“እጃችን ላይ መረጃና ማስረጃ ስላለ ወደ ሕጋዊ መስመር የማይመለሱትን ወደ ሕግ አደባባይ እንወስዳቸዋለን” አቶ ስለሺ ብሩ /የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንተርሚዲየሪ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት/

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር ላይ የማይሳተፍ ማን አለ? አሰልጣኝ፣ ህጋዊ ኤጀንት፣ ሕገ ወጥ ደላላ፣ የክለብ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች… ተብሎ በሰፊው ይወራል፡፡ ዘርፉ በርካታ ሚሊየን ብሮች የሚፈሱበት እንደመሆኑ የድርሻውን ለመቦጨቅ የማይጥር ማን አለ? ተብሎም ይተቻል፡፡ አለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር /ፊፋ/ ኢንተርሚዲየሪ /ሶስተኛ ወገን/ ብሎ ያስቀመጠውን ሕጋዊ መስመር ተከትሎ ለመስራት ከዘርፉ የሚቦጨቀውን /የመንግሥት ዝምታ ቢገርምም/ ለማስቆም ሁሉም በሕጋዊ መንገድ ሕጋዊ ግብር እንዲከፍልና ስፖርቱ ጤነኛ እንዲሆን ያወጣውን ሕግ ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ፉትቦል ኢንተርሚዲየሪ አሶሴሽን ከተመሰረተና 32 አባላትን ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወደ 2 ወራት አልፎታል፡፡ የውጪም ሆነ የውስጥ ትግል የገጠመው ይሄው ማህበር ከመንግሥታዊ አካላት ጋር ጠንክሮ እየሰራና በዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ተገቢ የዝውውር ገንዘብ ለማስጠበቅ እየታገለ ነው የዚህ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ብሩና ም/ል ፕሬዚዳንቱ አቶ በረከት ደረጄ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ዘርፉ ችግርና መፍትሔ፣ ማህበሩ ስለሄደበት መንገድና አሁን ፌዴሬሽኑ ሊከውን ስለሚገባቸው ጉዳዮች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ማህበራችሁ ስለሰራው ስራ እስቲ አስተዋውቁኝ?

ስለሺ፡- ያው እንደሚታወቀው በሌሎች ሀገሮች ላይ የተለያዩ ስያሜዎች ቢኖሩትም ለኢትዮጵያ ግን አዲስ ነው ኢንተርሚዲየሪ በኛ ሀገር አልነበረም፡፡ በሙያው በተናጠል ስንንቀሳቀስ ውጤታማ ባለመሆናችን ማህበር ለመመስረት ችለናል፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ 2 ወር ቢሆነው ነው የመጀመሪያ ስራችን የማህበሩን ምስረታና ተግባር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ለፌዴሬሽኑ፣ ለክለቦች፣ ለአሰልጣኞች፣ ለተጨዋቾች ለደጋፊዎችና ሌሎች ወገኖች የማስተዋወቅ ስራ ሰርተናል፡፡

ሀትሪክ፡-የዚህ ዘርፍ ትልቁ ችግር ምንድነው ትላላችሁ?

በረከት፡- ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ኢንተሚዲየሪ ምን ማለት ነው? ምንድነው ጥቅሙ? ምን ይሰራልኛል በሚለው ጉዳይ ላይ የመረጃ ክፍተት በተለይ በተጫዋቾች ላይ አለ አንዳንድ ክለቦች እኔ ባመጣሁት ኢንተርሚዲየሪ ብቻ ነው መፈራረም ያለባችሁ ይላሉ ይሄ ተገቢ ውሣኔ አይደለም በፊፋም ሕግ አይደገፍም ኢንተርሚዲየሪው ከከለቡ ጋር ከተቀናጀ ተጨዋቹ ቢጎዳ ከክለቡ ጋር በደመወዝ ቢጋጭ ኢንተርሚዲየሪው ለማን ሊከራከር ነው? መሰል ችግሮች ገጥሞናል በመተዋወቅ ሳይሆን ተጨዋቹ ይጠቅመኛል ለኔ ይሰራል ብሎ ያሰበውን ኢንተርሚዲየሪ የመያዝ መብቱ ሊከበር ይገባል እነዚህን መሰል ችግሮችም መስተካከል አለባቸው፡፡

ሀትሪክ፡- የዚህ የ3ኛ ወገን መኖር አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ ቢገልፁልኝ?

ስለሺ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ይሄ ሙያ ያስፈለገው ፊፋ እ.ኤ.አ በ2009 አካባቢ በ211 አባላት ሀገር ላይ ጥናት አድርጎ 70 በመቶ ዝውውር የሚካሄው በሕገ ወጥ መንገድ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ይሄ መቀጠል የለበትም በማለት በ2015 ህግና ደንብ ወጥቶ ኢንተርሚዲየሪ ተጀመረ፡፡ በኛ ሲተርጎም 3ኛ ወገን እንደማለት ነው፡፡ በዲክሺነሪ ላይ ስላልሰፈረ በግርድፉ ነው የምንጠሰራው፡፡ ሁሉም ፌዴሬሽኖች እንዲተገብሩት ተብሎ የመጣ ውሣኔ ነው፡፡ እኛም ሀገር የተለያዩና የማይመለከታቸው ወገኖች ተሳትፎ ያደረጉ ስለነበር ያንን ለመገደብና ሕገ ወጥ ዝውወርን ለማስቆም እንዲሁም ዘርፉን ነፃ ለማድረግ ነው በሙያ መልክ ኢንተርሚዲየሪ የተጀመረው፡፡ ማህበራችንም እንቅስቃሴ ሲጀምር በሕገ ወጡና በልማዳዊ አሰራር ለብዙ ጊዜ ስለተቆየ ያንን አጥርተን መድረኩን ነፃ ለማድረግና አለም ወደሚጠቅምበት አካሄድ ለመግባት እየጣርን ነው የቆየነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ሰብስቦ ሊያወያየን አገናኝቶ ሊያስተዋውቀን ሲገባ ያን ባለማድረጉ ነው በራስ ተነሳሽነትና ጥረት ስራውን የጀመርነው፡፡ ከፌዴሬሽኑ የበላይ የሆኑ አካላት ጋርም ቀጠሮ ይዘን እንገኛለን፡፡ በአጠቃላይ የተሻለ ስራ ለመስራት፣ ከዚህ በፊት ይሰራ የነበረውን ልማዳዊ አሰራር ለማስቀረት የምንችለው አድርገናል በቀጣይም ጠንክረን እንሰራለን፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ 50 የሚጠጉ ላይሰንስ ያላቸው ኢንተርሚዲየሪዎች መሀል 32 ናቸው በማህበሩ የታቀፉት… ቀሪዎቹን ለመመለስ ምን እየሰራችሁ ነው?

በረከት፡- ደውለናል እንዲመጡም ነግረናል ስልካቸው ዝግ ሆኖብን ያላገኘናቸው አሉ፤ አንዳንዱ ግን ሲቀልድ ሁሉ ነበር ማህበሩ የሚመሰረት ያልመሰለውም ቁጥሩ ቀላል አልነበረም፡፡ አሁን ሕጋዊ አይደለም ብለው ሚዲያ ላይ ቅሬታቸውን የሚያሰሙት እነሱ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ተቋም ነው ሕጋዊ ናችሁ ያለን.. ማነው ታዲያ ይህን የሚቃወመው? ሁሉን ቅድመ ሁኔታ አሟልተን ተመስረተናል፡፡ ነገር ግን ከትችት በመውጣት የግድ እኛ ካልመሰረትነው ከሚል ሃሣብ በመላቀቅ ማህበሩን ሊቀላቀሉ ሊያበረታቱ እውቅና ሊሰጡ ይገባል ብለን እናስባለን፡፡ ለውይይት አሁንም በራችን ክፍት ነው፡፡ የአገራችን እግር ኳስ እንዲያድግና ፕሮፌሽናል ሆኖ እንዲጓዝ የማድረግ ኃላፊነታችንን በጋራ ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡ ኮሮናም ስላለ በሰፊው ተገናኝቶ መወያየት አልቻልንም በቀጣይ ከኛ ጋር መስራት ከቻሉ መብታቸው ነው በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለን እናምናለን ኑ ብለን አናስገድድም በማህበሩ አማካይነት የሚገኝ የትምህርት እድል፣ የአቅም ግንባታ መሰል እድሎች ማግኘት ግን አይችሉም፡፡ ሁላችንም ያለንን የተለያየ እውቀትን በማህበሩ ስር በመታቀፍና በመስራት ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት በጋራ እንሰራ ማለት እፈለጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሕገ ወጥ ደላሎች ወይም የማይመለከታቸውን ከዘርፉ ዞር ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?

በረከት፡-ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና ከፌዴሬስኑ ጋር ተገናኝተን የተወሰነ ውይይት አድርገናል፡፡ በፊፋ ሕግ የተቀመጠውን መመሪያ እየተገበርን አይደለም ነገር ግን የመጀመሪያ እንደመሆኑ እግር በእግር እየተከታተልን ለማስተካከል እየሞከርን ነው፡፡ አሁንም ግን ሕጋዊ ሰውነት ኖሮን እየሰራን በጎን በደላላና ሌሎች በማይመለከታቸው ወገኖች የሚደረጉ ዝውውሮች እንዲቆሙ ከፌዴራል ፖሊስና ከፀረ-ሙስና እንዲሁም ሌሎች ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በጋራ የምንሰራበት ይሆናል፡፡ የሀገር ሀብት እየባከነ ነው በሕገወጥ ዝውውር መንግሥት ማግኘት ያለበት ግብር እየተሰወረ ነው፡፡ ይሄንን ነገር ለመቅረፍ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወሰድ እየጣርን ነው ከአንዳንድ የመንግሥት አካላት ጋርም ለውይይት ቀጠሮ ይዘናል፡፡ ውጤቱን በቀጣይ የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- አሁንስ ለሕገወጦች የምትሰጡት ማሳሳቢያ አለ? ቀጣይ ርምጃችሁስ ምን ይሆናል?

ስለሺ፡- ሶስት አይነት ኢንተርሚዲየሪዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ላይሰንሱን ይዘው አዝማሚያውና ትግሉ አላሰራ ሲላቸው ከነሰርተፌኬቱ ዝም ብለው የተቀመጡ፣ ሁለተኞቹ የተወሰነ ያህል ተፍጨርጭረዋል ነገር ግን ብዙ ተጠቃሚ ያልሆኑ ምንም ጠብ ያላለላቸው፣ ሶስተኞቹ በሕገ ወጥ መንገድ ሕጋዊ መንገድ ሳይከተሉ የሚሰሩ በተሻለ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ የዚህ ዘርፍ የበላይ አስተዳደሪ ፌዴሬሽኑ እንደመሆኑ ክትትል ተደርጎ ሕጋዊ ከሆኑት ውጪ ሌሎቹን የማስወጣት ስራ እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡ ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ማህበሩ ሲመሰረት መጥተው አባል በመሆን በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ተነጋግረን የመነቃቃት መንፈስ ውስጥ ናቸው ያም ቢሆን እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ እየሰሩ ያሉ ስለማያዛልቅ ወደ ሕጋዊ መስመር ሊመጡ ይገባል እጃችን ላይ መረጃና ማስረጃ ስላለ ወደ ሕጋዊ መስመር የማይመለሱትን ወደ ሕግ አደባባይ እንወስዳቸዋለን ከዚያ በፊት መንገዳቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል ሕጋዊ መንገድ ከተከተልን ፌዴሬሽኑም ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ከፌዴሬሽኑ አንድ የሥራ ክፍል በወሰዱት መረጃ ሕገወጥ ተግባር ላይ ከተሳተፉ ፌዴሬሽኑም ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ የጋራ ተጠያቂነት ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ወደ ሕጋዊ መንገድ መጥቶ ቢሰራ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለው፡፡ ለማንኛውም ጥያቄ በራችን ክፍት ነው፡፡ ይህ ማህበር ሊመሠረት ይሁን መመስረቱን የማያውቅ ኢንተርሚዲየሪ የለም፡፡ ለ48 ሰዎች ሳይቀር ደውለናል ምናልባት ያልጠበቁትን ጥንካሬ ስላዩ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ምስረታውን ያውቃልና በጋራ እንስራ ያልመጡ ጥቂት ኢንተርሚዲየሪዎችን እንዲመጡ ጥሪ አደርጋለው፡፡ በርግጥ የመምጣትም ግዴታ የለባቸውም እኛም የማካተት ግዴታ የለብንም ዋናው ግን በተገኘው ሰርተፌኬት ህገ ወጥ ስራ ከተሰራ የሁላችንም ስም ስለሚጠፋ ይህን በጋራ ልንከላከል ይገባል እላለሁ፡፡

በረከት፡- አንዳንድ መረጃዎች አሉን፡፡ የማህበሩ አባል የሆኑም ያልሆኑ አካላት ሕገ ወጥ ዝውውር ላይ እንደሚሰሩ እንሰማለን እንዲሁም የኢትዮጵያ ፉትቦለርስ አሶሴሽን አባል የሆኑና ያልሆኑ አካላት በዝውውር ላይ እንደሚሳተፉ መረጃዎች አሉ ይህን ለመቅረፍ ከማህበሩ አመራሮች ጋር በደንብ በመነጋገር እየሰራን እንገኛለን፡፡ እንደውም በነገው ዕለት በጋራ ማኅበሩ በሚያካሄደው የደም መለገስ ፕሮግራም ላይ አብረን የምንሰራ መሆኑን ሁለቱ ማኅበራት ጥሩ ግንኙነት ይዘው እየሰሩ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከዚያ ውጪ ተጨዋቹ በመረጠው ሕጋዊ ኤጀንት የፌዴሬሽኑና የፊፋ ሰርተፌኬት ባለው ጥቅሜን ያስከብራል በሚል መርጦና አወዳድሮ የሚፈልገውን ኤጀንቱ የ ማድረግ መብቱ ሊከበር ይገባል፡፡
ላይሰንሱ ኖሯቸው ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትም ለራሣቸው ለሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት ስለማይጠቅም ሕጋዊ መስመር እንዲኖራቸው ጥሪ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ የምትሉት ቃል አለ…?

ስለሺ፡- በመጨረሻም መናገር የምፈልገው የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ይህን ቃለ ምልልስ እንድንሰጥና ሃሳባችንን እንድንገልፅ ስላደረጋችሁን በማህበራችን አባላትና በራሳችን ስም አመሰግናለው፡፡ ሀትሪክ ስፖርት ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጎን የነበረች ጋዜጣ ነች፡፡ ዛሬም አብራችሁን ስላላችሁ ይሄ ጉዳይ የኛ ጉዳይ ነው ብላችሁ መድረክ ስለሰጣችሁን ከልብ እናመሰግናለን.. በቀጣይም በጋራ እንደምንሰራና ከማህበራችን ጎን እንደምትቆሙ ተስፋ እናደርጋለን እናመሰግናለን፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport