“በኳሱ ገና ጀማሪ ነኝ፤ ለታላቅ ተጨዋችነትም ለመብቃት ጠንክሬ እሰራለው”ብሩክ በየነ /ሐዋሳ ከተማ/

 

👉👉“በኳሱ ገና ጀማሪ ነኝ፤ ለታላቅ ተጨዋችነትም ለመብቃት ጠንክሬ እሰራለው”
👉👉“ለጌታነህ ከበደ ያለኝ አድናቆት አሁንም ቢሆን ከአህምሮዬ የማይጠፋ ነው”

ወጣት ነው፤ ብሩክ በየነ ይባላል፡፡ በሐዋሳ ከተማ በልዩ ስሟ ቀበሌ ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው፤ ይሄ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች የአሁን ሰዓት ላይ ለክለቡ ተደጋጋሚ ጎሎችን እያስቆጠረ በመምጣቱ ጥሩ እውቅናንም አግኝቷል፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታን ተወልዶ ባደገበት የቄራ አካባቢ ሜዳ ላይ በታዳጊነት ዕድሜው የጀመረው ይኸው ተጨዋች በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ የክለቡ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱም ታላቅ ተጨዋች መባልን ስለሚፈልግ ለእዛ ጠንክሮ እንደሚሰራም ይናገራል፡፡
የእግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት ከጀመረ በኋላ ለወልቂጤ ከተማ ቡድን ለሁለት ዓመታት የተጫወተው እና በመጀመሪያው ዓመት 7 በሚቀጥለው ዓመት 9 ግቦችን በማስቆጠር ጎል አዳኝ መሆኑን እያስመሰከረ ያለው ብሩክ በየነ በፕሪምየር ሊጉ የእዚህ ዓመት ተሳትፎውም ለቡድኑ 9 ግብ አስቆጥሮ የፕሪምየር ሊጉ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ራሱን ከቶ ይገኛል፡፡
የሐዋሳ ከተማ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋችን ቡድናቸው ፋሲል ከተማን ከ2ለ0 መመራት አንሰራርተው 3ለ2 ባሸነፉበት ጨዋታ አንድ ጎልን ያስቆጠረ ሲሆን ከእዚህ ተጨዋች ጋር በኳስ ህይወቱ ዙሪያ ስለቡድናቸው እንደዚሁም ደግሞ በሊጉ ምን ውጤትን እንደሚያስመዘግቡና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጥያቄዎችን አቅርቦለት በሚከተለው መልኩ ምላሾቹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀ ምር ለትልቅ ደረጃ እደርሳለው ብለህ ነው?

ብሩክ፡- አዎን፤ ያኔ በቄራ ሜዳ ላይ ነበር ኳስን የምንጫወተው፤ ብዙዎቻችንም የደቡብ ፖሊስ ደጋፊ ነበርን፤ እኔም ከቡድኑ ባሻገር ለአጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ ችሎታም የተለየ አድናቆትና ፍቅሩም ስለነበረኝ እንደእሱ በክለብ ደረጃ ተጫውቼ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስን አልም ስለነበርኩ በዚህ ደረጃ ነው ኳሱን መጫወት የጀመርኩትና ለትልቅ ደረጃም ለመብቃት ጥረትን እያደረግኩ ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ከምላሽህ እንደተረዳሁት ጌታነህ ከበደ የአንተ የልጅነት ዕድሜህ ሞዴልህ ወይንም ደግሞ ተምሳሌትህ ተጨዋች ነው ማለት ነው?

ብሩክ፡- አልተሳሳትክም፤ የደቡብ ፖሊስ ካምፕ እኛ ሰፈር ስለነበርና እሱም ሲጫወት በደንብ ስለተመለከትኩት ከልጅነቴ አንስቶ ነው ጌታነህ ከበደን አድንቄው ያደግኩት፤ በጊዜው እሱ ታዋቂ ተጨዋች ባይሆንም ለቡድኑ ግን ተደጋጋሚ ጎሎችን ከመረብ ያሳርፍ ነበርና በኋላም ላይ ነው የታዋቂ ተጨዋችነትን ክብር እያገኘ ሲጓዝ የበለጠም ወደድኩትና አሁንም ድረስ ለጌታነህ ከበደ ያለኝ አድናቆት እና ፍቅር ከአህምሮዬ ፈጽ ሞም የማይጠፋው፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ የተወለድክበት የሐዋሳ ከተማ አካባቢ እነማንን ተጨዋቾች አፍርቷል?

ብሩክ፡- ብዙ ተጨዋቾች አሉ፤ ከእነዛም መካከል እነ ጋዲሳ መብራቱ እና አሸናፊ ሽብሩን የመሳሰሉት ተጨዋቾች በጥቂቱ የሚገለጹ ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- ከባህር ማዶ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ….የምታደንቀውስ ተጨዋች?

ብሩክ፡- ሊቨርፑል እና ባርሴሎና የምደግፋቸው ሁለት ቡድኖች ናቸው፤ ሰይዶ ማኔን ደግሞ በጣም የማደንቀው ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሊያነሳ ተቃርቧል፤ በእዚህ ዙሪያ ያለ ስሜት ምን ይመስላል?

ብሩክ፡- ዋንጫውማ የእሱ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፤ በእዚህም በጣም ደስ ብሎኛል፤ በዋናነት የምፈልገው ግን በአንድ ወቅት በአርሰናል የተያዘውን የብዙ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ሪከርድንም ሰብሮ ዋንጫውን እንዲያነሳም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ቤተሰቦችህ ይፈቅዱልህ ነበር?

ብሩክ፡- አዎን፤ ከመፍቀድ ባሻገርም በብዙ ነገሮች ያበረታቱኝም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የቤተሰባችሁ ስፖርተኛ አንተ ብቻ ነህ…ስንት ወንድም እና እህተስ አለህ?

ብሩክ፡- ሶስት ወንድሞች እና አንድ እህት አለኝ፤ የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ በመጫወት ከሆነ አዎን እኔ ብቻ ነኝ የቤቱ ስፖርተኛ፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ ታናሽ ወንድሜ የእኔን ፍላጎት ለመከተል ወደተጨዋችነቱ መጥቶ ጋሽ ከማል አህመድ ጋር በፕሮጀክት ደረጃ ኳስን እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ሐዋሳ ከተማ የገባህበት የኳስ ሂደት ምን ይመስላል?

ብሩክ፡- የሐዋሳ ከተማ ተጨዋች የሆንኩት በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አማካኝነት ነው፤ እሱ መጀመሪያ ቄራ ሜዳ ላይ ስጫወት አይቶኝ ወደ ወልቂጤ ከተማ ቡድን ወስዶኝ ነበር፤ እዛም ለሁለት ዓመታት ተጫወትኩ፤ በኋላ ላይ የብቃቴን ጥሩነት ሲመለከትና ሐዋሳ ከተማን ማሰልጠን ሲጀምር የሙከራ እድሉን ሰጥቶኝ ወደ ቡድኑ እንድገባ አደረገኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርከው አጥቂ ሆነህ ነው?

ብሩክ፡- ልጅ እያለው የመሀል ተጨዋች ነበርኩ፤ በኋላ ላይ አጥቂ ሆንኩና በዚሁ ስፍራ መጫወቱን ቀጠልኩበት፡፡

ሀትሪክ፡- ለወልቂጤ ከተማም ሆነ አሁን ላይ ለሐዋሳ ከተማ ስትጫወት ተደጋጋሚ ጎሎችን እያስቆጠርክ ይገኛል፤ በእዚህ ዕድሜ ጎል ማስቆጠርህ የፈጠረብህ የተለየ ስሜት አለ?

ብሩክ፡- አዎን፤ በተለይ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ አሁን ላይ ለኮከብ ግብ አግቢነቱ መፎካከር መቻሌ በጣም ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማኝ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊት ደግሞ ብዙ መስራት ከቻልኩ ከእዚህም በላይም ጎሎችን አስቆጥሬ ለከፍተኛ ደረጃ እንደምበቃ ውስጤን እየነገረኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ለኮከብ ግብ አግቢነቱ እየተፎካከርክ ነው፤ አሁን ላይ ትልቅ ተጨዋች ነህ ማለት ነው?

ብሩክ፡- በፍጹም እንደዛም ብዬ ጨርሼ አላስብም፤ እኔ ገና ጀማሪ ተጨዋች ነኝ፤ ራሴን ለከፍተኛ ደረጃ ለማብቃትም ጠንክሬ እየሰራው ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ፉክክር ምን ይመስላል?

ብሩክ፡- የሊጉ ውድድር በጣም ከባድ ሆኗል፤ ሁሉም ክለቦችም ጠንካራ ሆነው መጥተዋል፤ ስለዚህም ይህን ለመወጣት ጠንክሮ መስራት አዋጪ ሆኗል፡፡

ሀትሪክ፡- ሐዋሳ ከተማ የሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜ አንስቷል፤ ላለፉት በርካታ ዓመታቶች ደግሞ ውጤት ርቆታል፤ በእናንተ ዘመን የቡድኑ የስኬታማነት ጊዜ ዳግም ይመለሳል?

ብሩክ፡- ይመስለኛል፤ አሁን ላይ ቡድናችን ጥሩ ነው፤ የመጀመሪያ ዙር ውድድራችንንም በ6ኛ ደረጃ ሆነን አጠናቀናል፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ የበለጠ ተጠናክረን ስለምንመጣ ውጤታችን ይሻሻላል፤ በአጭር ጊዜያቶችም ውስጥ የቀድሞ ስምና ዝናችንም ይመለሳል፡፡

ሀትሪክ፡- የሐዋሳ ከተማ የተጨዋቾች ስብስብ እና የቡድኑ ይዘት በምን መልኩ ይገለጻል? ጠንካራ እና ክፍተት ጎኑስ?

ብሩክ፡- ስብስባችን በጣም ጥሩ ነው፤ በወጣት ተጨዋቾችም ነው የተገነባው፤ ልምድ ያላቸውም ጥቂት ተጨዋቾች እኛን ያግዙናል፤ ያለን ጠንካራ ጎን በሜዳችን እስካሁን ያልተሸነፍን መሆኑ ሲሆን ክፍተታችን ደግሞ ከሜዳ ውጪ ጎሎች የሚቆጠርብን መሆኑ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪምየር ሊጉ የእስካሁን ጨዋታችሁ በጣም ያስደሰተህ?

ብሩክ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነው የእሁዱ ጨዋታ ነዋ! ይሄ ግጥሚያ ከ2ለ0 መመራት አንሰራርተን ያሸነፍነው ጨዋታ ስለነበር በጣም አስደስቶኛል፤ ከዚህ ጨዋታም ጠንክረህ ስራ እንጂ ምንም ነገርም ማድረግ እንደሚቻልም ትምህርትም አግኝተንበታል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ምን መልክ ነበረው?

ብሩክ፡- ጨዋታው እረፍት እስክንወጣ ድረስ በጣም ፈጣን ነበር፤ ጎል አግብተውብን ወዲያው ነበር ወደ ጨዋታው የተመለስነው፤ ፋሲሎች መርተውን እንደሌላ ቡድን ለመከላከል ወደኋላ አያፈገፍጉም ነበር፤ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ነበር የሚጫወቱትና ለተመልካቹም ለእኛም ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ታግለን ስለተጫወትን ግጥሚያውን ለማሸነፍ ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኳስ ውጪ የእረፍት ጊዜህን የት ታሳልፋለህ?

ብሩክ፡- ከቤተሰቦቼ ጋር እና ከጓደኞቼ ጋር በመጫወት ነው የማሳልፈው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ጂም በመስራትና ወደ ሐይቅ በመሄድም አሞራ ገደል እዝናናለው፡፡

ሀትሪክ፡- ሙዚቃ ትወዳለህ… ማንንስ ታደንቃለህ?

ብሩክ፡- አዎን፤ እወዳለው፤ የእሱባለው እና የቴዲ አፍሮም አድናቂ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በምን ባህሪህ ትገለፃለህ?

ብሩክ፡- ከሰዎች ጋር ብዙ አልቀራረብም፤ ዝምተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ሐዋሳ ከተማን በአንድ ቃል ሰትገልፃት?

ብሩክ፡- ይህቺ የትውልድ ሀገሬ የፍቅር ከተማ እና ሰዎችም በጣም የሚወዷት ናት፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህ እንዴት ይገለፃሉ?

ብሩክ፡- ለእኔ ሁሉ ነገሬ ናቸው፤ ላደረጉልኝ ነገሮች ሁሉ በጣሙን አመሰግናቸ ዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?

ብሩክ፡- በእግር ኳሱ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ እኔን በማሰልጠንም ሆነ በመምከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉልኝ ሁሉ ያለኝ ምስጋናና ክብር ከፍተኛ ነው፤ በተለይ ደግሞ አዲሴ ካሳ ለእኔ እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳልና እሱን በተለየ መልኩ አመሰግነዋለው፤ ከእሱ ውጪም ቤተሰቦቼና ጓደኞቼም ሌላው በምስጋናው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website