ባየርን ሙኒክ ኢትዮጵያ ውስጥ ያዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ሲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ ጋር ሐትሪክ ቆዬታ አድርጋለች

ባየርን ሙኒክ ኢትዮጵያ ውስጥ ያዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ተጠናቀቀ። ውድድሩን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ ጋር ሐትሪክ ስፖርት ቆይታ አድርጋ ነበር እንድታነቡት እንጋብዛለን።

ሀትሪክ:- በመጀመሪያ ባየርን ሙኒክ በኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታና ያዘጋጀው ውድድር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ እንኳን ደስ አሎት።

አቶ መኮንን :- እንኳን አብሮ ደስ አለን ባየን ሙኒኮች በጣም ጥሩ ቆይታ ነበር ያደረጉት ለታዳጊ ተጫዋቾች እና ለ አዲስ አሰልጣኞች ጥሩ እድል መፍጠር ችለናል።

ሀትሪክ:- ባየርን ሙኒኮች ወደ አዲስ አበባ የመጡበት ዋና ምክንያት ምን ነበር?

አቶ መኮንን:- የባየርን ሙኒክ አመጣጥ ዲፕሎማቲክ በሆነ ግንኙነት ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያውያና ጀርመን ባላቸው ሁለትዮሽ ግንኙነት ስፓርቱ በተለይ እግርኳሱ የግንኙነቱ አንድ አካል ነው። በዚህ መሰረት ነው የመጡት። ወደ ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው አንድ ጀርመናዊ ነበር እሱም ኢትዮ-ጀርመን ፍትቦል ፕሮጀክት በማለት ለ አምስት. . . ስድስት አመት የቆየ ስራ ሲሰራ ነበር ከዛ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ባየርን ሙኒክን ወደዚ ጋበዘልን ማለት ነው። ባየርንም ፍቃደኛ ሆኖ ወደ ሀገራችን መጣ። ባየርን ወደ አፍሪካ ሲመጣ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ናት።

በግንኙነቱ የኢትዮጵያ ዋና አላማ ምንድነው ብለህ ብትጠይቀኝ . . . ኢትዮጵያውያ ውስጥ የባየርን ሙኒክ ትምህርት ቤት መክፈት ነው።

በዚህም መሰረት ለትምህርት ቤቱ የሚሆኑ መምህራን አሰልጣኞችን የማሰልጠን ስራ ነበር ስንሰራ የነበረው። እንግዲህ በሁለት ዙር በሰጠነው ስልጠና ለትምህርት ቤቱ ብቁ የሆኑ አሰልጣኞች ተገኝተዋል ብለን ነው የምናስበው።

እንደገና ደግሞ አሁን የተጠናቀቀው የዩዝ ካፕ (የወጣቶች ዋንጫ) ባየርን ሙኒክ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ዓለም አቀፍ የወጣቶች የባየርን ዋንጫ” የተባለ የእግርኳስ ውድድር አለ እኛም ሀገራችንን ወክለው የሚሄዱ ተጨዋቾችን እንድንመርጥ ነበር ውድድሩን ያዘጋጀነው። እና በዚህ መልኩ ሁለት ቀን የፈጀ ውድድር አካሂደን ወደ 160 የሚሆኑ ታዳጊዎች ተሳትፈዋል። በአንድ ቡድን 10 ተጫዋቾችን እያደረግን ውድድር አካሂደን ዛሬ በተሳካ ሁኔታ ጨርሰናል።


ሀትሪክ:- ባየርን ሙኒክ ለአሰልጣኞች የሰጠው ስልጠና ምን አይነት ነበር?

አቶ መኮንን:- ሁለት የአሰልጣኞች ስልጠና ነው የሰጠነው። አንደኛው ለዚሁ ለባየርን ሙኒክ ትምህርት ቤት መምህርነት የሚሆኑ አሰልጣኞችን የማፍራት ሥራ ነው የተሰራው ቅድም እንደነገርኩህ ሁለት ዙር ነበር የመጀመሪያው መስከረም ላይ ነበር የተሰጠው አሁን ደግሞ ሁለተኛ ዙሩን ሰጥተናል። ጀማሪ አሰልጣኞችን ነበር ያሳተፍነው እንደነ አዳነ ግርማ አይነቱን ማለት ነው። ወደ 60 አሰልጣኞች ነበሩ የተሳተፉት ከዛ ውስጥ ባለን የመመዘኛ መንገድ ተጣርተው 9 ብቻ ነው የቀሩት። በማጣሪያው ከቀሩት አሰልጣኞች ጋር ወደ ፊት እንሰራለን ብለን እናስባለን።

እንደገና ደግሞ ወደ 24 የሚሆኑ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞችን 3 ቀን የፈጀ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መስጠት ችለናል።

 

ሀትሪክ: አሁን በውድድሩ ለተመረጡት ልጆች የተያዘው ቀጣይ እቅድ ምንድነው?

አቶ መኮንን:- በቀጣይ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከግንቦት 7 እስከ 10 በሚካሄደው የባየርን ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያውያን ወክለው የሚጫወቱ ይሆናል። ለኛ ይሄ ትልቅ ዕድል ነው በዚህ የዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ መሳተፏ ትልቅ ኩራት ነው።

ሀትሪክ: ኢትዮጵያ ይከፈታል የተባለው የባየርን ሙኒክ ትምህርት ቤት መቼ ይከፈታል?

አቶ መኮንን:- ይሄኛው ልዑክ ከተመለሰ በኋላ አንድ ሌላ ልዑክ ይመጣ እና የስምምነት ውል እንፈራረማለን። እርግጠኛ ነኝ በኔ ግምት መስከረም ላይ ይከፈታል ብዬ አስባለው ምክንያቱም አሁን መሰረታዊ የሚባሉት ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት። ከዚህ ውጪ የሚጠበቅብን አካዳሚያችንን ለስልጠና ምቹ ማድረግ ነው። አካዳሚያችን ሶስት ለስልጠና የሚሆኑ ሜዳዎች የሚሰራ ሰፊ ቦታ አለው ይህም ማለት 2 የተፈጥሮ ሳር እና 1 የአርቴፊሻል ሳር ያለበት ሜዳ መስራት እንችላለን። በተረፈ አካዳሚያችን አብዛኛው ነገር ሥራ ለማስጀመር የተሟላ ስለሆነ ባየርኖች ስልጠና የሚሰጡበት ቦታ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህም አልፎ ተርፎ የብሔራዊ ቡድኖቻችን መሰልጠኛ እና ማረፊያ ይሆናል።