አራተኛ ቀኑን በያዘው ትግራይ ዋንጫ ሥስት ክለቦችን በያዘው ምድብ ሁለት ሲዳማ ቡና ና ሰሎዳ ዓድዋ ያገናኘው ጨዋታ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።ጥሩ ፋክክር ያስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብዙ ሙከራዎችን ቢያስተናግድም በዕለቱ ኮከብ ሆነው በዋሉት ግብ ጠባቂዎች ሙከራዎቹ መክነዋል።የውድድሩ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሲዳማዎች የመጀመርያው አጋማሽ ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም እንደወሰዱት ብልጫ ብዙ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።ከርቀት እና ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች ግብ ለማግኘት ሙከራዎችን በተደጋጋሚ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች አብዛኞቹ ሙከራዎቻቸው በሰንደይ ሮቲሚ ና በጥብቅ ሲከላከል በነበረው የሰሎዳ ዓድዋ ተከላካይ ክፍል ሲጨናገፍባቸው ታይቷል።በተቃራኒው መልሶ ማጥቃት ላይ ትኩረት ያደረጉት ሰሎዳ ዓድዋዎች በአብዱሰላም የሱፍ አማካኝነት ያደረጉዋቸው ጠንካራ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ና በተከላካዮቹ ጥረት ግብ ከመሆን ተርፈዋል።

የሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር ና የሙከራ ብልጫ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ተጋባዦቹ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም አሸናፊ ሚያረጋቸው ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ አዲሱ ተስፋዬ ከሀብታሙ ገዛሀኝ የተላከለት ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅሞ ከሰንደይ ሮቲሚ ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።በተጨማሪ ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ ጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ሀብታሙ ገዛሀኝ አማካኝነት የተፈጠረለትን ግልፅ ግብ የማግባት ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።ሰሎዳ ዓድዋ በበኩላቸው ሁለተኛው አጋማሽ ላይ አብዛኛው ጊዚያቸው ከኳሱ ጀርባ በመሆን ያሳለፋ ሲሆን አልፎ አልፎ ያደረጉዋቸው ሙከራዎች መሳይን የፈተኑ ነበሩ።በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያ ላይ በአብዱልናፊ ኢድሪስ ና ተቀይሮ በገባው አላዛር ዘውዱ አማካኝነት ያደረጉዋቸው ሙከራዎች በምሳሌነት ሚጠቀሱ የሰሎዳ ዓድዋ ሙከራዎች ናቸው።በውጤቱም መሰረት የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያስተናገዱት ዓድዋዎች ጨዋታውን አቻ ማጠናቀቃቸው ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ የምድቡ መሪ ሲሆኑ ሲዳማዎች በበኩላቸው የምድቡ የመጀመርያ ጨዋታቸውን አቻ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ዓርብ ከስሁል ሽረ ሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል።
ቀጣይ ጨዋታዎች ሀሙስ ህዳር 4 2012
7:30 | አክሱም ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
9:30 | መቐለ 70 እንደርታ ከ ደደቢት
አስተያየት ይስጡ