በ 22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይርጋለም ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሰማያዊዎቹ ደደቢቶችን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በወንድሜነህ ዓይናለም ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ ሸኝቶታል።
በጨዋታው የመጀመሪያው 5 ደቂቃ ደደቢት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በዚህም 1ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ግብ ቢያስቆጥርም በእጅ ተነክቷል በሚል በመሐል ዳኛ ተሽራለች። በ14ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ፍፁም ተፈሪ የመታት ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታለች።

18ኛው ደቂቃ ላይ ጥፋት በመስራት ወንድሜነህ አይናለም የ ቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል። 25ኛው ደቂቃ የሲዳማ ቡናው መሳይ አያኖ የደደቢቱ ሽመክት ጉግሳ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የመሀል ዳኛው ሚካኤል ፍፁም ቅጣት ምት ሰተዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን ጌታነህ ከበደ ቢመታውም የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሳይ መልሶበታል። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ የደደቢት የማጥቃት እንቅስቃሴ ተዳክሞ የተስተዋለ ሲሆን ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በእንቅስቃሴ ጎልቶ ታይቷል። 34ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ሐብታሙ ገዛኸኝ አግኝቶ ያበከነው ኳስ በሲዳማ ቡና በኩል እጅግ የሚያስቆጭ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 2ደቂቃዎች ሲቀሩት 43ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ወንድሜነህ ዓይናለም አራት ተከላካዮችን አታሎ በመግባት ክለመንት አዞንቶ መረብ ላይ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ አስችሏል። በዚሁም የመጀመሪያው 45 ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል ያልነበረው ሲሆን በአብዛኛው የሲዳማ ቡና የበላይነት ታይቷል። ከ48-51 ባሉ ደቂቃዎች ሀብታሙና አዲስ ግዳይ 3 ያለቀላቸውን ኳሶች አምክነዋል። በሁለተኛው 45 ሲዳማ ቡና ሙጃይድ መሃመድን በዮናታን ፍሰሃ እንዲሁም ትርታዬን በ ወንዴሜነህ ቀይሯል። ደደቢት ሰለሞንን እና ፋሲካን ቢያስገባም ለውጥ አላመጣም። ከዚህ ባለፈ ደደቢት በመስመር ሄዶ ከሞከረው ሁለት ኳስ በቀር ሌላ ኳስ አልሞከረም። ሲዳማዎች ደግሞ ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ ኳስ ሲያጨናግፉ ተስተውሏል። በዚሁ ውጤትም 90 ደቂቃው ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 27 ማሳደግ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት፡
ዘርአይ ሙሉ —- ሲዳማ ቡና
“ውጤቱ ይገባናል፤ ፍፀም ቅጣት ምቱ አስደንግጦን ነበር፤ በሁለት ጨዋታ ላይ 6 ነጥብ አስመዝግበናል ፤ ቀጣይ ጨዋታ ላይ ትኩረት እናደርጋለን።”
የደደቢት አሰልጣኝ ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አስተያየት ይስጡ