የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ባለፈው አርብ ከፕሪሚየር ሊጉ
16 ክለቦች ጋር ለሚዲያ አካላት
ዝግ የሆነ ስብሰባ አካሄዶ የተለያዩ ውሳኔዎች
ተላልፈዋል፤ ከዚህ ውስጥ አንዱና ትልቁ
ውሳኔ የ2ዐ12 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌዴሬሽኑ
መዳፍ ወጥቶ በክለቦች የበላይነት እንዲመራ
የተወሰነው ውሳኔ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም
በኢትዮጵያ ቡናው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ
የሚመራ ሰባት አባላትን ያካተተ ኮሚቴ
ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ከዚህ ከፍተኛ ትኩረትን ከሳበው ውሳኔ
በተጨማሪ የስፖርታዊ ጨዋነትን ችግር
ይቀርፋል፣ እግር ኳሱም የተነጠቀውን
ሠላሙን እንዲያገኝ ይረዳል በሚል ክለቦች
በአቅራቢያቸው በሚገኝና የካፍን መመዘኛ
በሚያሟሉ ስታዲየሞች እንዲጫወቱ በሚል
የተወሰነው ውሳኔ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህም
መሠረት የአዲስ አበባ ክለቦች በአዲስ አበባ
ስታደየም፣ የትግራይ ክለቦች ማለትም ስሑል
ሽረ፣ መቐለ 7ዐ አንደርታና ወልዋሎ አዲግራት
በትግራይ ስታዲየም፤ሐዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ
ቡና፣ወልቂጤ ከተማና ወላይታ ድቻ በሀዋሳ
ስታዲየም፤ባህርዳርና ፋሲል ከተማ በባህርዳር
ኢንተርናሸናል ስታዲየም እንዲጫወቱ
ፌዴሬሽኑና ክለቦች በዕለቱ ስምምነት ላይ
መድረሣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህ የፌዴሬሽኑና የክለቦች ውሳኔ
ብዙዎችን ያስደሰተ ለችግሩም የመፍትሔ
ያህል የተወሰደ ቢመስልም ውሳኔው ወደ
መሬት ከመውረዱ በፊት ከወዲሁ የጠነከረ
ተቋውሞ የሚያሰሙ ክለቦች ድምፅ ከፍ
ብሎ እየተሰማ ነው፡፡ በዚህ በኩል የትግራይ
ወኪል የሆነው ከመቐለ 300ኪሜ ርቀት
ላይ የሚገኘው የስሑል ሽረ ቡድን በዋናነት
ይጠቀሳል፡፡
“በአቅራቢያችሁ ባለው የካፍን መስፈርት
በሚያሟላ ስታዲየም ሄዳችሁ ተጫወቱ
የሚለው ሃሣብ ለምን ተነሳ የሚል ሙግት
አንግጥምም፤ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት
ግን የክለባችንን አቅም፣የሚያደርሰው ጉዳት
በአግባቡ ሊታይ ይገባ ነበር” በማለት ውሳኔው
በሱሑል ሽረ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ
ሊያሳድር ይችላል በሚል ያላቸውን ሥጋት
በተለይ ለሀትሪክ በስልክ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ
አቶ ኪዳነ ገ/መድህን “መቐለ ሄዳችሁ
ተጨዋቱ የሚለው ውሳኔ የክለባችን አቅም፣
የደጋፊዎቻችን ስሜት ላይ የሚያደርሰውን
ጉዳት ያገናዘበ አይደለም፤ ፌዴሬሽኑ ቀጣዩን
የሊግ ውድድር በዚህ መንገድ እንድናደርግ
ከወሰነ ከሊጉ እስከመውጣት የሚያደርስ
ውሳኔ ልንወስን እንችላለን” የሚል ጠንከር
ያለ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ የሀትሪክ
ጋዜጣ ኤክሲኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ
ይስሀቅ በላይ ከአቶ ኪዳነ ገ/መድህን ጋር
ያደረገው የስልክ ቆይታ ከዚህ በታች ያለውን
ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡-ባለፈው አርብ ፌዴሬሽኑ ከ16ቱ
የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ባደረገው ስብሰባ
ከስታደየሞች ደረጃና ከፀጥታ ችግር አንፃር
በመነሣት የ2ዐ12 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር
የሚካሄድባቸውን ስታደየሞች ጠቁሟል
፤በዚህ ውሳኔ መሠረት የትግራይ ክለቦች
በትግራይ ኢንተርናሽናል ስታዲየም መቐለ
ላይ እንድታከናውኑ የሚለው ይገኝበታል
ውሳኔውን እንዴት አገኙት….?
አቶ ኪዳነ በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ
ነገር እንደሃሳብ ነው የተነሣው የተወሰነ
ነገር የለም፤ እንደ ሃሣብ መነሳቱ በራሱ
በእኛ በኩል በጣም ነው የምንቃወመው
ተቀባይነትም የለውም፡፡ አሁን አብይ ኮሚቴ
ስለተዋቀረና እስከሚፈቱት ነው ዝም ያልነው
እንጂ ሃሣቡ ራሱ እንደሃሳብ መነሳቱ በእኛ
በኩል ተቀባይነት የለውም፡፡
ሀትሪክ፡-በዚህ ደረጃ እስከመቃወም
ያበቃችሁና ያልተቀበላችሁበት ምክንያት
ምንድነው…?
አቶ ኪዳነ፡- ክለባችን በፕርምዬር ሊጉ
እየተወዳደረ ያለው የከተማችን አስተዳደር
በሚመድብልንና ህዝቡ በሚያዋጣው ገንዘብ
መሠረት በሚሊዮኖች ብር እያወጣን
ነው፤የምንቀሳቀሰውም በዚህ ነው፤የተለየ
ገቢ የለንም፡፡ የከተማው መስተዳደርም
ህዝቡም ከሌለው ገንዘብ ላይ ወይም ከሌሎች
አንገብጋቢ ጉዳዮች አስቀድሞ ለስፖርቱ በጀት
እያፈሰሰ ያለው እኮ የከተማውን ህዝብ በተለይ
ነገ ሀገር የሚጠቅሙ ወጣቶችን ለማፍራት
እግር ኳሱንም ለማገዝ ነው፡፡ ወጣቶች ቡድኑ
ውስጥ ገብተው እንዲሳተፉ እንደ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡና አይነት ቡድኖች
በሜዳችን መጥተው ሲጫወቱ የከተማውን
ወጣቶች እንዲያነሳሱ ልምድ እንዲቀስሙ
ከዚህ ውጪም ደጋፊዎች ሲመጡ የልምድ
ልውውጥ እንዲኖር ወንድማማችነት
እንዲጠነክር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ወደ
ከተማችን የማምጣት ስፖርቱን ለከተማችን
አንደኛው የማስተዋወቂያና የቱሪስቶች
መሳቢያ እንዲሆን በፖለቲካ፣ በባህልና
በኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለን
ነው፡፡ አሁን ግን ከሜዳ ጋር በተያያዘ ወደ
መቐለ ሄዳችሁ ተጨዋቱ ሲባል ብዙ ነገር
ያሳጣል፤ ክለቡ የተመሰረተበትን አላማም
ይስታል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ
ውሳኔ መወሰኑ ከተማችንን የከተማውን
ወጣቶችንም ይጎዳል፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገር ገና
ሃሣብ ነው ብለን ነው የምናምነው፤ አሁንም
ወደ ውሳኔ ከመሄዱ በፊት አሉታዊ ጎኖቹም
መታየት አለባቸው…
ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ በውሳኔው የሚፀና
ከሆነ እንደ ሱሑል ሽረ ውሳኔያችሁ ምንድነው
የሚሆነው…?
አቶ ኪዳነ፡- እንዳልኩህ ነው እስከአሁን
ይሄ ነገር ገና ያልበሰለ ሃሣብ እንጂ ውሳኔ
አይደለም በማለት እንደ ክለብም እንደ ክልልም
በጉዳዩ ላይ አልተነጋገርንም፤ ውሳኔም
አልወሰንም። ነገር ግን እንዳልከው ፌዴሬሽኑ
ይሄን ሃሣብ ወደ ውሳኔ የሚቀይረው ከሆነ
የራሳችንን ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ
እንድንገደድ ነው የሚጋብዘን። ለከተማችን፣
ለከተማችን ወጣቶች፣ ለሀገር እግር ኳስ
እድገት ትርፍ የማያመጣ ከሆነ ሳንወድ በግድ
ለስፖርቱ የተመደበውን በጀት ትምህርት
ቤትና ጤና ጣቢያ መስሪያ ላይ በማዋል
የከተማችን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን
ወደማድረጉ ለመዞር እንገደዳለን፡፡
ሀትሪክ፡- …ግልፅ አልሆነልኝም
…ውሳኔው ከፀና የክለቡ ቀጣይ እጣ
ፈንታ ምን ይሆናል…እያሉኝ ነው…?
አቶ ኪዳነ፡- …ይሄ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ
ትርጉሙ የገባው ስላልመሰለኝ እኔ በግሌ፣እንደ
ክለቡ ፕሬዚዳንትነቴ አንድ ድምፅ ቢኖረኝም
ፌዴሬሽኑ “መቐለ ሄዳችሁ ተጫወቱ”
የሚል ውሳኔ የሚወስን ከሆነ ከውድድር
እስከመውጣት ሁሉ ልንደርስ የምንችልበትን
ውሳኔ ልንወስን እንደምንችል ነው፡፡ በቃ
ከውድድር ወጥተንላቸው እናርፈዋለን፡
፡ ከከተማውና ለወጣቶች በማይጠቅም ነገር
ላይ ገንዘቡን ከምናፈስ ትምህርት ቤትና ጤና
ጣቢያ ሠርተን ነዋሪውን መጥቀሙን ነው
የምንመርጠው፡፡
ሀትሪክ፡- የአንድ ክልል ቡድኖች
ከመሆናችሁ አንፃር መቐለ ትግራይ
ኢንተርናሽናል ስታደየም ለመጫወት ችግሩ
ምንድነው…?
አቶ ኪዳነ፡- ከሽረ መቐለ በየጊዜው
ተመላልሰን ወይም እዛው ሆቴል ተቀምጠን
ለመጫወት በራሱ የተለየ የፋይናንስ አቅምን
አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ አሁን ሜዳችንን
እየሠራን ስለሆነ እስከ ህዳር መቐለ ተቀምጠው
እንዲጫወቱ ለማድረግ ነገሮችን አመቻችተን
ጨርሰናል፤ አመቱን ሙሉ ወይም በቀጣይስ
እንዴት ልንቀጥል ነው? በዚህ መሠረት
የምንጫወት ከሆነ የከተማችን ተጨዋቾችናና
ደጋፊዎቻችን ላይ መፍረድም ነው የሚሆነው
።2ዐ እና 3ዐሺ የሚሆነው ደጋፊያችን
እንዴት ነው ከዚህ መቐለ እየተንከራተተ
የሚደግፈው? በደጋፊያችን ታጅበን
በመጫወት የምናገኘው ብልጫን ማጣታችንም
ግምት ውስጥ የገባ አይመስልም፤ደጋፊው
የራሱን ክለብ እንዳያይ እንዲቸገር ታዳጊዎች
ወደ ሜዳችን የሚመጡ ታላላቅ ቡድኖች
አይተው ለታላቅነት እንዳይነሳሱም የሚጋፋ
ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ውሳኔውን መቀበል
ለእኛ ከባድ ነው፤ኢትዮጵያዊ የሚባለው
ከተማ የሚኖር ብቻ አይደለም፤ ክፍለ ሀገርም
ያለው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ወላይታ ድቻ
አፍሪካ መድረክ ላይ ቀርቦ አል-አህሊ ላይ
ያን የመሰለ ውጤት ያስመዘገበው ከክልል
ወጥቶ ነው፤ አል-አህሊን ያንበረከኩት እኮ
የወላይታ ድቻ ሜዳ የወለዳቸው ናቸው፡፡
ፌዴሬሽኑ ሜዳ የላችሁም ብሎ ቁጭ ብሎ
ለመፍረድ ከመሮጥ ከመንግሥትና ከፊፋ
ጋር ተነጋግሮ የሜዳ ባለቤት እንድንሆን ነው
መስራት ያለበት፡፡ ሁሉም ልክ እንደ እንግሊዝ
ፕርምዬር ሊግ ክለቦች የራሱ ሜዳ ቢኖረው
ጥሩ ነበር ግን ድሃዎች ነን አቅማችን
አምነን መቀበል ነው ያለብን፡፡ በቀጣይ
የምንወሰነውን ለፌዴሬሽኑም ለሚዲያውም
የምናሳውቀው ነገር ይኖራል፡፡ አሁን ግን እንደ
ፕሬዚዳንትንቴ በግል መልሱን ብሰጥህም
የኮሚቴው ውሳኔም ከከተማው ጥቅም አንፃር
ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ነው ግምቴ፡
፡ ፌዴሬሽኑ አሻፈረኝ ብሎ በውሳኔው ከፀና
ከሊጉ እስከመውጣት ልንገደድ እንደምንችል
ነው የምገልፅልህ፡፡
ሀትሪክ፡-ሱሑል ሽረን ጨምሮ ሶስቱም
የትግራይ ክለቦች ለዝግጅት ዱባይ ትሄዳላችሁ
ተብሎ ነበር.. የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ…?…
የሚለውን የመጨረሻ ጥያቄዬ ላድርገው…?
አቶ ኪዳነ፡-…እ…እሱ ነገር አሁን ብዙም
ተስፋ ያለው ነገር አይመስልም…የመሄዱ
ጉዳይም አነስተኛ ነው፤ ሙቀቱ ለተጨዋቾቹ
ጤንነት አስቸጋሪ ነው፣ይጎዳቸዋል የሚል
እሳቤ መኖሩ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡
አስተያየት ይስጡ