አዳማ ከተማ በዘጠኝ ነባር ተጨዋቾች ተከሰሰ

አዳማ ከተማ የ9 ነባር ተጫዋቾችን ህጋዊ ክፍያ አልከፈለም በሚል በተጨዋቾቹ ቅሬታ ቀረበበት፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስከ ሐምሌ 5/2012 ድረስ የተጨዋቾቹን ተገቢ ክፍያ ከፍለው አልጨረሱም በሚል ከማንኛውም የዝውውር ሂደት ካገዳቸው 6 ክለቦች መሀል አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ የማንኛውም ተጨዋች ደመወዝ ከ5ዐ ሺህ በር መብለጥ የለበትም የሚለው ሕግ ሳይፀድቅ በፊት የነበረን ውል በመሻር በአዲሱ የደመወዝ ክፍያ እየከፈለ መሆኑን ነባር ተጨዋቾቹን አስቆጥቷል፡፡

“በነባር የውል ስምምነቴ የሚከፈለኝ 15ዐ ሺህ ብር ነው አዲሱ ሕግ አይመለከተኝም፤ አየከፈሉ ያለው ግን 34 ሺህ ብር ብቻ ነው፤ ይሄ ሕገ ወጥ ተግባር ነው፤ ገና የ6 ወር ክፍያ አልተከፈለኝም በማለት ዳዋ ሁቴሳ ለሀትሪክ ተናግሯል፡፡ በነባሩ ውል የፈረሙ ወደ 9 ተጨዋቾች መሀል ለጊዮርጊስ የፈረመው ከነአን ማርከንህ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ምኞት ደበበ፣ ሱሌይማን መሀመድና ቡልቻ ሹራ ይገኙበታል፡፡ አዳማዎች ከሕጉ መውጣት በፊት የነበረ ውል አለማክበራቸው ፌዴሬሽኑ እንደማይቀበለው አሳውቋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የተናገሩት የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን “በክለቦች ዝርክርክ የሆነ አሰራርና ሕግን አክብሮ አለመስራት ፌዴሬሽኑ በፊፋ የሚቀጣበት ምክንያት የለም፤ ስለዚህ ሕግ የማስከበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ነገሮች እየከረሩ ሲመጡ ቅጣቱ ወደ ፌዴሬሽኑ የማይዞርበት ምክንያት ስለማይኖር’ እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም፡፡ ክለቦች በትክክለኛ መንገድ የሚጠበቅ ባቸውን እየከፈሉ መጓዝ መቻል አለባቸው” በማለት ለሀትሪክ ተናግረዋል፡፡ በክለቡ ውሣኔ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ወደ ፕሬዚዳንቱ አቶ ገመቹ ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸው ባለመቻላችን ምላሹን ማወቅ አለመቻላችንን እንገለፃለን፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport