በዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በተጋባዥነት ከሚወዳደሩ ክለቦች በብቸኝነት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፈው ሰበታ ከተማ መከላከያን በማሸነፍ ወደ ፍፃሜ መድረሱን ማረጋገጥ ችሏል።
የመከላከያዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ፣ የሰበታዎች ፈጣን የኳስ ሽግግር በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ፍሰት ያለው የኳስ ቅብብል ቢታይም ብዙ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር።በ 4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ጦሮቹ መሀል ላይ ያጣመሩት በኃይሉ ግርማ ና ተፈሪ አንለይ የነበራቸው ጥምረት መከላከያ መሀል ላይ ብልጫ አንዲኖራቸው ቢያግዝም፤በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ፍቃዱ ዓለሙ በሁለቱም መስመር ከተሰለፋት ዳዊት ማሞ እና አናገው ባደግ እንዲሁም ከጀርባው ከተሰለፈው ቴዎድሮስ ታፈሰ ጋር የነበራቸው መግባባት ጥሩ አለመኖሩ ተከትሎ በጥሩ ቅብብል የመጡት ኳሶች የሜዳው መጨረሻ ክፍል ላይ ሲደርሱ ጥሩ መናበብ በነበራቸው የሰበታ ተከላካዮች ሲጨናገፋና ሲነጠቁ ነበር።በአንፃሩ ሰበታዎች ከመሀል ሜዳ በሚነሱ በፈጣን ሽግግር የታጀቡ ቅብብሎችን በማድረግ የተወሰኑ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።

የዚህም ውጤት በ21ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ መሀል ሜዳ ላይ ያገኘውን ኳስ ቀኝ መስመር ላይ ወደ ነበረው ባኑ ጆዋር ልኮት፣ባኑም አጠገቡ የነበሩትን የመከላከያ ተከላካዮችን በመቀነስ ፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለነበረው ታደለ መንገሻ መሬት ለመሬት ሲመልስለት ታደለም በጥሩ አጨራረስ ሰበታዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።መከላከያዎች ከግቡ መቆጠር በኃላ በተደጋጋሚ እድሎችን የመፍጠር ችግራቸውን በመጠኑ መቅረፍ ችለዋል።በተለይ ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት ያደረገው የጦሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በ37ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ በዳዊት ማሞ አማካኝነት የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል።አናጋው ባደግ ከቀኝ መስመር ከሽመልስ ተገኝ የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ውስጥ ሲያጥፈው በፍፁም ቅጣት ሳጥን የመጨረሻ ክፍል(6 yard) ብቻውን የነበረው ዳዊት ማሞ በቀላሉ በማስቆጠር መከላካያን አቻ ማድረግ ችሏል።ከግቡ በኃላ መነቃቃታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በፍቃዱ ዓለሙ አማካኝነት ያደረጉት ጠንካራ ሙከራ በዳንኤል አጃይ ሊመልስባቸው ችሏል።ሰበታዎችም በመስዑድ መሐመድ አማካኝነት ያገኙት ንፁህ የግብ ዕድል በታሪኩ አረዳ ድንቅ ብቃት ሊመለስ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ጥፋቶች የተስተናገዱበት የውበቱ አባተ ቡድን የተሻለ የተንቀሳቀሰበት ሆኖ አልፏል።በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ላይ መስመር ላይ ትኩረት ያደረገ ፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴን የተገበሩት ሰበታዎች እንቅስቃሴያቸው በ54ኛው ደቂቃ በጎል ሊታጀብ ችሏል።ጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ባኑ ጀዋር ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ባኑ ጃዋር አስቆጥሮ ሰበታን በጨዋታው ለሁለተኛ ጊዜ መሪ መሆን ችለዋል።መከላከያዎች በድጋሚ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ዳዊት ማሞን በሀብታሙ ወልዴ፣ፍቃዱ ዓለሙን በአቤል ነጋሽ ቢቀይሩም ቡድኑ ተረጋግቶ መጫወት አለመቻሉ ተከትሎ ቅያሬዎቹ ያን ያህል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።በአንፃሩ ሰበታዎች ያደረጉዋቸው ስድስት ቅያሬዎች ቡድኑ ሚዛናኑን አንዲጠብቅ ና መከላከያዎች ኳስን ከኃላ ለመመስረት በሚሞክሩበት ጊዜ በአዲስ ጉልበት ጫና አንዲፈጥሩ አግዝዋቸዋል።የዚህም ውጤት በ85 ደቂቃ መከላከያ ኳስ ከኃላ ለመጀመር በሚሞክሩበት ጊዜ በታሪኩ አረዳ ና ምንተስኖት ከበደ መሀከል በተፈጠረ አለመግባባት የተገኘው ኳስ ቅርብ የነበረው ዳዊት አስጢፋኖስ አግኝቶት በቀላሉ በማስቆጠር የሰበታ ከተማ የፍፃሜ ጉዞን ማረጋገጥ ችሏል።
ጨዋታው ተጠናቆ በተጨመሩት የባከኑ ደቂቃዎች ጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኡጋንዳዊው ተከላካይ ሳቪዮ ካቩጎ ተፈሪ አንለይን ከኳስ ውጪ በመማታቱ በዕለቱ ዳኛ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማ ወደ ፍፃሜ ሲያልፍ ለዋንጫ ዛሬ የሚደረገውን ሸገር ደርቢ በበላይነት ሚያጠናቅቀውን ክለብ ሚገጥም ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ