“ለኢትዮጵያ ቡና መጫወትና በካሳዬ አራጌ መሰልጠን መቻል የተለየ ደስታን ይሰጥሃል”ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን /ችምስ/

“ለኢትዮጵያ ቡና መጫወትና በካሳዬ አራጌ መሰልጠን መቻል

የተለየ ደስታን ይሰጥሃል”

“ኢትዮጵያ ውስጥ በኳስ ችሎታው ታፈሰ ሰለሞንን የሚያህል ተጨዋች አላየውም”
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን /ችምስ/

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብን በተቀላቀለበት የዘንድሮ የው ድድር ዘመን ላይ የሊጉ ውድድር በኮቪድ 19 እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ አሳይቷል፤ ከዛ በፊት በነበረው
የኤሌክትሪክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የሐዋሳ ከተማ ክለብ የተጨዋችነት ቆይታው ላይም በተመልካቹ አይን ውስጥ የሚያስገባውን ጥሩ እንቅስቃሴን ሊያስመለክተንም ችሏል፤ በተጨዋችነት ዘመኑ በተለይ ከታፈሰ
ሰለሞን ጋር ያላቸውን የሜዳ ላይ ጥምረትንም ሁሌም በቀዳሚነት ያነሳዋል፤ ይሄ ተጨዋች ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ሲባል ተጨዋቹ በቤተሰቡ ከሚገኙት ሶስት ወንድሞቹና ሁለት እህቶቹ መሀልም አምስተኛው ልጅ
ነው፤ የኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀለበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ ለክለቡ ከመሀል በመነሳት ሶስት ግቦችን ያስቆጠረው ይኸው ተጨዋች የእግር ኳስ ውድድሩ መቋረጡን አስመልክተንና በሌሎች በርካታ ከእሱ ጋር
በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አናግሮት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ችምስ በሚለው የቅፅል ስምህ ትታወቃለህ፤ ለምን ተባልክ? ማንስ ነው ስያሜውን ያወጣልህ?
ፍቅረየሱስ፡- ችምስ ብሎ ያወጣልኝ አጎቴ ነው፤ ስያሜው የወጣልኝም የእግር ኳስን በሰፈር ደረጃ ስጫወትና ተደጋጋሚ ጎሎችንም ሳስቆጥር ግቡን ቸመሰው ከሚል ቃል በመውሰድ ነው ችምስ ሊለኝ የቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳሱ በኮቪድ 19 ከተቋረጠ ወደ አራት ወራት አስቆጥሯል፤ ያለ ኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ መቆየት መቻልህ ምን ስሜትን ፈጥሮብሃል?
ፍቅረየሱስ፡- ከእግር ኳስ አይደለም ለወራቶች ለቀናቶች መቆየት በራሱ በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ሁሉ ነገር ይደብርሃል፤ ያስጠላሃልም፤ ግን ምን ታደርገዋለህ? ፈጣሪ መልካሙን ጊዜ እንዲያመጣልን ልንፀልይ
ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- ከእግር ኳሱ ከራቅህ በኋላ ብዙ ጊዜህን በምንድን ነው እያሳለፍክ የምትገኘው?
ፍቅረየሱስ፡- አብዛኛውን ጊዜ ከቤት አልወጣም፤ ብወጣም ለትንፋሽ የሚሆን የሩጫ ልምምድን ለመስራት ነው፤ ከዛ ውጪም በጊቢያችንም ነው ሰፋ ያለ ቦታ ስላለ ወደዛ በማምራት የስፖርት እንቅስቃሴዎችን
እየሰራው የማሳልፈው፤ አሁን ጠዋት ላይ ራሱ ስትደውልልኝ ፑሽ ሀፕ እየሰራውም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ውስጥ በምትቀመጥበት ሰዓትስ ሌሎች የምታደርጋቸው ነገሮች አሉ?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ ብዙ ጊዜ መፅሀፍቶችን አነባለው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ አሁን ላይ የውጪዎቹ ኳሶች መጀመራቸው ጥሩ ስለሆነ እነሱንም እመለከታለው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ላይ በዋናነት ምን ናፍቆሃል?
ፍቅረየሱስ፡- የእግር ኳስ ነዋ! ከዛ ውጪ ምን ይናፍቀኛል ብለህ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችስ አልናፈቁህም?
ፍቅረየሱስ፡- እንዴት አይናፍቁኝም፤ እነሱን የምታገኛቸው እኮ መጀመሪያ ኳሱ ሲጀመር ነው፤ ኳሱ ናፈቀኝ ማለት ደግሞ እነሱም ናፍቀውኛል ለማለት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘኸው ሰው ማንን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- የክለባችን ግብ ጠባቂ ፈቱዲን ጀማልን እና ተክለማሪያም ሻንቆን ነው ማታ ላይ ውድድሩ ተቋረጠ ሲባል ያገኘዋቸው፤ ወዲያውንም እነሱ ጥለውኝ ወደ ሀገራቸውም ሊሄዱ ችለዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙ ጊዜ ሳትነጣጠሉ ስለማያ ችሁ ሁለቱ ተጨዋቾች ለአንተ የቅርብ ጓደኞችህ ናቸው ልበል?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን አልተሳሳትክም፤ ከሁለቱ ተጨዋቾች ጋር የተለየ ጓደኝነትም ነው ያለን፤ የቤተሰብ ያህልም ነው ቅርርባችን፤ አሁንም ድረስ ናፍቆታችንን ለመወጣትም እንደዋወላለን፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ለተለያዩ ክለቦች ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ አንተ ከተሳተፍክባቸው ውስጥ ምርጡ ጨዋታ የምትለው የቱን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- በጣም የማደንቀው እና ምርጡ ጨዋታዬ የምለው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምጫወትበት ሰዓት በድሬዳዋ ከተማ ቡድን ላይ ሀትሪክ የሰራሁበትን ነው፤ ያ ጨዋታ የተለየ እርካታ ሰጥቶኝ አልፎም ነበር፤
ጨዋታውን ያደነቅኩበት ዋንኛው ምክንያትም ከመሀል ተጨዋችነት ተነስቶ ሀትሪክ መስራት ከባድ ስለሆነም ነው፤ ሌላ ምርጡ ጨዋታዬ ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲጫወት ያደረገውን ነው፤ በዛ ጨዋታ ላይ
እንደውም ለድሬዳዋ ከተማ እና ለመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ይጫወት የነበረው የቀድሞ የመድን ተጨዋች ያሬድም ጥሩ ተጨዋች ነህ፤ ግን ለምንድን ነው ለብሔራዊ ቡድን የማትመረጠውም ብሎኝ ነበር፡፡


ሀትሪክ፡- ምርጧ ግብህስ?
ፍቅረየሱስ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስጫወት በወልዋሎ አዲግራት ላይ በመቐለ ስታድየም ያስቆጠርኳትን ነው፤ ግቧም ከርቀት መትቼም ያገባዋት ናት፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም እግር ኳስ የማን ተጨዋች አድናቂ ነህ? ከክለብ የምትደ ግፈውስ?
ፍቅረየሱስ፡- የሊዮኔል ሜሲ አድናቂ ነኝ፤ እሱ ማለት በቃ በትንሽ ቃላት ብቻ የምትገልፀው ተጨዋች አይደለም፡፡ ከክለብ የአርሰናልና የባርሴሎና ደጋፊ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ተጨዋቾች ውስጥ የማን አድናቂ ነህ?
ፍቅረየሱስ፡- ለበርካታ ጊዜ አብሬው ተጫውቼያለውና የታፈሰ ሰለሞን አድናቂ ነኝ፤ እሱን መግለፅም በጣም ይከብዳል፤ ኳስ እግሩ ስር ስትገባ ያዝናናሃል፤ ስለ እሱ እንደሌሎች ተጨዋቾች እንደውም ፈጣሪን ነው
የምልህ ብዙም አልተወራለትም፤ አስማተኛ እና ታምረኛም ተጨዋች ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እሱን የሚያህል ተጨዋችም ማንም የለም፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ደስተኛ ነህ?
ፍቅረየሱስ፡- በጣም ሁሌም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ተከፍተህ አታውቅም?
ፍቅረየሱስ፡- አውቃለው እንጂ፤ ግን ደስታዬ ስለሚበዛ ለተከፋሁበት ጊዜ ጆሮዬን አልሰጠውም፡፡
ሀትሪክ፡- ከተከፋክባቸው ጊዜያቶች አንዱን ብትጠቅስልን?
ፍቅረየሱስ፡- በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ነው ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ በበጀት እጥረት በቃ አትምጣ ተብዬ ሲነገረኝ በጣም አዝኜ ነበር፤ ያን የማስታውሰው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና እየተጫወትክ ይገኛል፤ ለቡና መጫወት መቻል ከሌሎች ክለቦች አንፃር ይለያል?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ ለቡና ስትጫወት ስሜቱ ከሌሎች ቡድኖች አኳያ በጣም ይለያል፤ ምክንያቱ ደግሞ የምትጫወተው በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ታጅበህም ስለሆነ ነው፤ በተለይ እነሱ ሲያበረታቱ ከልባቸው ስለሆነም
በውስጥህ የተለየ አይነት የደስታ ስሜትም ይፈጠርብሃል፤ እነሱን ለማስደሰትም ትጫወታለህ፤ ሁሌም ራስህን ጥሩ ለማድረግ ትዘጋጃለህ፤ ሌላው ክለብ ጋር ስጫወት ግን የተመለከትኩት ነገር ቢኖር ተጫውተህ መውጣት
ብቻ ነውና ከዛ አንፃር ቡናን ለየት ያደርገዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ባለህ የጨዋታ ሚና አጨዋወትህን ድብቅ እና የማይታይ ነው ብለው የሚያደንቁ አሉ፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
ፍቅረየሱስ፡- የእኔን የሜዳ ላይ ችሎታ እና እንቅስቃሴዬን በተመለከተ የአንተ እይታ ነው እንግዲህ የሚወስነው፤ ሰዉ እንደዛ ቢልም የእኔ አጨዋወት ግን በፊትም ሆነ አሁን ድብቅ ነው ብዬ ፈፅሞ አላስብም፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ማለት ለአንተ ምን ማለት ነው?
ፍቅረየሱስ፡- ኢትዮጵያ ቡና ለእኔ ሁሉ ነገሬ ነው፤ ክለቡ በጣምም ተመችቶኛል፤ ከመሀል እየተነሳውም ሶስት ግቦችን ከማስቆጠር ባሻገር ጥሩ ነገርን እያደረግኩለት ይገኛል፤ ቡና ከእነ ደጋፊውም ምርጥ የሆነም
ክለብ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በብዙ አሰልጣኞች ሰልጥነህ አልፈሃል፤ በቡና ደግሞ በካሳዬ አራጌ እየሰለጠንክ ነበር፤ በእነሱ መሀል ያየኸው ልዩነት አለ?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ በስልጠናው የተለዩ የምላቸውም በካሳዬ አራጌ ስትሰለጥን ተጨዋቾች ከፍተኛ ነፃነት አላቸው፤ እሱ ቡድኑን ሲመራ እንደሌሎቹ አሰልጣኞች ኳስ ሲበላሽብህ እንዲህ ለምን አታደርግም ብሎ
አይጮህብህም፤ ስፖርተኛን ይረዳል፤ ይህን እሱ እና ሌላኛው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ ነው ያየሁት፤ ካሳዬን ሌላ ለየት የሚያደርገው ኳስን ስትጫወት ነፃ ሆነ እንድትጫወት ነው የሚፈልገው፤ ኳስ ላይ ስትሳሳት ከሚነግርህ
ነገር አንፃር እንደምታርመው ያውቃልና ያ እሱን ለየት ያደርገዋል፡፡ ከዛ ውጪም ለኢትዮጵያ ቡና መጫወትና በካሳዬ አራጌ መሰልጠን መቻልም የተለየ ደስታን ይሰጥሃል፡፡
ሀትሪክ፡- ከካሳዬ አራጌ ጋር በተያያዘ ሌላው አንድ ነገር ላንሳልህ እያሰለጠናችሁ አብሯችሁ በልምምድ ሜዳ ላይስ ሲጫወት እንዴት አገኘኸው?
ፍቅረየሱስ፡- ካሳዬ ከእኛ ጋር አልፎ አልፎ ሲጫወት ስታየው በጣም ነው የምትገረመው፤ በተለይ ደግሞ መሀል ባልገባ ላይ ያስገርምሃል፤ ምናለ በጨዋታ ዘመኑ ላይ ባየው ብለህም የምትመኘው አይነት ተጨዋችም
ነው ከዛ ውጪ የሚነገርህ ነገርም ሜዳ ላይ የሚገጥምህንም ነው፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ አሪፍ ነበርም ይልሃል፤ ከዛ ውጪ ራስህን ሁሌም እንድትፈትሽም ያደርግሃል፤ በአጠቃላይ ኳስን በእውቀት እንድትጫወትለትም
ይፈልጋልና ካሳዬ ማለት ለየት ያለ ሰው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማጣጣም አልቻልክም፤ አይቆጭ ህም?
ፍቅረየሱስ፡- ይቆጨኛል እንጂ፤ ይሄን ድልም ኳስን ጥሩ ከሚጫወተው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በቀጣዩ ጊዜ የማጣጥመው ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችን እንዴት ነው የምትገልፃቸው፤ የትስ ተወልደህ ነው ያደግከው? አንድ አንዶች የአዲስ አበባ ልጅ ነው የሚሉህም ስላሉ….?
ፍቅረየሱስ፡- ተወልጄ ያደግኩት ሀሰላ አርዱ በሚባል አካባቢ ነው፤ የአዲስ አበባ ልጅም አይደለውም፤ አንድአንድ ሰዎች እንደዛ ሊሉኝ የቻሉት ብዙውን ጊዜ 22 አካባቢ ወንድሜ ጋር ስለኖርኩና በኳሱ
የማውቃቸውም ጓደኞች ስላሉኝ ከዛ ተነስተውም ነው የአዲስ አበባ ልጅ ነው ያሉኝ፡፡ ቤተሰቦቼን በተመለከተ ለእኔ ምርጥ ናቸው፤ በኳሱ እዚህ ለደረስኩበት ደረጃም ብዙ በመልፋት ትልቁን አስተዋፅኦም ያደረጉልኝ ናቸው፤
በተለይ የእናቴ ሚና በጣም ከፍ ያለም ነበርና የእሷ ፀሎትም ነው ለእዚህ ያደረሰኝና በእዚህ አጋጣሚ ሁሉንም ላመሰግናቸውም እወዳለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከቤተሰቦችህ መሀል የእግር ኳስ ተጨዋቹ አንተ ብቻ ነህ?

ፍቅረየሱስ፡- አይደለውም፤ ብዙዎቹ ከታሪኩ ስምኦን በስተቀር ለክለብ ተጨዋችነት አይታደሉ እንጂ የእግር ኳስን ሜዳ በአካባቢያችን ስለነበር ተጫውተው ያሳለፉ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ታሪኩ ስምኦን ማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች የነበረው ነው? ከእሱ ጋር ያላችሁ ትስስር ምንድን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- አዎ፤ ታሪኩ የበፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ነበር፤ ስለ እሱም ከካሳዬ አራጌ ጋር አንዴ አውርተን እንደሚያውቀው ነግሮኝም ነበር፤ ታሪኬ ለእኔ የአጎቴ ልጅም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከታሪኩ ስምኦን ጋር የማውራት አጋጣሚውንስ አግኝተህ ታውቃለህ?
ፍቅረየሱስ፡- አላውቅም፤ ከአውሮፓ ሁለት ጊዜ ወደ ሀገር ቤት በመጣበት ሰዓት እኔ ገና ወጣት ነበርኩ፤ በክለብ ደረጃ ያኔ ኳስን አልጫወትምም ነበርና እስካሁን ድረስ ከእሱ ጋር የማውራት አጋጣሚውን
አላገኘውም፤ ያም ቢሆን ግን እኔ አሁን ላይ የደረስኩበትን ደረጃ እቤት ደውሎ በነበረበት ሰዓት ነግረውታልና ይሄን ነው የማውቀው፡፡ አንድ ቀን እሱን ማግኘቴም የማይቀር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ ምን ሆነህ እናገኝህ ነበር?
ፍቅረየሱስ፡- ጥሩ ተማሪ ስለነበርኩ ምንአልባት መሀንዲስ ሆኜ ነበር የምታገኙኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በቤተሰባችሁ እና በክለባችሁ ውስጥ የሳቅ ደስታን የሚፈጥርላችሁ ማን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- በቤታችን ወንድሜ አብይ አለ፤ ጨዋታ አዋቂና ቀልደኛ ነው፤ እሱም ነው በጣም የሚያዝናናን፡፡ በክለባችን ደግሞ አዝናኙ ተጨዋች ታፈሰ ሰለሞን ነው፤ እሱ ካለ አይደብርህም፤ በኳስ ጨዋታ ችሎታው
ብቻ ሳይሆን በቀልዱም በጣም የተካነ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከክለባችሁ ተጨዋቾች ውስጥ በጣም ዝምተኛውስ?
ፍቅረየሱስ፡- እኛ ክለብ ጋር ሁሉም ይስቃል፤ ይጫወታል፤ ግን አስራት ቶንጆ ይመስለኛል ዝምተኛው፤ እሱ አልፎ አልፎ ብቻ ነው ሲያወራ የምትሰማው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ቡና ደጋፊዎች አንድ ነገር በል ብትባል ምላሽህ ምንድን ነው የሚሆነው?
ፍቅረየሱስ፡- የቡና ደጋፊዎች ክለባቸውን ሲደግፉና ሲያበረታቱ በጣም አሪፍ ናቸው፤ ይሄ ደጋፊ ውጤት መጣም አልመጣም በእዚሁም ነው መቀጠል ያለበት፤ እነሱ ከራሳቸው የሚጠበቀውን ነገር ብቻም ነው
ማድረግ ያለባቸው፤ ከዛ ውጪም አሁን ላይ በከተማው እንደምናየው ደግሞ ኮቪድ 19ን ታሳቢ በማድረግ የእጅ ማስታጠብን ማድረግ መስኮችን መሸጥ ፕሮግራምና ሌላም ሌላም ነገሮችን እየሰሩም ነውና እነዚህን
ምርጥ ደጋፊዎች በርቱም ማለትን እወዳለው፡፡
ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ስንት ሳኒታይዘር ጨረስክ?
ፍቅረየሱስ፡- ኸረ ብዙ ነው፤ አሁን ራሱ ብታይ የሀገር ሳኒታይዘርም ነው ከአጠገቤ ጋር ያለውና እነሱም ስፖርትን የምሰራ ከመሆኔ አንፃር ማለቃቸው የማይቀር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በአሁን ሰዓት ለተጨዋቾች ወርሃዊ ደመወዝ ከመክፈል እና ካለመክፈል ጋር በተያያዘ እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ ምን የምትለው ነገር አለ?
ፍቅረየሱስ፡- በእዚህ ዙሪያ የእውነት ነው የምልህ በአሁን ሰዓት ከባድ ነገር እየተፈጠረም ነው ያለው፤ በኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ ከክለቡ ጋር በመስማማት 60 ፐርሰንት፣ 40 ፐርሰንት ተብሎ ደመወዝ እየተከፈለ
ነው ያለው፤ ወደ አንድአንዶቹ ጋር ስታመራ ደግሞ ጭራሽ ደመወዝ አይከፈልምና ይሄ ባይሆን እንኳን በስምምነት የተወሰነ ወርሃዊ ክፍያን ለተጨዋቾች ቢፈፅሙላቸው በጣም ጥሩ ነው፤ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ
ክለቦች በአሁን ሰዓት መክፈል አቅቷቸው አይመስለኝም፤ የቅንነት ጉዳይ ነው፤ ቅንነት በጣም ይጎድላቸዋል፤ ስፖርተኛ ስለሆነ ምንም ነገር አያመጣም የሚልም አመለካከትና ውሳኔም ነው የሚታይባቸው፤ ይሄ
ለስፖርተኛው ቤተሰቡን ከመርዳት አኳያም ከባድ ነገርም ነው እየተፈጠረበት ያለው፤ አሁን ለመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ባይከፈለው እሪ ይላል አይደል፤ ለምንድን ነው ለስፖርተኛውስ የማይከፈለው፤ እሱ አሁን ቢሮ ውስጥ
ቁጭ ብሎ ደመወዙን ይበላል፤ ቢቋረጥበት እኮ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገባውና እኛ ሀገር እንዴት እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር በአገራችን ተቋቁሟል በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ ብዙ ጊዜ በስብሰ ባቸው ላይም ተገኝቼ ነበር፤ ይሄ ማህበር መቋቋሙና መኖሩ ለተጨዋቾች በጣም ወሳኙ ነገር ነው፤ ግን መቋቋም ብቻ አይደለም እታች ወርደው ስራ መስራትም
ይኖርባቸዋል፤ አሁን የስፖርተኛ ደመወዝን የማይከፍሉ ክለቦች ላይ ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል፤ ከተቋቋሙ ብዙ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል፤ ሲመስለኝ አሁን ላይ እየተንቀሳቀሱም ናቸው፤ ሲሰሩ ግን ሁሌም ሲሪየስ
ሊሆኑም ይገባል፤ ተጨዋቹም ቢሆን ከእነሱ ጎን ሊሆን ይገባል፤ በማህበሩ አማካኝነትም የራሱን መብት ማስከበርም ይኖርበታል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳሱ ወደነበረበት ዳግም እንዲመለስ ምን ትላለህ?
ፍቅረየሱስ፡- መጀመሪያ ሁላችንም በጤና ሚኒስቴር እና በመንግስት ደረጃ የሚወጡ መመሪያዎችን መከታተልና እነዛንም በተግባር ላይ ማዋል የሚጠበቅብን ይመስለኛል፤ ከቤት አትውጡ ከተባለም
አለመውጣት ነው፤ በሽታው እንዲቆም ከተፈለገ ራሳችንን በጣም መጠበቅ ይኖርብናል፤ አሁን ላይ ኳሱ በጣም ናፍቆናል፤ ይሄ በሽታ ካልቆመ ኳሱም የሚኖር አይመስለኝም፤ ስለዚህም አንድአንድ አስገዳጅ ሁኔታ
ካልተፈጠረ በስተቀር ህዝቡ ከቤት ባይወጣ ጥሩ ነው፤ በሽታውን ለመቆጣጠር ብንችልም ጥሩ ነው፤ ከዛ በተረፈ ደግሞ ሁሉም ሰው ወደ አምላኩ መፀለይ አለበት፤ ይህን በሽታ አይደለንም እኛ ያደጉት ሀገሮችም
አልቻሉትምና ጥሩ ጊዜው መጥቶልን ወደምንፈልገው እግር ኳሳችን እንድንመለስ እሱ ይርዳንም ነው የምለው፡፡


ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ በእናንተ ክልል ያለው ሁኔታ ምንድን ነው የሚመስለው?
ፍቅረየሱስ፡- እኛ ጋር እስካሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ ያ ሊሆን የቻለበት አንደኛው ነገርም ክፍለ ሀገር ስትሆን እንደ አዲስ አበባ ብዙ የህዝብ ቁጥር ስለሌለና ከተወሰነ ሰው ጋር ብቻ ስለምትገናኝም ያ ይመስለኛል
ነገሮች እዚህ ጥሩ እንዲሆን ያደረገውና በቫይረሱ የተያዥ ቁጥሩንም ክፍለ ሀገር ላይ ትንሽ ያደረገው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ……?
ፍቅረየሱስ፡- አሁን ላይ እቤት ካስቀ መጠን ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወጥተንና ፀልየን አምላካችንም ፀሎታችንን ሰምቶን ወደ ቀድሞ ስራችን ወደምንወደው እግር ኳሳችን ብንመለስ በጣም ደስ ይለኛልና፤ ያ እንዲሳካ
እኛም ሆንን ህዝቡ ራሱን በሚገባ መጠበቅ ይኖርበታል፤ እኔም በዚህ ዙሪያ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር፤ በሚዲያ ደረጃ ይነገራል፤ አሁንም ይነገራል ምንም መፍትሄ ስለሌለው እባካችሁ እንደው ከእዚህ ወረርሽኝ
እንድንላቀቅ ሀኪም የሚለውን ነገር ብንተገብር ጥሩ ነው ብዬ አስባለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website