በትግራይ ስታድየም ሀዋሳ ከተማን ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች በሰፊ የግብ ልዩነት ሀዋሳን በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሻሉ።ስሑል ሽረዎች ባሳለፍነው ሳምንት በመቐለ ከተሸነፈው ስብስብ ሸዊት ዮውሀንስን በረመዳን የሱፍ፣ዲዲዬ ሌብሪን በሰይድ ሀሰን፣ያሰር ሙገርዋን በሙሉአለም ረጋሳ ሲቀይሩ ሀይቆቹ በበኩላቸው ወላይታ ድቻ ላይ ጣፋጭ ድል ካስመዘገበው ስብስብ መስፍን ታፈሰን በዳንኤል ደርቤ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረው ጨዋታ ከመቐለ ደጋፊዎች ጋር አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ የገባው ያሰር ሙገርዋ ለደጋፊዎቹ በይፋ ይቅርታ ጠይቆ የጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፋክክር የታየበት ነበር።በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች የበላይነት የነበራቸው ስሑል ሽረዎች በፈጣን ቅብብሎሽ ወደ መስመር በሚወጡ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በተለይ ከቀኝ መስመር ዓወት ገብረሚካኤል አሻምቶት ሳሊፍ ፎፎና በግምባሩ ገጭቶት ከግቡ አናት ለትንሽ የወጣው ኳስ እንዲሁም አብዱለጢፍ መሐመድ ከግራ መስመር ያሻማው አደገኛ ኳስ ቢሊንጌ ኢኖህ ያዳነበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ስሑል ሽረዎች በግራ መስመር ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ሙሉአለም ረጋሳ ሲያሻማው በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ በቀኝ በኩል የነበረው ነፃነት ገብረመድህን በግምባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችልዋል።ከግቡ በኃላ መነቃቃትን ያሳዩት ሀዋሳዎች ከመሀል በሚላኩ ሰንጣቂ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል።የዚህ ማሳያ ሚሆኑት ከዘላለም ኢሳያስ እና ኄኖክ ድልቢ በሚላኩ ሰንጣቂ ኳሶች የተፈጠሩ የግብ እድሎች ናቸው።የስሑል ሽረ ተከላካይ ክፍል ወደ መሀል መጠጋቱን በመጠቀም ኄኖክ ድልቢ ያሾለከው ኳስ ዳንኤል ደርቤን ከግብ ጠባቂው ወንድወሰን ጋር ፊትለፊት ቢያገናኘውም በመስመር አጥቂነት የተሰለፈው ዳንኤል ከበረኛው አናት ለማሳለፍ ሲሞክር ወንድወሰን መልሶበታል።ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ ኄኖክ አየለ አግኝቶት በቀጥታ ቢመታውም የግቡ ቀዋሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል።ከስሑላውያን በተሻለ ሁኔታ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ሀዋሳዎች የመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ የተላከውን ኳስ ኄኖክ አየለ ጋር ደርሶ ለመምታት ሲሞክር በወንድወሰን ተጨናግፎበት ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ እግር የደረሰችውን ኳስ ብሩክ ሳይጠበቅ በቀጥታ ቢመታትም ጋናዊው ተከላካይ አዳም ማሳላቺ ከመስመር ሊመልሳት ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ እስከ 75 ደቂቃ ድረስ ተመጣጣኝ ፋክክር ያሳየ የነበረ ቢሆንም በጨዋታው የመጨረሻ15 ደቂቃዎች ስሑል ሽረዎች ፍፁም በላይነት የታየበት ነበር።የአዲሴ ካሳ ቡድን ሀዋሳ ከተማ ከሁለቱም መስመር በሚነሱ ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ስሑል ሽረዎች ሳጥን ቢደርሱም የጠራ የግብ እድል ሊፈጥሩ አልቻሉም።በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽ ያደረግዋቸው ሁለት ቅያሬዎች ጨዋታው ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ያልፈጠሩ ነበሩ።
ስሑል ሽረዎች በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ላይ በግራ መስመር በጨዋታው ኮከብ አብዱልለጢፍ መሀመድ አማካኝነት ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ሀዋሳዎች ሳጥን ቢያሻግሩም የሚላኩት ተቀባይ ማጣታቸውን ተከትሎ በቀላሉ በሀይቆቹ ተከላካዮች ሊመለሱ ችለዋል።
በ70ኛው ደቂቃ ሀይለአብ ሀይለሥላሴን ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቡት ስሑል ሽረዎች ጨዋታው ላይ ተወስዶባቸው የነበረውን የመሀል ሜዳ ብልጫ ከማስመለሳቸው በተጨማሪ አሸናፊነታቸውን ያረጋገጡ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
82ኛው ደቂቃ ላይ መድሀንየ ብርሃነ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ ሳሊፍ ፎፎና በግምባሩ ገጭቶ በማስቆጠር የስሑል ሽረን ግቦች ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።ከሁለተኛው ግብ በኃላም ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ስሑል ሽረዎች መሀል ላይ ከሀይለአብ ሀይለሥላሴ መነሻውን ያደረገ መልሶ ማጥቃት በጥሩ ቅብብል ሳሊፍ ፎፎና ጋር ደርሶ ከግዙፋ ግብ ጠባቂ ጋር ቢሊንጋ ጋር ተገናኝቶ፤ኮትዲቫራዊው አጥቂ ከእሱ የተሻለ ቦታ ለነበረው አብዱልለጢፍ መሀመድ አቀብሎት ጋናዊ የመስመር አጥቂ በቀላሉ ሊያስቆጥረው ችሏል።በዚህም መሠረት ጨዋታው በስሑላውያን በላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ የሳምሶን አየለ ቡድን ነጥባቸውን ወደ 19 ከፍ በማድረግ ደረጃቸውን ወደ አራተኝነት ከፍ ሲያደርጉ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ሁለት ደረጃዎችን ወደ ታች ተንሸራትተው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አስተያየት ይስጡ