“ሙጅብ ቃሲም ለምን አልተመረጠም? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ለብ/ቡድኑ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል

“በዙሪክ ከቬንገር ጋር ተገናኝተን ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎታቸውና የአርሰናል ተጨዋች ስለነበረው ጌዲዮን ዘላለም ጥልቅ ውይይት አድርገናል”

– “የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሀገር ውክልናዬ ዋጋ ሰጥቶ ላደረገልኝ ድጋፍ ከልብ አመሰግናለሁ”

– “ሙጅብ ቃሲም ለምን አልተመረጠም? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ለብ/ቡድኑ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል”
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ


በይስሐቅ በላይ

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ዕድገት ከብርሃን እየፈጠነ ነው፤ በሀገራችን የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን የተጀመረው የእግር ኳስ ሕይወቱ ውቅያኖስን አቋርጦ ሰማይን አሳብሮ ወደ አፍሪካና ወደ አለም እግር ኳስ ዘልቆ ለመግባት ብዙ ዓመታት አላስፈለጉትም፡፡ ኢትዮጵያ ካሏት ኤሊት የካፍ ኢንስትራክተሮች አንዱ የሆነው የዋልያዎቹ አለቃ አሁን ደግሞ በፊፋ ለከፍተኛ ኃላፊነት (ምደባ) በቅቷል፡፡ በቀድሞው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር የበላይነት በሚመራው ፕሮጀክት ውስጥ በመታቀፉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሚያደርገውን ታላቅ ኃላፊነት አግኝቷል፡፡ ከኢትዮጵያ አብራክ የተገኘው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አሁን ባገኘው ምደባ መሠረት ህንድን፣ ሊባኖስን ከአፍሪካ ደግሞ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዙምባብዌ፣ ዛምቢያ፣ ማላዊና የኬንያን እግር ኳስ እንቅስቃሴ እንዲገመግም አደራ ተሰጥቶታል፡፡ ከክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በኋላ በሙያው ወደ ካፍና ፊፋ በከፍተኛ ሁኔታ ጠጋ ጠጋ እያለ ያለውን ወጣቱን አሰልጣኝ አዲስ ስለተሰጠው ኃላፊነት፣ ከቬንገር ጋር ስለመገናኘታቸው፣ ስለ ሙጂብ ቃሲም አለመመረጥና ስለወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዮቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ አነጋግሮታል፡፡

ሀትሪክ፡- ኢንስትራክተር አብርሃም ለቃለ-ምልልሱ ስለተባበርከኝ ከልብ አመሰግናለሁ፤ዙሪክ ስዊዘርላንድ ድረስህ እንደመጣህ አውቃለሁ…አሁን በትክል የት ነው ያለኸው…?

ኢንስ. አብርሃም፡-…የት ነው ያለኸው… ?…ማለት…ጥያቄህ አልገባኝም….?

ሀትሪክ፡- Quarantine (ለይቶ ማቆያ) ወይም Self Isolate (ራስህን አግልለህ)…ነው ያለኸው…?

ኢንስ. አብርሃም፡-…(በጣም ያላባራ ሣቅ)…እንዴ…ምን እያልከኝ ነው…በኮረና ቫይረስ ተይዘሃል ብለህ ጠርጥረኸኝ ነው…ወይስ በኮረና የተጠረጠረው ጃፓናዊ እኔ መሰዬህ ነው…?(አሁን በጣም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …እንዴ አብርሃም ምን ማለትህ ነው…በቅርቡ ዙሪክ ደርሰህ ነው የመጣኸው…ስዊዘርላንድ ከአውሮፓ ሀገርም አንዷ ናት…አውሮፓ ደግሞ ከቻይና ቀጥሎ በቫይረሱ ከፍተና ጉዳት ከደረሰባቸው አንዷ ናትና ከዚህ አንፃር ብሰጋ ወይም ብጠረጥር ትፈርድብኛለህ…?

ኢንስ. አብርሃም፡-…(አሁንም የመገረም ሣቅ)…በጣም የምትገርም ነህ…ገና ለገና ከውጭ መጥቷል ብለህ ነው እንደዚህ ብለህ የምትጠይቀኝ…ታሳዝናለህ…(ሣቅ)…ወደ ጥያቄህ ስመለስ እንግዲህ…እግዚአብሔር ይመስገን ፍፁም ጤነኛ ነኝ አትስጋ፤ ፊፋ ከእኛ ፕሮግራም በኋላ ያሉ ፕሮግራሞችንና ልዩ ልዩ ሴሚናሮችን ሰርዟል፡፡ ይሄን ያደረገው ደግሞ ምንድነው ኢንፋንቲኖ ከኢትዮጵያዊው የአለም ጤና ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ በቀጥታ ከጄኔቫ ወደ ዙሪክ መጥተው በጽ/ቤታቸው መግለጫ ሰጡ፤በቀጣይ ለማካሄድ የታሰቡ ፕሮግራሞችም ለጊዜው እንዲተላለፉ አደርገዋል፡፡ እኛም ቢሆን ኮርሱ ከተጠናቀቀ በኋላ መጨረሻ ላይ የነበረው (Official Dinner) የስንብት ይፋዊ የእራት ግብዣ እንድንሰርዝ ተደርጓል፡፡ ዙሪክ ላይ ደግሞ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቫይረሱ ሠጋት አልነበረም ያም ሆኖ ግን ጥንቃቄ እንድናደርግ ተነግሮናል፡፡ በዚያ መሠረት ሀሉንም በጥንቃቄ አከናውኜ ስለተመለስኩ በጣም ደህና ነኝ…ከቫይረሱ ስጋት ውጪ መሆኔን አስረግጬ የምነግርህ፡፡

ሀትሪክ፡- ቫይረሱ የአለምን ታላላቅ ውድድሮች እንዲቋረጡ ከማድረጉ በተጨማሪ ከአሰልጣኞች አርቴታ፣ ከተጨዋቾች የጁቬንቱሱ ሩጋኔ፣ የቼልሲው ካሉም ሆድሰን ኦዶይ እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫ በተለይ መሰረዙን ስትሰማ በአዕምሮህ ምን መጣ?

ኢንስ. አብርሃም፡- እነዚህ የጠራሃቸው ብቻ ሣይሆኑ የስፔን ተጨዋቾች ምልክት ታይቶባቸው (ፖዘቲቭ) ሆነዋል ተብሏል፡፡ ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያዘ የአለም ስፖርቶች በሙሉ አደጋ ላይ ወደቀዋል፤ ከተለመደው እንቅስቃሴያቸው ውጪም እንዲሆኑም አድርጓቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያው ውድድሮች ብቻ ሣይሆን ሁሉም ውድድሮች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፉ ካፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ውድድሩ መተላለፉ ግድ በመሆኑ ተቀብለነዋል፤ምክንያቱም ውሣኔው የሰውን ህይወት ለመታደግ የተወሰነ በመሆኑ በአዎንታዊ ነው የተቀበልኩት። ከስነ ልቦና፣እዕምሮን ነፃ ከማድረግ አንፃር ውሳኔውን በአዎንታዊነት ነው ያየሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ከሁለት ሣምንት በኋላ ከኒጀር ብ/ቡድን ጋ ሊደረግ ለነበረው ጨዋታ የተጨዋቾት ምርጫ ይፋ አድርገህ ዝግጅት ለማድረግ እየተዘጋጀህ ነበር፤ አሁን ደግሞ ካፍ ውድድሩን አስተላልፏል፤ ከዚህ አንፃር የፕላን ለውጥ ታደርጋለህ ወይስ በዚህ ነው የምትቀጥለው?

ኢንስ. አብርሃም፡- ካፍ ለሁሉም ሀገሮች ሰርኩላሩን የላከው ተጨዋቾቼ ለዝግጅት ከሚገቡበት 1 ቀን ቀደም ብሎ ነው፤ጨዋታው እንዲቋረጥ በመደረጉ ምክንያት ብ/ቡድናችን ለረዥም ጊዜ ከእንቅስቃሴ ስለራቀ ከሪትም እንዳይወጣ ራሳቸውን መፈተሽ ስላለባቸው በመሀል እየተጠሩ ልምምድ የምናደርግበትን መንገድ ከፌዴሬሽኑና ከክለቦች ጋር ተነጋግረን ስራችንን እንደምንቀጥል ነው የምናስበው፤የውድድሩ ፕሮግራም በመቀየሩ ምክንያት ግን የዝግጅት ፕላናችንን እንደገና ለማየት እንገደዳለን፡፡

ሀትሪክ፡- አንተን በዚህ አጋጣሚ አግኝቼህ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ሙጂብ ቃሲም በብ/ቡድኑ ውስጥ ቦታ የተነፈገበትት አሣዛኝ ምክንያትህ ምንድነው? ብዬ ሳልጠይቅህ ብንለያይ አንባቢ ይታዘበኛልኛ ውሳኔህ የሚከበር ቢሆንም ሙጂብን ከብ/ቡድንህ ውጪ ያደረክበትን ምክንያት ግልፅ ማድረግ ይቻላል?

ኢንስ. አብርሃም፡-በመጀመሪያ ደረጃ አንድ እንድታውቅልኝ የምፈልገው ነገር ከሙጂብ ቃሲም ጋር የተለየ ችግር የለብኝም፤እንደውም በጣም ከማከብራቸው ተጨዋቹ፣ጥሩ ከሚባሉት እሱ አንድ ነው፤ነገር ግን ሙጂብ ለብ/ቡድን ያልተመረጠው አሁን ብቻ አይደለም፤ በአምናው ውድድር ለምሣሌ ከ16 በላይ ግቦች በማስቆጠር ምርጥ አግቢዎች ከሚባሉት እንዱ ነበር፤ነገር ግን ጠርቼው ሙሉ ስልጠናው ላይ ከጨዋታው ጋር ከነበረው አቋም አንፃር መልሸዋለሁ፡፡ የዚያን ጊዜ ስመልስው ሙጂብ እንዴት የሀገሪቷ ቁጥር አንድ አስቆጣሪ ሆኖ እንዴት ይመለሳል? ያለ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ይሄ ነገር በስፋት እየተነሳ ነው፤ይሄ ለምን የሆነ ይመስልሃል?ብ/ቡድኑ ትኩረት እየሳበ በመምጣቱ ነው፤ብ/ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቱ፣የስፖርት ቤተሰቡም ደግሞ ካለው ፍላጎት የተነሣ ስለሆነ ሁሉንም አስተያየቶች በአዎንታዊነት (በአክብሮት) እመለከታቸዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሙጂብን ያልመረጥክበት ትክክለኛው ምክንያት ምንድነው እንበል ታዲያ….?

ኢንስ. አብርሃም፡-…ምንም የተለየ ምክንያት የለኝም፤እኔ ለምፈልገው አጨዋወት ይጠቅሙኛል ብዬ ያሰብኳቸውን ተጨዋቾች በሙሉ መርጬያለሁ፤ስመርጥም ቆይቻለሁ፤ ከአንድ አመት በላይ ቆይቻለሁ…በዚህ ጊዜ ውስጥ በተጨዋቾች ምርጫ ዙሪያ አንድም አይነት ኮሽታ አልሰማሁም፤ነገር ግን አሁን ይሄ ስሜት መፍጠሩ ከቅሬታ ወይም ለምን ተነሣ ከማለት ይልቅ እንደ በጎ ጎን ነው የምወስደው። የስፖርት ተመልካቹ ሙጂብ ላይ ሣይሆን ብ/ቡድኑ ላይ እንደሆነ አድርጌ ነው የምወስደው፤ ከዚህ በተጨማሪ ይሄ ደግሞ አለም አቀፍ ባህሪ ያለው ነው፤ የስፔን ብ/ቡድንን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ሊዊስ አራጎሌዝ ራውል ጎንዛሌዝ የሪያል ማድሪድ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነበር፤ግን አሰልጣኝ እሱን ቀንሰው ዋንጫ አንስተዋል፤እሣቸውን ተክተው የመጡት ዴልቦስኬም ራውል ጎንዛሌዝን ትተው ከባርሴሎና የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾች ወስደው የአውሮፓንና የአለም ዋንጫን ወስደዋል።ይሄ ብቻ አይደለም ኤሚ ዣኪ 98 ላይ የፈረንሣይን ብ/ቡድንን ሲያሰለጥኑ ኤሪክ ካንቶናና ዴቪድ ዥኖላን እንዴት አይመረጡም? የሚል ጫጫታ ነበር፡፡ ነገር ግን እሣቸው ካልተመረጡ የተባሉትን ተጨዋቾች ትተው ያመኑባቸውን መርጠው የአለም ዋንጫን አንስተዋል፡፡ ይሄ የሚያሳይህ እኛ ሀገር ብቻ ሣይሆን አለም አቀፋዊ ባህሪ ያለውም እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የስፖርት ቤተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ ሃሣብ ማንሣቱ…የብሔራዊ ቡድኑን ማንኛውንም ጉዳይ በትኩረት እየተከታተለ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጊዜውን ማጠር ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ምክንያቱን ለማወቅም ይረዳል። ወደ ምፈልገው ሪትም ተጫዋቾችን ለማስገባት ጊዜው አጭር ስለነበር የጊዜውን ማጠር ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ለማድረግ የፈለኩት የኡጋንዳ፣ የሩዋንዳ ፣የማዳጋስካርና የኮትዲቫዋር ጨዋታ ላይ ለተጫወቱ ተጨዋቾች ነው ጥሪ ያደረኩት፡፡ አሸናፊውንና እየተሻሻለ የመጣውን 95 በመቶ የሆነውን ብ/ቡድን ይዘን ቀጥለናል ማለት ነው፡፡ ግን ምርጫው አሁንም ክፍት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአጥቂ ችግር በስፋት በሚታይበት ብ/ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ ያለውንና ግብ በማግባቱ የተሻለ የሆነውን ተጨዋቾች አለማካተት ግራ አጋብቶናል ለሚሉ የመጨረሻ ምላሽህ ምንድነው?

ኢንስ. አብርሃም፡- …. አሁንም የምመልስልህ ከአጨዋወት ጋር ከመነሳት ነው፤ ለምሣሌ አንዳንድ ሀገሮችን እንውሰድ በሀገራቸው ሊግ ውስጥ ከፍተኛ ግብ አግቢ የሆኑ ተጨዋቾች እያሉ ነገር ግን ፕሮፌሽናል ሆነው በአውሮፓና በኤሺያ ስለሚጫወቱ ብቻ ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ይመረጧቸዋል፡፡ ለምንድነው ይሄን የሚያደርጉት? ለአጨዋወታቸው ስለሚመቻቸው ብቻ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እስከ አሁን ድረስ የነበሩት ከፍተኛ ጎል አግቢዎቻችን አማኑኤልና ሙጂብ ቃሲም ናቸው፤ እነዚህ ጎል አግቢዎች እኮ ብ/ቡድኑ ውስጥ ቆይታ ነበራቸው፤ በቆይታቸው ምንድነው የሠሩት? የሚለውን ማየትና ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ልጆች እድሉ ተሰጥቶአቸዋል ፤ ነገር ግን በብ/ቡደኑ የነበራቸው እገልግሎት ምን ነበር? የሚለውን መለስ ብሎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው ምንድነው ከጊዜ ማጠር አንፃር 23 ተጨዋችን ብቻ መምረጣችን የሌሎችን እድል አሳጥሮታል፡፡

ሀትሪክ፡- የሙጅብ አለመመረጥ በማህበራዊ ሚዲያውና በዋና ሚዲያዎች በስፋት መነጋጋሪያ እየሆነ ነው፤በዚህ ደረጃ ጉዳይ መራገቡ እጅህን ጠመዝዞ ሃሣብህን አስቀይሮ እንደገና እንድትጠራው አያስገድድህም?

ኢንስ. አብርሃም፡- ኧረ …በፍፁም ከኮትዲቫርና ከማዳጋስካር ስንጫወት እኮ በፌስ ቡክ ጫና አይደለም ተጨዋቾችን የመረጥኩት፤አስተያየቶች ምንም ይሁኑ ምንም አከብራለሁ፤ለምን አስተያየት ተሰጠ የሚል ቅሬታም የለኝም፡ የምሰራውን የማውቅ፣ ትልቅ ኃላፊነትና ትልቅ የሀገር አደራንም የተሸከምኩ አሰልጣኝ መሆኔን ስለማውቅ ተጠንቅቄና አስቤ ነው የምሰራው። የሚሰጡ አስተያየቶችን ብ/ቡድኑ እንዲጠናከር ከመጓጓት የሚሰጡ አስተያየቶች እንደሆነ አድርጌ ነው የምወስዳቸው፡፡
ሀትሪክ፡- የቀድሞ የኢት.ቡና የአሜድላ በቅርቡ ከኃላፊነት እስከ ተነሳበት ድረስ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የነበረውን አንዋር ያሲንን በእነ ፋሲል እግር ተተክቶ የአንተ ረዳት አሰልጣኝ መሆኑ ተረጋግጧል….?

ኢንስ. አብርሃም፡ -…(ሣቅ)…ገና አላለቀም እንዳልከው አንዋር ከታጩት አሰልጣኞች አንዱ ነው፤ እስከ አሁን ግን የተወሰነ ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- …አንዋር ከእነ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም በልጦ ረዳት መሆኑ ተረጋግጧል በሚል ያገኘሁት መረጀ እኔን ስህተተኛ ያደረገኛል ማለት ነው?

ኢንስ. አብርሃም፡- …(ሣቅ)…በነገራችን ላይ መረጃው ልክ ነው ፤ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም አንደኛው እጩ ነው ፤ግን የወጣ ደረጃ ስለሌለና ስላልተወሰነ ትንሽ ብትታገስ ብዬ ነው የምመክርህ፡፡

ሀትሪክ፡- በቅርቡ የአለም እግር ኳስ ገዢ የሆነው ፊፋ ባዘጋጀው FIFA High Programs global Football Eco system ላይ ለመሳተፍ ወደ ዙሪክ አምርተህ ነበር፡፡ እስቲ ስለቆይታህ አውራኝ፤ ይሄ ፕሮጀክት በአርሴናል የቀድሞ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር የሚመራ ነው…?

ኢንስ. አብርሃም፡- አዎን ትክክል ነህ፤ የሄድኩት በአርሴን ቬንገር የበላይነት በሚመራው አዲሱ የሃይ ፐርፎርማስ ፕሮጀክት ፕሮግራም ግሎባል ፉትቦል ኤኮ አናሊስስ ሲስተም በሚባለው ላይ ለመሳተፍ ነው፡፡ ይሄንን እድል ያገኘሁት ሞሮኮ ላይ በነበረው ኤሊት ኮንትኔንታል ኮርስ ላይ የፊፋ ተወካዮች እዛ ነበሩ፡፡ በተለይ የቀድሞ የፊፋ የቴክኒክ የዳይክተር የነበሩት አሁን የካፍ የቴክኒክና ልማት ጉዳዮች አማካሪ ሚ/ር ጆን ሚሼል ሪንስ እና ዶ/ር ሀሰን ማሉሽ እሣቸውና ሌሎች የፊፋ ሰዎች ኢቫሉዌሽን /ግምገማ/ ይሰሩ ነበር፡፡ ከግምገማውና ከኮርሱ መጠናቀቂያ በኋላ በአርሴን ቬንገር የሚመራ ፕሮግራም አለ፤ እሱን በተመለከተ የሚደርስህ ጥሪ አለ ተባልኩ፤ ጥሪው ደረሰኝ፡፡ ጥሪው ከደረሰኝ በኋላ ሁለት ጊዜ በ On line ኢንተርቪው ነበረኝ፡፡ በስካይፕ፤ ይሄን ፈተና ካለፍኩ በኋላ ከማርች 9-13 ዙሪክ ላይ በተደረገው የአምስት ቀን ስልጠና ላይ እንድገኝ ተደረገ፡፡ በእዛ ስልጠና ላይ በብቃት ስለተወጣሁ ለፊፋ ሃይ ፐርፎርማንስ ከፍተኛ ኤክስፐርትነት በአርሰን ቬንገር ለሚመራው ፕሮጀክት እንዳገለግል ተመረጥኩ ማለት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ የተካተትክበትና በአርሴን ቬንገር የሚመራው የፊፋ ሃይ ፐርፎርማንስ ስራዎች አላማው ምንድነው….?

ኢንስ. አብርሃም፡- የዚህ ፕሮጀክት ትልቁ አላማ ከ2026ቱ የአለም ዋንጫ በፊት ሀገሮች በሴቶችም በወንዶችም ጠንካራ ብ/ቡድን ገንብተው የአለም ዋንጫ ውድድሮች ማለት በታዳጊ፣ በወጣቶች፣ በኦሎምፒክና በዋናው ብ/ቡድን የሚካሄዱ ውድድሮች ጠንካራና ተፎካካሪ ተቀራራቢ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ ሌላ Foot ball for all በሚለው ፕሮግራም ፊፋ በሚሰጠው ድጋፍ መሠረት የተጠናና ውጤታማ ለማድረግ የሚችል አካዳሚዎችን በሁሉም ሀገሮች መመስረትና ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ በየሀገሩ ቢያንስ 13 የሚሆኑ አካዳሚዎች የመጎብኘት ሃሣብ አለ፡፡ አስሩን በኦን ላይን ሶስቱን ደግሞ በኦን ሳይት /በአካል/ የመጎብኘት የሚገመገም ይሆናል፤ ከዚህ በመነሣት ፊፋ ለአካዳሚዎቹ ድጋፍ ይሰጣል፤ ሁለተኛው አላማው የአሰልጣኞች ብቃት በየደረጃው ከአህጉሮች ጋር በመነጋገር ማሳደግ ነው፤ የኤሺያን ከኤሺያ፣ የአፍሪካን ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር አብሮ የመስራትና የማሳደግ ፕሮጀክት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በዚህ በዙሪኩ ስልጠና ላይ አንተ በተለያዩ ሀገሮች እግር ኳሱን የብ/ቡድኖች የፕሮጀክት እንቅስቃሴውን እንድትጎበኝ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተሰጠህ ነው የሰማሁት እስቲ ትክክለኛውን ከአንደበትህ ልስማ…?

ኢንስ. አብርሃም፡- ትክክል ነህ በሙያዬ ትልቅ የምለውና ለሀገሬም ለራሴም ክብርን የሚያስገኝ (ምደባ) ነው የተሰጠኝ፤ የፈረንጆቹ 2020 እስኪጠናቀቅ ድረስ ግምገማው (አናሊሲስ) ከ180 ሀገሮች በላይ ይካሄዳል፡፡ ከ180 በላይ ወደሚጠጉ ሀገሮች በፊፋው ኮርስ ላይ የነበሩት ኤክስፖርቶች በየሀገሩ ይላካሉ፤ ለዚህ ምደባው ሲደረግ ለመመረጥ ቢያንስ በሁለት አህጉሮች ላይ የሰራ የሚል ነገር ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በማሰልጠንም በቴክኒክ ዳይሬክተርነትም በማስተማርም ኤሺያ ውስጥ አፍሪካ ውስጥም ተሳትፎ አለኝ፡፡ ይሄ እንደ አንድ ክሬዲት ተይዞልኝ ምደባውን አግኝቻለሁ፡፡ ምደባው ሲካሄድ 2 አህጉሮችን እንድመለከት አናሊስስ እንድሰራ ነው የተወሰነው አህጉሮቹን ለመጥቀስ ህንድና ሊባኖስ ከኤሺያ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ከአፍሪካ ደግሞ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያ፣ ማላዊና ጎረቤታችን ኬንያ ናቸው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሀገሮች በተቀመጡ የቴክኒክ አናሊስስ (መገምገሚያ) መሠረት በቦታው ላይ ተገኝቼ ሀገሮቹ የሚያደርጋቸውን የልማት ስራዎች፣ የብ/ቡድኑን እንቅስቃሴዎች እከታተልና ሪፖርቱን ለፊፋ ግሎባል አቀርባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያስ የእድሉ ተጠቃሚ ከሆነች ማን ተመደበላት… ?

ኢንስ. አብርሃም፡- ኢትዮጵያ እድሉን ከሚያገኙት 180 ሀገሮች አንዷ ናት፤ እኔም ሀገሬም ያገኘነውን እድል ስመለከት ኩራት ይሰማኛል፤ በጣምም ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ በፊፋ አዲሱ ፕሮጀክት ምደባ አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ሚ/ር ጆሴ ይባላሉ፤ ስፔን ማድሪድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የስፖርት ባለሙያ ናቸው፤ እሳቸው ናቸው ለተመሳሳይ ስራ ወደዚህ የመጡት፡፡ ለእሳቸው ምደባው ከተሰጣቸው 8 ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ በመሆንዋ ደስተኛ ናቸው፡፡ እሳቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ተጠቃሚ እንድንሆን ቅድመ ዝግጅቱን ከወዲሁ እንጀምራለን ጥሩ ነገርም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ዙሪክ በነበረህ ቆይታ በዋነኝነት ተሳትፎ ያደረግከው በአርሴን ቬንገር በበላይነት በሚመራው ፕሮጀክት ውስጥ ነውና እዛ በነበረህ ቆይታ ከስብሰባ ውጪ ከቀድሞ የአርሰናል አለቃ ቬንገር ጋር በግል የመወያየትና የመመካከር እድል አግኝተሃል…?

ኢንስ. አብርሃም፡- እንዳልከው ከአርሴን ቬንገር ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር አጋጣሚን አግኝቻለሁ? እሳቸው ተደራራቢ ስራና ኃላፊነት ስላለባቸው ከመክፈቻውና ከሁለተኛው ቀን በኋላ በስልጠናው ላይ አልተገኙም፤ እኔም አጋጣሚውን አግኝቼ ከእሣቸው ጋር በግለፅ ተወያይቻለሁ፤ በስልጠናው ላይም በግልም ከአርሴን ቬንገር ጋር ባደረግኩት ውይይት እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን ሳይሰስቱ የሚያካፍሉ ሰው መሆናቸውን የመረዳት እድል አግኝቻለሁ፤ በተለይ በተለይ የዓለም እግር ኳስን የሚረዱበት መንገድ ለእኔ እጅግ በጣም ተመችቶኛል፤ ብዙ ስራ መስራት እንዳለብኝም አስገንዝበውኛል፡፡ እሣቸው የፊፋ ዴቬሎፕመንት ፕሮግራም ኃላፊ እንደመሆናቸው መጠን ከፊፋ ቴክኒክ ዳይሬክተር ሚ/ር ስቲቨን ማርቲንስ ጋር ሆነው ድጋፋቸውን እንደሚሰጡን ነግረውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ዙሪያስ አላወራችሁም? በተለይ በሀገራችን በእ ሳቸው የሚመራው አርሴናል በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉትና እሳቸው የሀገር ልጅ ይመስል እንደሚከበሩና እንደሚወደዱ የተነጋገራችሁበት አጋጣሚስ የለም…. ?

ኢንስ. አብርሃም፡- በጣም የሚርምህ እሣቸው ይሄንን ያውቃሉ፤ እኔም በዚህ ዙሪያ አንስቼላቸው ነበር፤ ከእሣቸው ጋር በነበረኝ ቆይታ በዋናነት በርካታ አድናቂዎች ወደ አላቸው ኢትዮጵያ እንዲመጡና ሀገሪቱን የማየት እድል እንዳላቸው አንስቼላቸው ከዚህ በፊት ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር ተገናኝተው እንደ ነበርና ፕሬዚዳንቱም ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ጋብዛቸው እንደነበር አስታውሰው የፊፋ ኮንግረስ በኢትዮጵያ ሲካሄድ እግረመንገድ የማየት እቅድ እንደያዙ ነግረውኛል፤ ከዚያ በተጨማሪ በቀድሞ የአርሰናል ተጨዋች ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጌዲዮን ዘላለም ዙሪያም አውርተናል፤ ጌዲዮን በጣም ጥሩ ተጨዋች እንደሆነና በጊዜው ግንኙነት ብታደርጉና ጥረት ቢኖር ለኢትዮጵያ የመጫወት እድል ይኖረው እንደነበርና ግን እንዳልተጠቀምንበት ገልፀውልኛል፡፡ በሀገራችን ብዙ ደጋፊ እሳቸውም አርሰናልም እንዳላቸው የዚህ ምክንያትም እርስዎ ነዎት ብያቸው ይሄንን በተለያየ መንገድ እንደሚያውቁና ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀውልኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚህ ሌላ በዙሪክ ምን ያልታሰበ ወይም የተገረምክበት ነገር አለ ካጋጠመ አካፍለን?

ኢንስ. አብርሃም፡- በዙሪክ ከብዙ ታዋቂ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፤ አንዳንዶቹ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ እውቀቱ የላቸውም፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በኮትዲቮዋሩ ድል በጣም እንደተገረሙ አጫውተውኛል፡፡ ከዚህ ሌላ ግን አንድ እንድታመሰግንልኝ የምፈለገው በዙሪክ ነዋሪ የሆኑ የቀድሞ ተጨዋቾች ያደረጉልኝ አቀባበልና እውቅና በጣም ልቤን የነካው ነውና እነሱን ብታመሰግንልኝ ደስ ይለኛል፡፡ የቀድሞ የመብራት ኃይልና የብ/ቡድኑ ተጨዋች የነበሩት እነ አለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፔዩሮ) ተክሌ ብርሃኔና ሌሎች ተጨዋቾች ያለሁበት ቦታ ድረስ መጥተው የሀገራችንን ባንዲራ እና 100 ሚሊዮን ህዝብ የሚወክለው ብ/ቡድናችን አሰልጣኝ በመሆንህ ብቻ ሣይሆን በዚህ ታላቅ ቦታ ላይ ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም ወክለህ በመገኘትህ ኮርተናል ብለው ስልጠናውን የምከታተልበት ሙዚየም ድረስ መጥተው የእውቅና ሽልማት (ማበረታቻ) የሰጡኙን ለመልካሙ ፍቅራቸውና ክብራቸው ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሌላውና የመጨረሻው ጥያቄዬ ቪዛ ተከልክለህ ከዙሪኩ ታላቅ ፕሮግራም ለመቅረት ተቃርበህ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ነገር እውነት ነው…?

ኢንስ. አብርሃም፡- እዚህ ደረጃ ላይ ባልደርስም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ከፍተኛ ባለሙያዎች ድጋፍ ባይኖርበት ኖሮ ያልከው ነገር ላለመከሰቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደ ስዊዘርላንድ አይነት ኤምባሲዎች ቪዛ በአጭር ጊዜ በመስጠት በኩል የራሳቸው አሰራር አላቸው፡፡ እኔ ደግሞ ግብዣው የመጣልኝ በጣም ዘግይቶ ስለነበር በነበረኝ አጭር ጊዜ የመጨረሴን ነገር አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፡፡ ነገር ግን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ኃላፊዎች የኤምባሲውን ሰዎች በቀጥታ በማነጋገር የሚሄደው ሀገር ወክዬ እንደሆነና በፊፋ መጠራቱና በጉባኤው ላይ መገኘቱ እንደሀገርም ክብር በመሆኑ ትብብር እንዲደረግልኝ ጠይቄው ቪዛው ተሳክቶልኝ መሄድ ችያለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ትኩረት ሰጥቶ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ሃገሬን ወክዬ እንድገኝ ድጋፍ ስላደረገልኝ ከልብ ነው የማመሰግነው፡፡ የሚገርምህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ለዚህ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የምትሄደው ሀገር ወክለህ በመሆኑ በምሄድባቸው ሃገሮች ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥመኝ ከኤምባሲዎች እና በሚሲዮኖች አማካኝነት በማመቻቸት ከጎኔ እንደሚሆኑና እንደሚያግዙኝ ገልፀውልኛልና እባክህን ከልብ አመስግንልኝ፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሀገር ምስል ነውና ይዘህ የምትሄደው ውጭ ካሉት ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ጋር በመነጋገር ድጋፍ እናደርጋለን ብለውኛል፤ እነሱንም እንዳመሰግን ብትፈቅድልኝ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.

One thought on ““ሙጅብ ቃሲም ለምን አልተመረጠም? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ለብ/ቡድኑ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

Comments are closed.