“በኢት.ቡና ደጋፊዎች መዝሙር ታጅቦ መጫወት በጣም ናፍቆኛል”ፈቱዲን ጀማል

ፈቱዲን ጀማል ስለ ኮሮና ቫይረስ

“በኢት.ቡና ደጋፊዎች መዝሙር ታጅቦ መጫወት

በጣም ናፍቆኛል”


አለም ሁሉ በየሰከንዱ አንድ ቃል እንዲያወራ ተገዷል…ኮሮና ቫይረስ የሚል አስጨናቂ ቃል፤የሰው ልጅ ህይወትን፣ ጤናውን፣ ሠላሙንና ደስታውን፣ኢኮኖሚውን ሁሉን ነገሩን ይሄው ኮሮና ቫይረስ የተባለው አለም አቀፉ
ወረርሽኝ ነጥቆታል፡፡
የስፖርቱ መንደሮች ታላላቅና አለም አቀፉ ውድድሮች ከእንቅስቃሴው ውጪ ሆነው ቡድኖችና ተጨዋቾች፣አሰልጣኞች በጉልበተኛው ኮሮና ቫይረስ እገዳ ተጥሎባቸው በአንድነት ቦዝነው የሚያሳልፉበት ጊዜም ላይ
ደርሰዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የዜና አውታሮች የየዕለቱን ዜና በኮሮና ቫይረስ ጀምረው በኮሮና ቫይረስ መጨረስ የየዕለት ተግዳሮታቸው እንዲሆን በዚሁ ቫይረስ እጃቸውን ከተጠመዘዙም ውሉ አድሯል፡፡
ሁሉንም ነገር በጉልበቱ የተቆጣጠረው የኮሮና ቫይረስ የውድድር ሜዳዎችን፣ እንቅስቃሴዎች የመዝናኛ ቦታዎችንና በረራዎችን ጭምር ፀጥ ረጭ በማድረግ ሣይቆም ይሄ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ የ39 ሺህ
ሰዎችን ውድና መተኪያ የሌለው ህይወትንም አስገብሯል፤ከ800,000 በላይ ሰዎችንም በቫይረሱ ተጠቂ አድርጓል።
ይህ አለምን እያስጨነቀ ያለው ወረርሽኝ ወደ ሀገራችንም ብቅ ብሎም ብዙ ነገሮችን አመሰቃቅሏል እስከአሁን 21 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቂ እንዲሆኑ ምክንያትም ሆኗል፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ የኢት.ቡናውን ቁልፍ ተጫዋች ፈቱዲን ጀማልን ክፉኛ አስጨንቆታል፤“የመጣውን ነገር ከመቀበል በዘለለ አላህ ምህረቱን እንዲያወርድልን መፀለይ ብቸኛው መፍትሔ ነው” ሲል የሚመክረው
ፈቱዲን ጀማል “ከሁሉም ነገር በላይ የናፈቀኝ በቡና ደጋፊ ታጅቦ መጫወት ነው”ሲልም ተናግራል።
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዘጠኛ ይስሀቅ በላይ በኮሮና ቫይረስ ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ባጠናቀቀው ከፈቱዲን ጋር በነበረው ቆይታው በዚህ አስከፊ ቫይረስ ዙሪያ ፈቱዲን ጀማል የሰጠውን ቁም
ነገር ያለው ምላሽ ከዚህ በታች አቅርቦታል፡፡


ማስክ አድርገህ ነው የምትንቀሳቀሰው…?…የሠላምታ ስታይልህንስ ቀይረሃል…?

“እውነት ለመናገር አብዛኛውን ጊዜዬን እቤት ስለማሣልፍና ብዙም እንቅስቃሴ ስለማላደርግ እስከአሁን የፊት ማስክ አላደረኩም፤የሠላምታ ስታይሌን በተመለከተ ግን በጣም ቀይሬያለሁ…መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ
የሚባል ነገር የለም…በርቀት ከአንገቴ ጎንበስ…እጄን በደረቴ ላይ አድርጌ…በጣም አክብሮት የተሞላበት ሠላምታ ነው እየተለዋወጥኩ ያለሁት፡፡ ይሄን ስታደርግ የሚረዱህ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ… አንዳንዶች የምን ማካበድ
ነው…?…የሚሉ አሉ…አንደንዶች ደግም ሊጨብጡህ እጃቸውን ሲዘረጉ መጨባበጥ የለም ስትላቸው…የናቅካቸው ወይም እነሱ በሽተኛ ናቸው ብለህ የሸሸኻቸው ይመስል…በጣም የሚከፋ ሰዎች አጋጥመውኛል፤ግን
ምንም ማድረግ አይቻልም…ጊዜው ያመጣው ነው፡፡ የህክምና ባለሙያዎች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና መንግሥታችን ቫይረሱ እንዳይሰራጭ በሚል የሚሰጠንን መመሪያ መተግበር ግዴታችን ስለሆነ በዚህ መንገድ እየተ
ጓዝኩ ነው”

በእንግሊዝኛ ሶስት መመሪያዎች አሉ Stay Home (ቤት መቀመጥ) Social Distance (ርቀትን መጠበቅ) Safe Life (ህይወትን ማዳን) የሚሉ…አንተ የትኛውን እየተገበርክ ነው?

“እኔ እንግዳህ በተቻለኝ አቅም 3ቱንም ለመተግበር እየሞከርኩ ነው፤ አስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከቤቴ አልወጣም…ሰው በተሰበሰበት ቦታም አልገኝም…ርቀቴን ጠብቄ ነው የምገኘው…የሰዎችንም የራሴንም
ህይወት ለመታደግ ነው ይሄን የማደርገውና በግሌ እየሞከርኩ ነው”

 

በአሁን ሰዓት (እስከ ሰኞ ማለዳ) ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም ከ34,000 ሰዎች በላይ በሞት ሲነጠቁ ከ724,900+ ሰዎች በላይ ደግሞ በቫይረሱ ተጠቅተዋል፤ የቫይረሱን ጉልበተኛነትና ገዳይነት…አለምን እንዲህ ማሸበሩን

እንዴት ታዘብከው…?

 

“ይሄ ከሁላችንም አዕምሮ በላይ የሆነ ያልታሰበ ዱብ እዳ ነው የወረደብን፤ መጀመሪያ በሽታው ቻይና ላይ ተገኘ ሲባል ሁላችንም ጆሮ አለመስጠት ብቻ ሣይሆን እዛው ተጀምሮ እዛው የሚያልቅ አድርገን ነበር ያሰብነው፤
እንዲህ እንደ አሁኑ በመላው አለም የሚገኙ ህዝቦችን በሞት ይነጥቃል…ወደ እኛ ሀገርም ጎራ ብሎ ያስጨንቀናል ብለን ብዙም አልገመትንም፤በተለይ አቅም ያላቸው…ቴክኖሎጂ አላቸው የሚባሉ ሀገሮችን ክፉኛ
መፈታተኑ…ብዙ ነፍሶችን መንጠቁ የበሽታውን ጉልበተኝነትና ከባድነት ያሳያል፡፡ በተለይ በየሰዓቱ የምትሠማው ዜና ያስደነግጣል፣ይረብሻል…በ24 ሰዓት ከ800 ሰዎች በላይን ሲነጥቅ መስማት የቫይረሱን አስከፊነት በግልፅ
ያሳያል፤ እኔ የምለው አላህ በዚህ በቃችሁ ቢለን ነው”

 

ኮሮና ቫይረስ ባመጣው ጣጣ ከጨዋታም ከልምምድም ርቀህ ተቀምጠሃል፣ በዚህ መልኩ ማሳለፍ ያለው ስሜት ምን ይመስላል?

 

“የየዕለት ተግባሬ ከሆነው፣በጣም ከምወደው ነገር ባላሰብከውና ባልገመትከው ሁኔታ ያውም የራስህ ባልሆነ ችግርና ምክንያት አርፈህ ተቀመጥ ድርሽ እንዳትል የሚል ውሣኔ ሲተላለፍብህ አምነህ ለመቀበል
ይቸግርሃል፡፡ በየቀኑ ልምምድና ጨዋታ ሲያደርግ ሙያው እግር ኳስ ብቻ ለሆነ ሰው…እግር ኳስ ያለበት ቦታ ዝር እንዳትል ብሎ ኮሮና ውሳኔ ሲያስተላልፍብህ እውነቴን ነው የምልህ ከባድ የሆነ የህመም ስሜት እንዲሰማህ
ነው የሚያደርገው፤ይሄ አጋጣሚ ለእኛ ብቻ ሣይሆን አለም ላይ ላሉ ተጨዋቾች ሁሉ መጥፎና ከባድ የሚባል አጋጣሚ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።የለመድነውን፣የምንወደውን ነገር አጥተን እጅና እግራችንን አጣጥፈን እቤት
መቀመጣችን…በጣም…በጣም…ከብዶናል፤ሳንወድ በግድ ይሄንን መራራ ዕውነት መቀበል እጣ ፈንታችንም ሆኗል፡፡ ይሄንን የምልህ በመቀመጣችን ምን አይነት መጥፎ ስሜት በውስጣችን እንደተፈጠረ ለማሳየት እንጂ
ከበሽታው ከባድነትና በቀላሉ ከመሠራጨቱ የእግር ኳስ ውድድር ዋነኛ የመተላፊያ ቦታ ከመሆኑ አንፃር መንግስት ለህዝባችን ደህንነት ቀድሞ ይሄን እርምጃ መውሰዱ አግባብ በመሆኑ ከሚደርሰው ጉዳት አንፃር ውሳኔውን
እቀበለዋለሁ፡፡ መቀመጣችን ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነን ከምንወደው ነገር መራቃችን ከባድ እንደሆነ ባልክድም ይሄ ሁሉ ከክብሩ የሰው ልጅ ህይወት ስለማይበልጥ በአዎንታዊነት ነው የተቀበልኩት፡፡ መጀመሪያ እኛ ስንኖር
ነው እግር ኳስም የሚኖረው…ህዝባችን በሠላምና በጤና ሲኖር ነው ተመልካችም ኳስም የሚኖረው፡፡”

 

ሁለት ሳምንት ከኳስ ርቀሃል ጊዜውን ምን እየሠራህ ነው የምታሳልፈው?

“የሚገርምህ ከሙያዬ አንፃር አብዛኛውን ጊዜዬን ሳሳልፍ የነበረው ከቤተሰቦቼ ጋር ተራርቄ ነበር፤ አሁን አጋጣሚው ተራርቄያቸው፣ተነፋፍቂያቸው ከነበሩት ቤተሰቦቼ ጋር ናፍቆታችንን እንድናጣጥም በደንብ
እንድጠግባቸው ጥሩ እድል ፈጥሮልኛል፤ ከዚህ ውጪ በጋራ ልምምድ በመቆሙ የቤታችን ግቢ ውስጥ በጥንቃቄና በርቀት የተለያዩ ልምምዶችን እየሠራሁ አሣልፋለሁ፣ በተለይ ደግሞ ከታናናሽ ወንድሞቼ ጋር በጣም
በጥንቃቄ የጠረጴዛ ቴኒስ እየተጫወትኩ አሣልፋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ አጋጣሚው ጥሩ አንባቢ ጥሩ የመረጃ ሰው እንድሆን እድሉን ፈጥሮልኛል፣ ጋዜጦችንም መጽሔቶችንም አነባለሁ…የተለያዩ መረጃ የሚገኝባቸውን
ቻናሎችን እየተከታተልኩም ነው ጊዜውን የማሳልፈው”

ቡና ወደ ተሻለ አቋምና አሸናፊነት እየተመለሰ ባለበት ሰዓት ውድድሩ መቋረጡስ አላስቆጨህም?

“ትክክል ነህ ቡና ወደ አሸናፊነት እየመጣ ባለበት ሰዓት፣በቡድኑ ካምፕ፣በደጋፊዎች ውስጥ ጥሩ የመነቃቃት ስሜት እየተፈጠረ ባለበት ሰዓት ይሄ ነገር መከሰቱን እንደመልካም አጋጣሚ አላየሁትም፤በዚህ ወቅት
ባይሆን ብለህ የምትመኘው ነገር ሊኖር ይችላል…ግን ሁሉም ነገር ከሰው ልጅ ህይወት አይበልጥም፡፡ የሚገርምህ ቫይረሱ ሀገር ውስጥ ገባ በተባለበት ሰዓት ከጅማ አባጅፋር ጋር ለመጫወት ጅማ ነበረን…ደግነቱ ቫይረሱ እዚህ
መግባቱን የሠማነው ከጨዋታው በኋላ ነው፤በወቅቱ እንደሰማን በጣም ነው የደነገጥነው፣የተረበሽነው፤ከጅማ ጨዋታ በፊት ቢሆን የሠማነው ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስበው…ቫይረሱ ገባ የሚለው ዜና
ይረብሻል…ካለው አስከፊነት አንፃር መንግስት ይሄን መወሰኑ ያስመሰግነዋል፡፡ ይሄ ባይሆን ጨዋታ ቢካሄድ ደጋፊዎች በውጤቱ ተደስተው ቢጨባበጡ ቢተቃቀፉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ምን አይነት ዋጋን
እንደሚያስከፍለን ስታይ ውሳኔው ተገቢ መሆኑን ትረዳለህ፤ከሰው ህይወት የሚበልጥ ነገር ስለሌለ ውሳኔውን አከበርኩ እንጂ አልተከፋሁም፡፡”

 

ፕሪሚየር ሊጉ ስለመቋረጡ ሁላችንም እርግጠኞች ነኝ፣ ፕሪሚየር ሊጉ ከዚህ በኋላ ስለመጀመሩስ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይችላል?

“አሁን ያለው ሁኔታ በጣም አስፈሪ ነው፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይሄን ማሰብ ከባድ ነው፤ አለም ከኮሮና ቫይረስ ነፃ የወጣችበት ሣይሆን ይበልጥ እየተጠቃች፣የሰው ልጅ ህይወትም እየተነጠቀ ያለበት፣ በሀገራችንም
ከችግሩ የፀዳንበት ሁኔታ ስለሌለ ሊጉ ቶሎ ይጀመራል ብዬ እንዳላስብ አድርጎኛል፡፡ አሁን አለም ሁሉ እግር ኳስ ሣይመለከት ወደ 3 ሳምንት አካባቢ አስቆጥሯል፤ይሄን ያህል ጊዜ አስቆጥሮም እግር ኳሱ ስለመመለሱ ከግምት
ውጪ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛም ሊግ ቶሎ ይጀመራል ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል፤ደግሞም የከበደ ነገር እያለ ሊጉ መመለሱን አልደግፍም፡፡ ሁላችንም ማሰብ ያለብን ሊጉ ስለመመለሱ ሣይሆን ስለ
ሰው ልጅ ህይወት ነው፤መቅደም ያለበትም ይሄ ነው፡፡እኔ አሁን ላይ በተለይ በዚህ አመት ሊጉ ተመልሶ እንጫወታለን ብዬ ማሰቡ በጣም እየከበደኝ ነው፡፡

“ለጣልያን እንፀልይ” የሚል መልዕክት ቴሌግራም ፕሮፋይል ፒክቸርህ አድርገህ ተመልክቻለሁ…ይሄን ያደረክበት የተለየ ምክንያት አለህ…?…ወይስ ጣሊያን ዘመድ ስላለህ ነው?

“ጣልያን ዘመድ የለኝም፤ ያንን የደረኩት ዘመድ ስላለኝም አይደለም፤ጣሊያን ላይ በደረሰው ነገር በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን በመነጠቁ እንደ ሰው ከፈጠረብኝ ከፍተኛ ሀዘን በመነጨ ነው ያንን ያደረኩት፡፡ ይሄ ሁሉ
ሰው በአንድ ሌሊት እንደ ቅጠል እየረገፈ ሳይ…በሽታው በጣልያን ላይ በጣም መጨከኑን ስመለከት ሌላ ነገር ማድረግ ባልችል እንኳን የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለምን ለሌሎች አላጋራም…ከሚል ነው ያደረኩት እንጂ ዘመድ
ስላለኝ አይደለም…በአንድ ቀን 700 እና 800 ሰው በሞት መነጠቅ ለጣሊያን ብቻ ሣይሆን ለመላው አለም ጥቁር አሻራም የጣለ ነው፤ጣሊያን ስለሆነች አይመለከተኝም ማለት አይቻልም…የሰው ልጅ እየጠፋ በመሆኑ
ያምሃል…ደግሞም ነግ በእኔ ማለት ነው ያለብንና ከዚያ አንፃር ተነስቼ ነው ያንን ያደረኩት፡፡”
ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ለዋንዶውስኪና ሌሎች የአለማችን ታላላቅ ተጨዋቾች፣ክለቦች…ከሀገር ቤት ቅ/ጊዮርጊስ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ኃይሌ ገ/ስላሴ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና አሰልጣኝ ዘማርያም የኮሮና ቫይረስን ለመግታት ለሚደረገው

ጥረት ከስፖርቱ ማህበረሰብ ድምፃቸውን ሲያሰሙ እስከአሁን ግን የእናንተ የተጨዋቾች ድምፅ አልተሰማም…በሠላም ነው?

“አዎን ትክክል ነህ አልተሰማም፤ እስከአሁን አልተሰማም ማለት ግን ከዚህ በኋላ አይሰማም ማለት አይደለም፤ በጣም ይሰማል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተወሰንን ተጨዋቾች እየተነጋገርን ነው…እንዴት ይሁን? በጋራ ወይስ
በግል አሊያም እንደ ክለብ ነው…በሚለው ላይ እየተወያየን…በየጊዜው እየተ ነጋገርን ነው፡፡ ያው እንደምታውቀው የም ን ናኘው በአካል ሣይሆን በስልክ በመሆኑ ትንሽ ጎትቶብናል፡፡ ችግሩ ወይም የመጣው ወረርሽኝ በሀገር
ላይ በመሆኑ እኛንም ተጨዋቾች ይመለከተናል…በሽ ታው ሲጠፋ፣ሀገር ሠላም ስትሆን ነው እኛም ሥራችንን የምንሰራው፤የምንችለውን በገንዘብም ይሁን በቁሳቁስ አልያም ያለንን ተቀባይነት ተጠቅመን የበኩላችንን
አስተዋፅኦ እናደርጋለን፡፡”

ከጨዋታ ከራቅክ ወደ ሶስተኛ ሣምንት እየተሸጋገርክ ነው ምን ናፍቆሃል?

“በጣም የናፈቀኝ በናፍቆት እያሰቃዩኝ ያሉት የኢት.ቡና ደጋፊዎች ናቸው፤ በጣም ትልቅ ነገር (Miss) እንዳደረኩ እንዳጣሁም እየተሰማኝ ነው፤ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መዝሙር ታጅቦ መጫወት በጣም
ናፍቆኛል፤ በአይኔ እየመጣ እየረበሸኝ ያለውም የቡና ደጋፊዎች መዝሙር ነው። መቼ ነው በዚህ ማራኪ ደጋፊ መዝሙርና ደጋፊ ታጅቤ የም ጫወተው? እያልኩ ከናፍቆት በመነጨ ራሴን እየጠየኩ ነው”
በመጨረሻ ሀገራችንን ጨምሮ አለምን ሁሉ ካንቀጠቀጠው ወረርሽኝና ፈተና ተገላግላ ወደቀድሞ ሠላማዊ እንቅስቃሴዎቿ እንድትመለስ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

“ከሁላም በላይ ሁላችንም እንደየእም ነታችን መፀለይና አምላካችን ምህረትን እንዲያወርድልን ሌት ተቀን መለመንን ነው ማስቀደም ያለብን፤የመጣብንን አላህ እንዲ መልስልን መለመን አለብን፡፡ እኛ ሰበቡን
እናድርስ አላህ ከመድሃኒቱ ጋር አገናኝቶ ምህረቱን እንዲልክልን እንደየዕምነታችን አብ ዝተን እንፀልይ፤ ከዚህ ውጪ ህዝቡ በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት የሚሰጡትን መመሪያዎች ሠምቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው
ያለበት፤እኔ ራሴን ስጠብቅ፣ቤተሰቤን ስጠ ብቅ፣ ሀገርን እጠብቃለሁና ሁሉም ይሄንን ያድርግ ነው ምክሬ፡፡”

ቀሪ የምትለው አለ…?

“እናንተም ራሳችሁን ጠብቁ፣ ሠላም ሆኑ ጨርሻለሁ”

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.