በሩዋንዳ የሚካሄደው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ትናንት ተጀምሯል ።
በአገሪቷ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በሚካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አዘጋጇ ሩዋንዳ ፣ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ ይሳተፋሉ።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችና ሌሎች 10 ልዑካንን በመያዝ ከትናንት ወዲያ ወደ ሩዋንዳ በማምራት ማምሻውን የአገሪቷ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ መድረሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በሰላም ዘርአይ አሰልጣኝነት የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ትናንትና የሁለተኛ ቀን ልምምዱን ማድረጉም ተገልጿል።
ሉሲዎቹ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የውድድሩን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ከኡጋንዳ ጋር በሩዋንዳ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰዓት ከኡጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።
በአጠቃላይ አምስቱ አገራት እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ እንደሚሆን የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) አስታውቋል።
የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል።
የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ወጪ በተቀመጠለት ጊዜ ለአዘጋጇ ሩዋንዳ ባለመላኩ ውድድሩ ከግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲራዘም ቆይቷል።
አስተያየት ይስጡ