በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በቀድሞዋ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ነጋሽ መካከል ያለመግባባት ተከስቶ ለረጅም ጊዜ ሲያጨቃጭቅ የቆየ ሲሆን አሁን ድረስ እልባት ማግኘት አልቻለም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሲሰጥ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስቷል።
የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ደንድር እንደተናገሩት “የተጠየቀውን ገንዘብ በአንድ ጊዜ ክፍያ መክፈል አንችልም። አቅማችን በወር 40ሺ ብር መክፈል ነው፤ ቀሪውን ክፍያ ደግሞ በየወሩ 40 ሺ ብር እያደረግን በ4 ወር ከፍለን እንጨርሳለን በማለት ለአሰልጣኟ ነግረናታል ነገር ግን ሀሳቡን ልትቀበለው አልቻለችም።” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ኢሳያስ አያይዘውም ሲናገሩ “ሙሉውን ክፍያ ክፈሉ ተብለን የምንገደድ ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያልከፈለን ወደ 800ሺህ ብር የሚጠጋ የ2009 እና 2010 የሜዳ ገቢ ስላለን ከሱ ላይ እንዲከፈል ጠይቀናል፤ ያለን ብቸኛ አማራጭ ይህ ብቻ ነው።“ በማለት ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝደንቱ ሲያብራሩ “በቀደም በነበረው ውይይት ላይ የ10 ወር ክፍያ ለመክፈል ተስማምተናል መቼና እንዴት ይከፈል የሚለው አልተወሰነም፤ ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ አከፋፈሉን ተነጋገሩና አሳውቁ አሉ እንጂ በነጋታው ክፈሉ አላሉም።” ብለዋል።
የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ለማ ደበላ ደግሞ ሲያብራሩ “በአሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ዘመን እንጂ በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ጊዜ ውል እያለው የተሰናበተ አንድም ተጨዋች የለም፡፡ አሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ግን ውል ያላቸውን ተጨዋቾች አሰናብታ ከ600 ሺ ብር በላይ ከፍለናል፡፡” ሲሉ ምሬታቸውን አሰምተዋል። ስራ አስኪያጁ አከለውም “ከ16 ጨዋታ 12 ተሸንፋ መታገሳችን ካልሆነ በቀር አሠልጣኟ አልተበደለችም።” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ስራ አስኪያጁ “ክለባችን ስሙ ከጠፋ በሀገሪቱ ህግ መሠረት የመጠየቅ አቅጣጫም ይኖራል።” ብለዋል።
ይህን መግለጫ ተከትሎ አሰልጣኟ እንደገለጸችው “ኢትዮጲያ ቡና ይከፍለኝ የነበረው ደመወዝ 10 ሺ ብር ነበር፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ስቀላቀል የጠየኩት ብር የለም፤ የምፈልገው መስራትና አቅሜን ማሳየት ነው የፈለጋችሁትን ክፈሉኝ አልኩ እንጂ ያስቀመጥኩት የገንዘብ ጥያቄ አልነበረም።” አክላም ባለፈው አርብ ስራ አስኪያጁ አቶ ለማ ደወለና የሆነ ብር ለበዓሉ አውጥቼ ለመስጠት አስቤ አካውንታቱ አይታሰብም ብሏል። ስለዚህ እንፈራረምና ቀጣይ ሃሙስ እንጨርስ አለኝ። አይሆንም አልኩ አቶ ኢሳያስ ጅራ ደግሞ ቢያንስ 100ሺ ስጧትና ቀጣዩን መነጋገር ትችላላቹ አለን።” ስትል ተናግራለች። አሰልጣኟ ቀጥላም “ክለቡን 600 ሺ ብር ውል ማፍረሻ አስወጥታለች የሚሉት ውሸት ነው ውል ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው፤ እስቲ ልሞክራቸው ስል እሱ አንቺን አያሳስብም ካልፈለግሻቸው ችግር የለም፣ እኔ እጨርሰዋለው ያሉኝ የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ኢሳያስ ደንድር ናቸው።” ብላለች።