“አትጠራጠሩ… በእኛ የጨዋታ ዘመን ቡና ወርዶ መጥፎ ታሪክ አይመዘገብም”አቡበከር ናስር (ኢት.ቡና)

👉👉“አትጠራጠሩ… በእኛ የጨዋታ ዘመን ቡና ወርዶ መጥፎ ታሪክ አይመዘገብም”

👉👉“ጎል እየሳትኩ ሲታገሰኝ…አይዞህ እያለ ሲያበረታታኝ የነበረው ደጋፊ ደስታው ተመልሶ ማየቴ የተለየ ስሜትን ፈጥሮብኛል”

👉👉“ካሣዬን በቃላት መግለፅ ይከብደኛል፤ጎሉን ካገባሁ በኋላ 15 ቁጥር ማልያውን ያሳየሁት ለእሱ ያለኝን ክብር ለመግለፅ ነው”

 

ኢትዮጵያ ቡና ከረዥም ጊዜ ትዕግስትና ቆይታ በኋላ ማሸነፉ የሚያስገኘውን ጣፋጭ ድል አጣጥሞ ቀምሷል…ደረጃውንም 10ኛ ደረጃ አድርጎ አንደኛውን ዙር ጨርሷል…ወላይታ ድቻን 3ለ1 በማሸነፍ፤ በጉዳትና በግብ ረሃብ ክፉኛ ሲሰቃይ የቆየው አቡበከር ናስር ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ ግብ በማስቆጠር ደስታውን በተለየ መንገድ ሲገልፅ ታይቷል፤የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በርካታ ለመሳት የሚከብዱ ኳሶችን ሲያመክን የነበረውን የትንሽ ኪሎና እድሜ ባለቤት ግን ባለ ትልቅ ልቡን የኢት.ቡናውን የጎል ሰው አቡበከር ናስርን “እንኳን ወደ ግብ አግቢነት ተመለስክ፤ይሄ ሁሉ የደስታ አገላለፅ ስሜት ከምን የመነጨ ነው?” በማለት ከጨዋታው በኋላ አነጋግሮት ከዚህ በታች ያለውን ቆይታ አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡- በጉዳት ምክንያት የተ ወሰኑ ጨዋታዎችን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆነህ አሣልፈሃል፤ ሜዳ ውስጥ ሆኖ መጫወትና ተጠባባቂ ሆኖ ጨዋታ መከታተል ምን ስሜት ይፈጥራል?
አቡበከር፡- … በጣም ያስጨንቃል… ቤንች ላይ ሆኖ ጨዋታ መከታተል መሰቃየት ነው፤ በጣም ይከብዳል፡፡ እኔም ተጠባባቂ ሆኜ እንደተመልካችም ሆኜ ጨዋታ ሳይ ነበር ሣይሆን ስጨነቅ ነበር ብል ይቀለኛል፡፡ ጥሩም ባይሆን ውጭ ሆኜ ጨዋታ ከማይ ሜዳ ውስጥ ጎል ስስት የሚፈጠርብኝ ብስጭት ይሻለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- .. ከጎል ጋር በጣም የተነፋፈክ፣ በጣም የጓጓህ ስለመሆኑ…የምታደርገው እንቅስቃሴ ያሳብቅብሃል…ትክክል ነኝ…?

አቡበከር፡- …ሳቅ…ይመስላል…አይደል… ?…ልክ ነህ…በግሌ ጎል አግብቼ ለመደሰት ሣይሆን ጎል አግብተን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ደጋፊው ሲጨፍር ለማየት በጣም ትልቅ ጉጉት በውስጤ ነበር፤ ያ ይመስለኛል…ያሳበቀብኝ…ሳቅ…ደግሞም የእኔ ብቻ አይደለም፤ የአብዛኛው የቡድኑ ተጨዋች ስሜትም ይሄ ነበር…፡፡

ሀትሪክ፡-…በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ለማግባት ሣይሆን ለመሣት የሚከብዱ ኳሶችን ሁሉ ስታመክን ታይተሃል…ታስታውሰዋለህ…?

አቡበከር፡- …ሣቅ…አዎን…በጣም አስታውሳለሁ…ከአንድም ሁለት ያለቀላቸው የሚባሉ ኳሶችን እንደሳትኩ ትዝ ይለኛል፤በተለይ አንድ ንፁህ ኳስ ከበረኛ ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝቼ…አንድ ጊዜ ደግሞ ከኮርና የመጣ መሣት ኳስ የሌለበትን ኳስ ስቻለሁ፤እንኳን ተመልካቹ እኔም አገባሁት ብዬ ስቻለሁ ያንን ኳስ ድጋሚ ባገኝ መሳቴን እጠራጠራለሁ፡፡ መሣት የሌለብኝ ኳስ እንደሣትኩ አምኜ ሁሉ አንገቴን በግርምት ሜዳ ውስጥ እስከመነቅነቅ እስከመሳቅ የደረስኩበት ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-…ቡድኑ ከፍተኛ የደጋፊ ጫና ነበረበት ከዚያ የመነጨ ነው ይሄን ሁሉ ጎል የሚስቱት የሚሉ አሉ…እውነት ቡድኑ ውስጥ በትክክል ጫና ነበር…?

አቡበከር፡- …እውነት ለመናገር የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም…ማሸነፍን ታርጌት አድርገን እየገባን በአብዛኛው አቻ ውጤት ማስመዝገባችን የፈጠረው ጉጉትና ጫና ቀላል የሚባል አይደለም፤ኢትዮጵያ ቡናንን የሚያክል የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነ ክለብ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የተቀመጠበት ሁኔታ መፈጠሩ ክለቡንም ደጋፊውንም የሚመጥን ስላልነበር ይህ መሆኑ የተወሰነ የጫና ስሜት ፈጥሮብን ነበር፡፡ የሄንን ወደ አሸናፊነት ለመለስ፣ በውጤት ማጣት፣ ባለማሸነፍ የተከፋው ደጋፊ ሲደስት ለማየት ካለን ጉጉት አንፃር ጫናዎች ነበሩብን፡፡ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ተስኖን እንኳን ይሄ ሁሉ ደጋፊ እያበረታታን ግን እሱ ሣይደሰት ሲወጣ ማየት በራሱ ያስጨንቃል፣ይረብሻል፡፡

ሀትሪክ፡-.. ደጋፊው በዚህ ደረጃ እየገባ እናንተ ውጤት ለማስመዘግብ እየቸገራችሁ ጨዋታ ማከናወን ፈታኝ ነው ብሎ መናገር ይሻላል…?

አቡበከር፡- …በጣም እንጂ… !…በጣም የሚገርምህ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነን… ደጋፊው ተስፋ ቆርጦ ከሜዳ ከመቅረት ይልቅ በብዛት እየገባ ሲያበረ ታታን ማየት በራሱ ይረብሻል፤ለእነሱ የሚገባቸውን አለመስጠታችን ሁላችንንም አስጨንቆናል፤እውነቴን ነው የምልህ ውጤት ሳናስመዘግብ የቀረን ቀን ከሜዳ የምንወጣው በጣም ተሳቀን ነው፤ምክንያቱም በችግር ጊዜ አብሮን ለቆመ ደጋፊ ይሄ ስለማይገባው ከእነሱ በላይ በጣም የምንጨነቀውና የምንሳቀቀው እኛ ነን፡፡

ሀትሪክ፡- በወላይታ ድቻ ላይ ያስመዘገባችሁት የ3ለ1 ውጤት ይህንን ጫና ያራግፋል ብለህ ታምናለህ…?

አቡበከር፡- …በጣም እንጂ…አሁን በቡድናችን ውስጥ የአሸናፊነት መንፈስ ተመልሷል፤ በእኛም በደጋፊው ፊት ላይ የጠፋው ፈገግታም ተመል ሷል፡፡ ድሉ ለበለጠ ውጤት ይበልጥ የማነሳሳት ትልቅ አቅም አለው፤ ገጥሞን ከነበረው የአቻና የሽንፈት ድብርት ውስጥ ጎትቶ የማውጣት ትልቅ አቅም ስላለው ጫናውን በማራገፉ በኩል ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ከወላይታ ድቻው ድል በፊት ኢትዮጵያ ቡና በወራጅ ቀጠና ውስጥ በመሆኑ “ቡድኑ ሊወርድ ነው እንዴ?” የሚል ስጋት የነበራቸው ሰዎች ድምፅ ይሰማ ነበር…፤…አንተስ ስለ ቡና መውረድ ለሰከንድም ቢሆን ያሰብክበት አጋጣሚ ነበር….?

አቡበከር፡- …ቡድናችን በወራጅ ክልል ውስጥ ሆኖ እንኳን እኔም ሆንኩ የቡድኑ አጠቃላይ ተጨዋቾች ስለመውረድ ያሰብንበት ጊዜ አልነበረም፤ቡድናችን ጥሩ ነው…ጥሩ አሰልጣኝም ነው ያለን…በዚህ ውስጥ ሆነን ይሄን ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ መንገድ ላይ “ወራጅ፤ወራጅ” እያሉ ሲናገሩ ስሰማ በጣም እገረም ነበር፡፡ ምክንያቱም ቡናን የሚያክል ክለብ እንደዚህ አይነት ስያሜ አይገባውም፡፡ደግሞም ጨዋታው እኮ ገና ነው…ገና አንደኛው ዙር ማለቁ ነው…ሙሉ የሁለተኛው ዙር ጨዋታ አለ…አንድ ጨዋታ ስታሸንፍ በአንዴ ወደ ላይ ነው የምትወጣው…እውነታው ይህ ሆኖ ስለመውረድ ማሰብ ለእኔ የማይቻል ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ቡና አይወርድም አትስጉ ነው የምትለው…?

አቡበከር፡- …አትጠራጠሩ…በፍፁም!… ይሄ እኮ የማይታሰብ ነው…ነገሮች በፍጥነት ተቀይረው አሁን ያለው በሌላ ታሪክ እንደሚተካ እምነቴ ነው፤ደግሞም በእኛ የጨዋታ ዘመን ቡና ወርዶ እንደዚህ አይነት መጥፎ ታሪክ አይመዘገብም፡፡ ቡና ሊወርድ ነው ሲባል እኮ ይሄ የመጀመሪያ አይደለም… በ2008 ይመስለኛል…ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆኖ ሊወርድ ነው እየተባለ ሲወራ ቆይቶ በሁለተኛው ዙር ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረው ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰንበትና በሀዋሳ ከተማ ለትንሽ ተበልጦ ዋንጫ ያጣበት ሁኔታ ነው የነበረው…ያውም ሀዋሳ ላይ ሶስት ነጥብ የተቀጡት ስለነበር…ስለዚህ አሁንም ከዚህ የተለየ ነገር አይፈፀምም፡፡ ይሄን ደጋፊ ይዘን…ይሄን ስብስብ ይዘን…ስለመውረድ ስጋት ለሰከንድም አናስብም፡፡

ሀትሪክ፡- ጎሉን ካስቆጠርክ በኋላ የካሳዬ ስም ያለበትን 15 ቁጥር ማልያ ስታሣይ ነበር፤ ሁሉም የቡደኑ ተጨዋቾችም ቤንች ድረስ መጥተው ከካሳዬ ጋር ደስታቸውን የተጋሩበት ሁኔታ ነው የነበረው… እስቲ ስለዚህ ሁኔታ አጫውተኝ…?

አቡበከር፡-…ብዙ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል…እነሱ ለእኔ በጣም ባውለተኞቼና ጥሩ አሰልጣኞቼ ናቸው፤ ካሳዬ ደግሞ በጣም የተለየ…ጥሩ አሰልጣኝ ነው…ለተጨዋቾች የሚያስብ፣የሚመች የተለየ ስብዕና ያለው ሰው ነው፡፡ በአውሮፓ ስታንዳርድ የምናያቸው አሰልጣኞች አሉ አይደል…አብሬያቸው ሰርቼ ባላይም ከታሪካቸው ስረዳ ግን…በእነሱ ደረጃ ያለ አሰልጣኝ ነው፡፡ ካሳዬን ሁሉም ተጨዋች ቤንች የተደረገው ተጨዋች ሣይቀር ቤንች አደረገኝ ብሎ ሳያኮርፍ የሚወደው አሰልጣኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ጎል ካገባህ በኋላ የካሳዬ ስም ያለበትን 15 ቁጥር ማልያ ያሳየህበትን ምክንያት ሣትዘለው ንገረኝ….?

አቡበከር፡ …የካሳዬ ስም ያለበትን 15 ቁጥሩን ማልያ ከቤቴ ነው ይዤ የመጣሁት…ዛሬ ጎል ካገባሁ ደስታዬን የምገልፀው ለካሳዬ ያለኝን ክብር በመግለፅ ነው ብዬ ወስኜ ነበር የመጣሁት፤ጎል በጣም ሲጠምብኝ በጣም ተበሳጨሁ…በቃ ለካሳዬ ያለኝን ክብርና ደስታ ጎል አግብቼ ሳልገልፅ ልወጣ ነው? ብዬ ለብቻዬ እስከ ማውራት ሁሉ ደርሼ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ጎል ስናገባ ማልያውን ከያዘልኝ ልጅ ተቀብዬ ደስታዬን ለመግለፅ ሁሉ አስቤ ነበር ከጉጉቴ የተነሣ፤መጨረሻ ላይ ግን አላህ አላሳፈረኝም ራሴው አግብቼ ያሰብኩት አሣክቻለሁ ፤ደስታዬን በዚያ መልኩ መግለፄ፣ክብሬንም ፍቅሬንም በማሳየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-…ካሳዬን ግለፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምትገልፀው…?

አቡበከር፡- …ካሳዬን በቃላት መግለፅ ለእኔ ከባድ ነው፤ ካሳዬ የተለየ ስጦታም ስብዕናም የታደለ ሰው ነው፤የተጨዋቾችን ፣የደጋፊዎችን የሁሉንም ስሜት ጠንቅቆ የማያውቅ ነው፤ ቡና ውስጥ ረዥም ህይወቱን በማሳለፉ ክለቡ ምን እንደሚፈልግ የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ የሚገርምህ እኔ በባህርዬ ቸልተኛ የምባል አይነት ሰው ነኝ…ካሳዬ ሲያወራ ግን በጣም ከሚያዳምጡት አንዱ ነኝ…ካሳዬ የሚያወራው ነገር ሁሉ ይስባል…የሚለው ነገር ሁሉ ይስብሃል…ይለውጥሃል…፤…አንዳንድ ሰው ሙሉ ቀን ሲያወራ ውሎ ምንም ስሜት የማይሰጥህ አለ…የካሳዬ አንዷ ንግግር ግን ትለውጥሃለች…ውስጥህ የሚቀር ነገር ነው የሚናገረው፤ትልቅ ህልምና ራዕይም ያለው ሰው ነው ካሳዬ…በዚህ የተነሣ እኔ በጣም ነው የምወደው፡፡

ሀትሪክ፡- …የካሳዬ ፍልስፍናን በተመለ ከተ ሁለት የተለያዩ ሃሣቦች በደጋፊው መካከል ሲሰነዘሩ ይደመጣል… በዚህ ዙሪያ አንተ ምን ትላለህ..?…የካሳዬ ፍልስፍናስ ቡናን የት ያደርሰዋል…?

አቡበከር፡-…ካሳዬን የሚቃወሙትም…የሚደግፉትም ሌላ የተለየ ተንኮልና ክፋት ኖሮአቸው አይደለም… ሁለቱም ለክለቡ የሚያስቡ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፤አንዳንድ ደጋፊዎች ሲቃወሙ የነበረው የክለቡን ሽንፈት ማየት ካለመፈለግ…ሁሌም ድልን ከመመኘት አንፃር እንደሆነ ነው የምገነዘበው…ግን እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስቀመጥ የምፈልገው የካሳዬ ሃሣብ…ይዞት የመጣው ነገር ለሀገር የሚጠቅም ነው… ጊዜና ትዕግስት አጥብቆ ይፈልጋል…ስለዚህ ደጋፊውን የምለው ነገር በትዕግስት የነገውን በማየት ድጋፋቸውን እንዲሰጡን ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …አንደኛውን ዙር 10ኛ ደረጃን ይዛችሁ አጠናቃችኋል፤ በሀለተኛው ዙር ከቡና ምን እንጠብቅ…?

አቡበከር፡- …በውጤትም…በጨዋታም የተሻለውን ቡና ጠብቁ ነው የምለው…በአንደኛው ዙር ከነበሩብን ድክመቶች ተምረን ጠንካራውን ጎናችንን ይበልጥ አጠናክረን በመቅረብ ደጋፊዎችንን እንደምናስደስት በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ አሁን በጥሩ ሰዓት ላይ ነው ወደ አሸናፊነት የተመለስነው…ደጋፊዎቻችን ተጨዋቾቹ በሙሉ መጨረሻ ላይ ባገኘነው ድልና ወደ አሸናፊነታችን በመመለሳችን ተደስተው ነው የተመለሱት…በዚህ መልኩ አንደኛውን ዙር ጨርሰን ወደ ሁለተኛው ዙር መሸጋገራችን በቀጣይ በጥሩ ስሜት እንድንዘጋጅ ይረዳናል…አሰልጣኛችንም ከአንደኛው ዙር ጥንካሬያችንም ድክመታችንም ተነስቶ የተሻለ ነገር ለመስራት በቂ ጊዜ ስለሚያገኝ በዚህ መሠረት ተዘጋጅተን በውጤትም በጨዋታም የተሻለው ቡናን ይዘን እንቀርባለን፡፡

ሀትሪክ፡- ኢት.ቡና ከውጤት በተጣላበት ጊዜ ደጋፊው ተስፋ ሣይቆርጥ ከቡድኑ ጎን ሆኖ ሲያበረታታ ታይቷል…የክለቡን ደጋፊ በተመለከተ ምን ትላለህ…?

አቡበከር፡- …የቡናን ደጋፊ የተለየ የሚያደርገው ትልቁ ኳሊቱያቸውም ይሄ ይመስለኛል…ደጋፊውን የበለጠ እንድትወደ ውና እንድታከብረው የሚያደርገው… ውጤት ሲኖር ብቻ ሣይሆን ውጤት ሲጠፋም ተበሳጭቶ ከሜዳ ከመቅረት ይልቅ ከጎናችን ሆኖ ሲያበረታታን ነበር፡፡ ሰኞ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታ ሲኖረን እንኳን ውጤት የለም ብሎ ከሜዳ ከመቅረት ይልቅ ስራ ያለው ስራውን ትቶ ቤተሰቦቹ ሌሎች ችግሮችን ከመፍራት ይቅርብህ ሲሏቸው ቃላቸውን ጥሰው መጥተው ይደግፉናል ያበረታቱናል፡፡ እውነት ነው የምልህ የተለየ ደጋፊ ነው፤እንደ ኢት.ቡና አይነት ደጋፊ አሁን ያለው ውጤት አይገባውም… በየአመቱ ዋንጫ ማግኘት ራሱ የሚበዛበት ሣይሆን የሚያንሰው ደጋፊ ነው፤ በሁለተኛው ዙር በውጤትም በጨዋታም እንደምንክሳቸው ነው መናገር የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ ቀረ የምትለው ካለ…?

አቡበከር፡- …ምንም የቀረ የለም…የቀረ ነገር ካለ እናንተን (ሀትሪኮችን) ከልብ አመሰናግለሁ…ሁሌም ለምትሰጡኝ ማበረታቻና መድረክ…ከዚህ በተረፈ…ስለደጋፊው ተናግሬ አልወጣልኝም…በተለይ እኔ ጉዳት ሲገጥመኝ አብሮ እየተጎዳ…ስታመም እየታመመ…ሜዳ ውስጥ ገብቼ ጎሎችን ሶስት 90 ደቂቃ ሙሉ እየታገሰ… እያበረታታ “አቡኪ፤አቡኪ” እያለ ድጋፉን ያለስስት ስለሚሰጠኝና ስለሚያበረታታኝ በጣም ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ሌላው ሣልናገር ማለፍ የማልፈልገው ደጋፊው ውጤት በመጥፋቱ ሊበሳጭ ይችላል…ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው…ግን ቡደኑ ነጥብ የጣለው ተበልጦ ሣይሆን በልጦ መሆኑን መርሳት የለብንም…ሁላችንም ትዕግስት ያስፈልገናል፤እኔም ደጋፊ ሆኜ ስላየሁት የውጤት መጥፋት ሊያበሳጨን ይችላል…ግን ካሳዬ ይዞት የመጣው ነገር ለቡና አይደለም ለሀገር ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ልንታገሰው ይገባል፤ ትዕግስት የተሻለ ደስታን ለክለባችን ይዞልን ይመጣልና እባካችሁን ታገሱን ማለት እፈልጋለሁ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.