ለኤሌክትሪክ፣ለሸዋ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብ/ቡድን የተጫወተው ፍቃደ ሙለታ በጠና ታሟል

 

“ብዙ ዓመት ያገለገልኩት ትልቅ ታሪክ ያፃፍኩበት ክለቤ እንኳን ሊያሳክመኝ የት እንደወደኩ አያውቅም”
“ከባልቻ ሆስፒታል ውጣ በመባሉ ቤተዛታ ለማስተኛት ጥረት እያደረኩ ነው፤ያለበት ሁኒታ ስሜት የሚነካ ነው”
ሸዋረጋ ደስታ

አሁን ያለበት ሁኔታ ልብ ይነካል፤ያ ቀልደኛው የትልቅ ችሎታ ባለቤትና በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይ በኤሌክትሪክ(መብራት ሀይል)የደመቀ ታሪክ ያለው ፍቃደ ሙለታ በገጠመው ህመም በጠና ታሞ አልጋ ላይ ከወደቀ ቀናቶች ተቆጥረዋል።
ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ከኤሌክትሪክ ታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን በመጫወት ክለቡን ውጤታማና ከሀገሪቱ ስመ ጥር ክለቦች ተርታ ካስቀመጡት ባለውለተኞች አንዱ የሆነው ፍቃደ ሙለታ በገጠመው የዲስክ መንሸራተትና የስትሮክ ህመም በጠና ታሞ በባልቻ ሆስፒታል ተኝቶ ህክምናውን በመከታተል ላይ ይገኛል።
ለኤሌክትሪክ፣ለሸዋ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብ/በቡድን በመጫወት ታሪክ የማይዘነጋው ውለታን የዋለው ፍቃደ ሙለታ አሁን ያለበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝንና ለከፋ ችግር የሚዳርገው እንደሆነ ነው ማየት የተቻለው።
ሰውን ለመለየትና ለማስታወስ ሲቸገር እንዲሁም የህመሙን ስሜት ለመናገር አንደበት ሲያጥረው የታየው ፍቃደ ሙለታ በተሰባበረና በተቆራረጠ ድምፅ “ለሀገሬ በተለይ ለኤሌክትሪክ ብዙ ለፍቼ፣ደክሜ ዛሬ አልጋ ላይ በወደኩበት ሠዓት አስታዋሽ፣ ጠያቂና ዞር ብሎ የሚያየኝ ሰው በማጣቴ ውስጤ በሀዘን ተኮማትራል” ብሏል።
ጡረታ እስከወጣህበት ጊዜ ድረስ የሠራህበትና ትልቅ ታሪክ ያፃፍክበት ኤሌክትሪክ ምን ያህል ድጋፍ እያደረገልህ ነው?በሚል የተጠየቀው ፍቃደ ሙለታ በተሰባበረና ሲቃ በተሞላበት ሁኔታ”እንኳን ሊደግፉኝ የት እንደወደኩ እንኳን አያውቁም፤መጠየቁን ተወውና ዞር ብሎ ያየኝ ሠው እንኳን የለም”ሲል ተናግራል።
አሁን ከፍቃደ ሙለታ ህመም በላይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ህክምና እየተከታተለበት ያለው ባልቻ ሆስፒታል ከአቅማችን በላይ ነው በአስቸኳይ ከዚህ አስወጥታችሁ ወደ ቤተ ዛታ ውሰዱት መባሉ ካለባቸው ከፍተኛ የአቅም ውስንነት ምክንየያት ተጨማሪ ችግር ሆኖበት ህይወቱን ይበልጥ ለከፋ አደጋ አጋልጦታል።
ሁሌም ለተቸገሩና በህመም ምክንያት አልጋ ላይ ለወደቁ የሀገር ባለውለተኞች ቀድሞ በመድረስና እጁን በመዘርጋት ተለይቶ የሚታወቀው የቀድሞ የተጫዋቾችና ደጋፊዎች መረዳጃ ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሸዋረጋ ደስታ ባየው ነገር ክፉኛ ማዘኑንና መደንገጡን በተለይ ለሀትሪክ ገልጿል።
“የቀድሞውን ባለውተኛ ለመጠየቅ ሄጄ ባየሁት ነገር በጣም ደንግጫለሁ፤ከሆስፒታልም የወጣሁት በለቅሶ ነው፤ከህመሙ በላይ ጠያቂ፣አይዞህ ባይ ማጠቱን ሲናገር ልብ ይነካል”የሚለው ሸዋረጋ”በዚህ ህመሙ ላይ ከአቅማችን በላይ ነው ከሆስፒታል ውጣ መባሉ ሁላችንንም ረብሾናል፤አቅሜ በፈቀደ መጠን ከሆስፒታል አስወጥቼ በቀጣይ ቀናት ቤተ ዛታ ተኝቶ በቂ ህክምና እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ፤በዚህ አጋጣሚ ሁላችንም ህይወቱን ለማትረፍ እንረባረብ”ብሏል።
በገጠመው ህመም ምክንያት በጠና ታሞ አልጋ ላይ የወደቀው ፍቃደ ሙለታ ለኤሌክትሪክ ከ1959-1972 ድረስ የተጫወተ ሲሆን በ50 ክለቦች ጊዜ ኤሌክትሪክን ካሳደጉ አንዱ ሲሆን በሸዋ ምርጥና በኢዮጵያ ብ/ቡድን በተለይ ለ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተመርጦ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴው ብዙዎች የሚያስታውሱት ባለውለተኛ ተጫዋች ነው።
የጨዋታ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በሃላም ፍቃደ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከውጤታማው አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ጋር መብራት ሀይልን ያሰለጠነበት አጋጣሚ እንደነበረም ይታወቃል።

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.