በ3ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው የወልዋሎና የስሑል ሽረ ጨዋታ በቢጫ ለባሾቹ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።3 ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ወልዋሎዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን ከገጠመው ስብስብ ሰመረ ሃፍታይን በጁንያንስ ናንጂቡ፣ሄኖክ መርሹን በኢታሙና ኩሜይኒ ሲቀይሩ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው አብዱሰላም አማንን በክፍሎም ገብረሂወት፣ሳሊፍ ፎፎናን በመድሃንየ ብርሃነ ቀይረው ገብተዋል።
ተመጣጣኝ ፋክክር በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት በኣንጻሩ ወልዋሎዎች ያገኝዋቸውን እድሎች በመጠቀም ተሽለው የታዩበት ነበር።ፊት ላይ ጁንያስ ናንጂቦ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ኢታሙና ኩሜይኑ ያጣመሩት ወልዋሎዎች ከቆሙ ኳሶች እና በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል።የዚህ እንቅስቃሴ ውጤትም በ16ኛው ደቂቃ ግራ መስመር ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ሳሙኤል ዮውሃንስ ኣሻግሮት ገናናው ረጋሳ በግምባሩ በመግጨት ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ሽረዎች አቻ ሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ከመስመር እንዲሁም ከርቀት በሚመቱ ኳሶች እድሎችን ቢፈጥሩም ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቷል።በተለይ ዲድዬ ሌብሪ ከሃብታሙ ሸዋለም የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ኣየር ላይ የመታው ኳስ አብዱላዚዝ ኬይታ መልሶበታል።ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረገው የወልዋሎ አጨዋወት በ33ኛው ደቂቃ ለሁለተኛው ግብ መቆጠር ምክንያት ሊሆን ችሏል።ከኬይታ በረጅሙ የተላከው ኳስ የሽረ ተከላካይ ስህተት ታክሎበት ቅርብ የነበረው ጁንያስ ናንጂቦ አግኝቶት በጥሩ አጨራረስ የወልዋሎን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።በዚህም የመጀመርያው 45 ሊጠናቀቅ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሳሊፍ ፎፎናን በክፍሎም ገብረህይወት ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ስሁል ሽረዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ የግብ እድሎችን ቢፈጥሩም ያገኝዋቸውን እድሎች በመጠቀም ላይ የነበራቸው ክፍተት ወደ ጨዋታው እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኖባቸው ታይቷል።በተለይ ሳሊፍ ፎፎና ከዲድዬ ሌብሪ ያገኘውን ኳስ ግልፅ የግብ እድል ባለመጠቀሙ ቀጥታ ያሄደ ኳስ በመልሶ ማጥቃት የወልዋሎ 3ተኛ ግብ ሊሆን ችሏል።ራምኬል ሎክ በቀጥታ የላከው ኳስ የጨዋታው ኮከብ ጁንያስ ናንጄቦ አስቆጥሮ የወልዋሎን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎ ሥስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሽነፍ በሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።
አስተያየት ይስጡ