“ከፋሲል ከነማ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ዋንኛው እልሜ ነው” ሀብታሙ ተከስተ /ፋሲል ከነማ/

ለፋሲል ከነማ በመሀል ሜዳው ላይ በመጫወት እና ክለቡንም በጥሩ መልኩ በማገልገል ይታወቃል፤ ይኸው ወጣት የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀብታሙ ተከስተ /ጎላ/ም ይባላል፤ ሀብታሙ በሜዳ ላይ ባለው የኳስ ብቃቱ ብዙዎቹ የሚያደንቁት ተጨዋች ሲሆን ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል በሚልም በበርካታዎች ዘንድ ግምትም ተሰጥቶታል፤ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ከዚህ ተጨዋች ጋር ስለኳስ ህይወቱና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አውርቶት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ጅማሬህ ምን ይመስላል?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት የጎንደር ከተማ ውስጥ ሲሆን ሜክሲኮ በሚባል ሜዳ ላይም ነው ልጅ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር ለመጫወት የቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- በልጅነታችሁ የተጫወታ ችሁበት ሜክሲኮ ሜዳ እንዴት ስያሜውን ሊያገኝ ቻለ?
ሀብታሙ፡- ስለ ሜዳው ያኔም ሆነ በኋላ ላይ ካደግኩኝ በኋላ ኳስን ስለመጫወቴ እንጂ ስለ ስሙ ትርጓሜ እንኳን ፈፅሞ አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- በጎንደር እንደ መወለድህ አካባቢያችሁ ልዩ መጠሪያ አለው?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ ብልኮ ነው የሚባለው፤ ስለዚህ መጠሪያ ስያሜም የተወለድኩበት አካባቢ ከመሆኑ ውጪ ሌላ ምን ማለት እንደሆነ አሁንም ድረስ አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ከቤተሰብ ተደብቀህ ወይንስ ተፈቅዶልህ?
ሀብታሙ፡- በራሴ ፍላጎት ነበር ኳስን የምጫወተው፤ ኳስን አትጫወት፤ ተው ይቅርብህ የሚለኝ ቤተሰብ ፈፅሞ ስላልነበር በእዚሁ ነው ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት ዓለም ውስጥ ዘልቄ ለመግባት የቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስክበት ደረጃ የቤተሰብህ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ እነሱ ትጥቅ ከመግዛት አንስቶ ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችንም ያደርጉልኝ ስለነበር የእነሱን ውለታ መቼም ቢሆን ፈፅሞ አልረሳሁም፡፡
ሀትሪክ፡- በልጅነት ዕድሜህ የእግር ኳስን ስትጫወት ለትልቅ ደረጃ እደርሳለው ብለህ ነው?
ሀብታሙ፡- በፍፁም፤ በዛ ደረጃ አላሰ ብኩም፤ ምክንያቱም ኳስን በዛ ሰዓት የምትጫወተው ለስሜት እና ለእርካታ ስለሆነም ነው፤ እያደግክ ስትመጣ ግን ሌሎች ተጨዋቾች ስለደረሱበት ደረጃ ምኞትን ታሳድራለህና በዛ መልኩ ነው እኔም ለመጫወት የቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በየት ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
ሀብታሙ፡- ከባድ ጥያቄ ነው፤ ሁሌም ኳስን ስለመጫወት ብቻ ነበር ሳስብ የነበርኩት፤ ምንአልባት ግን ይመስለኛል ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ ልሆን የምችለው በትምህርቴ ድራፍቲንግ ሙያ ዲፕሎማ ስላለኝ እሱን አሳድጌ እና ወደ ድግሪ ደረጃም ወስጄ በዛ ስራ ውስጥ የምሰማራ ሰው እሆን ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ሜዳው ላይ ስንመለከትህ በተክለ ሰውነትህ ቀጠን ያልክ ነህ፤ በኳስ ህይወትህ ላይ ይህ ተፅህኖን አሳድሮብህ ያውቃል?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ እንደዛም ሆኖ ደግሞ በአንድ በኩል ደግሞ የጠቀመኝም ነገር አለ፤ የሚገርምህ ይህ የሆነው ለዳሽን ወጣት ቡድን በምጫወትበት ሰዓት ነው፤ ያኔ የመጀመሪያው ዓመት ላይ 5 ልጆች ወደ ዋናው ቡድን አድገው ነበር፤ እኔ ደግሞ አላደግኩም፤ ቀጭን ስለሆንኩ ነው ያላደግኩት፤ ይህ በጊዜው ተፅህኖ ሊፈጥርብኝ ቢችልም ከዛ አሰልጣኛችን ተገኝ እቁባይ ጥሩ ሰው ነበርና ለምን እንዳላደግኩ ስጠይቀው የአንተ ሰውነት ቀጭን ነው፤ ስለዚህም ወደ ላይ ሄደህ በአንዴ እንድትጠፋ ስለማልፈልግ፤ እዚህ ሆነህም በደንብ መስራት ስላለብህ ለዛ ነው ያቆየሁክ ሲለኝ ያን ተቀብዬና ጠንክሬም ሰርቼ ነው ለዛሬው ደረጃ ልደርስ የቻልኩትና አንድ አንዴ እንደዚህ ያሉ ጥቅሞችን የምታገኝበት ሁኔታም አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ከጥቂት ዓመታት በፊት የፈረሰው ዳሽን ቢራ የመጀመሪያ ክለብህ ነበር ማለት ነው?
ሀብታሙ፡- ዳሽን ቢራ አዎን፤ እዛም ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣት ቡድኑ ደረጃ የተጫወትኩት፤ ከዛም ወደ ዋናው ቡድን በጊዜው አሰልጣኝ በነበረው ሳምሶን አየለ አማካኝነት አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ማለትም የእኛ ወጣት ቡድን ከጎንደር ዩንቨርስቲ ቡድን ጋር ስንጫወት አይቶኝ እኔንና የሰበታ ከተማ ግብ ጠባቂ የነበረውን ፋሲልን ከወጣት ቡድኑ ማደግ አለባቸው በሚል አሳደገንና ዳሽን ቢራ ነው የመጀመሪያ ክለቤ፡፡
ሀትሪክ፡- ለዳሽን ቢራ ያደረግከውን የመጀመሪያ ጨዋታህን ታስታውሳለህ?
ሀብታሙ፡- መች አድርጌ፤ በዛን ወቅት ወደ ዋናው ቡድን ላድግ ብችልም የመጫወት እድሉን እንኳን አላገኘውም፤ ያ የሆነውም ክለቡ በወራጅ ቀጠና ላይ ይገኝ ስለነበርና የአሰልጣኞቹ ትኩረት ደግሞ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ላይ ስለነበር በዛ የተነሳ ነው ለመጫወት ያልቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ዳሽን ቢራን በአጠቃላይ የለቀቅከው ምንም ሳትጫወት ነው ማለት ነው?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ ያኔ 5 ጨዋታ እየቀረ ቡድኑ ተቀጥቶ ነበር፤ ከሜዳው ውጪም አንድ አንድ ጨዋታዎችን እንዲያደርግም ውሳኔ ተላልፎበትም ነበርና ወደ አዳማ ከተማ ለመሄድ በቻለበት ጊዜ እኔ፣ አማኑሄል ገብረ ሚካሄል እንደዚሁም ደግሞ ግብ ጠባቂያችን ፋሲል ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሙከራ ተብለን በሄድንበት ሰዓት ደብረ ብርሃን ከነማዎች አዩንና እኔንና የአሁን ሰዓት ላይ ለመቐለ 70 እንደርታ የሚጫወተውን አማኑኤልን ወሰዱን፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ጉዞዬም የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታዬን ያደረግኩት የደብረ ብርሃን ከተማ ተጨዋች ሆኜ ከቡራዬ ከተማ ጋር የተደረገውን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከአንተ ጋር ከዳሽን ወጣት ቡድን ጀምሮ አብሮህ የተጫወተው አማኑኤል ገ/ሚካኤል እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የመመረጥ እና የመጫወት እድልን አግኝቷል፤ አንተንስ በዛ ደረጃ መቼ እንመለከትካለን?
ሀብታሙ፡- በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከዚህ በፊት ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ብሔራዊ ቡድናችን የመመረጥ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ባላወቅኳቸው አንድ አንድ ጉዳቶች ሳልጫወት ልቀር ችያለው፤ በሌላ አጋጣሚም በአሰልጣኞች ደረጃ ተዘጋጅ ልትመረጥም ነው እየተባልኩም የቀረሁባቸው ወቅቶችም አሉና ከዚህ በኋላ እነዛን ነገሮች ረስቼ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ለወደፊቱ ይሄን የመመረጥ ዕድልን አግኝቼ ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ ጥሩ እንቅስቃሴን በሜዳ ላይ ከሚያሳዩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ አንተ ነህ፤ ከዚህ በመነሳት በኳሱ አሁን ላይ የላቀ ደረጃ ላይ ነው የምገኘው ማለት ትችላለህ?
ሀብታሙ፡- ለፋሲል ከነማ በምጫወትበት ሰዓት ብዙ ጊዜ ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ ሰዎች ጥሩ ተንቀሳቅሰካል ይሉኛል፤ እንደዛ ቢሉኝም እኔ ግን በኳስ ተጨዋችነቴ የማስበው ከዚህ በላይ ተጫውቼና ችሎታዬንም አሳድጌ መገኘት ነው የምፈልገው እንጂ ራሴን ክቤ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሻለው የምል አይነት ተጨዋች አይደለውም፡፡
ሀትሪክ፡- ለመቐለ 70 እንደርታ የሚጫወተው አማኑኤል ገ/ሚካሄል ለአንተ የቅርብ ጓደኛህ እንደሆነ ሰማን?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ የእውነት ነው፤ ከእሱ ጋር ለአምስት ዓመታት ያህል በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ማለትም በዳሽን ቢራ ወጣት ቡድን፣ በደብረብርሃን ከተማ ቡድንና በመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ውስጥ አብረን ተጫውተናል፤ በቆይታችንም ጊዜያችንን በጥሩ ሁኔታም አሳልፈናል፤ ከዛ ባሻገርም በእግር ኳስ ዓለሙ አሁንም ድረስም እሱ የእኔ ጓደኛም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመቐለ 70 እንደርታ እና በፋሲል ከነማ ያሳለፍካቸውን የእግር ኳስ ጊዜዎችህን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
ሀብታሙ፡- በሁለቱም ክለብ የተጨ ዋችነት ቆይታዬ ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፤ መቐለ በነበርኩበት ሰዓት ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲሸጋገር ከማድረግ ባሻገር የቀጣይ ዓመቱ ላይ ገና በመጣንበት ወቅት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እስከመፎካከር ደረጃ የደረስንበት እና አራተኛም የወጣንበት ውጤት የሚገለፅ ሲሆን በፋሲል ከነማ የሁለት ዓመት ቆይታዬ ደግሞ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት የተሰራው ቡድን ጥሩ እግር ኳስን ተጫውቶና ውጤታማም የሆነን ቡድንን ገንብቶ ለጥቂት በሚባል የራሳችን ስህተቶች ዋንጫውን ለማግኘት ሳንችል ሶስተኛ ለመውጣት የቻልንበት እና ዘንድሮ ደግሞ ለሁሉም ክለብ አስፈሪ በመሆን ጭምር የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየመራን በኮቪድ 19 ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ ምርጥ ቡድን ነበርንና የእዚህ ቡድን የእስካሁኑ ቆይታዬ በጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫም የታጀበ ስለነበር ቆይታዬ በጣም አስደሳች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያጣው በራሱ ችግር እና ስህተቱ ብቻ ነው?
ሀብታሙ፡- በስፖርት ዓለም ውስጥ መጀመሪያ ጥፋተኛ ማድረግ ያለብህ ራስህን ነው፤ ምክንያቱም የራሳችንን ነገር ብናስተካክል ኖሮ ሌሎችን ነገሮች መሸፈን እንችል ነበርና፤ እኔ በግሌ የራሳችን ችግር ነው ዋንጫውን አሳጥቶናል ብዬም የማስበው ያኔ በተለይ በሜዳችን ላይ የምናደርጋቸውን አንድ አንድ ጨዋታዎች ነጥብ የምንጋራበት አጋጣሚ ስላለ እነዛ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊ ይለያል?
ሀብታሙ፡- በጣም እንጂ ስለ እነሱ ለመናገር ቃላትም የለኝም፤ ድሬዳዋ ለመጫወት ስንሄድ ለሁለት ቀናት እንቅልፍ ሳይተኙ ጭምር በመምጣት የሚደግፉን ናቸው፤ ረጅም ጉዞ ያለበት ስፍራና በሜዳችንም ስንጫወት ሁሌም ከጎናችን ስላሉ እና ብርታትም ስለሚሆኑን በጣሙን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ኳሱ ቆመ፤ እስካሁን ያለውን ጊዜ እንዴት እና በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?
ሀብታሙ፡- ጠዋት ተነስቼ ስፖርት እሰራለው፤ ሌላውን ጊዜ ደግሞ በቤቴ ሆኜም ሆነ ወደ ውጪ በምወጣበት ሰዓት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ነው የማሳልፈው፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ሰዓት የናፈቀህ ነገር ምንድን ነው?
ሀብታሙ፡- የፋሲል ከነማን ማልያ በማድረግ በምርጦቹ ደጋፊዎች ፊት መዝሙራቸው እየተዘመረ ኳስን መጫወት ነው በጣም የናፈቀኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከባህር ማዶ ተጨዋቾች የምታደንቀው?
ሀብታሙ፡- የባርሴሎናውን ቡስኬት ነዋ! እሱ ለእኔ ልዩ ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ሊቨርፑል የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከ30 ዓመት በኋላ አንስቷል፤ ይገባዋል?
ሀብታሙ፡- በጣም፤ ያለቸውን ሁሉ አውጥተው ስለሚጫወቱም ድሉ ሲያንስ ባቸውም ነው፤ ጥሩ ቡድንም ነው ያላቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ ምርጡ ጥምረትህ ከማን ጋር ስትጫወት ነው?
ሀብታሙ፡- ምርጡ ጥምረቴ ከሱራፌል ዳኛቸው እና ከበዛብህ መላዬ ጋር ስጫወት ነው፤ ከእነሱ ጋርም በሜዳ ላይ በጣምም ነው የምንግባባው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ሀብታሙ፡- በፋሲል ከነማ ቆይታዬ አሁን ላይ ክለቡም ደጋፊውም እያሰበ ያለው ነገር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነውና ያን ድል ከክለቡ ጋር ማሳካት እፈልጋለው፤ ሀገሬንም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተጫውቼ ማገልገልና በፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም መጫወትን እፈልጋለው፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ደግሞ በኳሱ አሁን ላይ ለደረስኩበት ስፍራ መጀመሪያ የአምላኬን እናት ድንግል ማሪያምን የፋሲል ከነማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችንና ከእኔ ጎን የሆኑትን ሁሉ በጣም አመሰግናቸዋለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website