“በመቐለ 7ዐ አንደርታ ቡና እያለሁ ያገኘሁትን ጥሩና ተመሳሳይ ነገሮች ተመልክቻለሁ”ተስፋዬ በቀለ /ጃምቦ/ (መቐለ 70 አንደርታ)

🔑“በመቐለ 7ዐ አንደርታ ቡና እያለሁ ያገኘሁትን ጥሩና ተመሳሳይ ነገሮች ተመልክቻለሁ”

🔑“ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወቴ ብዙ ነገሮችን አትርፌያለሁ”
ተስፋዬ በቀለ /ጃምቦ/ (መቐለ 70 አንደርታ)


በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ቆይታው ለኢትዮጵያ ቡና፤ ለመከላከያ እና ለአዳማ ከተማ ክለቦች በተከላካይ ስፍራ ተጫውቶ አሳልፏል፤ ዘንድሮ ደግሞ የመጀመሪያ ዙርን ክለብ አልባ ሆኖ በቤቱ ካሳለፈ በኋላ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት ወደ መቐለ 70 እንደርታ አምርቶ ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል፤ በተጨዋችነት ዘመኑ ከቡና ጋር የፕሪምየር ሊግን ዋንጫለ ከመከላከያ ጋር የጥሎ ማለፍን ዋንጫ ያነሳው ይኸው ጠንካራና ስኬታማ ተጨዋች በአሁን ሰዓት ወደ አዲሱ ክለቡ ስለተቀላቀለበት ሁኔታና ሌሎችን ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አንስቶለት ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል፡፡


ሀትሪክ፡- ኮሮና ቫይረስ የዓለም ስጋት ሆኖ በርካታ ሰዎችን እያሳታን ይገኛል? መጀመሪያ ላይ ስለዚሁ ቫይረስና በሽታ ስትሰማ ምን አልክ?

ተስፋዬ፡- ምን እላለው ብለህ ነው፤ የዓለም ህዝብንም ሆነ እኛን ኢትዮጵያኖች እግዚአብሄር ይተብቀን ከማለት ውጪ፤ ከዛም ባሻገር በሽታው በሌላውም ዓለም ላይ በታም እየተስፋፋና እስከሞት በሚደርስም ደረጃ ችግር እና ጉዳትንም እያስከተለ ስለሆነም እኛም ላይ አያድርስብንም ለማለት ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- ቫይረሱ ልክ ወደ ኢትዮጵያ ውስት መግባቱንስ የሰማህ ቀን የነበረህ ስሜት በምን ደረጃ ላይ የሚገለጽ ነበር?

ተስፋዬ፡- መጀመሪያ ላይ እንደ ማንኛውም ሰው በጣም ነው የደነገጥኩት፤ ምክንያቱም ስለበሽታው የሚነገረውና የምትመለከተው ነገር በጣም ያስፈራልና፤ በተለይ ደግሞ በሽታው ትላልቅ የሚባሉ ሀገሮችን እንዲህ እያሽመደመዳቸው ከመጓዙ እና ከእኛ ሀገርም አኗኗር አኳያ ስትመለከተው ነገሮች ከበድ ስለሚሉ ለእዚሁ ሁሉ ፈጣሪ ይጠብቀንም ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- የኮሮና ቫይረስን በምን መልኩ ለመከላከል እንደሚቻል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ የማስ ሚዲያዎች እና ስልኮች ላይ ለህዝቡ መግለጫን በማውጣት መመሪያን አስተላልፏል፤ አንተስ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ነዋሪና የእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ይህንን ተንተርሶ ምን የምታስተላልፈው መልዕክት አለ?

ተስፋዬ፡- በእዚህ ጉዳይ ዙሪያ እኔ ማለት የምፈልገው መጀመሪያ ፈጣሪ ይጠብቀን የሚለውን ነው፤ ከዛ ቀጥሎም የጤና ጥበቃ ያወጣውንና ለህብረተሰቡም እያስተላለፈ ያለውን መልዕከት በጥንቃቄ በመቀበል ተግባራዊ ማድረግም መቻል ነው፤ ከዛ በመቀጠልም በሽታው እንዳያስፋፋ እና ወደ ወረርሽኝ ደረጃም እንዳይቀየር ሰዉ ንክኪውን መቀነስ፤ በሶሻል ግንኙነቱም ወቅት በተወሰነ ርቀትና ደረጃም በመራራቅ መቆምና እጁንም በየሰዓቶቹ መታጠብ ይኖርበታል፤ ከሁሉ በላይ ከራስ በላይ ማንም የለምና ራስህንም ስትጠብቅ ማህበረሰቡንም ትጠብቃለህና እንደዚህ እያደረግን በሽታው እንዳያስፋፋ ማድረግ እንችላለን፡፡

ሀትሪክ፡- በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ የእግር ኳስ ውድድሮችም ቆመዋል? ከእነዛ መካከልም አንዱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግና ሌሎች ውድድሮቹ መቋረጥ መቻላቸውም ነውና ይሄን ጊዜስ ምን ማለት ቻልክ?

ተስፋዬ፡- ውድድሮቹ መቋረት መቻላቸውማ የግድ ነው፤ መሆንም ያለበትም ነው፤ ምክንያቱም በአንድ አካባቢ በጀማ ተሰብስበህ መገናኘት መቻል አግባብም ስላልሆነ ነው፤ ሰው ጤና ሲኖረው ነው የሚኖረው፤ ጤና ከሌለ ከሰው ጋር የምትገናኝበት የምትግባባበት እንዲሁም ሌላ ምንም የምታደርግበት ነገር የለምና መመሪያውን ማክበር ዋንኛው ጉዳይ

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ክለብ አልባ ተጨዋች ነበርክ፤ በቅርቡ ደግሞ የሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮት ሲከፈት አዲሱን ክለብህን መቐለ 70 እንደርታን በመቀላቀል ለቡድኑ እየተጫወትክ ይገኛል? እንዴት ወደእነሱ ልታመራ ቻልክ?

ተስፋዬ፡- የአሁን ሰዓት ላይ በሊጉ እየተጫወትኩ ላለሁበት የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ላመራና ወደ እነሱም ገብቼ ለመጫወት የቻልኩት ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ክረምቱ ላይ ውሌ አልቆ ነበርና በድጋሚ ለቡድኑ እንድጫወት ተፈልጌ ፊርማዬን እንዳኖር ከተደረግኩኝ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ በኋላ ለተጨዋቾች የሚከፈላቸው ወርኃዊ የደመወዝ ክፍያ 50 ሺ ብርና ከዛ በታች ነው የሚል መመሪያን በማውታቱ እና እኔ ደግሞ ለቡድኑ ለመጫወት ፊርማዬን ያኖርኩት ይሄ መመሪያ ከመውታቱ ከ20 ቀናት በፊት በመሆኑ የሊጉ ውድድር ሊጀመርና የዝውውር መስኮቱም ወደመዘጋቱ በሚቃረብበትና ሌሎች እኛን የሚፈልጉንም ቡድኖች ተጨዋቾችን አስፈርመው እያጠናቀቁ ባለበት ሰዓት ላይ አዳማዎች መልሰው ቃላቸውን በማጠፍ እናንተም ወደ 50 ሺዎቹ ደመወዝ ትገባላችሁ ሲሉን ጊዜ አንድአንድ ተጨዋቾች ሌላ ምርጫው ስላልነበራቸው ከክለቡ ጋር ተስማምተው በመቀተል ለመጫወት ሲችሉ እኔ ግን በእዚሁ መልኩ እንዴት ብዬ ነው ቃላችሁን አጥፋችሁ ለእናንተ የምጫወተው ስራዬንስ እንዴት አድርጌ ነው ለቡድኔ የምሰራው በሚል ሳልስማማ ቀረውና በስተመጨረሻም ምንም ነገር ይቅርብኝ በማለት መብቴን ማስከበር አለብኝ በሚል ከቡድኑ ጋር ከተለያየው በኋላ የአንደኛውን ዙር ወደየቱም ቡድን ሳላመራና ሳልጫወት በመቅረት እንደዚሁም ልምምዴንም በግል እና ጂም በመስራት ከዛ ውጪም የመጀመሪያው ዙር ሊተናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት አዳማዎች መልሰው ጠርተውኝ ከእኛ ጋር ሆነህ ልምምድህን እየሰራህ የሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮት እስኪከፈት ድረስ መተበቅ ትችላለህ ሲሉኝ እኔም ከእነሱ ጋር እየሰራው በመቆየት በስተመጨረሻም በጣም ለፈለገኝ የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ፊርማዬን ለማኖር ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- የተጨዋቾች የደመወዝ ክፍያ 50 ሺ ብር የሚለው ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት በነበረው የመጀመሪያውና ከፍተኛው ክፍያ እንደአንተ ሁሉ ለአዳማ ከተማ የፈረሙት ሌሎቹ ተጨዋቾችስ እነማን ነበሩ? በኋላ ላይስ ከክለቡ ጋር በእዚሁ የብር ክፍያው ዙሪያስ ያወራችሁት የተለየ ነገር ነበር?

ተስፋዬ፡- የአዳማ ከተማ ክለብን በቀጣይነት ለማገልገል በፊት በነበረው ክፍያ ፊርማችንን ካኖርነው ተጨዋቾች መካከል ከእኔ ውጪ ሲኒየር የሚባሉት ተጨዋቾች ነበሩበት፤ ከእነዛም መካከል እነ አዲስ ህንፃ፣ ሱሌይማን መሀመድን ሌሎች የመሳሰሉ ተጨዋቾችም የሚጠቀሱ ናቸው፤ ያኔ እኛም በተስማማነው ብር ቢሮ ውስጥ ከፈረምንም በኋላ ወደ ፌዴሬሽን ሄደን አልፈረምንም ነበርና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ስናናግራቸው እናንተ እኮ ለቡድኑ የደከማችሁና ሲኒየርም ተጨዋቾች ናችሁ በተስማማነው መልኩም ነው ክፍያውንም የምንፈፅምላችሁ ካሉን በኋላ መልሰው ደግሞ ያሉትን ቃል አጥፈው በእዚህ ፌዴሬሽኑ ባወጣው የደመወዝ ህግም ነው የምትጫወቱት ሲሉን እኛ ገንዘቡ አይደለም ይሄ ህግ ግን ለሁሉም የሚሰራ ከሆነ እኛ አይደለም በ50 ሺብር በ10 ሺ ብርም እንጫወታለን፤ ሆኖም ግን እኛ የፈረምነው ህጉ ከመውጣቱ አስቀድሞ ስለነበር በእናንተና በእኛ መካከል መተማመን መኖር አለበት፤ እናንተ ግን አሁን እኛን የትም መሄድ አይችሉም ብላችሁ ነው አይደል ስምምነቱን ለማፈረስ የተዘጋጃችሁት በማለት ከክለቡ ለቅቄ ወጣው፡፡

ሀትሪክ፡- ከአዳማ ከተማ ጋር ያኔ ለመቀጠል እና ለመስማማት ባልቻልክበት ሰዓት ወደሌላ ቡድንስ ለማምራት አልተዘጋጀህም ነበር?

ተስፋዬ፡- በእዛን ወቅት አንድአንድ ቡድኖችማ ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ እኔን ለማስፈረም ፍላጎት ነበራቸው፤ ያም ሆኖ ግን ከአዳማ ከተማ ጋር መቀጠሌን ነግሬያቸው ስለነበር በኋላ ላይ ሊያናግሩኝ አልቻሉም፤ ቀጥሎ ደግሞ ከእነሱ ጋር በፊርማው ክፍያ ላይ መስማማት ሳልችል መቅረቴን ያወቅኩት የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ አራት ቀን ያህል ጊዜ በቀረበት ወቅትና እነሱም ከዚህ በኋላ ወደ የትም ቡድን አይሄድም ብለውም ያሰቡበት ጊዜም ስለነበር ወደ ሌላ ክለብ የምሄድበት አመራጭ ኖረም አልኖረም ለሁሉም ነገር እግዚአብሄር ያለውም ነው የሚሆነው በሚል ከእናንተ ጋር አልሰራም፤ ቤቴም ቢሆን እቀመጣለውም በሚል ወደ ሌሎች ቡድኖች ሳልገባም ቀረው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙርን ልምምድ ከመስራት ባሻገር ሌላስ ያደረግከው የተለየ ነገር ነበር?

ተስፋዬ፡- አዎን፤ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሆኜ በማኔጅመንት በመማር ድግሪዬን አግኝቼ ነበር፤ በእዚህ ዓመት የአንደኛው ዙር ላይ ደግሞ በእረፍት ላይ ስለነበርኩ ያደረግኩት የተለየ ነገር ቢኖር በማኔጅመንት አድሚኒስትሬሽን ደረጃ ትምህርቴን በመማርም ነው ጊዜውን ሳሳልፍ የነበርኩት፤ በእዛ ላይ ደግሞ እኔም ላለፉት 9 እና 10 ዓመታትም በተጨዋችነት የቆየሁበት ሁኔታም ስለነበርና ያለ እረፍትም ስለቆየው እስኪ ደግሞ ትንሽ ልረፍ ለቤተሰቦቼም ጊዜ ልስጥ በሚልም ሁኔታ ነው የቆየሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ መቐለ 70 እንደርታ ማምራትህ ትክክለኛ ምርጫ ነው?

ተስፋዬ፡- አዎን፤ ለምን መሰለህ? በመጀመሪያ ይሄ ቡድን እኔን በጣም ፈልጎኛል፤ ሲቀጥል ደግሞ ከአሰልጣኙ ገብረመድህን ሀይሌ ጋር በቡናም ሆነ በመከላከያ ሳለው አብሬው የሰራውና ጥሩ አሰልጣኝም ስለሆነ ከዛ ባሻገር ደግሞ ቡድኑ ለዋንጫ የሚጫወት በመሆኑና እኔ ደግሞ በእንዲህ ያለ ክለብ ውስጥ መጫወትን አጥብቄ ስለፈለግኩ ነው የገባሁት፡፡

ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጉ የሚቀጥልበት ሁኔታ ሲኖር የቀድሞ ቡድንህን ኢትዮጵያ ቡናን ነው በቅድሚያ የምትፋለመው፤ ያን ጨዋታ በምን መልኩ ትጠብቀዋለህ? ስለ ቡናስ ምን የምትለው ነገር አለ…?

ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ ቡና ምንም ነገርን ሳላውቅ ኳስንም በፕሮጀክት ደረጃም እንኳን ሳልጫወት በመምጣት ስምና ዝናን ያስገኘልኝ ቡድን ስለሆነ ከእነሱ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ለእኔ በጣም ነው አስደሳች የሚሆንልኝ፤ ጨዋታውንም በጉጉት እየጠበቅኩትም ነው፤ ቡና ማለት ለእኔ ብዙ ነገሮችን ያስገኘልኝ ቡድን ነው፤ በእዚህ ቡድን ብዙ ነገሮችንም አትርፌያለው፤ ይሄ ክለብ ጋር ስኖርና ስጫወትም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያገኘሁበት፤ የህዝቡንና የደጋፊውን ፍቅር ያገኘሁበትና ቡድኑም እኔን አስተምሮኝም በማኔጅመንት ደረጃም ለድግሪ እንድበቃም አድርጎኛልና የእዚህ ቡድን ቆይታዬን መቼም ቢሆን አልረሳውም፤ ለክለቡና ለደጋፊውም ያለኝ ፍቅር አሁንም ድረስ ከውስጤም ያልወጣ በመሆኑ ላመሰግናቸውም እፈልጋለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ለመቐለ 70 እንደርታ ስትጫወት የተለየ ነገርስ ገጥሞአል?

ተስፋዬ፡- አዎን፤ ወደ ክለቡ ገና ከመግባቴና ለሁለትም የ90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜያቶች ከመጫወቴ ከወዲሁ የገጠሙኝ ነገሮች ጥሩ ጥሩ የሆኑ ናቸው፤ በአዲሱ ቡድን ውስጥ ከደጋፊው ምርጥ ድጋፍ አንስቶ እስከ ክለቡ አመራሮች ድረስ እያየሁት ያለው ነገርም እንደ ቀድሞው ክለቤ ኢትዮጵያ ቡናም ጥሩና ተመሳሳይ ነገሮችም ናቸውና በቡድኑ የቀጣይ ጊዜ ቆይታዬም የምወደውን ነገር እንደማሳልፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታን በምን መልኩ እንጠብቀው?

ተስፋዬ፡- ቡድኑ ጥሩ እና ጠንካራ ክለብ ነው፤ የዓምናም ሻምፒዮና ነው፤ ዘንድሮ ሀገራችንን በሁሉም ነገር ሰላም ያደርጋት፤ የመጣውንም በሽታ ያጥፋልን እንጂ ዘንድሮም ይሄን ዋንጫ ለማንሳት እንጫወታለን፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ?

ተስፋዬ፡- በእግር ኳሱ ህይወቴ አስደሳች ጊዜያትን ነው ያሳለፍኩት፤ ለእኔ በእዚህ ደረጃ መጓዝ ከአምስት አመት በፊት ያገባዋትና የሁለት ልጆቼ እናት የሆነቸው ባለቤቴና እናቴ እንደዚሁም ደግሞ ከዓመታት በፊት ብዙ ነገር ያደረገልኝ አባቴና በርካታ ሰዎች ጥሩ ነገርን አድርገውልኛልና ለሁሉም ምስጋና ይግባቸው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website