“ቅ/ጊዮርጊስ ለተጨዋቾቹ ደመወዝ ከመክፈል ባለፈ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል የሚጠይቅበት ሁኔታ የክለቡን ታላቅነት ይበልጥ አሳይቶኛል”ጌታነህ ከበደ /ቅ/ጊዮርጊስ/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመኑ ላይ ከደቡብ ፖሊስ ጋር የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን፤ ከደደቢት ጋር ደግሞ የኮከብ ተጨዋችነትንም ሆነ የኮከብ ግብ አግቢነት ሽልማቶችን በመውሰድ የጣምራ አሸናፊ ሆኗል፤ ከዛም በተጨማሪ የፕሪምየር ሊጉንም ዋንጫ ለአንድ ጊዜ ያህል ከደደቢት ጋር ከማንሳት ባሻገር ብሔራዊ ቡድናችንንም ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፍ የበኩሉን አስተዋፅኦም አድርጓል፤ ይሄ ተጨዋች ጌታነህ ከበደ ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት አዲሱን ክለቡን ቅዱስ ጊዮርጊስን በመቀላቀል እየተጫወተ ይገኛል፤ ይህን የአገሪቱን ምርጥ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በኮቪድ 19 ምክንያት መቋረጡንና መሰረዙን አንስተን ከእግር ኳስ ስለመራቁ፤ ከዚህ በፊት በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ምርጥ ስለሚላቸው ተጨዋቾችና ግቡ እንደዚሁም ደግሞ በሌሎች ተያያዥ በሆነ ጥያቄዎች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሹን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን ከገባ ሶስተኛ ወርን ሊያስቆጥር ተቃርቧል፤ የሀገሪቱ የሊግ ውድድርም ተሰርዟል፤ ይህን ወቅት በምን እያሳለፍክ ነው? በዋናነት የናፈቀህስ ነገር ምንድን ነው?
ጌታነህ፡- በአሁን ሰዓት በጣም የናፈቀኝ ነገር ቢኖር ኳስ ወደ ሆነው ስራዬና እንጀራዬ በፍጥነት መመለስ ነው፤ ይህን ልል የቻልኩበት ዋናው ምክንያትም ኳስ ደስታን ከመስጠቱ ባሻገር በክለብ ደረጃ አብረካቸው የምትጫወታቸውን ጓደኞችህን አግኝተህ ከእነሱ ጋር ስትጫወት የምትቀላለደውም ነገር ስላለ ነው፤ ያ ነገር ይናፍቅሃል፤ ከዛ ውጪም ይህን ወቅት እያሳለፍኩ ያለሁት ትዳር ይዤ የምኖር ስለሆነና ባለቤቴም ከስራዋ ፈቃድን ወስዳ በቤት ውስጥ ስለምትገኝ ከእሷ ጋር ነው፤ በተለይ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎቸን በመስራት ነው የምናሳልፈው፤ ያ ስለሆነም አጋጣሚው ለባለቤቴም ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ስፖርቶችን ሰርታ ስለማታውቅ ይህን እንቅስቃሴ ለማድረግ መቻሏ ጥሩም ነው ሊሆንላት የቻለው፡፡

ሀትሪክ፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማድረግ ባሻገር ኳስንስ ገፋ ገፋ፣ እንደዚሁም ደግሞ ጠብ ጠብ እና መታ መታ የምታደርግበት አጋጣሚውስ አለ?
ጌታነህ፡- እሱ ላይ እንኳን በአዲስ አበባ ያሉ ግቢዎች ብዙዎቹ አይመቹምና የአካል ብቃቱ ላይ ብቻ ነው በአብዛኛው አተኩሬ እየሰራው ያለሁት፤ አልፎ አልፎ ብቻ ግን በበረንዳችን ላይ ኳስን የማንቀረቅበት ጊዜም አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ከእግር ኳስ ጨዋታ ለእንደዚህ ያህል ጊዜ መራቅ ምን አይነት ሁኔታን ፈጥሮብሃል?
ጌታነህ፡- ከዚህ ቀደም ለእንደዚህ ያህል ጊዜ ርቀንም ሆነ የኳሱ መቆምን ምክንያት በማድረግ በቤት ውስጥ መዋልን ለምደን አናውቅም፤ ብንርቅም ክረምት ላይ እረፍት ስለሚሰጠን ያኔ ለአንድ ወር ነው፤ እሱንም ቢሆን ወደ ትውልድ ክልል በምንሄድበት ሰዓትም እዛ ሄደን እንጫወታለንና አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ከኳስ መራቁ በጣም ከባድ ነው የሆነብኝ፤ ከኳስ መራቅ ከስራ እንደራቅክም ነው የሚቆጠረውና ወደዛ ወደምንወደው ስራችን በፍጥነት እንድንመለስ ፈጣሪ ይርዳን፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙዎች በእዚህን ወቅት እቤታቸው ተቀምጠው ፊልሞችን ይመለከ ታሉ፤ አንተስ?
ጌታነህ፡- እኔም እመለከታለው፤ እንደ ውም ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈውም በእሱ ነው፤ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ መፅሀፍቶችንም አነባለው፤ ከዚህ በፊት የማንበቡ ልምድ የለኝም ነበር፤ አሁን ላይ ግን ይሄን ልምድ ለ ማግኘትም ከፍተኛ ጥረትን እያደረግኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የቱን ፊልም ተመልክተህ ወደ ድክ?
ጌታነህ፡- የአሁን ሰዓት ላይ “ዘመኒስት” የሚል ተከታታይ ፊልምን ነው እየተመለከትኩ ያለሁት፤ እሱ ተመችቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያለህ ጥንቃቄ ምን ይመስላል? ከበጎ አድራጎት ተግባር ጋር በተያያዘስ የአንተ ሚና በምን መልኩ ይገለፃል?
ጌታነህ፡- በአሁን ሰዓት እያደረግኩ ያለሁት ጥንቃቄ ከቤት ስለማልወጣ እና እዛም ስለማሳልፍ እጄን በመታጠብ ነው፤ ከበጎ አድራጎት ስራ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ላይ ባይሆንም ሰሞኑን ወደ ሐዋሳ ከተማ እና ዲላ በመሄድ ሁለቱም ጋር ከእነ አስቻለው ታመነ፣ አዳነ ግርማ እና ሎዛ አበራ ከመሳሰሉት ጋር ሆነን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን ሰርተናል፤ ዲላ ላይም ስራውን እየሰራን ቢሆንም ገና አልጨረስነውም፤ ምክንያቱም ወደዛ ስታመራና ስለሁኔታው ስታስረዳ ትንሽ አስቸጋሪም ነገር ስለሚያጋጥምህ ነው፤ በእዚህ ወረርሽኙን በተመለከተና በመረዳቱ በኩል የአዲስ አበባ ሰው ይሻላል፤ ክልል ላይ ምንም ነገር ስላላዩና ቫይረሱም የለም ብለው ስለሚያስቡ ወጥተህ ስታስተምር ጫና አለው፤ ሰዎች እስከመጣላትም ይደርሳሉ፤ ጫናውም ቢኖር እኛ በቻልነው አቅም እየሰራን ነው፤ ከዛ ውጪም ዲላ ላይ ከዚህ ቀደም አረጋውያንን እና ብዙ የተቸገሩ አካላቶችን የሚያይ አካላት አልነበረምና ከዲላ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን እነሱን የመርዳት እና ከከተማው አመራሮች ጋርም በመነጋገር ለእነዚህ አካላቶች ማቆያ የሚሆን የመኖሪያ ቦታ ለማግኘት ስራን እየሰራን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እስካሁን በኮሮናው ስንት ሳኒታይዘር ጨረስክ?
ጌታነህ፡- ብዙ ጊዜ ከቤቴ ስለማልወጣ እና ሳኒታይዘርም ስለማልጠቀም እኔ እጄን ነው በተደጋጋሚ ጊዜ የምታጠበው፡፡ ስለዚህም ሳኒታይዘርን በተመለከተ አንድ አንዴ ገመድ ስዘል ብቻ ነው የምጠቀመው፡፡


ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ምክንያት የእግር ኳስን ከመጫወት ርቀሃልና፤ ከምግብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስፖርተኛ እንደመሆንህ አሁን ላይ የአመጋገብህ ሁኔታ ተቀይሯል?
ጌታነህ፡- በፍፁም፤ ከምግብ ጋር በተያያዘ እኔ ብዙም ችግር የለብኝም፤ አመጋገቤም አልተቀየረም፤ በፊት በስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኜ ብዙ ላብ የማፈስ ቢሆንም አሁንም በእዛ መልኩም ነው እየተመገብኩ ያለሁት፤ ሳውዝ አፍሪካ እያለው ብቻዬን እኖር ስለነበር ለስፖርተኛ አስፈላጊ ናቸው የምላቸውን ምግቦች ሰርቼ እበላ ነበር፤ አሁን ደግሞ እዚህ ከባለቤቴ ጋር ስኖር ውዷ ባለቤቴም ሰውነቴ እንዳይጨምር የሚያስችሉ ምግቦችንም እየሰራችልኝ የምመገብበትም ሁኔታ አለና ይሄን ነው ልል የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ የአንተ ምርጡ እና ቁጥር አንዱ ጨዋታ የቱ ነው?
ጌታነህ፡- ምርጡ ጨዋታዬ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ቦትስዋና ሄደን ከቦትስዋና ጋር ያደረግነውንና እኔና ሳላህዲን ሰይድ ግቦች አስቆጥረን ያሸነፍንበትን ነው፤ ያ ጨዋታ በጣም ጠንካራ ነበር፤ ከዛ ውጪም ቦትስዋና በምድብ ድልድሉ ጎረቤቷ ለነበረችው ደቡብ አፍሪካም ጭምር ሁኔታዎች እንዲመቻች የምትፈልግና ብዙ የደቡብ አፍሪካ ሰዎችም ወደዛ ይሄን ጨዋታ ለመመልከት ስለመጡ እና ያንን ጨዋታም ማሸነፋችን ወደ ዓለም ዋንጫው የመጨረሻው 10 ቡድኖች ወደሚገቡበት የማጣሪያው ፍልሚያ እንድንገባም እድሎችን ስላመቻቸልን ያ የማይረሳኝ ግጥሚያ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- የምንግዜም ምርጡ ጎልህ?
ጌታነህ፡- ብዙ ቢኖሩም፤ ባለቀ ሰዓትም ያስቆጠርኳቸው ቢገኙም ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ጎሌ የምላት ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከተደረገው የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች መካከል ወደ አምዱራህማን ተጉዘን በሱዳን 5ለ3 ስንሸነፍ 1ለ0 ከመሩን በኋላ እኔ ያስቆጠርኳትን የአቻነት ግብ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የምንግዜው ምርጡ ተጨዋ ችህ?
ጌታነህ፡- አሁንም ብዙ አሉ፤ ከሁሉም ግን ሳላህዲን ሰይድን አስቀድመዋለሁ፤ ሳላ ለእኔ የምንግዜም ቁጥር አንዱ ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ምርጡ ጥምረቴ ብለህ የምታደንቀው ተጨዋች ማንን ነው? እንደ አጥቂነትህስ ለአንተ ግብ ማስቆጠር በቀዳሚነት የምታስቀምጠውስ?
ጌታነህ፡- በደደቢት አብረን ነበርንና ዳዊት ፍቃዱ /አቡቲ/ ከእኔ ጋር ሲጫወት ምርጥ ጥምረቴ እና የማደንቀውም ተጨዋች ነበር፤ ሁለታችን ያኔ ለክለባችን በርካታ ግቦችን ማለትም በጋራ ከ40 ግቦች በላይ ያስቆጠርንበትና ለቡድናችንም የፕሪምየር ሊግ ድል ትልቁን አስተዋፅኦ ከማበርከት ባሻገር ለኮከብ ግብ አግቢነቱም ሁለታችን ስንፎካከር የነበርንበት ጊዜ ነበርና እሱን አልረሳውም፤ ለእኔ ግብ ማስቆጠር ደግሞ በቀዳሚ ቦታ ላይ የማስቀምጠው ተጨዋች ብዙዎቹን ከመስመር በሚመጡ ኳሶች አገባ ነበርና በሀይሉ አሰፋ /ቱሳን/ ነው፤ ከእሱ ውጪም የመሀል ሜዳው ላይ የእነ ታደለ መንገሻ፣ ምንያህል ተሾመ እና አዲስ ህንፃም አስተዋፅኦ ለግብ አግቢነቴ ጠቅሞኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙዎቹ ክለቦች የአሁን ሰዓት ላይ ለቡድናቸው ተጨዋቾች ወርሀዊ ደመወዝ በማይከፍሉበት ሰዓት ለእናንተ ግን እየከፈላችሁ ይገኛል፤ በእዚህ ዙሪያ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?
ጌታነህ፡- ቅ/ጊዮርጊስ በደመወዝ ብቻ አይደለም፤ ከዛ ውጪም በወር ቢያንስ ለአምስት እና ለስድስት ጊዜም ለሁሉም ተጨዋቾች ከበላዩ አቶ አብነት ገብረ መስቀል አንስቶ ከስር እስካሉት አመራሮች ድረስ በምን ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ እና እንደዚሁም ደግሞ ስለ ጤንነታችንም በመጠየቅና ያለንበትንም ሁኔታ ለማወቅ ስልክ ይደወልልናልና ከደመወዝ ውጪ ያ ነገር መኖር መቻሉ ቡድኑን በእዚህ መልኩ ለየት ያደርገዋል፤ ሌላ ክለብ እንዲህ ያደርጉ እንደሆነ አላቅም፤ ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም እኔ ለደቡብ ፖሊስም ሆነ ለደደቢት ክለብ ስጫወትና እረፍት በምንወጣበት ሰዓት ከክለቦቹ በኩል በምን ሁኔታ ላይ ነው የምትገኙት በሚል ስልክ አይደወልልንም ነበር፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ ሄጄም ስጫወት ለምንሰራው ስራ ወረቀት ነበር የሚሰጠንና እኛ ቤት ውስጥ ስልክ ከመደወል ባሻገር የሚያስፈልጋችሁ ነገር ካለ መጥታችሁ መውሰድ ትችላላችሁ ስለሚሉንና ደመወዛችንንም ወር ሳይደርስ በፊትም በአካውንታችን ስለሚያስገቡልን ክለባችን ለየት ብሎብኛል፤ በእዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸውም ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- ጌታነህን በተጨዋችነት ዘመኑ ማን ያስቀዋል?
ጌታነህ፡- በፊት ብሄራዊ ቡድን እያለን አዳነ ግርማ ነበር እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ተጨዋቾች ጭምር ቀልድ እየፈጠረ የሚያስቀን፤ የአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ክለባችን ውስጥ ጋዲሳ መብራቴ አለና እሱ ነው እያዝናናን ያለው፤ በተለይ ደግሞ ሰሞኑን በቪዲዬ የለቀቃቸው እና የሚያስጨፍራቸው ጭፈራዎች አስቂኝ ሆነው አግኝቼያቸዋለው፡፡


ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የተመለከትካቸው ለየት ያሉ ነገሮች ካሉና እግር ኳሱ ዳግም እንዲመለስስ የምትለው ካለ?
ጌታነህ፡- ኮቪድ 19 ላይ ከተመለከትኩት ነገር ስነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ቸልተኝነት በዝቷል፤ ብዙም ቦታዎች ላይ በተለይ ደግሞ ወደ ክልል ስታመራ ኮሮና እንደሌለም ነው የሚታየውና ህዝባችን መዘናጋት ይታይበታል፤ ስለዚህም የከፋ ነገር ከመፈጠሩ በፊት ሁሉም ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፤ የእግር ኳሱ ዳግም እንዲመለስ በሚለው ላይ ከአውሮፓ አገሮች አሁን አንድአንዶቹ ውድድራቸውን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጀምረዋል፤ የጀርመን ሊግንም እያየን ነው፤ ያም ሆኖ ግን እኛ በእነሱ አቅም ላይ አይደለም የምንገኘውና ኳሱ ዳግም ወደ ውድድር ይመለስም ሆነ ይጀመር ማለት ሌላ ችግር ውስጥ መግባት ነውና የማይታሰብ ነው፤ ስለዚህም ኳሱ እንዲመለስ መጀመሪያ ኮሮናን ከሀገራችን ማጥፋት ነው ያለብን፤ ለዛም ልንጠነቀቅ እና ልንፀልይም ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን በኮቪድ 19 ምክንያት ሊጉን ከመሰረዙ በተጨማሪ በመጪው ዓመትም ክለቦቻችን ምንም አይነት የኢንተርናሽል ተሳትፎ እንዳ ይኖራቸው አድርጓል፤ በተለይ ተሳትፎውን ክለቦቻችን በማጣታቸው ዙሪያ አንድ አንድ ክርክሮች ተፈጥረው ታይተዋል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
ጌታነህ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን አወዳዳሪው አካል ሊግ ካምፓኒው የአገራችን ውድድሮች በአንድ አንድ ምክንያቶች ሲቋረጡ ሊጉን በመጀመሪያው ዙር የሚመራው ቡድን ሻምፒዮና ይሆናል፤ ወይንም ደግሞ ሊጉ መካሄዱን ቀጥሎ በሚቋረጥበት ሰዓት ውድድሩን የሚመራው ቡድን ሻምፒዮና ይሆናል የሚል ህጎችን አለማውጣቱና በደንቡም ላይ ለማስቀመጥ አለመቻሉ አሁን ለወሰነው ውሳኔ ክርክር እንዲፈጠር ለማድረግ መቻሉ የጎዳው ቢሆንም የወሰነውን ውሳኔ በተመለከተ ግን አሁን ላይ ከተወሰኑ ተጨዋቾች ጋር በስልክ በመደዋወል እንዳወራሁት የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ትክክል ነው የሚለው ይበዛል፤ ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አንደኛ እና ሁለተኛ የሆኑትን ቡድኖች በኢንተርናሽናል የውድድር መድረኩ ላይ እንዲሳተፍ ቢያደርግ በውስጠ ታዋቂነት ሊጉን የሚመራው ቡድን ሻምፒዮና ሆነ እንደ ማለት ነው፤ ይህን ከወሰንክ ደግሞ ወራጅ ቡድንም የለም ማለት አትችልም፤ በታችኛው ሊግም አንደኛ አንደኛ ሆነው የሚመሩት ሶስቱ ክለቦችም እኛም ማለፍ አለብን ሊሉህ ነው፤ ስለዚህም ፌዴሬሽኑ ያን ባያደርግ እንኳን በአማራጭነት ሌሎች ነገሮችን ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታዎች ነበሩ፤ ለምሳሌ እነ ናይጄሪያን የመሳሰሉ ሀገራት ያደረጉት ነገር አለ፤ እሷ ለምሳሌ ከ1-6 ያሉትን ቡድኖች ብቻ ለማወዳደር ቀጠሮን ይዛለች፤ የእኛም ሀገር ላይ በተወሰነው ውሳኔ ላይ መስማማት ባይቻል እንኳን የተወሰኑትን ከአንድ እስከ ስምንት ወይንም ደግሞ ከአንድ እስከ ስድስት ካልሆነም ደግሞ ከአንድ እስከ አራት ያሉትን ቡድኖች በማጫወትም በመውረድና መውጣት ላይ ደግሞ ከታችኛው ሊግ እየመሩ ያሉትን ሶስት ክለቦችና በፕሪምየር ሊጉም ላይ በደረጃው ሰንጠረዥ መጨረሻ ላይ የሚገኙትን ሶስት ቡድኖችን በጥሎ ማለፍ ደረጃ የሚጫወቱበትንም ነገር ብትፈጥር በአማራጭነት እንኳን መቅረብ ይችል ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የተወሰነው ውሳኔ በችኮላ ጭምር ቢሆንም በአንድ በኩል ስታየው ደግሞ ውሳኔው ትክክልም ነው ማለት ይቻላል፤ እንደውም አሁን ክርክሩ በአጭርም ሊቆም እና እንዲቀጭም ያደረገውም ውሳኔው ጥሩና ትክክልም ሊሆን ስለቻለም ነው ብዬም አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
ጌታነህ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሮች ማለት የምፈልገው ነገር አለ፤ ይኸውም የአሁን ሰዓት ላይ በብዙ ክለቦች አካባቢ ወርሀዊ ደመወዝን ካለመክፈል ጀምሮ እና በታችኛው ሊግ ላይም ይህንን የደመወዝ ጥያቄን በሚያቀርቡ ተጨዋቾች ላይ ከክለባቸው ጋር አለመግባባቶች እየተፈጠሩ ወደ አላስፈላጊ ነገሮችና እስከ እስር ደረጃም ተጨዋቾች የደረሱበትን ሁኔታ በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ የሰማንበትም ሁኔታ ስላለ የእኛ ክለብ አመራሮች በእዚህ ወቅት በምንም ነገር እንዳንቸገር እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ በጣሙን ላመሰግናቸው እፈልጋለው፤ ሌላው ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝን አስመልክቶም በመንግስት ደረጃ እየተሰራ ባለው ነገርና የኢትዮጵያ ህዝብም በየአካባቢው ለተቸገሩ እና ለአቅመ ደካማም ሰዎች እያደረገ ባለውም የበጎ አድራጎት ስራ እነሱም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website