በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጨረሻ 1ጨዋታ ዛሬ አ/አ ስታድየም ላይ ተከናውኖ ደደቢት ከጅማ አባጅፋር ጋር ተገናኝተው ተጋባዦቹ ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያዎቹ 20ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች ደደቢትን 2-1 ማሸነፍ ችሏል።
ደደቢት አሸናፊነቱን በማስቀጠል መሪነቱን ለማጠናከር እንዲሁም ጅማ አባጅፋርም ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ያደረጉት ጨዋታ በመሆኑ በብዙ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት ተጠብቆ ነበር። ጨዋታው ሲጀመር በደደቢት በኩል 4-3-3 እንዲሁም በጅማ አባጅፋር በኩል 4-5-1 የጨዋታ ዘይቤ ይዘው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ጨዋታው ከጅማሬው ሞቅ ያለ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ የፈጀበት 4ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 4ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ የጅማ አባጅፋሩ ተመስገን ገ/ኪዳነን በግሩም ሁኔታ ክሌመንት አዞንቶ መረብ ላይ በማሳረፍ ጅማ አባጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ደደቢቶች ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም 17ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሰለሞን ሐብቴ ከ ሽመክት ጉግሳ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ደርሰው ሽመክት ሞክሮት ከክለቡ በፍርድ ቤት ጉዳይ ርቆ የነበረው እና ቡዱኑን ባሳለፍነው ሳምንት የተቀላቀለው የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኦጄ በግሩም ሁኔታ ያዳናት ኳስ በደደቢቶች በኩል በመጀሪያዎቹ 20ደቂቃዎች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። ከዚህ ሙከራ 1ደቂቃ በኋላ የጅማ አባጅፋሩ ዮናስ ገረመው ከመሐል ከፍል የተሻገረለትን ኳስ ከደደቢት የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ክለቡን 2-0 እንዲመራ አስችሏል።

በጨዋታው 22ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችል ሁኔታ ተፈጥሯል። የደደቢቱ አጥቂ እና አምበል ጌታነህ ከበደ የጅማ አባጅፋሩ ሄኖክ ኢሳያስ ላይ በሰራው ጥፋት በእለቱ አርቢትር ሀይለእየሱስ ባዘዘው በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። የጌታነህ ከበደን ከሜዳ መውጣት ተከትሎ የቅርጽ ለውጥ ለማድረግ የተገገዱት ደደቢቶች አቤልን በብቸኛ አጥቂነት በመጠቀም ወደ 4-4-1 አሰላለፍ ለውጥ ሲያደርጉ በተቃራኒው የቁጥሩ ብልጫውን የወሰዱት አባጅፋሮች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ሙሉ ለሙሉ ብልጫውን በመውሰድ ተመልካች የሚያዝናና ጨዋታ ማሳየት ችለዋል።
በ40ኛው እና በ41ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ደደቢቶች በሽመክት ጉግሳ እና አቤል አማካኘነት ወደ ግብ መቅረብ ቢችሉም በእለቱ ድንቅ የነበረው የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ሲስኮ አዳማ ወደ ግብ ክልል እንዳይጠጉ ያደረገበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። በዚሁም ጨዋታው በጅማ አባጅፋር 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ደደቢቶች 2ተጫዋቾችን ማለትም ብርሀኑ ቦጋለን እና ኤፍሬም አሻሞን ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ተጭነው በመጫወት ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በአንጻሩ ጅማ አባጅፋሮች 3ነጥብ ይዞ ለመውጣት አፈግፍጎ በመልሶ መጥቃት መጫወትን ምርጫቸው አድርገው ተስተውለዋል። በ55ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ተጫዋቾች ወደ ግብ የሞከሯትን ኳስ የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ሔኖክ አዱኛ በእጅ ኳስ በመንካት ግብ እንዳትሆን በማድረጉ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ይህንንም ተከትሎ ለደደቢት የተሰጠችውን ፍጹም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሎ ነበር። ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ በተደጋጋሚ ወደ ጅማ አባጅፋር ክልል መድረስ የቻሉት ደደቢቶች የመሐል ተከላካያቸውን አንዶህ ኩዌክን በ ፋሲካ አስፋው ቀይረው ቢያስገቡም ነጥብ ተጋርተው መውጣት አልቻሉም። 75ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ቅብብሎሽ ወደ ግብ ደርሰው ወጣቱ አጥቂ አቤል ያለው የሳታት ኳስ ለባለሜዳዎቹ ደደቢቶች እጅግ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይሄ ነው የሚባል የረባ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በጅማአባጅፋር 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ ደደቢት በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ሲያስተናግድ ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ርቀት የሚያሰፋበትን እድል አምክኗል። ውጤቱንም ተከትሎ ደደቢት 1ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አሁንም በ25 ነጥቦች ሊጉን ሲመራ ባለድል መሆን የቻለው ጅማ አባጅፋር ደግሞ ከመሪው ደደቢት በ4 ነጥቦች ርቆ በ21 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ —– ደደቢት
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በዳኛ ምክንያት ተሸነፍን ብዬ ማሳበብ ባልፈልግም የእኛን ሀገር እግርኳስ የሚገሉት ዳኞች ናቸው። የተሰጠብን ቀይ ካርድ አግባብ አይደለም። ይሄ ደደቢትን ለመግደል የተደረገ ሴራ ነው ብዬ ነው የማስበው። በአጠቃላይ ግን ተጨዋቾቼ በጣም ብዙ መስዋዕትነት ነው የከፈሉት፤ ግን እግርኳስ ነው እና በፀጋ እንቀበላለን።”
አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ —– ጅማ አባጅፋር
“ጨዋታው ጥሩ ነበረ፤ እነሱም(ደደቢቶች) መሪ ስለሆኑ እኛም ወደ እነሱ ለመጠጋት ያደረግነው ጨዋታ ስለነበር ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው 45 ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል፤ በስኬትም ተወጥተነዋል፤ ያንን ውጤት ይዞ ለመውጣት ከነበረንን ጉጉት የተነሳ በሁለተኛው አጋማሽ አስቸግረውናል።”
አስተያየት ይስጡ