“መጠላለፉና ጉተታው በአፍሪካ ውስጥ ያለንን የመሪነት ሚና አሳጥቶናል”አቶ ባህሩ ጥላሁን /የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ/

“በአፍሪካ ደረጃ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጊዜ የነበረንን መሪነትና ተሰሚነት ለማስቀጠል መጠላለፉና መጓተቱ መቆም አለበት”

“መጠላለፉና ጉተታው በአፍሪካ ውስጥ ያለንን የመሪነት ሚና አሳጥቶናል”

አቶ ባህሩ ጥላሁን /የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ/


ከተመረጡና ትልቁን የእግር ኳስ ኃላፊነት ማለትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊነት ሥልጣን ከያዙ ዛሬ 59ኛ ቀናቸውን ይዘዋል… ቦታው ይፋጃል የብዙዎች ሰዎች ስሜትና ፍላጎት እንዲተገበርላቸው ከውስጥና ከውጭ ከፍተኛ ጫና የሚያደርጉበት ቦታ ነው፡፡ ኃላፊነቱ ጥንካሬ፣ አቅምና ከሁሉም በላይ ችሎ ማለፍ አይቶ እንዳላየ መሆንንም ይጠይቃል… ከስራ አስፈፃሚ እስከ ክለቦች፣ ከክልል ፌዴሬሽን ኃላፊዎች እስከ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውና የማይመለከታቸው ሰዎችም አይን ማረፊያ ነው… ወጣቱ ጋዜጠኛ ባህሩ ጥላሁን የህዝብ ግንኙነት ሆኖ ይህን መስሪያ ቤት ከተቀላቀለ በኋላ ምክትል ፀሐፊና የህዝብ ግንኙነትን ደርቦ ሰርቶ ብቃቱን በማሳየቱ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጋራ ዋና ፀሐፊ አድርገው ሰኔ 10/2012 ሹመቱን አፀደቁለት፡፡ ጋዜጠኛ ስለነበር ከሚዲያው ጋር መልካም ግንኙነት ያለው አቶ ባህሩ ጥላሁን ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው የስልክ ቆይታ ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡


ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ከሆንክ በኋላ የጨጓራ ህመም ያዘህ ይባላል፤… እውነት ነው?

ባህሩ፡- /ሳቅ በሳቅ/ እስካሁን ሠላም ነው ቦታው ቀላል ነው ማለት ግን አልችልም፡፡ የህዝብ ግንኙነትም መሆን ትልቅ ኃላፊነት ነው… የተቋሙ ጠቅላላ ጉዳዮች ወደ የህዝብ ግንኙነቱ ስለሚመጣ ኃላፊነቱ ቀላል አይደለም… ጉዳዩ ከባድም ይሁን ቀላል የሚያልፈው በእኔ በኩል በመሆኑ ጠንከር ማለቱ አይቀርም ያም ሆኖ ጤነኛ ነኝ ጨጓራዬ አልተላጠም/ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ቦታው አያቃጥልም…?

ባህሩ፡- ቦታውማ ትልቅ ኃላፊነት ነው ያለው ማቃጠል ጋር ግን አይደርስም፡፡ አስቸጋሪ ኃላፊነት ያለበት ቦታ እንደመሆኑ ውሳኔ መወሰን ይጠበቅብኛል ውሳኔው ደግሞ ፌዴሬሽን ውስጥ የሚፈጥረው ነገር ይኖራል ስራ አስፈፃሚው ማወቅ እያለበት ነው ይህን የወሰንከው የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ሁሉ ይችላሉ በዚያ ላይ የተለያዩ ፍላጎቶች ከተለያዩ ቦታዎች ሊመጡ ይችላሉ እነርሱን የማስተናገድ ኃላፊነት የኔ ነው የሚሆነው… የዋና ፀሐፊነት ቦታ ፈታ የምትልበት ቦታ ነው ማለት አልችልም ነገር ግን እስካሁን አላቃጠለኝም እንደሚሆነው እያደረኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-የዋና ፀሐፊነት ቦታው ከነሙሉ ክብሩ ተሰጥቶሃል ማለት ይቻላል… የስራ አስፈፃሚ ጣልቃ ገብነት የለም?

ባህሩ፡- እስካሁን ባለው ጊዜ ከባድ ነገር አልገጠመኝም በነፃነት ነው እየሰራሁ ያለሁት.. ሙሉ በሙሉ አምኖ የመተው ነገር ነው ያለው.. ይሰረዋል ይወጣዋል የሚል እምነት አግኝቻለሁ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ነገሮች ይቀጥላሉ ብዬ አምናለው፤ ለኳሱ የምናስብ ከሆነም መሆን ያለበት እንደዚህ ነው የሥራው ነፃነቴ ሳይነሳ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ… እስካሁን እንግዲህ 3ኛ ወር ላይ እገኛለሁ፡፡ የተሾምኩት ሰኔ 10/2012 ላይ በመሆኑ ቀጣይ ሀምሌ 10/2012 ገና 2 ወር ይሞላኛል፡፡

ሀትሪክ፡-በ59ኙ ቀናት የዋናው ፀሐፊነት ቆይታህ ሰራው የምትለው አንኳር ጉዳዮችን ግለፅልኝ?

ባህሩ፡- የተጨዋቾች ዝውውር መመሪያ አዘጋጅተን ለክለቦች በመበተን ግብአት እየጠበቅን እንገኛለን፤ የካፍ አካዳሚው መመሪያ ወጥቷል፡፡ የቦታው ኃላፊነት ለፌዴሬሽኑ ስላልነበር ኃላፊነቱን የራሣችን ለማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፤ የ2013 የሊግ ውድድር እንዴት መቀጠል አለበት በሚል ሰነድ አዘጋጅተናል፤ የ2012 የስራ ዘመን የፌዴሬሽኑ ዲፓርትመንት የስራ ሂደት ሪፖርት ምን ይመስላል? ምን አቅደው ምን ያህሉ ተሳካ? የነበረውስ ክፍተት ምን ነበር በሚል ተቋማዊ የስራ ባህል ለማምጣት የስራ ግምገማ አድርገናል ግምገማም እያደረግን ነው በአጠቃላይ ይህን ስራ እንደ ቡድን በጋራ ነው እየሰራን ያለው በግል የሚያዝ ነገር አይኖርም ብለን ተንቀሳቅሰናል.. ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ በውሳኔዎች ላይ ያፈገፍጋል.. ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…. ይህን ለማስተካከል ምን ተሰራ?

ባህሩ፡- ለምሣሌ ከተጨዋቾች ደመወዝ ጋር በተያያዘ ያልከፈሉ ክለቦች ላይ እገዳ ጥለናል ይሄ አንድ የውሳኔ አካሄድ ነው… ተግባራዊነቱ የሚታየው ደግሞ በቀጣዩ አመት የዝውወር መስኮቱ ሲከፈት የሚታይ ይሆናል ያኔ የሚያስፈርሙ ከሆነ ሁኔታው ከባድ ይሆናል፡፡ ስማቸው መጥራት የማልፈልጋቸው ክለቦች ስናይ እያስፈረሙ ነው በምን ወኔ ነው? ማን የልብ ልብ ሰጣቸው እንድንል ያደርገናል.. ወይስ ሌላ ፌዴሬሽን አለ? እንድንል ያደርጋሉ መቼም አይናቸውን በጨው አጥበው ፌዴሬሽኑ ውላቸውን ያድስልን ብለው ይመጣሉ ብዬ አላምንም፡፡ ችግራቸውን የታገዱበትን ጉዳይ መፍታት አለባቸው፡፡

ሀትሪክ፡-ከጅማ አባጅፋር ጋር ተያይዞ ፊፋ የ3 የዝውውር መስኮት አግዷል… ከዚህ እገዳ በፊት በናንተም ታግደዋል የተጋነነው የፊፋ ነውና የምትለው ነገር አለ?

ባህሩ፡- እኛ በክለቦቸችን መታገድ አንደሰትም ለፌዴሬሽናችንም ክስረት ነው፡፡ ነገር ግን ሕጎች መክበር አለባቸው ፕሮፌሽናል ሆነው እድገት እንዲያሳዩ ነው የምንፈልገው… ያን ካልተከተሉ መቅጣት ደግሞ የግድ ይጠበቅብናል ያለበለዚያ መዘዙ ነገ ከነገ ወዲያ ፌዴሬሽኑ ላይ ነው የሚመጣው፡፡ ክለቦች የሚሰሩት ስህተት እንደ ሀገር ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል በዚያ ላይ ኢንተርናሽናል ተጨዋቾች ሲሆኑ ነገሩ ይገናል፡፡ አሁን ሀገራት ከሀገራት ጋር ሲጋጩ ለዳኝነት የሚቀመጠው ፊፋ ነው እንጂ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አይደለም በእርግጥ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሣኔዎች ይጣሳሉ ሣይሆን አንዳንዴ የምታየው ነገር ይኖራል ክለቦቻችን ጫና ውስጥ እንዲገቡ አንፈልግም ብለን ልናስብ እንችላን ፊፋ ግን ይህን ሁሉ ማሰብ አይፈልግም እንደ ክለብ ከተመዘገብክ ጀምሮ ሁሉንም እኩል ያያል ውሳኔውም ተመሳሳይ ነው ክለቦች የሚያመጡት የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ መሰል ምክንያቶች ፊፋ ጋር ተቀባይነት የላቸውም፡፡ የሀገሪቱ ፌዴሬሽንም ለክለቦቻቸው ያግዛሉ ብሎ ያስባል የፊፋ ውሳኔ ካልተተገበረ ደግሞ ክለቡ ብቻ ባይሆን ቅጣቱ ፌዴሬሽን ላይም ሊያርፍ ይችላል፡፡ በክለቦቹ ችግር ፌዴሬሽኑ ሀገሪቱ ከተቀጣች ሁሉም ጣቱን የሚቀስረው ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ወይም ዋና ፀሐፊው ላይ ነው፤ ሆደ ሰፊ ሆነን እንዴት ነገሮችን እንዳሳለፍን ማንም አይረዳምና ዋጋ ያስከፍላል… ጅማ አባጅፋር በፊፋ ከመቀጣቱ በፊት አስቀድመን በሌሎች የሁለት የአፍሪካዊያን ተጨዋቾች ክስ አግደናል ብዙ የተባለው ፊፋ ስለቀጣ ነው ለማንኛውም የፊፋ ደብዳቤ ደርሶናል ጅማ አባጅፋርም በሀገርና በውጪ ሀገር የዝውውር መስኮት ለ3 ተከታታይ ጊዜያት እንዳያስፈርም ታግዷል፡፡

ሀትሪክ፡-ከፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ትናበባለህ… በምታቀርበው በሳልና ጠንካራ ሀሳብ ተቃውሞ ገጥሞህስ አያውቅም?

ባህሩ፡- ኧረ በፍፁም አልተፈጠረም… በዚያ ደረጃ የተወያየንበት ጉዳይና ልዩነት የፈጠረ ነገር አልገጠመኝም እንዲያውም የሚገራርሙ ሃሣቦች ይነሱና ሼፕ አድርጌ በዚህ በኩል ብናየው እንዲህ ብናደርገው ብለህ በጋራ ታነሳለህ እንጂ የተፈጠረ ልዩነት የለም… የእውነትም የተከሰተ ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡-አሁን ምክትል ሆኖ እየሰራ ያለው አቶ ሠለሞን ገ/ስላሴ ነው ባለው የስራ ቆይታ ደግሞ ከአንተ የተሻለ ጊዜ ፌደሬሽኑን ያውቀዋልና አሁን አንተ አለቃ ስትሆን የተፈጠረ ችግር የለም… በሚገባ ተናበናል ብለህ መናገር ትችላለህ…?

ባህሩ፡- አቶ ሰለሞን ዋና ፀሐፊ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ይታወቃል ቁጭ ብዬ አናግሬዋለው የኔ እዚህ ቦታ ላይ መቀመጥ የተሻለ ስራ ከመስራት አንፃር ስለሆነ ተባብረን መስራቱ መልካም ነው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ መጠላለፍ በሽ ነው ብዙ ምሣሌዎችም ማቅረብ ይቻላል ያ ግን ማናችንም አይጠቅምም፡፡ ቦታው ላይ እንድሰራ በስራ አስፈፃሚው እስከታመነብኝ ድረስ አንተ የኔ ጠንካራ ጎን እኔም የአንተ ጠንካራ ጎን መሆን አለብን.. ልታግዘኝ ይገባል እንጂ የጎንዮሽ አካሄዶች አይጠቅሙንም በኢትዮጰያ እግር ኳስ አብሮ የመስራት ምሣሌ ማቅረብ ይከብዳል. ምሣሌ ላገኝ አልችልም ያንን ታሪክ እኛ መቀየር አለብን ብዬ አናግሬዋለው እርሱም ከለውጡ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ገልጾልኛል ያ በተግባርና የሚታየው ለወደፊቱ በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ይሆናል… የተሻለ ስራ ለመስራት ሰለሞን ለኔ እኔም ለርሱ ጠንካራ እንጂ ደካማ ጎን መሆን አይገባንም፡፡ መጠላለፍ ካለ ሰው ላይ ታተኩራለህ ሰው ላይ ካተኮርክ ደግሞ ሀገርህን ትረላሳለህ… ያኔ ደግሞ ፌዴሬሽኑ የተለመደ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ይሄ መቀየር አለበት፡፡

ሀትሪክ፡-ከሚዲያ ጋር ፌዴሬሽኑና ስራ አስፈፃሚው መሃል ያለውን ክፍተት ከማጥበብ አንፃር እንደ ጋዜጠኛነትህ ምን ሰርቻለሁ ብለህ ታምናለህ…?

ባህሩ፡- ከሚዲያ ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት አለኝ፡፡ እንዲያውም ሚዲያው ለኔ አጋዤ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አጋዤ ስል ደግሞ ባልሰራሁበት ጉዳይ ሰርቷል ይላል እያልኩ አይደለም፡፡ ሚዲያ ያልተረዳውን በማስረዳት ደረጃ ቀሎኛል በደንብ ይረዱኛልና… ወደዚህ ቦታ የመጣሁት ሚዲያውን ፀጥረጭ ለማድረግ አይደለም /ሳቅ/ ክፍተቶች ሲኖሩ ትችቶች ያስፈልጋሉ ትችቶች ግን ምን አይነት ይሁን? የሚለው ላይ ጥሩ ስራ እየሰራሁ ነው ብዬ አምናለው፡፡ ሚዲያው አካባቢ ከበፊቱ የተሻለ ነገር አለ በጋራ ልናስተካክላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸው ሳይረሳ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-አንተ ኃፊነቱን ከያዝክ በኋላ ከሚዲያ ጋር በተያያዘ አድርጌዋለሁ ከውኜዋለሁ የምትለው ጉዳይ ምንድነው?

ባህሩ፡- የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ ሁሉን ነገሮች ግልፅ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ በዌብሳይት፣ በጋዜጣዊ መግለጫ በአካል በመሄድ በተቻለ መጠን ነገሮችን ለመግለፅ እየሰራሁ ነው፡፡ የተነሱ ጉዳዮች የጋራ መግባባቶች ላይ እንዲያደርሱን የምችለው ሰርቻለሁ፡፡ ሚዲያ አካባቢ በተሳሳተና በተጋነነ መንገድ የሚነሱትን ስልክ በመደወል ሳይቀር በተገኘው መንገድ ከሚዲያው ጋር የተፈጠረውን ልዩነት የማጥበብ ስራ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡ ስራ አስፈፃሚ አባላትም ደግሞ ያልተረዷቸው ዘገባዎች የተሳሳተ ትርጉም የሰጧቸውን የማስረዳትና በቀናነት እንዲያዩ የማድረግ ስራም ሰርቻለሁ፡፡ በዚህም ጥሩ ድልድይ ሆኛለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የ2013 የውድደር አመት በተመለከተ የተዘጋጀው ፕሮቶኮል አርብና ቅዳሜ በካፍ አካዳሚ ለውይይት ይቀርባልና፣ /ቃለ ምልልሱን የሰራነው ባለፈው ረቡዕ ነው/ ሂደቱ ምን ይመስላል?

ባህሩ፡- የአርብና የቅዳሜው መድረክ ፌዴሬሽኑ ላዘጋጀው ፕሮቶኮል ግብአት እንዲሰጡ ነው፡፡ ጉዳዩን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር አይተነው ለክለቦች ቀርቦ አዳብረውት ለውሳኔ እንዲቀርብ ለማድረግ ነው፡፡ በ2013 ይካሄዳል ብለን ተስፋ ለምናደርገው ውድድር ክለቦች እንደ መመሪያ የሚዳኙበት ነው እኛ ባላየነው ባልተስማማነው ጉዳይ አንመራም እንዳይሉ የጋራ ለማድግም ታልሞ የተጠራ የውይይት መድረክ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-አይነኬ የሚባል ክለቦች የግድ እንዲተገብሩት የሚገደዱበት ሃሣብ አለ?

ባህሩ፡- አዎ አይነኬዎች ይኖራሉ… መንግሥትም ሆነ ፌዴሬሽኑ ያስቀመጧቸው ጉዳዮችማ አሉ፡፡ ከፕሮቶኮሉ ጋር ስናየው ውድድር በዝግ ይካሄዳል፣ ከ72 ሰዓት በፊት የምርመራ ውጤት ማቅረብ አለባቸው የሚልም አለ… ምናልባት ሰዓቱ ሊስተካከል ይችላል እንጂ… ውሃ ሲጠጡ በስማቸው በቀረበ ውሃ ነው በውድድር ሰዓት 30ና 70ኛ ደቂቃ ላይ እረፍት ሲኖር የሚጠጡት በስማቸው ነው… የሚባሉት አይነት ደንቦች አይነኬ ናቸው ሊቀየሩም አይችሉም ያም ሆኖ ግን ክለቦች አይተው አዳብረውት ሰነዱ በድጋሚ ለመንግሥት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡-ጋዜጠኞች፣ ዳኞች ኮሚሽነሮችስ ምርመራው የግድ ይመለከታቸዋል?

ባህሩ፡- ከጋዜጠኞች የግድ የምርመራ ውጤት ማቅረብ የሚጠበቅባቸውና የማይገደዱ ጋዜጠኞች ሊኖሩ ይችላሉ ጨዋታውን ብቻ አይተው ለሚሄዱና ለሚዘግቡ ጋዜጠኞች የምርመራ ውጤት አይጠየቅም ነገር ግን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚከታተሉ ከጨዋታው በኋላ ከአሰልጣኞች ጋር የሚገናኙ ጋዜጠኞች ግን የምርመራ ውጤት የግድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ዳኞችና ኮሚሽነሮችም የግድ ይመረመራሉ፡፡ በነገራችን ላይ በሰነዱ ላይ የህክምና ምርመራውን ወጪ መንግሥት እንዲችል ጥያቄ እናቀርባለን በዚህ በኩል አጋርነቱን ያሳያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለ1 ተጨዋች ከ2 ሺህ በር በላይ ለምርመራ ወጪ የሚደረግ መሆጉ የክለቦችን ወጪ ከፍ ስለሚያደርግ የምርመራውን ገንዘብ መ ንገሥት እንዲችል ለማድረግ እንሞክራለን፡፡

ሀትሪክ፡-ውድድሮችስ በተመለተ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ባህሩ፡- ፕሪሚየር ሊግ ቱር እንዲሆን ታስቧል፡፡ ለምሣሌ የፕሪሚየር ሊግ 5 ሳምንት ጨዋታዎች መቐለ ላይ እንዲካሄድ የማድረግ እቅድ አለ ያ ደግሞ ክለቦችን ለሆቴል ብቻ እንዲያወጡ ያደርጋል፡፡ ከ1 ሳምንት በኋላ ከ6-10ኛ ሳምንት ያለውን ጨዋታ ባህር ዳር ላይ እንዲካሄድ ከአንድ ተጨማሪ ሳምንት ዕረፍት በኋላ ከ11-15ኛ ሳምንት ያለው የ1ኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ በአጠቃላይ የቱር ግጥሚያ እንዲሆን ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ያም በቲቪ ይተላለፋል ጨዋታዎቹ በዝግ የሚካሄዱ ይሆናል፡፡ የከፍተኛ ሊግ ግጥሚያዎችን ካየን በርካታ ክለቦች እንደመኖራቸው ስታዲየሞቹም በዛ ያሉ ሆነዋል አሁን ግን ጨዋታዎቹ በ2 ስታዲየሞች ብቻ እንዲካሄድ ስታዲየሞቹም ተመርጠው አብዛኛውን ክለቦች በሚያማክል መልኩ እንዲሆን ለማድረግ ታስቧል፡፡ የ1ኛ ሊግ ክለቦች ጨዋታዎች ከተመለከትን ቅርብ ቅርብ አካባቢ ያሉትን ክለቦች አንድ ምድብ የማድረግ ስራ ይሰራል ምድባቹ ካለቁ በኋላ በአንድ ቦታ የማጠቃለያ ውድድር የማድረግ ስራ ይሰራል ብለን እናስባለን፡፡

ሀትሪክ፡-ጨረስኩ.. የመጨረሻ መልዕ ክት?

ባህሩ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ መጠላለፍና ተንኮል የበዛበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለሀገራችን እግር ኳስ የተሻለ እንሰራለን ብለን ካሰብን በፊት ከሄድንበትና ካልጠቀመን መንገድ መውጣት አለብን፡፡ መጓተቱና መጠላለፉም መቆም አለበት አንዱ ለአንዱ ብርታት መሆን አለበት አመራሩም ሆነ የኳሱ ባለድርሻ አካላት እጅ ለእጅ መያዝ አለባቸው ትችት ይቅር ባልልም ትርጉም ያለው መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ፌዴሬሽኑ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክል ተቋም እንደመሆኑ መደገፍ አለበት መጠላለፉና ጉተታው በአፍሪካ ውስጥ ያለንን የመሪነት ሚና አሳጥቶናል፡፡ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጊዜ የነበረንን መሪነትና ተሰሚነት ለማስቀጠል መጠላለፉና መጓተቱ መቆም አለበት፡፡ መሻኮታችን በአህጉር ደረጃ የነበረንን ቦታ አሳጥቶናል ይሄን ማስተካከል የግድ ይላል …ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናችንን ማስመለስ ካለብን እርስ በእርስ አንዱ ለአንዱ ጥንካሬ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ቢዚ የሆነው በሌሎችና በአላስፈላጊ ጉዳዮች በመሆኑ ይህን ማስተካከል አለብን ባይ ነኝ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport