“ለሶስተኛ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ስለማንሳት እያለምኩ ነው”ዮናስ ገረመው /መቐለ 70 እንደርታ/

ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ መቐለ 70 እንደርታ በአማካይ ስፍራ የሚጫወተው ዮናስ ገረመው /ሀላባ/ ክለባቸው የመጪው ዘመን ውድድርንም ዳግመኛ በድል እንደሚወጣ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታው ዮናስ በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎው ሁለት ጊዜ የድሉን ዋንጫ ከጅማ አባጅፋር እና ከአሁኑ ክለቡ መቐለ ጋር ያነሳ ሲሆን በሁለቱም ክለብ ቆይታው ስኬታማ ብቃቱንም በሜዳ ላይ ለማሳየት ችሏል፤ ከእዚህ በመቐለ70 እንደርታ የውል ዘመኑን አራዝሞ ከቀጠለው ተጨዋች ጋር ሀትሪክ ስፖርት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስታለት እሱም ምላሹን በተገቢው መልኩ ሰጥቷል፤ ቃለ-ምልልሱም አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል፡፡

ሀትሪክ፡- በመቐለ 70 እንደርታ ውልህን አራዝመሃል፤ ክለቡ ተመቸህ ማለት ነው?

ዮናስ፡- አዎን፤ መቀለ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍኩበት ቡድን ነው፤ የሊጉን ዋንጫም አግኝቼበታለው፡፡ ከዛ በነሳት በመጪው የውድድር ዘመንም ከዚሁ ቡድን ጋር መልካምና የስኬት ጊዜን ዳግም አሳልፋለው ብዬ ስላሰብኩ ውሌን ላራዝም በቅቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ምርጥ ጊዜን ነበር ያሰለፈው ማለት ይቻላል?

ዮናስ፡- የውድድር ዓመቱ ሲጀመር ጥሩ አልነበርንም፤ በመዘናጋት ተደጋጋሚ ነጥቦችንም እንጥል ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻልን በማሳየታችን ውጤታማ ሆነን መጣንና ተመልሰን ጠንካራ እና ውጤታማ ቡድን መሆናችንን ዳግም ልናስመሰክር ችለናልና ዘንድሮ ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 እስከገባ ድረስ የሊጉን መሪ ፋሲል ከተማን ስትከተሉ ነበር፤ ውድድሩ ባይሰረዝ ኖሮ እናንተን በመጨረሻ በምን ደረጃ ላይ እናገኛችሁ ነበር?

ዮናስ፡- በሻምፒዮናነት ነዋ! ምክንያቱም ክለባችን እየተሸሻለ ነበር የመጣው፤ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር የነበረን የነጥብ ልዩነትም በጣም የጠበበ ስለነበር እና ካለን ጥንካሬ አንፃርም ከነበሩት ቀሪ ጨዋታዎች አኳያ የዓምናውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ድል ዘንድሮም እንደግመው ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜ አንስተሃል፤ ሶስተኛው ዋንጫስ አልናፈቀህም?

ዮናስ፡- በጣም ናፍቆኛል፤ በተጨዋችነት ዘመንህ ለእዚህ ድል መብቃት መቻል መታደል ነው፤ ስለዚህም ሶስተኛውን ዋንጫ ስለማንሳት ከወዲሁ እያለምኩ ነው፤ ይህንንም ድል ከክለቤ መቐለ 70 እንደርታ ጋርአሳካዋለሁኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪምየር ሊጉ ለሀላባ ከተማ፣ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለድሬዳዋ ከተማ፣ ለጅማ አባጅፋር እና ለመቐለ 70 እንደርታ ክለቦች ለመጫወት ችለሃል፤ ምርጡ ጊዜ ለአንተ የቱ ነው?

ዮናስ፡- የእግር ኳሱ ምርጥ ጊዜዬ ብዬ የምጠቅሳቸው በስኬታማነት ያሳለፍኩባቸውን ነው፤ ለጅማ አባ ጅፋር እና ለመቀለ ስጫወት የሀገሪቱን ትልቅ ዋንጫን ስላነሳው እነዛ አይረሴ ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ስለመጫወት ምን ትላለህ?

ዮናስ፡- ያ የሁልጊዜም እልሜ ነው፤ ለብሔራዊ ቡድን መጫወትን እንደማን ኛውም ተጨዋች እፈልጋለው፤ ያም ሆኖ ግን የመመረጥ እድሉ ወደ አንተ እስካልመጣ ድረስ ነገሮችን በትዕግስት ነው መጠበቅ የሚያስፈልግህ፤ ለብሔራዊ ቡድን አልተመረጥኩም ብለህም ሳትቆጭ ሁሌም ነው ጠንክረህ እየሰራ በመምጣት ለመመረጥም ከፍተኛ ጥረትን ማድረግ ያለብህና ከእዚህ በመነሳት ለብሔራዊ ቡድን በቀጣዩ ጊዜ ለመመረጥ እንደምችል ተስፋን አደርጋለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ከእግር ኳሱ ለረጅም ወራቶች ስትርቅ ምንድን ነው የተሰማህ?

ዮናስ፡ ከኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ መራቅ አይደለም ለእኛ ተጨዋቾች ኳስን ለሚወድ ሰው በጣም ከባድ ነው፤ አልተጫወትክም ማለት ያለ ስራ ተቀመጥክ ማለት ነውና በፈጣሪ እርዳታ እና ራሳችንንም ከእዚህ ወረርሽኝ በምንጠብቅበት ሁኔታ ላይ ሆነን ወደምንወደው የእግር ኳሳችን እንድንመለስ ነው ምኞቴ፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 በኋላ ጊዜውን የትና በምን መልኩ ነው እያሳለፍክ የምት ገኘው?

ዮናስ፡- ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የማሳልፈው፤ የምኖረውም አዲስ አበባ ነው፤ በግሌ የስፖርት እንቅስቃሴዎችንም በመስራት ላይ ነው ያለሁት፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website