“አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን የመቅጠር ዕቅድ የለንም” ቅዱስ ጊዮርጊሶች

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለቀድሞ የዋሊያዎቹ አለቃ ከአብርሃም መብራቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልጀመረ አስታውቋል፡፡ ከአሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር የክለቡ 3 አመራሮች ተነጋግረው እንደተስማሙና ነሀሴ 1/2ዐ12 አሰልጣኙ በይፋ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል የሚሉ መረጃዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
ይህን ተከትሎ ከክለቡ አመራሮች ከተገኘ መረጃ አንድም የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራር ከአሰልጣኝ አብርሃም ጋር እንዳልተነጋገረ አሰልጣኙንም የመሾም እቅድ እንደሌለው በአጽንኦት ተናግሯል፡፡ አሰልጣኝ አብርሃምም ጉዳዩን በወሬ ደረጃ ከመስማቱ ውጪ ከአንድም የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራር ጋር እንዳልተነጋገረ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ2ዐ13 የውጪ አሰልጣኝ የመቅጠር ፍላጎት እንዳላቸው ነገር ግን ውድድሮች መቼ እንደሚጀመሩ ሳይታወቅ ከአሰልጣኞች ጋር የውል ስምምነት ማድረግ ከባድ እንደሆነባቸው ለሀትሪክ የደረሰው መረጃ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላሀዲን ቤርጌቾ እና ሳላሀዲን ሰይድ ወደ ሌሎች ክለቦች ሊያመሩ ነው የሚለውን ዜና ጊዮርጊሶች አስተባብለዋል፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች እስከ ሰኔ 3ዐ/2ዐ13 ድረስ ውል ያላቸው በመሆኑ ወደየትም እንደማይሄዱ እናረጋግጣለን ሲሉ መረጃዎቹን አስተባብለዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport