መነሻ ገጽ ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ ​ከአንድም ሶስት ቡድኖችን ወደ ፕሪምየር ሊግ እያሳደኩ መሰናበቴ አልፈታ ያለኝ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል”     አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ (የጅማ ከነማ ዋና አሰልጣኝ)
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

​ከአንድም ሶስት ቡድኖችን ወደ ፕሪምየር ሊግ እያሳደኩ መሰናበቴ አልፈታ ያለኝ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል”     አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ (የጅማ ከነማ ዋና አሰልጣኝ)

አጋራ
አጋራ


“ሰው የለፋበትን በመንጠቅ ዛሬ ኪሳችን ሊደልብ፣ 

ሆዳችን ጠግቦ ሊያድር ይችላል፤ ሁሌም ግን 

የሕሊና እስረኛ እና ተወቃሽ ከመሆን አንድንም”

– “የእኔ ድክመትና ለስንብት የሚያበቃኝ ውጤት 

ማምጣቴ ብቻ ነው ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ”

አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ (የጅማ ከነማ ዋና አሰልጣኝ)

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በእልህ 
አስጨራሹና በፈታኙ የሱፐር ሊግ ውድድር 
ከአንድም ሶስት ጊዜ ቡድኖችን ወደ ላይ 
በማሳደጉ “The Promotion Expert” የሚል 
ቅፅል ስምን ለማግኘት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ 
ውሃ ስፖርትን፣ ዳሽን ቢራን እና አሁን 
ደግሞ የጅማ ከነማን ቡድንን ሱፐር ሊጉ 
ላይ ባለው ምትሃታዊ ጥበቡ ከህልማቸው 
ጋር በማገናኘት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ 
ሶስት ቡድኖችን ወደ ላይ በማውጣት ሀትሪክ 
ሰርቷል፡፡ የጅማ ከተማ ቡድን በእግር ኳስ 
ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ታላቁ ሊግ 
በመቀላቀልና የእልህ አስጨራሹና ፈታኙን 
የሱፐር ሊግ አጠቃላይ ሻምፒዮን በማድረግ 
በታሪክ ላይ ታሪክ ማፃፉን የቀጠለው 
አሰልጣኝ መኮንን ገ/ዮሃንስ ባገኘው ድል 
ተደስቶ ሳያባራ ለአዲስ ታሪክ ካበቃው ክለቡ 
እንደሚሰናበትና በምትኩ ሌላ አሰልጣኝ 
እንደ ተተካ በስፋት መናፈሱ ውጤታማውን 
አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን ዜናውን የሰሙትን 
ሁሉ አስደንግጧል፡፡ 
“ውጤት ባመጣሁ ማግስት ከክለቡ 
መሰናበቴና በሌላ መተካቴ ለእኔም 
ለራሴም አልፈታ ያለኝ እንቆቅልሽ ሆኖብኝ 
ተቸግሬያለሁ፤ ለምን የዚህ ዓይነቱ ችግር 
ሰለባ እንደምሆን አላውቅም” በማለት 
የሚናገረው አሰልጣኝ መኮንን ከክለቡ 
ሊሰናበት ነው በሚለው፣ ክለቦችን ወደ ላይ 
እያሳደገ ስለ መሰናበቱ፣ ስለ ቀጣይ ዕቅዱ 
እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሁለት 
የተዘበራረቁ ስሜቶች ውስጥ ሆኖ ከሀትሪክ 
ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ 
በላይ ጋር ከዚህ በታች ያለውን ቃለ-ምልልስ 
አድርጓል ፡፡
ሀትሪክ፡- በመጀመሪያ የጅማ ከነማን ቡድን 
ወደ ፕሪምየር ሊግ በማስገባትህ፤ የሱፐር ሊግ 
የዋንጫ አሸናፊ እንዲሁም በይፋ ባልገልፅም 
የዘንድሮው የውደድር ዘመን የሱፐር ሊግ ኮከብ 
አሰልጣኝ ሆነህ በመመረጥህ እንኳን ደስ አለህ?
መኮንን፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን…!


ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ 
የጅማ ከነማ እግር ኳስ ቡድን በአገሪቱ ትልቁ 
ሊግ ውስጥ እንዲሳተፍ የሱፐር ሊግ ዋንጫን 
በታሪክ ለመጀመሪያው ጊዜ እንዲያነሳ በማድረግህ 
በውስጥህ የተፈጠረውን የደስታ ስሜት እንዴት 
ትገልፀዋለህ? 
መኮንን፡- የጅማ ከነማ ድል ብዙ 
ትርጉም ያለው ድል ነው፤ በአካባቢው የነበረ 
ሌላ ወኪል ክለብ ከፕሪምየር ሊጉ ወርዶ፣ 
ጅማ ላይ በፕሪምየር ሊጉ ውክልና የማጣት 
ሰጋት ባንዣበበት ወቅት የተገኘ ድል በመሆኑ 
በውስጥህ የማያባራ የተለየ የደስታ ስሜት 
እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የጅማ ከነማ በአገሪቱ 
ትልቁ ሊግ ውስጥ ተወካይ ያሰፈለገው ነበርና 
ይሄ ደግሞ በእኔ ቡድን በመሳካቱ በእኔም 
በህዝቡ ስሜት ውስጥም የተለየ ደስታን 
ፈጥሯል፡፡ ጅማ አባቡና በመውረዱ ውክልና 
አጣን በሚል አንገቱን ለደፋው ህዝብ ትልቅ 
መፅናኛ የሚሆን ድል በመመዝገቡ በቃላቶች 
ለመግለፅ የሚከብድ የደስታ ስሜት ነው 
በሁላችንም ልብ ውስጥ የተፈጠረው፡፡ 
ሀትሪክ፡- ጅማ ከነማን ወደ ፕሪምየር ሊግ 
ስታሳልፍ 3ተኛው ክለብ ነው፤ በኢትዮጵያ እግር 
ኳስ ሶስት ክለቦችን ወደፕሪምየር ሊግ በማውጣት 
ሀትሪክ የሰራህም ብቸኛው አሰልጣኝ ሆነህ በታሪክ 
መዝገብ ላይ በመመዝግብህስ ምን ትላለህ?
መኮንን፡- ይሄ እንዲሆን የፈቀደው 
የፈጠረኝ አምላክ ነው፤ ሶስት ክለቦችን ማለት 
ውሀ ስፖርትና ዳሽን ቢራን በ2004 እና 
በ2005 በተከታታይ ዓመት እንዲሁም አሁን 
ደግም ጅማ ከነማን ከዘመናት ህልማቸው ጋር 
አገኛኝቻለሁ፤በዚህ ስኬትም እኔም ክለቦቹም 
የየራሳችንን ደማቅ ታሪክ በኢትዮጵያ እግር 
ኳስ ውስጥ አፅፈናል፤ በዚህ በጣም ነው 
የምደሰተውና የምኮራው። እጅግ ፈታኝና እልህ 
አስጨራሽ በሆነው የሱፐር ሊግ ውድድር ላይ 
ከአንድም ሶስት ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊግ 
ማሳለፍ ለአንድ ለማደግ እየተፍጨረጨረ ላለ 
ትንሽ አሰልጣኝ ትርጉሙ በጣም ብዙ ነውና 
ይሄ እንዲሆን የፈቀደውን አምላኬን ደጋግሜ 
ማመስገን እወዳለሁ፡፡ 
ሀትሪክ፡- ሶስት ክለባችን ማለትም ውሀ 
ስፖርት፣ዳሽን ቢራን አሁን ደግሞ ጅማ ከነማን 
ከሱፐር ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳለፍህን 
የተመለከቱ “The Promotion Expert” የሚል 
ስያሜ ሰጥተውሃል፤ ይሄንን ስያሜ እንዴት 
እገኘኸው? ወይም እንዴት ነው የምታስተናግደው?
መኮንን፡- እኔ ራሴን በዚህ ደረጃ ወይም 
በዚህ ታላቅ ስያሜ ለመጥራት እቸገራለሁ፤ነገር 
ግን ሰዎች ወይም ባለሙያተኞች ከአንድም 
ሶስት ቡድኖችን ከሱፐር ሊግ ወደ አገሪቱ ታላቅ 
ሊግ ማሳደጌን ተመልተው “ይገባዋል” ብለው 
ስያሜውን ከሰጡኝ ግን ከታላቅ ምስጋናና ክብር 
ጋር እቀበላለሁ፡፡“The Promotion Expert” 
ብለው ይሄንን ስያሜ የሰጡኝ ሰዎች በሙሉ 
አፋቸው ለመጥራት የደፈሩበት የራሳቸው 
ምክንያትና ሚዛን አላቸው ብዬ ስለማምን 
ስያሜው ከባድና የበለጠ ለሌላ ሃላፊነት 
የሚያነሳሳ በመሆኑ በከፍተኛ የደስታ ስሜትና 
ምስጋና ጋር እቀበለዋለሁ፤ ብዘ ሰዎች የእኔን 
ስኬታማነት ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳለፍኳቸው 
ሶስት ክለቦች ጋር ብቻ አያይዘው ያነሳሉ እንጂ 
ከዚህ ሌላም ስኬት አለኝ…
ሀትሪክ፡- …ከሶስቱ ታላላቅ ስኬቶችህ 
ውጪ…?
መኮንን፡- …ምንአልባት ከውድድሮቹ 
ልዩነትና ከስያሜው አንፃር እንደሆነ አላውቅም 
እንጂ የባህር ዳር ከነማን ቡድን ከሶስተኛ 
ዲቪዚዮን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን በማሳለፍ 
የራሴ የምለው ሌላ ትልቅ ታሪክ አለኝ፡፡ 
የባህር ዳር ከነማ ቡድን አሁን ለሚወዳደርበት 
ሊግ የበቃውና ከታች ወደ ላይ ያደገው በእኔ 
የአሰልጣኝነት ዘመን ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ 
በ2008 ዓ.ም ቡድኑን ስቀላቀል ከነበረበት ሊግ 
ወደ ላይ ከፍ ከማድረጌ በተጨማሪ የአማራ ሲቲ 
ካፕ አሸናፊ እንዲሆን አድርጌያለሁ፤የኢትዮጵያ 
ውሃ ስፖርት አሰልጣኝ እያለሁም ቡድኑን ወደ 
ፕሪምየር ሊግ ከማሳለፌ ውጪ ወደ ብሄራዊ 
ሊግ በወረደበት ዓመት በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ 
ተጋባዥ ቡድን ሆነን ከ7 የአዲስ አበባ ቡድኖች 
ጋር ተወዳድረን ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ 
ሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተሸላሚ ሆነናል፡
፡እነዚህ ለስልጠና ህይወቴ ለስራዬ የበለጠ 
ጉልበት የሆኑኝ ትላልቅ የምላቸው ሰኬቶች 
ናቸው፡፡ 
ሀትሪክ፡- ከአንድም ሶስት ክለቦችን ወደ 
ፕሪምየር ሊግ አሳድገሃል፤ ይሄ ደግሞ በሌሎች 
አሰልጣኞች ያልታየ ነውና ለዚህ ስኬት የምትበቃበት 
ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚወስድህን መንገድ ከሌሎች 
በተለየ ያወክበት የተለየ ምስጢር አለህ?
መኮንን፡- የተለየ ምስጢር የምለው ሁል 
ገዜም ለስራዬ የተለየ ቁርጠኝነት መኖሩንና 
ታታሪነቴን እንዲሁም የፈጠረኝ አምላክ ስራዬን 
መባረኩና ለፍሬ ማብቃቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ 
ውጪ የተለየ የምለው ምስጢር የለኝም፡፡ 
ሀትሪክ፡- እስቲ አንድ ድፍረት ያለው 
የሚመስል ጥያቄ ልጠይቅህ የዘንድሮው የሱፐር 
ሊግ ዋንጫ የማነው…?
መኮንን፡- እንዴ… የእኛ ነዋ…! 
ሀትሪክ፡- ጥያቄዬን ፍርጥ ሳደርገው 
የዘንድሮው ድል የመኮንን ነው? ወይስ ከአንተ 
በፊት የነበረውና አንደኛውን ዙር በመሪነት 
የጨረሰው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና? በዚህ ነገር 
ላይ በሁለት የተከፈሉ ሃሳቦችን ስለሚሰሙ ነው?


መኮንን፡- (ፈገግ አለ) እንግዲህ እውነት 
ለመናገር ለዚህ ታሪካዊ ድል አስተዋፅኦ ያደረጉ 
በርካታ አካላቶች አሉ፤ሁሉንም የስኬቶች 
ምክንያት ለአሰልጣኝ ብቻ ሰብስቤ አልሰጥም። 
ተጫዋቾች፣ የክለቡ አመራሮች፣ ደጋፊዎች፣ 
እኔም ራሴ፣ እንደ መጀመሪያ አሰልጣኝ ክፍሌ 
ቦልተናም በዚህ ድል ውስጥ የየራሳቸው ድርሻ 
እንዳላቸው መካድ አያስፈልግም፡፡ ዋንጫው 
የማነው? ላልከው በዚህ አጋጣሚ እኔ 
የክፍሌ ቦልተናን አስተዋፅኦ ከመካድ ይልቅ 
መልካም አስተዋፅኦ የነበረው ብዬ በመልካም 
ጎኑ ማንሳትን ነው የምፈልገው፡፡ ሀቁ ይሄ 
ቢሆን ግን ሀለተኛው ዙር ላይ ጠንካራ ስራ 
መስራት ባልችል ኖሮ አሁን ለሚገኝበት ክብር 
ይበቃ ነበር ወይ? ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ 
ምክንያቱም…
ሀትሪክ፡- …ምክንያቱም ምን…?
መኮንን፡- …ሁለተኛው ዙር… ለእኔም 
ለክለቡም በጣም ከባድ ነበር፤ ክብደቱን ደግሞ 
የምገልፀው በሁለት መንገድ ነው፤አንደኛው 
ምክንያቴ ሁለተኛው ዙር በባህሪው ለዋንጫና 
ላለመውረድ የሚጫወቱ ክለቦች እየተለየዩ 
የሚወጡበት በመሆኑ ሁሌም ከጨዋታ ወደ 
ጨዋታ በጣም ከባድ ነው፤ እያንዳንዱን 
ጨዋታ የምታደርገው የፍፃሜ ያህል ነው፤ 
ለዋንጫና ላለመውረድ ከሚደረግ ትግል 
መነሻነት በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ 
ቡዱኑን ለዋንጫም ሆነ ከመውረድ ለመትረፍ 
ቡድናቸውን በተለያዩ ደረጃዎች ከፍ ባሉ 
ተጫዋቾች ያጠናከሩበት ጊዜ በመሆኑ 
ፈተናው ከአንደኛው በእጥፍ የጨመረ ነበር፡፡ 
ሁለተኛው ምክንያቴ ደግም እኔ በማላውቃቸው 
ተጨዋቾች ነው ወደ ስራ የገባሁት፤ ሰኞ 
ክለቡን ማሰልጠን ጀምሬ በቀጥታ ነው 
ወደ ቅዳሜና እሁድ ጨዋታ የገባሁት፤ 
ይሄ በራሱ በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም 
የቡድኑ ተጫዋቾች ምንድነው ያላቸው? 
እኔስ ምንድነው ልጨምርላቸው የምችለው 
የሚለውን ለመየት በቂ ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ይሄ 
ሁሉ ፈተና እያለብኝ ሃላፊነት (ሪስክ) ወስጄ 
ነው የገባሁበት። ካደረኳቸው 15 ጨዋታዎች 
አንድም ጨዋታ ለእኔ ቀላል አልነበረም፡፡ 
በ15ቱም ጨዋታዋች ተፈትኜ ነው ለስኬት 
የበቃሁት፤ ስለ አስተዋፅኦው ግን ለክፍሌም 
የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው ብዬ ብናገርም 
በሁለተኛው ዙር የነበረውን ከባድ ፈተና 
አልፈን ለዚህ ስኬት እንደበቃን ግን ሳልሸሽግ 
ነው መናገር የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- የጅማ ከነማን ቡድን የማሰልጠን 
ሃላፊነት እንደተሰጠህ “አትጠራጠሩ ቡድኑን ወደ 
ፕሪምየር ሊግ በማሳለፍ ከምኞቱና ከህልሙ 
ጋር አገናኘዋለሁ” ብለህ ቃል ገብተህ ነው ስራ 
የጀመርከው የሚል ነገር ሰማሁ፤ እንደዚህ 
እርግጠኛ የሆንከው ከምን መነሻነት ነው?
መኮንን፡- እውነት ነው…! ቡድኑን ወደ 
ፕሪምየር ሊግ እንደማሳልፈው አትጠራጠሩ 
ብዬ ቃል ገብቼ ነው ስራ የጀመርኩት፤ 
እንደዚሁ ብዬ እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር 
የበቃሁት ደግሞ በስራዬ ስለምተማመንና 
እግዚአብሄር የሰራሁትን ስራ እንደሚባርክልኝ 
በማመኔ ብቻ ነው። ክለቡ 1ኛውን ዙር 
በመሪነት በመጨረሱ በነበረው የሽልማት ስነ-
ስርዓት ላይ አትጠራጠሩ በመጪው ዓመት 
ጅማ ከነማን የምታገኙት ፕሪምየር ሊግ 
ውስጥ ነው ብዬ ቃል ገብቼላቸው ህልማቸውን 
አሳክቻለሁ፤ ቃሌ ባለመታጠፉና እውን ሆኖ 
በመታየቱም ደስተኛ ነኝ፡፡


ሀትሪክ፡- በተለያዩ ሚዲያዎች፣ በማህበራዊ 
ድረ-ገፆች የጅማ ከነማን ቡድን በታሪክ 
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪየምር ሊግ ያስገባውና 
የሱፐር ሊግ ዋንጫ ባለቤት የሆነው አሰልጣኝ 
መኮንን ተባሮ በምትኩ ሌላ አሰልጣኝ ተሹሟል 
የሚል ወሬ በስፋት እየተናፈሰ ነው፤ እስቲ አንተ 
በአንደበትህ አረጋግጥልኝ ውጤት ባመጣህ ማግስት 
ከክለቡ ተባረሃል?
መኮንን፡- ይሄ የምትለውን ነገር በወሬ 
ደረጃ ፣ ሚዲያ ላይ፣ ማህበራዊ ድረ-ገፆች 
ላይ እኔ ተሰናብቼ ሌላ አሰልጣኝ እንደተተካ 
በስፋት እየተነገረ ነው፤ ከዚህ ሌላም ሙያው 
ውስጥ ያሉም የሚዲያ ሰዎችም በዚህ ጉይ 
ላይ ደጋግመው ይጠይቁኛል፡፡ አንዳንዶች 
ደግም በመቆጨት ስሜት አንተ ክለቡን 
ለታላቅ ስኬት አብቅተህ እንዴት ያባርሩሃል? 
በማለት በመቆርቆር ስሜት ይጠይቁኛል፤ በዚህ 
አይነት መልኩ ወሬዎችን ከመስማቴ ውጪ 
ከጅማ ከነማ ስፖርት ክለብ ሃላፊዎች ይፋዊ 
በሆነ መንገድ የተገለፀልኝ ወይም ያስታወቁኝ 
ነገር የለም። ከክለቡ ይፋዊ ደብዳቤ ሲደርሰኝ 
ነው ተባርሬያለሁ ወይም እቀጠላለሁ ልል 
የምችለው፡፡
ሀትሪክ፡- መኮንን በፍርሃት ተሸብበህ ወይም 
ለመሸፋፈን ፈልገህ ካልሆነ በስተቀር ቡድኑን ወደ 
ፕሪምየር ሊግ ካስገባህ በኋላ የክለቡ የቀጣይ 
እቀድ አካል በመሆን በተጫዋቾች ዝውውርና 
በቀጣዩ በፕሪምየር ሊጉ በሚኖረው ጨዋታ ዙሪያ 
በንቃት መሳተፍ ሲገባህ የተጨዋች ምልመላ 
እያከናወኑ የሚገኙት በአንተ ምትክ የሚመጡት 
አሰልጣኝና ሌሎች መሆናቸው የሚነግርህ ወይም 
ከክለቡ ጋር እንደማትቀጥል የሚያረጋግጥልህ ነገር 
የለም?
መኮንን፡- በእርግጥ ከወሬዎቹ መደጋ 
ገምና በሚዲያ ለይ ሳይቀር መቅረብ ለእኔም 
የሚሸቱኝ መጥፎ ጠረኖች አሉ፤በጥያቄህ 
እንዳነሳኸው በተለይ በተለይ ክለቡን 
ለፕሪምየር ሊግና የሱፐር ሊግ ዋንጫ ካበቃሁ 
በኋላ በሌሎች ክለቦች ካለው ልምድ አንፃር 
በተጫዋቾች ዝውውርና የቡድን ግንባታ፣ 
የፕሪምየር ሊግ ዝግጅት ዙሪያ በንቃት 
አለመሳተፌ ብቻ ሳይሆን ከክለቡ ሃላፊዎች 
አንዱም መጥቶ አለማነጋገሩና እንዴት እና 
ድርግ አለማለታቸው እንዲሁም ሌሎች ሰዎች 
ከእኔ ይልቅ ሲሳተፉ መታየቱ በወሬ ደረጃ 
የሚነገረውን ሁሉ ወደ እውነትነት እየቀረው 
ለእኔም የሚሰጠኝ ትልቅ መልዕክት እንዳለው 
አልክድም፤ ይሄም ቢሆን ግን ከክለቡ ይፋዊ 
ደብዳቤ ካልተሰጠኝ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ 
እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ይቸግረኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ከክለቡ ሃላፊዎች ጋርስ ስለመቀጠልና 
አለመጠቀልህ በግልፅ ለመነጋገርና ለመወያየት 
አልሞከርክም?
መኮንን፡- እስከአሁን በዚህ ጉዳይ ከማንም 
ጋር አልተነጋገርኩም፤ ምናልባት ለእኔ ምልክት 
የሚሆኑ ነገሮችን ከማየት ውጭ። እውነት 
ለመነጋገር ከዋናው ውድድር በፊት የሚሰሩት 
ስራዎች ናቸው የነገውን የቡድንህን ማንነት 
የሚናገሩት፤ አሁን አሁን የሚወራውና 
የሚባለው ነገር ትክክለኛ ይሆን እንዴ 
የሚል ስሜት እየተፈጠረብኝ ነው ። ክክለቡ 
ጋር ብቀጥል እነሱም ከእኔ ጋር ተገናኝተው 
በመነጋገር ወደ ስራ እንደምንገባ ሳሰብ ይሄ 
ነገር እንዴት ነው? ብዬ ራሴን እንድጠይቅ 
ያደርገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ክለቦችን እየወጣህ መሰናበትህን 
እንዴት ነው የምታስተናግደው? ከጅማ ከነማስ 
ተመሳሳይ እጣ ይገጥመኛል የሚለው ግምቱ 
አለህ…? የሚወራው እውነት ከሆነ የአንተ 
አስተያየት ምንድነው?
መኮንን፡- …እጅግ በጣም ታዝናለህ፤ 
ያምሃልም፤ ውጤት ስታመጣ ክለቡ 
የሚፈልገውን ሳታሳካ እንድትሰናበት ቢደረግ 
ወይም በምትክህ ሌላ አሰልጣኝ ቢሾም 
ውሳኔዎችን አምነህ ትቀበላለህ። በክለቡ ታሪክ 
ያልተመዘገበ አዲስ ታሪክ አምጥተህ ክለቡን 
ከህልሙ ጋር አገናኝተህ በሌላ እንድትተካ 
ሲደረግ በጣምም ይሰማሃል፡፡ ለአንድ 
አሰልጣኝ ስንብትም ሆነ ቅጥር መለኪያው 
ውጤትና ውጤት ብቻ ነው የሚል እምነት 
ነው ያለኝ፤ ሀቁም ይሄው ነው። እኔ ደግሞ 
በሌሎችም ሆነ በጅማ ከነማ ውስጥ ለስንብት 
ሳይሆን ለሽልማት የሚያበቃ የሚየኮራ ታሪክ 
እንደሰራሁ ነው ሁሉም የሚያውቀው። ጅማ 
ከነማን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገሪቱ 
ትልቅ ሊግ በማስገባት ፊታኙን የሱፐር ሊግ 
በሻምፒዮናነት በማጠናቀቅ በክለቡ የእግር 
ኳስ ታሪክ አዲስ ወርቃማ ታሪክ እንዲያፅፍ 
አድርጌዋለሁ፡፡ ክለቡ ውስጥ ለመቀጠል ከኪህ 
በላይ ምን መስራት፤ ምን አይነት ውጤት 
ማምጣት እንዳለብኝ ሊገባኝ አልቻለም። ነገሮች 
እየተደጋገሙ ሲሄዱ ሁሉም ነገር አልፈታ ያለ 
እንቆቅልሽ እየሆነብኝ ነው። ፈታኝና አስቸጋሪ 
በሆነው የሱፐር ሊግ ውድድር ከአንድም ሶስት 
ቡድኖችን ወደላይ በማሳደግ ሀትሪክ (3 ጊዜ 
በማሸነፍ) ሰርቻለሁ፤ ከዚህ በላይ ለእኔነቴ 
መገለጫ ከየት ነው የሚመጣው? የያዝኩትን 
ክለብ ውጤታማ ከማድረግና ከህልሙ ጋር 
በማገናኘት ታሪክ ከመስራት በላይ ምን 
ማድረግ እንለብኝ ግራ ተጋብቻለሁ፤ ነገሮች 
ሁሉ አልፈታ ያሉ እንቆቅልሽ ሆነውብኝ 
ተቸግሬያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄኔን ነገር በሌላው ጎን ብናየውስ? 
የነገሮች መደጋገም ክለቦችን ባወጣህ ቁጥር 
የመሰናበትህ ጉዳይ አንተ ጋር ድክመት ስላለ 
ይሆን እንዴ የሚሰናበተው ብዬ ባስብ ከድፍረት 
ይቆጠርብኝ ይሆን?
መኮንን፡- (ፈገግ እንደማለት እያለ) 
ይሄንን ከእኔ ይልቅ ውጤቴራሱ አፍ አውጥቶ 
ይመሰክራል፤ እኔ ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት 
በገዛ ራሴ ነው የወጣሁት፤ ዳሽን ቢራ ግን 
በታሪኩ ለፕሪምየር ሊግ አብቅቼው ከ30 
የፕሪምየር ሊግ ጨወታዎች አምስቱን ብቻ 
አድርጌ ነው እንድሰናበት የተደረገው፤ አንድን 
አሰልጣኝ አቅም አለው የለውም ለማለት 
አምስት ጨዋታ ብቻ እንዴት መመዘኛ 
ይሆናል? ፊታኙን የሱፐር ሊግ ጨዋታ በድል 
ማጠናቀቅና ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳለፌ የአቅም 
ጉዳይ እንዳይነሳ የሚያደርግ ይመስለኛል፡
፡ ከአንድም ሶስት ቡድኖችን ያሳለፍኩት 
በአስማት ወይም በአቦ ሰጡኝ አይደለም፤ 
ስለሰራሁና ፈጣሪ ስለረዳኝ ብቻ ነው። አንድ 
ክለብ አንድን አሰልጣኝ የሚቀጥረው “ውጤት 
አምጣልኝ፤ ከህልሜ ጋር አገናኘኝ” ብሎ ነው፡
፡ እኔም የሚፈልገውና የተጠየቀውን እያሳካሁ 
ፈተናውን በድል ተወጥቼ ከጨረስኩ በኋላ ነው 
በሌላ የምትካው? ነገሩ እውነት ሆኖ የስንብቴ 
ምክንያት የመኮንን ድክመት ነው ከተባለ 
ድክመቴ ሊሆን የሚገባው ውጤት ማምጣቴ 
ብቻ ነው፤ ውጤት ማምጣት ክለቡን ስኬታማ 
ማድረግ እንደ ደድክመት የሚቆጠርበት ጊዜ 
ላይ ከደረስን ማለቴ ነው። ከዚህ ውጭ ለጊዜው 
እኔ ሌላ ምክንያት አይታየኝም፡፡
ሀትሪክ፡- የመኮንን ድክመት ካልሆነ ታዲያ 
ክለቦችን ወደ ላይ እያወጣህ መሰናበትህን ከምን 
ጋር እናያይዘው?
መኮንን፡- እውነት ለመናገር ይሄን ነገር 
ለእኔም ሊያስረዳኝ የሚችል ሰው ባገኝ በጣም 
ደስተኛ ነበርኩ፤ ነገሩ ለእኔ ለራሴ አልፈታ 
ያለ እንቆቅልሽ ሆኖብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ 
በሰራሁባቸው ክለቦች ሁሉ ማለትም በባህር ዳር 
ከነማ፣ በውሃ ስፖርት፣ በዳሽን ቢራና በጅማ 
ከነማ ቡድኖች ትልቅ የውጤት ታሪክ እያለኝ 
ውጤት ባመጣሁ ማግስት ለምን የዚህ አይነቱ 
ችግር ሰለባ እንደምሆን አላውቅም፤ በውሃ 
ስፖርት፣ በዳሽን ቢራ ትልቅ የውጤት ታሪክ 
እያለኝ ክለብ አጥቼ ስድስት ወር ስራ ፈትቼ 
ቤቴ ቁጭ ብዬ አሳልፌያለሁ፤ በተቃራኒው 
ደግም ብዙም የሚነገር ውጤት የሌላቸው 
አሰልጣኞች ከክለብ ወደ ክለብ እየተገላበጡ 
ሲሰሩ ታያለህ፡፡ በአጭሩ የአሰልጣኝ 
መቅጠሪያና ማሰናበቻ መስፈርቱ ምን እንደሆነ 
ሊገባኝ አልቻለም፤ ውጤትና ውጤት ብቻ ነው 
እንዳልል እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ በሆነው 
ውድድር ላይ ውጤት አምጥቼ ለታላቅ ክብር 
አብቅቼ እሰናበታለሁ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ስራ 
ፈትቼም የምቀመጥበት ሁኔታ ሲኖር እያለሁ፡፡ 
አንድን አሰልጣኝ ከፊት የሚያቆመው ውጤቱና 
ውጤት ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ እኔም እኮ 
ውጤት ከሌለኝ ውጤት ያላቸው ሰዎች ናቸው 
ከፊት መቆም ያለባቸው፤ አሁን ግን ይሄን 
አታይም፤ ይሄ ለእኔ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እግር 
ኳስ አደጋ አለው፡፡ እኔ ትናንትም ውጤት 
አምጥቼ ታሪክ አስፅፌ ተሰናብቻለሁ፤ ዛሬም 
በተመሳሳይ ልሰናበት እችላለሁ፤ ይሄን መሰል 
ውሳኔዎች ግለሰቦችን ጠቅመው እግር ኳሱን 
ሊጎዱ እንደሚችሉ ነው መረዳት ያለብን፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄን መሰሉ ቡድኖችን እያወጣህ 
ለሌላ ሲሳይ እያደረክ መሰናበትህ ተስፋ 
እንድትቆርጥ አላደረገህም?
መኮንን፡- እኔ በቀላሉ ለተስፋ 
መቁረጥ እጅ የምሰጥ ወይም የምንበረከክ 
ሰው አይለሁም፤ ሁልጊዜም አንድን ነገር 
ከተቃራኒው ነገር ጋር ነው የማስበው፤ ስቀጠር 
መባረር መኖሩን እያሰብኩ ነው የምዋዋለው፡
፡ በእግር ኳስ ሁልጊዜም ለአንድ ክለብ 
ስፈርም በራሴም ሆነ በክለቡ ምክንያት አንድ 
ቀን ልለቅ እንደምችል ሁልጊዜም አስባለሁ፡፡ 
አሳማኝ በሆነ ምክንያት ለሚመጡ ስንብቶች 
ሁልጊዜም ራሴን አዘጋጃለሁ፤ ሁልጊዜ ለተስፋ 
መቁረጥ እጅ እንድሰጥ የሚያደርጉኝ ፍትሃዊና 
ለእኔ መልስ የማይሆኑ ውሳኔዎች ሲወሰኑብኝ 
ነው። በክለቡ ታሪክ ውጤት አምጥተህ 
ሻምፒዮን አድርገህ እንዲህ እንደአሁኑ አይን 
ያወጡ ነገሮች ስትሰማ ሰው ነኝና ስሜቴ 
መጎዳቱ አይቀርም፤ በተደጋጋሚ ከዚህ ሁሉ 
ስልጠናውን ትቼላቸው ለምን ዞር አልልም 
የሚል ሃሳብም ይመጣብኛል፡፡ ለእኔ መልስ 
በማይሆነኝና ለእርምት በማይረዳ ሁኔታ 
ስባረር በጣም ይከብደኛል፤ ያበሳጨኛል፡
፡ በዚህ አይነቱ በደል በመማረር በጣም 
ብዙ ጊዜ ከስልጠናው ለመራቅ እየወሰንኩ 
ተመልሼያለሁ፡፡ የሙያው ፍቅር አይለቅህም፤ 
ጨክነህ አንድትሄድም ሳይሆን ከእነ ችግሩ 
እንድትኖር ነው የሚፈረድብህ። እስቲ ህዝቡ 
ይፍረደኝ ውጤት ከማምጣት በላይ ምንድነው 
ከእኔ የሚጠበቀው? ይሄን የሚያስረዳኝ ሰው 
ፈልጌ ማግኘት አቅቶኛል፡፡
ከእኔ ጋር ቡድናቸውን ወደ ፕሪምየር 
ሊግ ያወጡ አሰልጣኞች ሊባረሩ ነው ሲባል 
አለመስማቴ በእኔ ላይ ምንድነው ነገሩ እንድል 
እያደረገኝ ነው።
ሀትሪክ፡- አሁን አሁን እግር ኳሱ አካባቢ 
የተዘረጋ የጥቅም ኔት-ወርክ አለ፤ አንድ አሰልጣኝም 
ሆነ ተጨዋች አንድ ክለብ ውስጥ ለመቀጠርም ሆነ 
ክለቡ ውስጥ ለመቆየት ከኮሚቴዎች፣ ከአመራሮችና 
ከአሰልጣኞች ጋር አርባ ስልሳ መካፈል አለበት 
በሚል በህግ ያልተፃፈ አሳፋሪ ህግ አለ በሚል 
ብዙዋች በምሬት ይናገራሉ በዚህ ላይ አንተ 
የምትለው ምንድነው?
መኮንን፡- ይሄን የምትለው ነገር እንደ 
አንተም እኔ በወሬ ደረጃ እሰማለሁ፤እንደውም 
አሁን ነገሩ ከወሬ ከፍ ብሎ የአደባባይ 
ምስጢር ሆኗል፡፡ አንዳንዴ ውጤት መለኪያ 
መሆኑ ቀርቶ ውጤት ያላቸው ተቃምጠው 
ውጤት የሌላቸው ደካማ ውጤት ያስመዘገቡ 
አሰልጣኞች ሲቀጠሩ ስታይ ይሄ የሚወራው 
ወሬ ለካ እውነት ነው ብለህ እንድትደመድም 
ያደርግሃል፡፡ በዚህ መንገድ መጓዝ ነገሮችን 
ሁሉ እንደሚያቀልና ጥሩ አቋራጭ መንገድ 
እንደሆነ ነው የምትሰማው፡፡ ይሄ ግን 
የግለሰቦችን ኪስ አደልቦ እግር ኳሱን ከመግደል 
ውጪ አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡ ይሄንን 
የተሳሳተ መንገድ ባለመከተሌ እንደተበደልኩና 
የአንዳንድ ክለቦችና ኮሚቴዎች የመጀመሪያ 
ምርጫ እንዳልሆንኩ በወሬ ደረጃ እሰማለሁ፡
፡ ምንአልባት ሰዎች በዚህ በተሰሳተ መንገድ 
ሄደው ከኮሜቴ ጋር ተሞዳምደው ሰው 
የለፋበትን በመንጠቃቸው ዛሬ ኪሳቸውን 
ሊያደልቡ ሆዳቸውን ሊሞሉ ይችላሉ፤ ነገር 
ግን ሁሌም ከህሊናቸው ጋር ሲጣሉና ሲወቀሱ 
ይኖራሉ፡፡ ለገንዘብ ብሎ ህሊናን መሸጥ አግባብ 
ነው ብዬ አላምንም፡፡ በዚህ ደረጃ የምንጓዘው 
በዚህች ምድር ላይ ምን ያህል ዓመት ለመኖር 
ነው? እንዳተባለው ይሄን መንገድ ባለመከተሌ 3 
ክለቦችን ወደላይ አውጥቼ ስራ ፈትቼ ልቀመጥ 
እችላለሁ፤ በዚህም ራሴንና ቤተሰቦቼን ልጎዳ 
እንችል ይሆናል፤ በዚህ አይነት መንገድ 
ሄጄ ክለብ ከማገኝና ህሊናዬን ሸጪ ገንዘብ 
ከማጋብስ እኔም ቤተሰቦቼም በረሃብ ማለቅን 
ነው የምመርጠው፡፡ 
ሀትሪክ፡- አሰልጣኞች እርስ በርስ 
መነጣጠቃችሁ፤ አንደኛው ሌላኛውን ሰርስሮ 
የማደሩን ነገርስ እንዴት ነው የምታየው?
መኮንን፡- በዚህ በጣም ነው የምታዝነው፤ 
ህይወት እኮ አጭር ናት፤ ስንት ዓመት በልተህ 
ለመኖር ነው የሙያ ወንድምህን ቀምተህ 
እንጀራ ለመብላት እንቅልፍ የምታጣው? 
ሁላችንም ከአንድ ኩርማን እንጀራ በላይ 
በልተን እናድራለን? በፍፁም። አሁን በእግር 
ኳሱ የምታየው ነገር ግን በጣም ያሳፍራል፡፡ 
በደከመው እግር ኳሳችን ላይ ይሄ ክፉ ቫይረስ 
ሲጨምር ምን እንደሚከሰት አስበው፤ አንተ 
ባልሰራህበት የእኔን እንጀራ ነጥቀህ በልተህ 
ስታድር እኔ ፆሜን ሳድር ከህሊናህ ጋርስ 
አትጣላም? አዕምሮህስ ሰላም ይሆናል? በጣመ 
ከባድ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መጓዝ ለእግር ኳሳችን 
አደጋ ነው፤ አሰልጣኛች መረዳዳትና መከባበር 
እንጂ አንዱ አንዱ የለፋበትን ነጥቆ ለመውሰድ 
ማድፈጥ መልካም ነው ብዬ አላስብም፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ በኋላስ በምስራው ስኬታማ 
ስራ የስራ ከለላ ወይም ዋስትና የለኝም የሚል 
ስጋት በውስጥህ አይፈጠርም?
መኮንን፡- በጣም ይፈጠራል…፤በዚህ 
አይነቱ ችግር በተደጋጋሚ ሰለባ ሆኛለሁ፤ 
ወደፊትም ለፍቼ ደክሜ የሰራሁት ስራ 
መነጠቁ አይቀርም የሚል ከፍተኛ ስጋት በው 
ስጤ ቢኖርም አሁን ግን ህይወት አስተምሮኝ 
የራሴን ዘዴ ቀይሻለሁ…
ሀትሪክ፡- …ምስጢር ነው ካላልክ… ምን 
አይነት… ዘዴ… እንደሆነ… ትነግረኛለህ…?
መኮንን፡- ከአንድም ሶስት ክለቦችን 
ለፕሪምየር ሊግ በማብቃት ሀትሪክ ሰርቼ 
መነጠቄ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል፤ ከዚህ 
በኋላስ ክለቦችን ሳሰለጥን ከመደበኛው ውል 
በተጨማሪ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ 
አወጣለሁ፤ካወጣሁ በኋላም አብሬ መስራት 
አለብኝ የሚል አንቀፅ እንዲካተተልኝ እያደረኩ 
ነው መዋወል የምፈልገው፤ …የቸገረው… 
እንደሚባለው ይሄንን ሃሳብ የደረሱብኝ ችግሮች 
ወልደውልኛል፡፡
ሀትሪክ፡- መኮንን ብ/ሊግን እንጂ ፕሪምየር 
ሊጉን የማስልጠን አቅም የለውም፤ ለብ/ሊግ 
የተፈጠረ አሰልጣኝ ነው በሚል ለፕ/ሊጉ ብቁ 
እንዳልሆንክ አድርገው የሚያስቡ አሉና ለእዚህ 
መሰሉ አስተያየት ምን መልስ አለህ?
መኮንን፡- ይሄንን ነገር እኔም ሰምቻ ለሁ፤ አንዳንድ ሰዎች ከምን መነሻ እንደሆነ 
አላውቅም እንደዚህ አይነት የተሳሳተ አስተ 
ያየት ይሰጣሉ፡፡ ምን አልባት ብዙዎች 
ያል ቻሉትን እኔ በማሳካቴ ይሄ አስተያየት 
ተሰጥቶ ከሆነ አላውቅም፤ ከዚህ ውጪ 
ሱፐር ሊግ ላይ በተደጋጋሚ ስኬታማ የሆነው 
መኮንን ፕሪሚየር ሊግ ለማሰልጠን አቅሙ 
ያንሰዋል የሚል እምነቱ የለኝም፡፡ ምክንያቱም 
በአገራችን ማሰልጠን የሚከብደው ፕሪምየር 
ሊግ ሳይሆን ሱፐር ሊግ ነው፤ እንደውም 
አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት ውጤታማው 
አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ መድንን በመያዝ 
ከፍተኛ ሊግ ወርዶ ሲሰራ “ከፍተኛ ሊግ 
እንደዚህ አይመሰለኝም ነበር፤ እጅግ በጣም 
ፈታኝና ጠንካራ ውድድር ያለበት ነው” 
በማለት ሲናገር ስምቻለሁ፡፡ ፈታኝና እልህ 
አስጨራሽ ውድድር ያለው ፕ/ሊግ ሳይሆን ብ/
ሊግ ነው፤ በከፍተኛ ሊግ ስኬታማ የምትሆነው 
እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነህ ነው፤ ሱፐር 
ሊግ የአሰልጣኞች እውነተኛው የመፈተኛ ቦታ 
ነው። በዚህ ቦታ ተፈትነህ ወጥተህ የተሻለ 
የውደድር ሜዳ፣ የተሻለ የገንዘብ አቅምና 
ፋሲሊቲ፣ የተመረጡ ተጨዋቾችን ይዘህ 
በምትወዳደርበት ፕሪምየር ሊግ ማሰልጠን ያን 
ያህል ከባድ ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ፡
፡ እኔ ይቅርታ አድርግልኝና በአዲስ መልክ 
ከተጀመረው ከ20 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 
ውድድሮች 14ቱን ለብቻው ያነሳው ቅዱስ 
ጊዮርጊስ ነው፤ ከእሱ ውጪ ቀሪውን ያነሱት 
ከሶሰት የማይበልጡ ክለቦች ናቸው፡፡ ከዚህ 
አንፃር ቢጠፋ ቢጠፋ አንድ የፕሪምየር ሊግ 
ክለብ ይዘህ በየዓመቱ መሃል ላይና ወራጅ 
ቀጠና ውስጥ አድርጎ መጨረስ ያን ያህል 
ከባድ ነው ብዬ አላስብም፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ይፋዊ የሆነ ደብዳቤ 
አልተሰጠኝም እያልክ ትከራከራለህ እንጂ ዛሬም 
ድረስ ከጅማ ከነማ እንደተሰናበትክ በስፋት 
መወራቱን ቀጥሏል፤ የተባለው እውነት ከሆነ 
ቀጣዩ ማረፊያህ የት ነው ብዬ ብጠይቅህ መልስ 
አለህ?
መኮንን፡- ምንም አይነት መልስ የለኝም፡
፡ እስከአሁንም ለቀጠረኝ ክለብና ለውሌ ታማኝ 
ሆኜ መቀጠሌን ብቻ ነው የማ ውቀው፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜና እረፍትዜናዎች

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜናዎች

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...