“ለብሄራዊ ቡድን ዳግም በተመረጥኩብት ሰዓት በፋሲሎች ተፈልጌ የቡድናቸውአካል ስለሆንኩ በጣም ተደስቻለሁ”ይድነቃቸው ኪዳኔ /ፋሲል ከነማ/

“ለብሄራዊ ቡድን ዳግም በተመረጥኩብት ሰዓት በፋሲሎች ተፈልጌ የቡድናቸውአካል ስለሆንኩ በጣም ተደስቻለሁ”

“ለአንድም ቀን ቢሆን ራሴን የሀገሪቷ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ አድርጌ አላውቅም”
ይድነቃቸው ኪዳኔ /ፋሲል ከነማ/

ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪነቱን ማሳየት ከጀመረ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ አንድ ጊዜም የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ለማንሳት ችሏል፤ ከዛ ባሻገርም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እስከ መጨረሻው ድረስ ተጉዞም ለጥቂት አጥቷል፤ በዘንድሮ የሊጉ ተሳትፎም ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን ከገባበት ጊዜ አንስቶም ውድድሩ ቢቋረጥም በመሪነት ደረጃ ላይ ሆኖም የእዚህ ዓመት የሊጉ ሻምፒዮና መሰረዙ ይታወቃል፤ ፋሲል ከነማ ለመጪው የውድድር ዘመን ተሳትፎውም አሁንም ቡድን በማጠናከር ስራው ላይ ተጠምዶ የተለያዩ ተጨዋቾችን በክረምቱ የዝውውር መስኮት እያስፈረመ ሲሆን የነባሮቹን የውል ዘመንም እያራዘመው ይገኛል፡፡
ፋሲል ከነማ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሣት ዋንኛ እልሙ ባደረገበት የአሁኑ ሰዓት ላይ እስካሁን የኢትዮጵያ ቡናውን አማኑኤል ዩሃንስን፣ የመከላከያውን ፍቃዱ ደነቀን፣ የባህር ዳር ከተማውን ግርማ ዲሳሳን ያስፈረመ ሲሆን በግብ ጠባቂነት ደግሞ የወልቂጤ ከተማውንና የብሔራዊ ቡድናችንን ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔን ሊያስፈርም ችሏል፡፡
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተለያዩ ተጨዋቾችን እያስፈረመ ባለበት የአሁን ሰዓት ላይ በግብ ጠባቂነት ክለቡን የተቀላቀለውን ይድነቃቸው ኪዳኔን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አነጋግሮታል፤ ተጨዋቹም ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማን በእዚህ ወቅት እቀላቀላለው ብለህ ጠብቀህ ነበር?

ይድነቃቸው፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ ስራህን በጥሩ መልኩ ከሰራ ሁልጊዜም ቢሆን ጥሩ ነገር ይገጥመኛል ብለህ ታስባለህ፤ ያም ሆኖ ግን ይሄ የክለቡ ጥሪ በእዚህን ሰዓት ይደርሰኛል ብዬ ባልጠብቅም ጥሩ ነገር እንደሚገጥመኝ ግን አስብ ነበር፤ ያ ያሰብኩት ነገርም ከክለቡ ፈርምልን የሚል ጥያቄን ይዞልኝ ሲመጣ ቡድኑን በጥሩ መልኩ ለማገልገል ነው እየተዘጋጀው ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ ፊርማህን ካኖርክ በኋላ ከእንግዲህ ምንም አይነት የውድድር ጊዜያትን አሳልፋለው ብለህ ታስባለህ?

ይድነቃቸው፡- ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን መቀላቀል ከቻለበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱ ትልቅና አስፈሪ እንደዚሁም ደግሞ ስኬታማም ቡድን ነው፤ ለሻምፒዮንነት ፉክክር የሚጫወትም ክለብ ነው፤ የዘንድሮ ውድድር በኮቪድ 19 ምክንያት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም ሊጉን እየመራ የነበረ ክለብ ስለሆነና ሁሌም ለዋንጫ የሚጫወት በመሆኑ ወደ እዚህ ክለብ ዝውውርን ሳደርግ እኔም በተጨዋችነት ዘመኔ ሌሎች ዋንጫዎችን አግኝቼ ያላገኘሁትን ብቸኛ የፕሪምየር ሊግ ድል ግን ማጣጣም ስለፈለግኩኝ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ይሄ ከአዲሱ ክለቤ ጋር የሚሳካልኝ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜ ተመርጠህ ተጫውተሀል፤ አሁን ላይም ከበርካታ ጊዜ ቆይታዎች በኋላ በድጋሚ የመመረጥ እድሉን አግኝተሃል፤ ይሄን ወደኋላ ሄደህ ስታስብ ምን አልክ?

ይድነቃቸው፡- ከላይ እንዳልከው በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተመርጬም ሆነ ተጫውቼ ያለፍኩባቸው ጊዜያቶች ብዙ ናቸው፡፡ በእዚህም እንደ ክለብ ተጨዋችነቴ ሁሉ ትልቅ ልምድ ያለኝ ተጨዋችም ነኝ፤ በስፖርት ዓለም ውስጥ ስትኖር ሁልጊዜ ዝግጁ ልትሆን ይገባል፡፡ ዛሬ ጠንክረህ ከሰራህ ሁልጊዜም የአንተ ልፋት ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ ግን አንድ አንዴ በመሀል የራስህ የሆኑ ክፍተቶች ሊመጡ ይችላሉ፤ ያ ሲያጋጥምህ ነገሮችንና ፈተናዎችን ተቋቁመህ በማለፍ ወደፊት የምትሰራ ከሆነ ጥሩ ነገር የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ ስለዚህ እኔ ሁልጊዜ ጠንክሬ እሰራለው፡፡ በእዚህ አመት በወልቂጤ ከተማ ቡድን ውስጥ ካሳለፍኩት ቆይታ እና ጥሩ አቋሜ አንፃርም ለብሔራዊ ቡድን መመረጡን ጠብቄው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ብሔራዊ ቡድናችን ዳግም መመለስን በጣም ከመፈለጌ አንፃር ለወልቂጤ ከፈረምኩበት ጊዜ ጀምሮም ከግብ ጠባቂው አሰልጣኛችንና ለእኔ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስም ትልቁን ክሬዲት ከሚወስደው በለጠ ወዳጆ ጋርና እንደዚሁም ደግሞ ከክለቡ ዋና አሰልጣኝ ደግአረግ ጋርም የተነጋገርናቸው አንኳር አንኳር ጉዳዮችም ስለነበሩ እነዛ እኔን በጣም ጠቅመውኛል፡፡ በወልቂጤ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የውጪ ዜጋ አስቀምጦ የተሰለፈ ብቸኛ ግብ ጠባቂ ተብሎም ይነገርልኝ ነበርና ወደዛ ስሄድ ዓላማ ያደረግኩት ወደ ቀድሞ አቋሜ መመለስና የብሔራዊ ቡድኑን ጥሪም ደግሞ አግኝቼ ሀገሬን በድጋሚ ማገልገል የሚለውም ስለነበር በእግዚያብሔር እርዳታ ይሄን ላሳካው ችያለው፡፡ በእግር ኳስ ጠንክረህ ከሰራክና ከታገስክም ምን የማይሆን ነገርም የለም፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮትዲቭዋርን ካሸነፈ በኋላ ነው የዋልያዎቹ ጥሪ የደረሰህ፤ በቀጣይነት ደግሞ የአንተም ሚና ይኖራልና በእዚህ ላይ ምን አይነት ተሳትፎ ይኖርሃል?

ይድነቃቸው፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮትዲቭዋርን ካሸነፈ በኋላ ያለው መነቃቃት እና የቡድኑ መንፈስ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ለቡድኑ ስጠራም ይሄንን ነገር ለማስቀጠል እና የሀገራችንንም ስም ከፍ ለማድረግም ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ ከዛ ውጪም የአፍሪካ ዋንጫ ዳግም ተሳትፎም እንዲኖረን እያለምኩም ነው ያለሁትና ከብሔራዊ ቡድን አባላቶች ጋር ባለኝ የጨዋታ ልምድ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን ዳግም ለጥሩ ውጤት እንደማበቃው ተስፋን አደርጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ብዙ ጊዜ አንድ ግብ ጠባቂ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ከተጠራና ለተወሰነ ጊዜም ከተጫወተ በኋላ በሌላ በረኛ ይተካል፤ ከዛ የእዚህ በረኛ ቀጣዩ ጉዞ በተለያዩ ክለቦች ደረጃ ብቻ መጫወት ላይ ይገደባል፤ አንተ ግን አሁን ላይ ከቆይታዎች በኋላ ለብሔራዊ ቡድን ዳግም ተመርጠሃል፤ ከዛ ውጪም የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ በሆነው ፋሲል ከነማም ተፈልገህ ወደ ቡድኑ አምርተሃል፤ ይሄ ሲታይ አሁን ላይ የሀገሪቱ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ነህ ማለት ይቻላል?

ይድነቃቸው፡- /እንደ መሳቅ ብሎ/ እኔ እንኳን ለአንድ ቀንም ያህል ቢሆን እንደዛ ነኝ ብዬ ፈፅሞ አላስብም፤ ከዛ ይልቅ ሁልጊዜ ራሴን በአዕምሮም ሆነ በአካል ደረጃ ዝግጁ አድርጌ እቀርባለው፡፡ በአጠቃላይ ኳሱ በሚፈልገው መሠረታዊ ነገር ሁሉ ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዛ ውጪም ለብሔራዊ ቡድን ብመረጥም ባልመረጥም፤ በምጫወትባቻው ክለቦች ውስጥ ብሰለፍም ባልሰለፍም የራሴ የሆነ መመሪያ ስላለኝ ማለትም እየተጫወትኩ ቤስት ነኝ፤ ተጠባባቂ ሆኜም ቤስት ነኝ፤ አውት ኦፍ ስሆንም ቤስት ነኝ በሚል አዕምሮዬን አዘጋጅቼው ስለምቀርብና ተጠባባቂ ሆኜም ወደ ሜዳ ስገባ ያለኝን ነገር ሁሉ ስለምሰጥ፤ ኳስን ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮም አሰልጣኞቼ የሚናገሩኝን ነገሮችም ስለምሰማም ምክንያቱም የእግር ኳስ ተጨዋች ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መቅረብ አለበት ስለሚሉ፤ ከዛ ውጪም በባህር ማዶ ኳስ ላይም ለአንድ ተጨዋች 5 ደቂቃ 10 ደቂቃ ሰጥተህ ሲጫወት ስታየው የተሻለ ግብ ጠባቂ ሆነህ ስለምትመከተውና ለሀገራቸውም የሚሰሩትን ጥሩ ስራ ስለማውቅ እኔም በተጠራው ሰዓት ያለኝን ነገርም ስለምሰጥ ይሄ ነገር ጠቅሞኛል፡፡ አሁንም ወደፊትም ሁልጊዜ ራሴን ለፋሲልም ለብሔራዊ ቡድንም ብቁ አድርጌ መቀጠልንም ነው የምፈልገው እንጂ የሀገሪቷ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ አድርጌ ራሴን አልቆጥረውም፤ እኔ በተጨዋችነት ዘመኔ ለአንድም ቀን ቢሆን ራሴን አንደኛ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ነኝ ብዬም የማውቅ አይነት ተጨዋችም አይደለውም፡፡

ሀትሪክ፡- በግብ ጠባቂነቱ የተካበተ የጨዋታ ልምድ አለህ፤ ይሄን ለሌሎች ወጣት ተጨዋቾች የማካፈል ልምድ አለህ

ይድነቃቸው፡- አዎ! በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ደረጃ ስጫወት ያለኝን የጨዋታ ልምድ ሁሌም አካፍላለው፤ ምክንያቱም እኔም የመጣሁበት እና ያደግኩበት መንገድ አለና፤ ለብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ስጠራ ይመክረኝና ልምዱንም ያካፍለኝ የነበረው ታዲዎስ ጌታቸው ነው፤ ታዲዎስ ያኔ ትልቅ በረኛ ነበር፤ ጠንክረህ ስራ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርሳለህም ይለኝ ነበር፤ እሱን ሳላውቀው ነው ጥሩ ምክርና ፍቅርም ይለግሰኝ የነበረው፤ ከዛም ተነስቼ ነው እንግዲህ እኔም በምጫወትባቸው ክለቦች ስለጠንክሮ መስራት፣ ስለትዕግስት ማድረግ፣ በተለይ ደግሞ በረኛ ስትሆን ከሌሎች የሜዳ ላይ ተጨዋቾች አንፃር በተደጋጋሚ ጊዜ ለረጅም ጊዜያት ተሰልፈህ ልትጫወት ስለማትችል እነዚህን የመሳሰሉ ልምዶቼንም ነው ለእነሱ የማካፍላቸው፤ ያኔ እነሱም የሚሰማቸው ጥሩ የሆነ ስሜትም እንዳለ ተመልክቻለው፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 የእግር ኳሳችን ተሰርዟል፤ ለአራት ወራት ያህልም ከሜዳ ተርቋል፤ ይሄን ስትመለከት ምን አልክ? ጊዜህንስ በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው

ይድነቃቸው፡- ኮቪድ በዓለም ጭምር ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የመጣ ወረርሽኝ ነው፤ ወደ እኛ ሀገር ገብቶም ኳሱ በቆመ ሰዓት ነገሮች ሁሉ ለእኛ እግር ኳስ ተጨዋቾች ከባድ ነው የሆነብን፤ በኳሱ መቆም በአህምሮም ሆነ በአካል ደረጃ ልንጎዳ ችለናል፤ ያም ሆኖ ግን ይሄ ወረርሽኝ ክፉና ምንም ነገርንም ማድረግ እንዳንችል ስላደረገን የአሁን ሰዓት ላይ ይሄ ወረርሽኝ እስኪጠፋ ድረስ በየቤታችን ሆነን ልምምዳችንን እየሰራን ይገኛል፤ እኔም በዛ መልኩ ነው የራሴን እና የቤተሰቦቼንም ጤንነት እየጠበቅኩ ወቅቱን በስፖርት እንቅስቃሴዎች እያሳለፍኩ የምገኘው፡፡ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የኳሱ መቆም ጉዳት ያለው ቢሆንም በአንድ በኩል ደግሞ የእግር ኳሱ በመቆሙ እና በቤትህ ውስጥ ማሳለፉን ስትመለከተው ለቤተሰቤ ሰፊ ጊዜን መስጠትን አግኝቼበታለሁ፤ አንድ አንዴ ነገሮችን ለክፉ ብቻ መውሰድ የለብህም፤ በጎ ነገሮችንም ይዞ የመጣበት ነገር አለ፤ አስተማሪነቱ እንዳለ ሆኖ በቻልከው አቅም እንቅስቃሴ ማድረግ መልካም ነው፤ ፈጣሪም ሁሉንም ነገር ሠላም አድርጎልን ወደምንወደው ስፖርታችን እንድንመለስም ይርዳንም ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

ይድነቃቸው፡- በእግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመኔ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ቅድሚያ አምላኬ የሆነውን የድንግል ማሪያም ልጅን መድሃኒዓለምን አመሰግናለው፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ያደረገችልኝን እናቴንና ለሁላችንም የኳስ መሰረት የሆነልንን ወንድሜን በምስጋና አስቀጥላለው፤ ሌላዋ ምርጥ ተጠቃሽ ደግሞ ባለቤቴና የሶስት ልጆቼ እናት የሆነችው እኔ እናትዬ ነው የምላት ሰላማዊት መብራቴን አመሰግናለው፤ የምወዳቸው ልጆቼም እኔን በሚመለከቱኝ ሰዓት ብራቮ አባቢ ብለውም ብርታትን ስለሚሰጡኝም እነሱንም እንደምወዳቸውና እንደማመሰግናቸው ልናገር እፈልጋለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website