“ለኢትዮጵያ ቡና ያስቆጠርኩት ጎል በሊጉ የመጀመሪያዬ ስለሆነች ለየት ያለ ደስታ ተሰምቶኛል” ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና)

 

ኢትዮጵያ ቡና በፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ስዑል ሽረን በሰፊ ግብ በማሸነፍ ከነበረበት የ11ኛ ደረጃ ወደ ስምንተኛ ሊሸጋገር ችሏል፤ ኢትዮጵያ ቡና ከተጋጣሚው በጣም ተሽሎበት በተገኘበት እና በርካታ ግቦች ባስቆጠረበት በእዚህ ጨዋታ ባለድል ሲሆንም ለክለቡ የተገኙትን ግቦች ሶስቱን አቡበከር ናስር ሁለቱን ሀብታሙ ታደሰ እና አንዷን ደግሞ ሚኪያስ መኮንን ሊያስቆጥሩ ችለዋል፡፡ ቡና ስዑል ሽረን ማሸነፉን በተመለከተ እና በክለቡ የሊጉ ተሳትፎ ዙሪያ በቅዳሜው ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ሚኪያስ መኮንንን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ነበርና ቆይታቸው ይሄን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ስዑል ሽረን 6-1 አሸንፏል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
ሚኪያስ፡- ስዑል ሽረን ድል ያደረግንበት ጨዋታ ለእኛ በጣም አሪፍ እና ጥሩም ነበር፤ ግጥሚያውንም ተቆጣጥረን ተጫውተናል፤ ብዙ ጎልም አስቆጥረናል፤ የተሻልንም ስለነ በርን ማሸነፉ ይገባናል፡፡
ሀትሪክ፡- በጨዋታው ላይ ከሳታችሁት ግብ አንፃር ስድስት ግብ ብቻስ በቂ ነው?
ሚኪያስ፡- አዎን፤ ጎሉ በዝቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ሌሎችን ግቦች አልሳትንም ነው የምትለው?
ሚኪያስ፡- የሳትነው ኳስማ አለ፤ ግን ስድስት ግብ ማስቆጠራችን በጣም ብዙ ነው፤ ለእኛ ዋናው ጎል ጋር መድረሳችንና ሙከ ራዎችን ማድረጋችን ነውና ሌላው ነገር ይስተካከላል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከአንደኛው ዙር አንፃር በጅማሬው አሁን ላይ ተለውጧል?
ሚኪያስ፡- በሚገባ!
ሀትሪክ፡- ምን ላይ ነው ለውጡ?
ሚኪያስ፡- የሚታይ ነገር አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ለምሳሌ?
ሚኪያስ፡- ኳሱን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣ ጥረንና መሰረት አድርገን እንጫወታለን፤ ቅዳሜ ዕለት ያሳየነውንም አይነት ጥሩ እንቅስቃሴም በእዚህ ሳምንት መጨረሻም ጅማ አባጅፋርን ስንገጥም እንደምንደግመው እርግጠኞች ነን፤ ጥሩ የቡና ቡድን እየተሰራም ነው ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ቀጣይ ጨዋታውን ከጅማ አባጅፋር ጋር የሚያደርገው ከሜዳው ውጪ ነው?
ሚኪያስ፡- ይሁና! እናሸንፈዋለን፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር ተሳትፎው ስኬታማ ውጤት ያመጣል?
ሚኪያስ፡- በሚገባ ነዋ! ምክንያቱም አጀማመራችን ጥሩ ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ቀጣዩን ጨዋታ ስናሸንፍም ወደ መሪዎቹና ወደ ደረጃው ተፎካካሪዎቹ ክለቦችም በነጥብ ስለምንጠጋ ጥሩ ውጤት ይኖረናል፡፡
ሀትሪክ፡- ከስዑል ሽረ ጋር በተጫወታችሁ በትና በሰፊ ግብ ባሸነፋችሁበት ጨዋታ የመጨረሻው ሰዓታቶች አካባቢ ከእነሱ ተጨዋች ጋር ስትጨቃጨቅና ለመጣላትም ስትሞክር ታይተሃል፤ በዕለቱ ቢጫ ካርድም ተመልክተሃል፤ ምንድን ነው የተፈጠረው ነገር?
ሚኪያስ፡- በቅዳሜው ዕለት ጨዋታ የእነሱ ተጨዋች ዝም ብዬ በምሄድበት ሰዓት ከኳስ ውጪ በክርን ሲመታኝና አስፀያፊም ስድብ ሲሰድበኝ በጨዋታው ላይ በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር፤ ለዛም ነው ልጣላው የነበርኩት፤ ያም ሆኖ ግን እንደዛ መሆን አልነበረብኝም፤ ስለዚህም በእዚህ በኩል ላደረ ግኩት ነገር የቡድናችን ደጋፊዎችን የእነሱን ተጨዋችና የስፖርት አፍቃሪውን ይቅርታ ማለትን እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ስዑል ሽረን በሰፊ ግብ ስታሸንፉ አጥቂያችሁ እና የቅርብ ጓደኛህ የሆነው አቡበከር ናስር ሀትሪክ ሊሰራ ችሏል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ሚኪያስ፡- አቡኪ ጎል ሲያገባ ሁሌም ነው ደስ የሚለኝ፤ ራሴ ያገባው ያህልም ነው የሚሰማኝ፤ ከዛ በላይም ጎል ማስቆጠር ይችል ነበር፤ ወደፊት ለክለባችን ገና ብዙ ጎልም ያስቆጥራል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ስዑል ሽረን ባሸነፈበት ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምት ልትመታ ሄደህ ስትከለከል ተበሳጨህ፤ አቡበከርም ኳሷን መትቶ ጎሉን አስቆጠረህ፤ ሌላ የፍፁም ቅጣት ምት ስታገኙ ደግሞ አቡበከር አንተ እንድትመታ ፈልጎ ኳሱን ሰጠህ፤ አንተም ለቡና ጎል በማስቆጠር በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነልህን ግብ በስምህ አስመዘገብክ፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለህ?
ሚኪያስ፡- በቅዳሜው ጨዋታችን ላይ ቡድናችን 2-0 ከመራ በኋላ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ለመምታት የፈለግኩት በፕሪምየር ሊጉ የክለቡ ታሪክ አንድም ግብ በስሜ የተመዘገበ ስለሌለ ያን የፍፁም ቅጣት ምት በመምታትና ጎልም በማስቆጠር ወደ ግብ ማስቆጠር ሪትም ለመግባት ፈልጌ ነው፤ አቡኪ ቢሰጠኝም ዋናው ወሳኙ አሰልጣኝ ነውና ሳልመታ ቀርቻለው፤ በጊዜው በእኔ ላይ የታየብኝ ስሜት መበሳጨት ሳይሆን ጎል ለማስቆጠር የነበረኝ ጉጉት ነውና ምቱን ለአቡኪ በመልቀቅ ከቦታው ልሄድ ችያለው፤ በጨዋታው ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የፍፁም ቅጣት ምቱን ስናገኝ ደግሞ አቡኪ ሀትሪክ ሰርቶም ነበርና ለእኔ እንድመታ ሰጥቶኝ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሬያታለው፤ ለቡናም የመጀመሪያ የሆነችዋን ጎሌን በማስቆጠሬም በጣም ተደስቻለው፡፡


ሀትሪክ፡- ለሁለተኛ ጊዜ ያገኛችዋትን የፍፁም ቅጣት ምት ታፈሰ ሰለሞንም ሊመታ የፈለገ ያህል ስሜትም ይስተዋልበት ነበር፤ በኋላ ላይ በመበሳጨት መልክ ወደኋላ ሲመለስ አቡበከር የሆነ ነገር ይለው ነበር፤ ምንድን ነው የሆነው ነገር?
ሚኪያስ፡- ታፈሰ የፍፁም ቅጣት ምቱን ሊመታ አይደለም የፈለገው፤ ከዚህ ቀደም እነ ዳንሄል ቴሪ ሆነሪ እና ሮበርት ፔሬስ እንዳደረጉትና ግብ ለማስቆጠር እንደሞከሩት አይነት ኳሷን ሊያቀብለኝና ግቧን እንዳስቆጥር ነበር የፈለገው፤ እኔ ግን ጎል ማግባት በጣም ናፍቆኝና አጓጉቶኝ ስለነበር እንደዚሁም ደግሞ የበለጠ ጎሉን ለማስቆጠር ሰፊ እድሉ የነበረውም በቀጥታ መትቼም ነው በሚል ስላሰብኩ በዛ መልኩ ኳሷን መታዋትና ጎል አስቆጠርኩ፤ እነታፈሰና የቡድኔ ተጨዋቾችም በእኔ ግብ ማስቆጠር ተደስተውም መጥተው አቀፉኝ፡፡ ግቡን ግን ተቀባብለንም ቢሆን ማስቆጠራችን አይቀርም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- የመጀመሪያ ግብህን መታሰቢ ያነት ለማን ታደርጋለህ ተብለህ ሳትጠየቅ ራስህ ምላሽን ሰጠህ?
ሚኪያስ፡- አዎን፤ ይሄን ጥያቄ አልተጠየቅኩም፤ ያም ሆነ ይህ ግን የግቧን መታሰቢያነት ለወላጅ አባቴ አድርጌዋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በሚያሸንፍባቸው ጨዋታዎች በርካታ ጎሎችንም እያስቆጠረ ነው፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ሚኪያስ፡- ብዙ ጎሎችን አስቆጥረን የማሸነፋችን ሚስጥር ኳስን መስርተን በመጫ ወታችንና ቶሎቶሎም የተቃራኒ ቡድን የጎል ክልል ጋር በመድረስ ወጥ የሆነ ጨዋታንም ስለምንጫወት ነው፤ እንደውም ከመጓጓት አኳያ ስለሆነም ነው እንጂ በሌሎች ጨዋታዎች ላይም ግብ የምናስቆጥርበት እድልም ስናገኝ ነበርና፤ ይሄ ብዙ ጎል ማስቆጠራችን ወደፊ ትም የሚቀጥል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ስዑል ሽረን ባሸነፈበት ጨዋታ ለአንተ ምርጡና ስኬታ ማው ተጨዋች ማን ነበር?
ሚኪያስ፡- ሁላችንም በጣም ጥሩ ነበርን፤ የበለጠ ደግሞ አቡኪና ሀብታሙ የተለዩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡- ከስዑል ሽረ ጋር በነበራችሁ ጨዋታ አሰልጣኝ ካሳዬ ላይ የተመለከታችሁት የተለየ ነገር አለ? በእረፍት ሰዓትስ ምን አላችሁ?
ሚኪያስ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ ላይ በእዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ሁሌም የምትመለከትበት አንድ ነገር ቢኖር ሜዳ ላይ እንደሚታየው እና በተደጋጋሚም እንደሚናገረው ነው፤ ጨዋታ የማንበብ ብቃቱ በጣም ይገርመኛል፤ በቅዳሜው ዕለት ጨዋታም እረፍት ላይ የነገረን ነገር እነሱ የሰው ቁጥርን በማብዛት ተጭነውን ሊጫወቱ እና ሊያስቸግሩንም እንደሚችሉ ነውና ለዛ ተነጋግረን ወደሜዳ ስለገባን ሳንቸገር ጨዋታውን አሸንፈን ልንወጣ ችለናል፤ ስለዚህም ቡድናችን ጥሩ አሰልጣኝ አለው ብዬ አስባለው፤ ስኬትንም ያገኛል ብዬ በእርግጠኝነት መናገር እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ስዑል ሽረ በጨዋታው እንዴት ነበር?
ሚኪያስ፡- የመጀመሪያው ዙር ላይ ቡድ ናችን ገና እየተሰራና የቅድሚያም ግጥሚያ ችን ነበርና በጣም ጫና ፈጥረውብን አሸን ፈ ውናል፤ አሁን ደግሞ እነሱ በምንም መልኩ ጠ ንካራ አልነበሩምና በቀላሉ ነው ያሸነፍናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ሚኪያስ ጎል የማስቆጠር ዕድልን በተደጋጋሚ ጊዜ እያገኘ ብዙ ተከላካዮችን ለማለፍ ስለሚፈልግ ብቻ እነዛን አይጠቀምባቸውም እየተባለ ነው?
ሚኪያስ፡- ጎል ማስቆጠርን በጣም እፈልጋለው፤ እንደዛም ሆኖ ደግሞ ራስ ወዳድ መሆንም ጨርሶ አልፈልግም፤ ለእኔ ትልቁ ነገር ኳስን ወደ ግብ ከመምታት ይልቅ የራሴን ኳሊቲ ስለማውቅ ባቀብል ነው የሚሻለኝ፤ ምክንያቱም ሹት ብመታ ኳሊቲዬ አነስ ያለ ስለሆነ ግብ ጠባቂዎች በቀላሉ ይይዙብኛል፤ ስለዚህም እኔ ጎል ማስቆጠሩ ላይ ለመጠቀም ካለመፈለግ ሳይሆን የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችን በእንቅስቃሴ ቀንሼ የእኛን ሰው ነው የምፈልገው፤ የተመቻቸ ነገርም ካለ ደግሞ ወደ ግብ እመታና ጎል ለማስቆጠር እሞክራለው፡፡
ሀትሪክ፡- ሚኪያስን በችሎታው ከዚህ በላይ እንጠብቀው?
ሚኪያስ፡- አዎን፤ ሁሉም ይጠብቀኝ፡፡ ከዚህ በፊት ውድድሩ ሲጀመር አካባቢ ሰዎች ይሄ ልጅ ጠፋ… ምናምን ሲሉም እሰማ ነበር፤ የተሻለ ነገርን መስራት ማንም ይፈልጋል፡፡ ሁሉም ነገር እንደራስህ ጥረትም ነው የሚወሰነው፤ ስለዚህም ራሴን የማውቀው ራሴ ነኝና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስለማውቅ የተሻለ ቦታም ላይ እደርሳለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website