሩ የሆነ የሚሰማህ
የሚከፋህ ነገር ይኖራል፤ ደግሞም እንደዚህ
አይነቱ ወሬ ብዙ ጎድቶኛል፡፡ ብዙ ነገርም
አሳጥቶኛል፤ “ዳዊት ኳስ ይችላል… ግን…
በጣም ይዝናናል…” የሚል ቅፅል ስም
አሰጥቶኝ ብዙ ነገር አሳጥቶኛል፡፡ “…
ጥሩ… ነው… ግን …” ካልክ አይሆንም፡፡ …
ጥሩ ከሆንኩኝ… ጥሩ ነኝ…፡፡ መገምገም፣
መዳኘትም ያለብኝ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴዬ
ብቻ ነው መሆን ያለበት፤ከሜዳ ውጪ
ያለውን ማንም አይመለከተውም።ባለሙያው
ጋ ይህንን ሀቅ የመረዳት አቅማቸው በጣም
አናሳ ነው፤ ይሄ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ ስሜታዊ ከሚያደርግህ ጉዳይ
ልውጣና ረጅም ዓመት ከተጫወትክበት ኢትዮጵያ
ቡና ከወጣህ በኋላ ህይወት በመብራት ሃይል
ምን ይመስላል?
ዳዊት፡- ህይወትን ከኢትዮጵያ ቡና በኋላ
በሌላ አዲስ መልክ እያስቀጠልኩት ነው፡፡
ከኢት.ቡና ከወጣሁ በኋላ ለድሬደዋ ከተማ
ገብቼ ነበር፤ ቡድኑ የክልል ቡድን ከመሆኑ
አንፃር በክልል ደረጃ ያለን የእግር ኳስ ህይወት
ስለማላውቅ ትንሽ አስቸግሮኝ ነበር፡፡ ድሬደዋ
ከሙቀቱም ከባህልም አንፃር አዲስ መሆኑ
ከብዶኝ ነበር፡፡ እግር ኳሱ ጋር ስትመጣ ግን
ድሬዳዋ የአገር ባለውለተኛ የሆነች አገር ናት፡
፡ እግር ኳስ ወዳድ ደግ ህዝብ ያለባትም
አገር ናት፡፡ አቅም ላለው ታለንትድ ለሆነ
ሰው ድጋፍ የሚሰጡ መሆናቸው ነገሮችን
በተቃራኒው አቅልሎልኛል፡፡ በዚህ ምክንያት
በድሬዳዋ ምርጥ የሚባል ጊዜን አሳልፌያለሁ፡
፡ እኔ በነበርኩበት ሰዓት ወደ ፕሪምየር ሊግ
የገባበት አመት ስለ ነበር በሊጉ መቆየት
ምርጫቸው ቢሆንም በተወሰኑ ጨዋታዎች
ላይ ወደፊት የመጠጋት ሁኔታ ነበር፡
፡ አጠቃላይ የድሬደዋ ቆይታዬ ኢትዮጵያ
ቡና እንደነበርኩበት ነበር ባልልም መልካም
የሚባል ጊዜ ግን አሳልፌያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ያለህበት የመብራት ሃይል
ህይወትስ?
ዳዊት፡- ከመብራት ሃይል ጋር እንግዲህ
ገና ሰባትና ስምንት ወር አካባቢ ሊሆነኝ ነው፡፡
የተሻለ ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን ነው ያለን
ብዬ ለመዋሸት ባልፈልግም በዲሲፕሊን ደረጃ
አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ወጣት በመሆናቸው
የመቀበል አቅማቸው፤ አሰልጣኞቹም እግር
ኳስን በትልቅ ደረጃ ተጫውተው ያሳለፉ ነገን
ተስፋ አድርገው የሚሰሩ ወጣት አሰልጣኞች
በመሆናቸው በመብራት ሃይል መልካም
የሚባል ጊዜን እንዳሳልፍ አድርጎኛል፤ ነገር
ግን ትልቅ ለመሆን ብዙ መሰራት አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንወስደው
ለአዲስ አበባዎቹ ኢት.ቡና እና መብራት ሀይል
ተጫውተሃል፤ በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው
አንድነትና ልዩነትን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ዳዊት፡- አንድነቱ ሁለቱም እግር ኳስ
ወዳጆች መሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም
መብራት ሃይል ጋርም ተመሳሳይ ነገር አለ፡
፡ ኢት.ቡናን ስትወስድ እንደ ፍልስፍና የተያዘ
አንድ ነገር አለ፡፡ እግር ኳስን ባማረ፤ በሚስብ
መልኩ ተጫውተህ ውጤት ማምጣት
የሚል፤ መብራት ሀይሎች ጋርም ይሄ ስሜት
ነው ያለው፡፡ መብራት ሃይሎች ተጫዋች
እንኳን ሲያስፈርሙ በዋናነት በእግር ኳስ
ችሎታ ላይ የተመሰረተ ተጨዋችን ነው
የሚያስቀድሙት፤ ተመሳሳይነታቸው ውጤት
ቢፈልጉም ውበት ያለው ሳቢ እግር ኳስን ግን
በጣም ያስቀድማሉ፡፡
ሀትሪክ፡- ልዩነታቸውስ?
ዳዊት፡- ልዩነታቸው በዋናነት የደ
ጋፊው ጫና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን ስት
ወስድ ደጋፊው ውበት ነው፡፡ ውጤትን
አጥብቆ የሚፈልግ ለውጤትህም እንደ
12ተኛ ተጨዋች የሚያግዝህ ደጋፊ ነው፤
ተጨዋቹም ለውጤት በርትቶ እንዲሰራ
ለአፍታ እንኳን እንዳትዘናጋ ሁሌም የተሻለ
ነገር እንድትሰራ ጫና ውስጥ የሚከት
ደጋፊ ነው፡፡ መብራት ሃይል ጋር ስትመጣ
የምታገኘው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በመብራት
ሃይል የተወሰነ ደጋፊ እንኳን ያየሁት በ1993
ዓ.ም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ ነው፡
፡ ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት እኔ ራሴ
ተጋጣሚም፤ ተመልካችም፤ ተጨዋችም ሆኜ
አይቻለሁ፡፡ በደጋፊ ደረጃ ጫና ሲፈጠር እንደ
12ተኛ ተጨዋች ያህል ሲያግዙ አላየሁም፡፡
ኢት.ቡና ውስጥ ግን ታሪኩ ፍፁም የተለየ
ነው፡፡ ገና ከአምስትና አራት ጨዋታ በፊት
ስለ ጨዋታ፤ ስለድል ትጨነቃለህ ታስባለህ፡
፡ ቤተሰቦችህ በአንተ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ስለ
እግር ኳስ ያወሩሃል፤ “ዛሬ ከአንተ ይሄን
እንጠብቃለን፤ እንዲህ ብናደርግ፤ ባለፈው
በዚህ ነው የተሸነፍነውና” የመሰሰሉትን
ነገሮች እያነሱ ሲያወሩህ ጫና ውስጥ
ሃላፊነት ውስጥ ይከቱሃል፡፡ መብራት ውስጥ
ይሄ የለም፡፡፡ ብዙም ደጋፊ የላቸውም፡፡ ያም
ቢሆን ግን መብራት ሃይል ውስጥ ብዙ አሪፍ
አሪፍ ልጆች ስላሉ ያ ሁኔታ በራስህ አንድ
ነገር ለማድረግ እንድትነሳሳ ያደርግሃል፡፡
መብራት በሊጉ እንዲቆይ፤ ከዚህ ከፍ ሲል
ዋንጫ ለማንሳት እንድትመኝ ያለው ነገር
ያስገድድሃል፡፡ ቡድን ለቡድን ግን በሁለቱ
መካከል በዚህ በኩል ትልቅ ልዩነት አለው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢት.ቡና ውስጥ እያለህ “ዳዋ ለቡና
ይሰራል ገና” እየተባለ የሚዘመርልህ ተጨዋች
ነበርክ፤ መብራት ከመጣህ በኋላ ይሄን ነገር
አግኝተሃል?
ዳዊት፡- (በጣም ሳቀ) በመብራት ሃይል
እንዳልኩህ ነው፡፡ የደጋፊ ልዩነት ስላለ
ብዙም እንደዚህም አይነት ነገር አትሰማም፡
፡ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ግን እንኳን ተአምር
አሳይተህ ቀርቶ የእጅ ውርወራ ስትወርወር
እንኳን ስምህ ተጠርቶ ይዘመርልሃል፡፡
ደጋፊው የሚዘምርልህ ደግም ዳዊት ስለሆንኩ
ብቻ አይደለም፡፡ ከአንተ የሚፈልገውን ነገር
ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ደጋፊውን በጨዋታው
ስትማርከው፤ በእንቅስቃሴ የደስታ ባህር
ውስጥ ስታሰምጠውና ስምህን ጠርቶ
የሚዘምርልህ፤ እኔ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሁሌም በየጨዋታው ስሜ ከፍ ብሎ ሳይጠራ፤
ሳይዘመርልኝ የወጣሁበት ጊዜ አላስታውስም፡
፡ በዚህም ፍቅራቸውን ያለስስት የሰጡኝን፤
በአደባባይ ስሜን ጠርተው የዘመሩልኝን
ደጋፊዎችን ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
መብራት ሃይል ውስጥ ግን ይሄን ባልጠብቅም
ደስ የሚል አጋጣሚ ማግኘቴን ግን
አልደብቅም፡፡ የክለቡ የቀድሞው ተጨዋቾች
በሚገርም ሁኔታ አስተያየት ይሰጡናል፡
፡ መብራት ሃይል ገብቼ ካገኘሁት ትልቅ
ነገር አንዱ የቀድሞው የክለቡ ተጨዋቾች
ምክርና ድጋፍ ነው፡፡ ኳስ ተጫውተው ያለፉ
በመሆናቸው ደጋፋቸውና ምክራቸው ጉልበት
ይሆነናል፡፡
ሀትሪክ፡- ትናንት በአደባባይ የተዘመረልህ
ተጨዋች ነበርክ ዛሬ፤ ላይ ስምህ በመዝሙር
ሳይነሳ ሲቀር የሆነ ቁጭት ውስጥ የከተተህ ወይም
የጎደለህ ነገር ያለ ያህል እንዲሰማህ አላደረገህም?
ዳዊት፡- እውነቱን ልደብቅህ አልፈልግም፡
፡ የሆነ አንድ ትልቅ ነገር ያጣሁ ያህል
ይሰማኛል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች
የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታዎች አያለሁ፡፡
የደጋፊውን ሁኔታ ሳይ ወደ ኋላ በሃሳቡ ፈረስ
ጋልቤ ሜዳ ውስጥ የነበረውንና ሲዘመርለት
የነበረውን ዳዊት በቁጭት እንዳስታውሰው ነው
የሚያደርገኝ፡፡ በጣም ትልቅ ነገር እንዳጣሁ
ነው የምረዳው፡፡ በዚህም በጣም እቆጫለሁ፡
፡ ይሄንን ክብርና ፍቅር የትም አታገኘውም፡
፡ ደጋፊው ስምህን ጠርቶ ሲዘምርልህ
በውስጥህ አንዳች እሳት ነው የሚጫረው፡
፡ ለእነሱ በአፀፋው ምላሽ ለመስጠት
ትነሳሳለህ፡፡ ደጋፊው በሚሰጠኝ ድጋፍ እኔ
ብዙ ጊዜ ስሜታዊ ነው የምሆነው፡፡ ከዳኛ
ጋር የምጨቃጨቀው፤ የምነጫነጨውም
ደጋፊ ስለሚቀይረኝ ለእነሱ ምላሽ ለመስጠት
ስለምጓጓ ነው፡፡ በብዛት ግን ትልቅ የሞራል
ስንቅ ስለሚሆነኝ አልዋሽህም በዚህ በኩል
ትልቅ ነገር አጥቻለሁ፤ በውስጤም ትልቅ
ቁጭት አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እኮ የተዘመረልህን ያህል
“ዳዊት ከክለቡ በላይ አይደለም፤ ለምን ለዳዊት ብቻ ከሌሎች በተለየ ይደረጋል ወይም
ይዘመርለታል” የሚሉ ቅሬታዎችም ይቀርቡ ነበር፤
ይሄንንስ ታውቃለህ?
- ማሰታውቂያ -
ዳዊት፡- ልክ ነህ እንደዚህ አይነት
ለሁለት የተከፈሉ ሀሳቦች እንደነበሩ አስታ
ውሳለሁ፡፡ ለእኔ በዚያ መልኩ ስሜ እየተጠራ
መዘመሩ ኢት.ቡናን የበለጠ እንድጠቅም፣
ያለኝን ሁሉ ያለስስት እንድሰጥ ድጋፋቸው
ጉልበት ስለሆነኝ የዘመሩልኝን “ለምን ዘመራ
ችሁልኝ” ብዬ አልወቅሳቸውም፡፡ እንዲያውም
“እንዳከበራችሁኝ ክበሩ” ብቻ ነው የምላቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናን
ማሊያ ዳግም ለበሰህ እናይሃለን ወይስ የአንተና
የኢትዮጵያ ቡና እህል ውሃ አበቅቷል?
ዳዊት፡- እኔ ኢትዮጵያ ቡናን የቤተሰቤ
አካል ያህል አድርጌ ነው የማየው፡፡ ከኢትዮጵያ
ቡና ጋር የቤተሰብ ያህል ተዋደን ተፈቃቅረን
አሳልፈናል፡፡ ያ ፍቅራችንም የኮንትራት
ባለመሆኑ ዳዊት እንደ ቤተሰብህ በሚያየው
በኢትዮጵያ ቡና ላይ የሚጨክን አንጀት
ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አንዳንድ አመራሮችና ደጋፊዎች ጋር
ደግሞ ከአንተ በተቃራኒው የሚቆሙ አሉ፤ ለዚህስ
ምን ትላለህ?
ዳዊት፡- የውስጤን የልቤን ንገረኝ ካልከኝ
የክለቡን ማሊያ ዳግም ለብሼ ብጫወት ሁሌም
ደስታዬ ነው፡፡ ያም ባይሆን ግን ማለትም
ባልጫወትም ግን ሁሌም የምፅናናበትና
ከኢትዮጵያ ቡና ታሪክ ጋር ስሜ አብሮ
የሚነሳበት የራሴ ታሪክ ስላለኝ በጣም
ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔ ለስድስት አመታት ያህል
ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውቻለሁ፡፡ በእነዚህ
አመታት የአገሪቱን ትልቁን ዋንጫ አሸንፈን
ደጋፊውን አስደስተናል፤ ታሪክም አፅፈናል፡፡
የዚህ ወርቃማ ታሪክ ባለቤት የሆኑት አንዱና
ዋናው በመሆኔ የተለየ የኩራት ስሜት ነው
የሚሰማኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ለክለቡ ብጫወት ደስ
ይለኛል፡፡ ባልጫወትም ግን በክለቡ የማይፋቅ
ታሪክ ስላለኝ ሁሌም ሰድሰት ነው የምኖረው፡፡
ሀትሪክ፡- የመብራት ሃይል ቆይታህን እንዴት
ነው የምትገልፀው?
ዳዊት፡- – አዲሱን ክለቤን በሁለት
መንገድ ከፍዬ ነው የማየው፡፡ በመጀመሪያዎቹ
ልጆች አቅም ነበራቸው፤ አቅማቸውን
አውጥተው የሚጫወቱበት ሁኔታ ነው
የነበረው፡፡ በአብዛኛው ክለቡ የተገነባው
በወጣቶች ነው፤ ሲኒየር የሚባሉ ተጨዋቾች
በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ሲጀመር ሲቲ ካፑን
ሁሉ በማሸነፍ የተነቃቃ ነገር የታየበት ቡድን
ነበር፡፡ በኋላ ላይ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ግን
ሁለተኛው የመብራት ሃይል ገፅታ መጣ፡
፡ ፕሪሚየር ሊጉን ከልምድ ጋር ይያያዛል፤
ልምድ ያላቸው ልጆች በማነሳቸው በፕሪምየር
ሊጉ ብዙም ገፍተን አልሄድንም፡፡ ይሄ ትልቁ
ክፍተታችን ቢሆንም እስከ አሁን በፕሪምየር
ሊጉ ፍሰት ያለው እግር ኳስ የምንጫወተው
ግን እኛ ብቻ ነን፡፡ የሁሉንም የፕሪምየር ሊግ
ጨዋታዎች እከታተላለሁ፤ ጥሩ አይደለም
እያልኩኝ ሳይሆን እኛ ግን ኳስን ጀምረን
ለመጫወት ጥረት በማድረጋችን ጥሩ የኳስ
ፍሰት በብቸኝነት የምናሳየው እኛ ብቻ ነን
የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለየ መልኩ የበለጠን
ቡድን አላጋጠመኝም፡፡ ይሄ ደግሞ በመብራት
ቆይታዬ ይበልጥ እንድደሰት ካደረጉኝ ነገሮች
አንዱ ነው፡፡ ይሄን ነገር ግን በደንብ ማሳደግ
የሚችሉ ልምድ ያላቸው ልጆች ተካተው
ቢሆን የተሻለውን ተፎካካሪውን መብራት
ሃይልን እንፈጥር ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- አንተን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ
ተጨዋቾች ክለቡ ቢያስፈርምም መብራት
ዘንድሮም ልክ እንዳለፉት ዓመታት ላለመውረድ
ነው የሚታገለው፤ የዚህን ምስጢር ደርሰህበታል?
ዳዊት፡- ከላይ ከገለፅኩልህ የልምድ
ችግር በተጨማሪ በአሁኑ አመት ያየሁት
የመብራት ሃይል ትልቁ ችግሩ ተፅዕኖ
ውስጥ መወደቁ ነው፡፡ ላለፉት ሁለትና ሶስት
አመታት መብራት ላለመውረድ መጫወቱ
የቡድኑን ስነ-ልቦና እና የአሸናፊነት መንፈስ
ሰርቆታል፡፡ ዘንድሮ የተሻለ ተፎካካሪ መሆን
የሚያስችል አቅም ያለው ቡድን ይዘው
አዕምሯቸው እዚያኛው ተፅዕኖ ውስጥ ነው፡
፡ በተከታታይ ላለመውረድ መጫወቱ በስነ-
ልቦናው ረገድ ክፉኛ እንዳያገግምና እንዲጎዳ
አድርጎታል፡፡ ይሄንን የስነ-ልቦና ችግር
አስወግዶ ቡድኑ ውስጥ የአሸናፊነት መንፈስን
ለመመለስ ከሜዳ ላይ ስልጠና በተጨማሪ
ብዙ ስራ መስራትን ይጠይቃል፡፡ እኛ ሲኒየር
የምንባለው ተጨዋቾችም፤ ኮቺንግ ስታፉም
እየለፋን ያለነው ይሄንን መንፈስ ከቡድኑ
ውስጥ ለማጥፋት ነው፡፡ ከተጫወትናቸው
ወደ ሰባትና ስምንት በሚጠጉ ጨዋታዎች
ላይ ቀድመን የምናገባው እኛ ነን፡፡ አንዳንድ
ልጆች በስነ-ልቦና በመጎዳታቸው ልክ እና
እንዳገባን ጨዋታዎች ቢያልቅ ሁሉ ደስተኞች
የሚሆኑ ተጨዋቾች አሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የዚያ
ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡ እንዴት አሸንፈንም
ሆነ ውጤት አስጠብቀን መውጣት አለብን
የሚለው መንገድ የጠፋባቸው አሉ፡፡ ላለፉት
ሶስትና አራት አመታት መብራት ላለመውረድ
መጫወቱ ጉዳት ብቻ ሳይሆን መጥፎ ጠባሳም
አሳርፎበታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ማሳለፋችን ሳይ
ምነው በዚህ አመት ባልገባሁ የሚል ስሜትም
የተፈጠረብኝ ጊዜ አለ፡፡
ሀትሪክ፡- መብራት ሃይል በአሁኑ
ሰአት በሊጉ በ29 ነጥብ በ11ኛው ደረጃ ላይ
ነው የሚገኘው፡፡ ከዚህ በመነሳት መብራት
በእናንተ የተጨዋችነት ዘመን ይዋርዳል
ወይስ አይወርድም፤ ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጠኝ?
ዳዊት፡- በጭራሽ አይወርድም፡፡
ሀትሪክ፡- እንዴት…? አይወርድም ላልክበት
አሳማኝ መልስ አለህ?
ዳዊት፡- በወረቀት ደረጃ ውጤቱን
ስተመለከት እኛ ብቻ አይደለንም ከሰባተኛ ደረጃ
ጀምሮ ያሉት ቡድኖች ዋስትና የላቸውም፡፡
ግን ይሄ በወረቀት ስሌት ደረጃ ነው፡፡ እኛ
አሁን የምንገኝበት ደረጃ ብዙም ስለመውረድ
እንድናሳብና እንድንጨነቅ የሚያደርገን ነው
ለማለት ይቸግረኛል፤ ደህና የሚባል ደረጃ ላይ
ነው ያለነው፡፡ ወደታች ስለመውረድ ብዙም
የሚያሳስበን አይደለም፡፡ ከእኛ ከአራትና
አምስት ደረጃ ከፍ ብለው የሚገኙ ቡድኖች
31 እና 32 ነጥብ አካባቢ ነው ያሉት፡፡ አንድ
ጨዋታ ብዙ ነገር ይቀይራል፡፡ ከዚህ በኋላ
ያሉትን ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች በማሸነፍ
በተሻለ ደረጃ ላይ ሆነን እንደምናጠናቅቅ
እንጂ እንደምንወርድ ለሰከንድም አስቤም
አላውቅም፡፡ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው
ዳዊትም ሆነ መብራት በእኔ የተጨዋችነት
ዘመን ወረደ የሚባል ጎደሎ ታሪክ እንዲኖረን
አንፈልግም፡፡
ሀትሪክ፡- ዳዊት በግሉስ የዘንድሮው የውድድር
ዘመን አቋሙ በራሱ አንደበት እንዴት ነው
የሚገለፀው?
ዳዊት፡- እኔ ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ ወይም
በጣም ቶፕ የሆነውን ዳዊት እስጢፋኖስን
አሳይቻለሁ ባልልም ነገር ግን ባለፉት ሶስትና
አራት ዓመታት ወይም ድሬዳዋ እና ኢትዮጵያ
ቡና ከነበረው የተሻለውን ዳዊት እስጢፋኖስን
ፈጥሬያለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄን ያህል ትንሽ ስለ ራስህን
ያጋነንክ አይመስልህም?
ዳዊት፡- ስለ ራሴ የሌለኝን ነገር
በመመስከር የማምን ሰው አይለሁም፡፡ አሁን
ያለው ዳዊት በጣም የተለወጠው ዳዊት ነው፡፡
ቀደም ሲል በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እታማ
ነበር፡፡ ማጥቃቱ ላይ ተሳትፎው አናሳ ነው
እባልም ነበር፡፡ ዘንድሮ በመብራት ሃይል
ግን ይሄንን ሃሜት ያስወገደ እንቅስቃሴ ነው
የደረግኩት፡፡ ብዙ ጎል ባላገባም ፔናልቲ ቦክስ
አካባቢ በጣም እደርስ ነበር፡፡ ይሄ አዲሱ ነገሬ
ነው፤ ከዚህ ሌላ በማጥቃቱ ላይ ንቁ ተሳታፊ
ሆኜ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችንም አቀብል ነበር፡፡
መብራት ሀይል እንደዚህ የተጨዋች ከፍተት
ኖሮበት ራሱ ብዙ ጎሎችን አስቆጥረናል፤
ብዙ ጎልም አልገባብንም፤ ጥሩ ፍሰት ያለው
ኳስም እንጫወታለን፤ ይሄ ደግሞ የሚሆነው
በተወሰኑ ተጨዋቾች ነው፤ እኛ ደግም
በተወሰነ ደረጃ መብራት ሃይልን ረድተነዋል፡
፡ ዳዊት ደግሞ በተፈጥሮው የቡድን ተጨዋች
ነው፡፡ እኔን በግል በጣም ላታየኝ ትችላለህ፤
ቡድኔ ግን በጣም እንደንቀሳቀስ በማድረግ
ስራ ነው የምጠመደው፡፡ እኔ በራሴ መጥፎ
ወይም ዝቅ ያለ ሳይሆን ዘንድሮ ጥሩ ብቃት
አሳይቻለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እንዲህ የመሰከርክለት ዳዊት
እኮ ለብሄራዊ ቡድን ከተመረጡት 30 ተጨዋቾች
ዝርዝር ውስጥ ስሙን ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፡
፡ ጥሩ ከሆንክ ካለፉት ጊዜያት የተሻለው ዳዊት
ከተፈተጠረ እንዴት አገርህን ወክለህ እንድትጫወት
አልተጠራህም?
ዳዊት፡- እባክህ በዚህ በብሄራዊ ቡድን
ምርጫ ጉዳይ ባታነሳብኝ ደስ ይለኛል፡፡ አዎን
ለብ/ቡድን አልተመረጥኩም፤ በዚህም በጣም
አዝኛለሁ፡፡ በውስጤ ትልቅ ቁስል አለ፡፡
የመጣው አሰልጣኝ ሁሉ አገሬን እንዳላገለግል
ክፉ ፍርድ እየፈረደብኝ ነው፤ በዚህ
በጣም ነው የማዝነው፤ ውስጤም በእነዚህ
አሰልጣኞች ስራ ክፉኛ ተጎድቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ለምን አልተመረጥኩም ብሎ
እንደዚህ ዓይነት አስተያየት አለ እንዴ? እንደዚህ
ከማለትህ በፊት አሁን ያለህ ወቅታዊ ብቃት
ብሄራዊ ቡድን የሚያስመርጥ ነው?
ዳዊት፡- አሁን ያለኝ አቋሜ በብሄራዊ
ቡድን መመረጥ ብቻ አይደለም ቋሚ ተሰላፊ
ሆኜ መጫወት የምችልበት አቅም ነው ያለኝ፡፡
ግን አይናቸው የእኔን ችሎታ አያይም መሰለኝ
አልተመረጥኩም፡፡ በየጊዜው በሚመጡት
አሰልጣኞች አገሬን እንዳላገለገል ፍትሃዊ
ባልሆነ በምለው ምርጫቸው እገዳ እየጣሉብኝ
ነው፤ ይሄ ደግሞ በውስጤ ትልቅ ሃዘንን
ፈጥሯል፡፡
ሀትሪክ፡- ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ ነበረብኝ
በለሀል፤ ለምን እንዳልተመረጥክ አሰልጣኙን
ጠይቀኸዋል?
ዳዊት፡- እኔ በመብት አምናለሁ፤
የመምረጥ ሃላፊነት የተሰጠው አሰልጣኙ
ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አለመምረጥ መብቱ
ነው፡፡ እኔ ለምን አልመረጥኩኝም ብቻ
አይደለም ጥያቄዬ፤ ለምን ፍትሃዊ አይሆን
ነው እንጂ፡፡ ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ
ራሴን በአካል ብቃት፣ በስነ-ልቦናውም፣
በቴክኒኩም ጭምር በጣም ያዘጋጀሁበት፤
ከባለሙያዎች ከሚሰጠኝ አስተያየትም በጣም
በተሻለ ብቃት ላይ የምገኝበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ጥሩ ስሜት በሚሰማኝ፣ ከሌላው ጊዜ
በተሻለ አገሬን እረዳለሁ፣ ለውጤታማነት
የበኩሌን አደርጋለሁ ብዬ በተዘጋጀሁበት
ወቅት ተዘልያለሁ፡፡ የምርጫውን ውጤት
ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እውነቴን ነው
የምልህ ስሜቴ በጣም ተጎድቷል፡፡ ጥሩ ሆኜ
ካልተመረጥኩ ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ
ምንድነው የሚያስፈልገው የሚል ጥያቄ
በውስጤም ተፈጥሯል፡፡ ብቃቴን ከማሳየት
ውጭ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ? ለእኔ
ይሄ ነገር አልፈታ ያለ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡
፡ እንደውም አሁን አሁን አለመመረጤን
በተመለከተ ምን እንደተሰማኝ ታውቃለህ?
በቅርብ ጊዜ ሚዲያ ላይ ቀርበው “ለብ/ቡድን
መጫወት በቃን ያሉ ተጨዋቾች አሉ፡፡
ምናልባት እኔ ያልኩ መስሏቸው የዘለሉኝ”
ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እኮ አንተ ለብሄራዊ ቡድን
ስትመረጥ የቀረኸው ዘንድሮ ብቻ አይደለም?
ዳዊት፡- ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ የበለጠ
የቆጨኝ በጣም ጥሩ ብቃት ላይ የምገኝ
በመሆኔ ነው፡፡ ጥሩ ብቃት ላይ ሆኜ አገሬን
የማገልገል በውስጤ የሚንተከተክ ስሜት
እያለኝ አለመመረጤ አበሳጭቶኛል፤ ሙያዬን
እንድጠላውም እያስገደደኝ ነው፡፡ በየጊዜው
የሚሾሙት አሰልጣኞች የተለያየ ቅፅል ስም
እየሰጡ ከምርጫው ውጭ ያደርጉኛል፡፡ በሜዳ
ውስጥ ብቃቴ ብቻ መመዘን ሲገባኝ “ዳዊት
ይዝናናል፤ ይጠጣል፤ ይነጫነጫል” የሚሉ
ቅፅል ስሞችን እየሰጡኝ አገሬን እንዳላገለግል
ክፉ ፍርድ ይፈርዱብኛል፡፡ እውነት እናውራ
ከተባለ ከዚህ በፊትም የተመረጥኩት እኮ
በብቃቴ ታምኖብኝ ሳይሆን የቡና ደጋፊ
ተቃውሞን ለማብረድ ታስቦ ነው፡፡ ለዚህ
ማረጋገጫው ደግሞ ተመርጬ እንድሰለፍ
አልተደረግኩም፡፡ ተመርጠህ አለመሰለፍና
አገርህን አለግማገልገል ደግሞ ሁለተኛ ሞት
ነው፡፡ አገርን መወከል ስሜቱ ምን እንደሆነ
ይገባኛል፡፡ የህዝብ መዝሙር ሲዘመር፣
ባንዲራህ ሲውለበለብ ከማየትና አገርህን
ከመወከል በላይ ምን አለ? እኔ ይህንን ነው
አለአግባብ የተነጠቅኩት፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ከምትለው ውጪ
ያልተመረጥከው በቦታህ ከአንቱ የተሻሉ ተጨዋቾች
ስላሉ ቢሆንስ?
ዳዊት፡- የምናገረው ግልፅ ነገር ነው፤
ቁጭት ውስጥ የከተተኝም ይሄው ነው፤
በሌሎች በማልጫወትበቸው ቦታዎች ላይ
አልዘባርቅም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ
ግን በቦታዬ በሜዳ ላይ በሚታይ እንቅስቃሴ
ከእኔ የተሻለ ተጨዋች የለም፡፡ ይሄንን ስልህ
ግን መመፃደቄ አይደለም፡፡ እደግመዋለሁ
በቦታዬ ከእኔ የሚሻል ተጨዋች የለም፡፡
ደግሞስ ይሁን አለ ብሎ የሚከራከር ሰው ብቅ
ቢል እንኳን እኔ በምጫወትበት አታኪንግ
ሚድፊልደር እና በፕሌይ ሜከር ቦታ ላይ
ነው፤ እዚህ ቦታ ላይ 4 እና 5 ተጨዋቾች
ይስፈልጋሉ፡፡ አንደኛ ምርጫስ አልሁን፤
እንደተባለው እንዴት ሁለተኛ እና ሶስተኛ
ተመራጭ አልሆንም? ከዚህ በፊት በቦታዬ
የተሻሉ ተጨዋቾች ሲመረጡ እኮ አጨብጭቤ
ተቀብያለሁ፤ አሁን ግን ፍትሃዊ ባለመሆኑ
ነው የምናገረው፤ በጣም የሚገርምህና
ይበልጥ የሚያበሳጨኝ ደግሞ…
ሀትሪክ፡- ምንድነው የሚያበሳጭህ?
ዳዊት፡- ውስጤ የበለጠ በቁጭት
እንዲብሰለሰል የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ
አሰልጣኞች በክለብ አሰልጣኝነታቸው
ወቅት በተቃራኒ እኔ ያለሁበትን ቡድን
ሲገጠሙ የጨዋታ ስትራቴጂያቸው
በእኔ ላይ ጅምሮ በእኔ ላይ ማለቁ ነው፡
፡ “ዛሬ አሸንፈን ውጤት ይዘን መውጣት
ከፈለጋችሁ ዳዊትን ወጥራችሁ ያዙ፤ ዳዊትን
እንዳይንቀሳቀስ ካደረግነው ቡድኑ ይቆማል፤
እሱን ከለቀቃችሁት ኳስ እንዲይዝ ዕድል
ከሰጣችሁት ግን ጉድ ይሰራናል” እያሉ በእኔ
ለይ ታክቲካቸውን የሚነድፉ አሰልጣኞች
ወደ ብሄራዊ ቡድን ሲመጡ አይመርጡኝም፡
፡ ለምን እዛጋ “ዳዊትን ወጥራችሁ ያዙት”
ይላሉ? አንድ የሚያሳምን ነገር ስላለኝ
መሰለኝ፡፡ ታድያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሲመጡ
ለምን ይሄ ይጠፋቸዋል? በዚህ ስራቸው
ውስጤ በጣም ተጉድቷል፡፡ አገሬን አቅሜ
ጥሩ በሆነበት ሰአት እንዳላገለግል ክፉ ፍርድ
ተፈርዶብኛል፡፡ በአጭሩ አገሬን የማገልገል ስ
ሜቴን አሰልጣኞች ገድለውታል፤ ከሁሉም በ
ጣም የምታሳዝነኝ ግን አገሬ ኢትዮጵያ ናት፡፡
ሀትሪክ፡- ማለት?
ዳዊት፡- ኢትዮጵያ በጣም ታሳዝነኛለች፡
፡ አገሬ በጣም ተጎድታለች፡፡ ኢትዮጵያ
የተጎዳችው አንድ ዳዊት ስለተመረጠ
ስላልተመረጠ ሳይሆን በእንደዚህ አይነት ፍርደ
ገምድል ምርጫ ብዙ ተጨቸቾች አገራቸውን
እንዳያገለግሉ ስለ ተፈረደባቸው ነው፡፡ እኔን
ጨምሬ አገራቸውን ማገልገል የሚችሉ
በርካታ ተጨዋቾች እየባከኑ ነው፡፡ ሌሎች
ከሜዳ ውጪ ያሉ የማይመለከቱንን ቅጥያ
ስሞች እየሰጡን አገራችንን የምናገለግልበት
እድሜን እያባከኑብን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ይህ ሁኔታ በቀጣይ አገርህን
የማገልገል ስሜትህን ላይ ጉዳት ያደርሳል?
ዳዊት፡- ምን እሱ ብቻ? ለምን ኳስ
መጫወት የሚባል ነገርን አላቆምም
እስከማለት የምደርስው ብዙ ጊዜ ነው፡
፡ ዳዊት ከዓመት ዓመት እየተደቆሰ አገሩን
እንዳያገለግል እየተፈረደበት ነው፡፡ ይሄ
ከብሄራዊ ቡድን አይደለም ከእግር ኳሱ አለም
ጥፋ ጥፋ የሜል ስሜትም እየፈጠርብኝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጫማ ስለመስቀል ያሰብክበት ጊዜ
አለ ማለት ነው?
ዳዊት፡- እድሜዬ ኳስን በእውቀት
የምጫወትበት እንጂ ጫማ እስከመስቀል
የሚያደርስ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ግን
እንደዚህ አይነቱ ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ
ሲፈረድ ሳይ፤ የመጣው አሰልጣኝ ሁሉ
አገሬን እንዳላገለግል ሲፈርድብኝ ጫማ
መስቀል የሚለው ስሜት ይመጣብኛል፡
፡ ሁሌም የብሄራዊ ቡድን ምርጫ ሲመጣ
አዕምሮዬን በጥያቄ የሚወጥረው ለምን
ጫማህን ሰቅለህ አትገላገልም የሚለው ነው፡
፡ ከብሄራዊ ቡድን ምርጫ ውጪ ግን ስለዚህ
ነገር አስቤ አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት
ትጫወታለህ?
ዳዊት፡- ከእነ ሙሉ አቅሜ አምስት
ዓመትና ከዚያም በላይ መጫወት እችላለሁ፤
ግን አቅሜ ወርዶ መጫወት አልፈልግም፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ የማይረሳው ትዝታህ?
ዳዊት፡- 2003 ዓ.ም ነዋ፤ በፕሪሚየር
ሊጉ መሳተፍ ከጀመርኩ በኋላ ያገኘሁት አንድ
ዋንጫ ነው፤ እሱንም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር
በ2003 ዓ.ም፤ ያ መቼም የማይረሳ አመት
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አብረሃቸው ከተጫወትካቸው
ተጨዋቾች ሜዳ ላይ በጣም የሚረዳህ?
ዳዊት፡- በተለያዩ ክለቦች ከአንድና ሁለት
ዓመት በላይ አልተጫወትኩም፡፡ ኢትዮጵያ
ቡና ስድስት አመት መመጫቴ ግን ከአንድ
ሰው ጋር በደንብ እንድግባባ አድርጎኛል፤
ከመስዑድ መሐመድ ጋር፡፡ ከመስዑድ ጋር
በእግር ኳስ በጣም ነው የምንተዋወቀው፡፡
ስለምንናበብ ሁሌም አብረን ብንጫወት ብለህ
የምትመኘው ተጨዋች ነው፡፡ ከእሱ ሌላ
መድሃኔ ታደሰ፡፡ እሷም ልዩ ናት፡፡ ገና እግሬ
ጋር ኳስ ሳይገባ የት ጋር እንደምሰጠው
ስለሚያውቅ ቀድሞ ይጠብቀኛል፡፡ የእኔን
ኳሶች በጣም ነው የሚረዳቸው፡፡ ሌላው
በጣም ያጣሁት ተጨዋች በረከት አዲሱ ነው፡፡
ባንክ አብረን ተጫውተናል፤ እሱም ይረዳኛል፡
፡ አቅሙ በጣም ከባድ ተጨዋች ነው፤ እሱን
በማጣቴ በጣም ነው የሚቆጨኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ቀጣዩ ዕቀድህ የሚለው የመለያያ
ጥያቄያችን ቢሆንስ?
ዳዊት፡- የኢትዮጰያ እግር ኳስ እንዲድግ
ለውጥ እንዲመጣ የምፈልግ ሰው ነኝ፤
እንደ እኔ ዓይነት የእግር ኳሱ ሰለባ ሆነው
አገራቸውን እንዳያገለግሉ በአሰልጣኞች
የተፈረደባቸው ተጨዋቾች አሉ፡፡ ይሄ ነገር
እኔና በእነሱ እንዲያበቃ ለለውጥ የመስራት
እልሁ በውስጤ አለ፡፡ አብዛኛውን ህይወቴንም
ለእግር ኳስ የሰጠሁ ሰው በመሆኔ ከእግር ከስ
ውጪ ማሰብ አልፈልግም፡፡ የጨዋታ ዘመኔ
ሲጠናቀቅ ከእግር ኳስ መራቅ ስለማልፈልግ
በአሰልጣኝነቱ ብቅ የማለት ዕቅድ አለኝ፡፡
ቂመኝነት፤ ጥላቻን ከእግር ኳሱ ለማጥፋት
ጥረት ከማድረግ ውጪ በስልጠናው ብቅ
ብዬ ፍሰት ያለው፣ ንፁህ የሆነ፣ በታክቲክ
ያልታጠረ እግር ኳስ እንዲኖር እጥራለሁ፡
፡ እውነቴን ነው የምልህ ለአዲስ አበባ
ተመልካች በጣም ነው የማዝነው፡፡ ተመልካቹ
የሚያዝናና ኳስ ለማየት አልታደለም፡፡ ከሚ
ወደው ክለብ ውጪ ኳስ አያይም፡፡ ኢትዮጵያ
ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወቱ ነው ጠጠር
መጣያ ቦታ የሚጠፋው፡፡ ይሄ ደግሞ የሜዳ
ላይ እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ሆኖ ሳይሆን
ክለባቸውን ስለሚወዱ ብቻ ነው፡፡ እኔ አሁን
መብራት ሃይል እየተጫወትኩ ከጋዜጠኛና
ከፖሊስ ውጪ ብዙ ሰው ጨዋታችንን ገብቶ
አያይም፡፡ በአጭሩ ሰው እንደ ፊልም እየመረጠ
ነው ጨዋታ የሚያየው፡፡ ይሄ እንዲቀር
አዝናኝና ፍሰት ያለው እግር ኳስ በሚኖርበት
ዙሪያ ራሴን መስዋዕት ለማድረግ፤ እንደ
እኔ የተበደሉ ተጨዋቾችን ነፃ ለማውጣትና
በድሉን በቃ ለማለት የጨዋታው ዘመኔን
ስጨርስ ወደ ስልጠናው አለም የመምጣት
ዕቅዱ በትልቁ አለኝ፡፡