በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ተከናውኗል።
በቅዳሜ ብቸኛ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ መደረግ እያለበት በአንዳንድ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በገለልተኛ ሜዳ እንዲደረግ የተወሰነው የፋሲል ከተማ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ዛሬ(ቅዳሜ) 10፡00 ሲል አ/አ ስታዲየም ላይ ተደርጎ ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

በደማቅ የደጋፊዎች ዝማሬ እና ጭፈራ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር የተስተዋለበት ሲሆን እንደ ደጋፊው ሁሉ ጨዋታውም በጋለ መንፈስ የጀመረ ነበር።
8ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ የመቐለ ከተማው ያሬድ ከበደ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል። ከ1 ደቂቃ በኋላ 9ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው አማካይ ዓመለ ሚልክያስ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ወደውጪ ወጥቷል። 14ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው አጥቂ ጋይስ አምፖንግ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሣማኪ ሚካኤል በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ የፋሲል ከተማው ሰዒድ ሀሰን ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 38ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ በግሩም ሁኔታ አታሎ ወደግብ የሞከረው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 5ደቂቃዎች ሲቀሩት 40ኛው ደቂቃ የመቐለ ከተማው አቻምፖንግ አሞስ ከ35ሜ ርቀት ላይ የመታውን ቅጣት ምት በረኛው በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይህ ነው የሚባል የረባ ሙከራ ሳይደረግበት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት ገብተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ዓመለ ሚልክያስ፣ ያሬድ ከበደ እና ሃብታሙ ተከስተ ከመቐለ ከተማ በኩል ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተዋል። ወጣቱ አጥቂ ኣማኒኤል ገ/ሚካኤል በቀድሞው ብቃቱ ላይ አለመገኘቱ የቡድኑን ግብ የማግባት አማራጭ ቀንሶት ተስተውሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ፋሲል ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በጨዋታው ብልጫ ወስደዋል።
ፍፁም ከበደ እና ፊሊፕ ዳውዝ ድንቅ ሆነው ባመሹበት በዚህ ጨዋታ ሙከራ በማድረጉ ረገድም ቅድሚያውን የወሰዱት ፋሲል ከተማዎች ነበሩ።
49ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ሀይሉ ከርቀት የሞከረው ኳስ በርቀት ወደ ውጭ ወጥቷል። በተደጋጋሚ ወደ መቐለ ከተማ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ፋሲል ከተማዎች 54ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አለሙ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ አግኝቶ በድንቅ ሁኔታ የመታውን ኳስ ፍሊፕ አቮኖ እንደምንም ብሎ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። ከ5 ደቂቃዎች በኋላ 59ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ፊሊፕ ዳውዝ በግንባሩ ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሀይል የተቀላቀለበት እና ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ጥንቃቄ የበዛበት ከዚህም በተጨማሪም ወደኋላ በማፈግፈግ አጋጣሚዎች ሲገኙ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10ደቂቃዎች ሲቀሩት 80ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ኤርሚያስ ሀይሉ ከርቀት የሞከረው ኳስ በርቀት ወደ ውጭ ወጥቷል። በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት መቐለ ከተማዎች ኢላማውን የጠበቀም ሆነ ኢላማውን ያልጠበቀ አንድም ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በስታዲየሙ ዙሪያ ስርዓት አልበኝነት ተስተውሏል። በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች እና በፀጥታ ሀይሎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። እንደዚህ አይነት ስርዓት አልበኝነቶች መወገድ አለባቸው።
የአሰልጣኞች አስተያየት

የፋሲል ከተማው አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ
“በኳስ ቁጥጥሩ የኛ ቡድን የተሻለ ነበር፤ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችንም መፍጠር ችለናል። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ችግር ቢሆንም ጨዋታው በሰላም መጠናቀቁ አስደስቶኛል። እንዳገኘናቸው አጋጣሚዎች ግን የኛ ቡድን ጨዋታውን ማሸነፍ ነበረበት።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የመቐለ ከተማው ዮሐንስ ሳህሌ
“ጨዋታው ለሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች የሚያስደስት ነው ብዬ አላስብም፤ ብዙ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የግብ ማግባት ሙከራዎች አልተስተዋሉበትም። በታክቲካል ዲስፕሊን ረገድ ጥሩ ብንሆንም በውጤቱ ግን ደስተኛ አይደለሁም።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ይስጡ