“በወጣቶች የተገነባ እና ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድንን ይዘን ልንቀርብ ዝግጁ ነን” የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አስቻለው ሀይለ ሚካኤል

 

የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከበርካታ ተጨዋቾቹ ጋር ለመለያየት ቢችልም የመጪው ዘመን ቡድኑን በወጣት ተጨዋቾች ላይ አተኩሮ ለመስራት እና የፕሪምየር ሊጉም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚዘጋጅ የቡድኑ አሰልጣኝ አስቻለው ሀይለ ሚካሄል ለሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከአሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ እና 10 ከሚደርሱ ተጨዋቾቹ ጋር ከተለያየ በኋላ የቡድኑን የማሰልጠን ሀላፊነት የተረከበው ረዳቱ አስቻለው “ክለባችን ምንም እንኳን ከአቅም ውስንነት አኳያ በርካታ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾቹን ቢያጣም ተጨዋቾቹም የተሻለ ጥቅምን ፍለጋ ወደ ሌሎች ቡድኖች ቢያመሩም እኛ ግን ባለን አቅም እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም ባስቀመጠው መመሪያ እና ደንብ መሰረት በመጓዝ በወጣቶች የተገነባ እና ጥቂት ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በማካተት ጥሩ እና ጠንካራ ቡድንን ለመስራት ዝግጁ ነን ሲል ሀሳቡን አክሎ ገልፃል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ለኢችንኮ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ለፐልፕና ወረቀት እና ለአዳማ ከተማ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው እና አዳማ ከተማንም በ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታቶች ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲሸጋገር ጎል በማስቆጠር ጭምር ትልቁን ሚና የተወጣው በአሰልጣኝነትም ለእዚሁ ክለብ ለ6 ዓመታት ረዳት ሆኖ የሰራው እንደዚሁም ደግሞ እነ አብይ ሞገስን የመሳሰሉ ምርጥ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾችን ከባሌ በማስመጣት እና ወደሚያሰለጥነው የሪፍት ቫሊ ቡድን ውስጥም እንዲካተቱ ያደረገው እና የአማራ ውሃ ስራዎች ቡድንንም በረዳትነት ያሰለጠነው አስቻለውን የአዳማ ከተማ ክለብን በመጪው የውድድር ዘመን በሀላፊነት ይዞ ከመቅረቡ አኳያ አጠር ባለ መልኩ አናግረነዋል።

የአዳማ ከተማ በርካታ ተጨዋቾች ከክለቡ ጋር ስለመለያየታቸው እና በመጪው ዘመን ስለሚገነቡት ቡድን?

“ወደ ተለያዩ ክለቦች የሄዱብን ተጨዋቾች ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር በጣም ጠቃሚ የነበሩ ተጨዋቾች ናቸው። ያም ሆኖ ግን ቡድናችን ካለበት የፋይናንስ እጥረት አኳያ እነዚህ ወሳኝ ልጆቻችን የውል ዘመናቸውን በማጠናቀቃቸው እና የተሻለ ጥቅምንም ስላገኙ ከክለቡ ጋር ሊለያዩ ችለዋል። የእግር ኳስ ተጨዋቾች በጨዋታ ዘመናቸው መጠቀም አለባቸው የሚል እምነቱ አለኝ። ክለባችን አሁን ላይ አቅም ኖሮት እነዚህን ልጆች ቢያስቀር ኖሮ ደስም ይለኝ ነበር። ግን አቅሙ ስለሌለው ያን ማድረግ አልቻለም። ይሄ በመሆኑም እነዚህ ተጨዋቾች ለቡድናችን ላበረከቱት የእከዚ ቀደም አስተዋፅኦዋቸው ልናመሰግናቸው ይገባል። ይሄን ከተረዳን በኋላም የእነዚህን ተጨዋቾች ቦታ ለመሸፈን በአሁን ሰዓት ለአራቱ ቡድኖቻችን ማለትም ለዋናው ለሴት እና ለተተኪዎቹ ቡድኖች የተመደበውን በጀት በማብቃቃት እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም ያስቀመጠውን መመሪያ እና ደንብም በማክበር በወጣቶች የተገነባ እና ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድንን ለመስራት እየተዘጋጀን ይገኛል። ይሄ ቡድንም የሚያካትታቸው ወጣት ተጨዋቾች በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በሱፐር ሊግ ደረጃ የተጫወቱ እና ከተተኪዎቻችንም የምናሳድጋቸው ይሆናል ሲልም አስተያየቱን ጨምሮ ሰጥቷል “።

እንደ አዳማ ከተማ ክለብም ሆነ እንደ አሰልጣኝነትህ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ስላላችሁ እምነት?

“አዳማ ከተማ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ያለው እምነት ከፍ ያለ ነው። የከዚህ በፊት ቡድኑንም በዛ ደረጃ በመገንባት ጠንካራ ተፎካካሪነቱን አሳይቷል። በርካታ ተጨዋቾቹንም ለእውቅና አብቅቷል። ይሄ ቡድን ከተተኪ ቡድኑ ያፈራቸው ተጨዋቾችም ናቸው የዋናውን ቡድን ካገለገሉ በኋላ ዛሬ ላይ ወደተለያዩ ቡድኖችም እያመሩብን ያሉት እና ይሄን በወጣት ተጨዋቾች ላይ እምነትን ማሳደር ልንቀጥልበት ይገባል።
እንደ ክለብ ብቻ ሳይሆን እንደ አሰልጣኝም ሳየው በወጣት ተጨዋቾች ማመን ጥቅሙ ለክለብ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር ነው። በዓለም እግር ኳስ ዛሬ ላይ በ17 ዓመታቸው በርካታ ተጨዋቾች ቡድናቸውንም አገራቸውንም እየጠቀሙ ተደናቂነትን አትርፈዋልና እኛም ይሄን ነው ልንከተል የሚገባን። በወጣት ተጨዋቾች ላይ ለመስራት ትልቁ ነገር ከአንተ ድፍረት ነው የሚጠበቀው እና እኔም ሆንኩ ክለቤ ይሄን አምነንበት ተጨዋቾችን ከታዳጊ ቡድን በማሳደግ እንደዚሁም ደግሞ ሊጠቅሙን የሚችሉ ወጣት ተጨዋቾችን ከተለያየ ቦታ አምጥተን በማካተት ጠንካራ የፕሪምየር ሊጉ ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት እየሰራን ነው”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website