“ለምን ለብሄራዊ ቡድን አልተመረጥኩም የሚል ምንም ስሜት የለኝም ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው” ፍቅሩ ወዴሳ

🔑 ለኔ አርአያዬ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሀኑ ነው

🔑እግዚአብሄር የኮሮና ወረርሺኝ በሽታ እንዲያጠፋልን በጋራ እንፀልይ።

🔑ለምን ለብሄራዊ ቡድን አልተመረጥኩም የሚል ምንም ስሜት የለኝም ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው


ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ባዕድ ያደረገው የሀገራችን ሊግ በራሳቸው ጥረት ወደ ሊጉ ብቅ በማለት ድንቅ ብቃታቸውን እያስመለከቱን ከሚገኙ ግብ ጠባቂዎች መሀከል አንዱ የሆነው የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ በዘንድሮው አመት በ7 ጨዋታዎች በመሰለፍ 6 ግቦችን ብቻ አስተናግዶ በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ማዳን ችሏል። ግብ ጠባቂው ስለ እግር ኳስ ሂወቱ እና ስለ ኮሮና ቫይረስ ከሀትሪክ ስፖርት ጋር በነበረው ሰፋ ያለ ቆይታ አቅርበንላችኋል።

ፍቅሩ ወዴሳ ስለ እግር ኳስ ሂወቱ እና ስለኮሮና ቫይረስ መልክት አስተላልፏል!!!


ስለ ትውልድህ እና የእግር ኳስ አጀማመር ሂወትህ ብታወራኝ በቅድሚያ

ተወልጄ ያደኩት ሀዋሳ አላሙራ ሰፈር በሚባለው አካባቢ ነው። እግር ኳስን የጀመርኩት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰፈር ውስጥ ነው። ቤተ ክህነት ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት እየተማርኩ በነበረበት ስዓት እዛው ኳስ እጫወት ስለነበር አሁን ላለሁበት የእግር ኳስ ሂወቴ መሰረት የጣልኩበት ብሎም አሁን ላለኝ የእግር ኳስ ሂወት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገልኝ ነው። በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመርኩት 2004 ለደቡብ ፖሊስ ነበር። ከዛ 2006 ላይ ወደ ሲዳማ ቡና መጥቼ በመጫወት ላይ እገኛለው።

በየጨዋታዎች የምታደርጋቸው ምርጥ እንቅስቃሴ ከየት የመጡ ናቸው

ያው እንደምታቂው ለሲዳማ ቡና መጫወት የጀመርኩት ከ2008 ከሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ ነው። ከዛ ግዜ አንስቶ በርካታ ጨዋታዎችን አድርጊያለው። በዚህው አመት በሁለተኛው አጋማሽ በ13 ጨዋታ 5 ግቦች ብቻ ነበር የተቆጠሩብኝ። ይህ ደግሞ ጠንክሮ ከመስራት የመነጨ ነው። በተጨማሪም ደግሞ የቡድን አጋሮቼ ስለሚረዱኝ ብዙ ግቦች እንዳይቆጠሩብኝ ምክንያት ነው ለዚህም ላመሰግናቸው እወዳለው። ጠንክሬ በመስራት ከዚህ በተጨማሪ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደማደርግ አስባለው።

የሀገር ውስጥ ብቻ ግብ ጠባቂዎችን ብቻ ከሚጠቀሙት ክለቦች መካከል አንዱ ሲዳማ ቡና ነው እስኪ ስለ ክለቡ ያለህ ነገር ?

ሲዳማ ቡና እጅግ በጣም የምወደው እና የማከብረው ክለብ ነው። የክለቡን አመራሮችንም ላመሰግን ወዳለው ምክንያቱም ከአቅማቸው በላይ ካልሆነ  የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ማምጣት አይፈልጉም። እኛ እንድንለዎጥ፤እድሉን እንድናገኝ ብሎም ከዚህ የተሻለ ደረጃ እንድንደርስ ነው ሚፈልጉት ከማንም በላይም እንደምንችል ይነግሩናል በሀገር ውስጥ ተጫዋች ከፍተኛ እምነት ስላላቸው አመራሮቹ ከምንም በላይ ሊመሰገኑ ይገባል።

እግዚአብሔር ፈቅዶ ሊጉ ቢጀምር አምና በአንድ ነጥብ ያጣችሁትን ዋንጫ ለማሳካት ምን አስበሀል

እኛ እንደክለብ ሊጉ ሲጀምር ዋንጫ ለማንሳት ነው እቅዳችን። ሌሎችም ክለቦች እንደዛው ነገር ግን እኛ መቶ በመቶ ለዋንጫ ነው እምንጫወተው። ከዚህ ቀደም የነበሩን ደረጃዎቻችን ሲዳማ ቡና ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን መሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ዘንድሮ አይምሮዬ ውስጥ ያለው ዋንጫውን እንዴት ነው ምናነሳው የሚለው ነገር ነው፤ አምና በሚያስቆጭ ሁኔታ ያጣናውን ዋንጫ በመጀመሪያው ዙር የነበሩብንን ስህተቶች አርመን በሁለተኛው ዙር እግዚአብሔር ክፉውን በሽታ አስወግዶልን ሊጉ ጀምሮ ዋንጫውን እንደምናሳካው እርግጠኛ ነኝ።

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለተጫዋቾች ጥሪ ተደርጓል መመረጥ ነበረብኝ ብለህ ታስባለህ ?

ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፤ ውሳኔውን ደግሞ ግዴታ ልናከብር ይገባል። ምክንያቱም ያመነበትን ተጫዋች ነው እሚመርጠው። ከዛ በተጨማሪ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራህቱ አሁን ላይ ጥሩ ስራ እየሰራ ነው ሊመሰገኑ እና ሊበረታቱ የገባል ለምን ቢባል የአገራችን እግር ኳስ አንድ እርምጃ ከፍ እንዲል እየጣሩ ነው። ለምን ለብሄራዊ ቡድን አልተመረጥኩም የሚል ምንም ስሜት የለኝም ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው። አንድ መናገር የምፈልገው ነገር ግን ዘንድሮ ባልመረጥም ለቀጣይ ግን ያሉብኝን ድክመቶች አሻሽየ ለብሄራዊ ቡድንም ሆነ ለክለብ ለረጅም አመታት ቋሚ ተሰላፊ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ። እዛ እንድንደርስ ግን እግዚአብሄር የኮሮና ወረርሺኝ በሽታ እንዲያጠፋልን በጋራ እንፀልይ።

አርአያ እና የምታደንቀው ግብ ጠባቂ ማነው ?

(ሳቅ እያለ) ለዚህ ጥያቄ እድሉን ስለሰጠሺኝ አመሰግናለው። ከሀገር ውስጥ እኔ እማደንቀውም አርአያየ ነው እምለው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሀኑ ነው፤ለምን ብትይኝ ለአለም ትልቅ ስብእና ያለው ግብ ጠባቂ ነው። ለእኔ እሱ ግብ ጠባቂ ብቻ አይደለም አባትም ጭምር እንጂ። ከሱ ቀጥሎ በሀገራችን መጥተው ከተጫወቱ ግብ ጠባቂዎች የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ እና የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራ አድናቂ ነኝ። ከባህር ማዶ ደግሞ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ የነበረው ኤዱዊን ቫንደር ሰን አድናቂ ነኝ።

 

ለእኔ በእግር ኳስ ህይወቴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው የምትላቸውን አሰልጣኞች እነማን ናቸው

እኔ እዚህ ስደርስ በበርካታ አሰልጣኞች አልፊያለው፤ሁሉም ለኔ በጣም ጎበዞች እና ስብእና ያላቸው አሰልጣኞች ናቸው። ከልጅነቴ ጀምሮ ጥሩ ስነምግባር ይዤ እንዳድግ ያደረገኝ የአሁኑ የሲዳማ ቡና ረዳት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ነው፤ያሬድ እኔን ብቻ ሳይሆን በርካታ ተጫዋቾችን ማሳደግ የቻለ ጎበዝ አሰልጣኝ ነው። ማመስገን ስላለብኝ ሳይሆን እንደ አባት ሆኖ ነው ያሳደገኝ ለአሁን ደረጃየም መሰረት ያሲያዘኝ እሱ ነው። በፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ግዜ እንድጫወት ያደረገኝ አሰልጣኝ ቾምቤ ገብረህይወት እጅግ በጣም ላመሰግነው እፈልጋለው። ምክንያቱም በወቅቱ በኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ብዙም እምነት አልነበረም እሱ ግን ኃላፊነቱን ወስዶ በርካታ ጨዋታዎችን እንድጫወት አድርጎኛል ሁሉም ማድረግ ያለባቸው በተጫዋቾቻቸው ማመን ነው። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጎበዝ አሰልጣኝ ነው ብዙ እገዛ አድርጎልኛል በሁሉም ነገር ሜዳ ላይ ቆራጥ እንዲሆን አስችሎኛል። በተጨማሪም የአሁኑ አሰልጣኜን ዘርዓይ ሙሉን ያለኝን ችሎታ አውጥቼ እንድጠቀም ስለሚያደርገኝ ማመስገን እፈልጋለው።

የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በምን ትገልፃቸዋለህ

የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በጣም እወዳቹሀለው በዚሁ ቀጥሉ። በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ ያላቹህ ስነስርአት ሳላደንቅ አላልፍም። ከምንም በላይ ደግሞ ማንም ያሸንፍ ማን ውጤት በፀጋ ስለምትቀበሉ ላመሰግናቹህ እፈልጋለው።  አሁንም ከጎናችን ሁኑ ከዚህ በኋላም በርካታ ነገሮችን ከእናንተ እንጠብቃለን እላለሁ። እኛም በቀሩት 13 ጨዋታዎች እስከመጨረሻው ድረስ የምንችለውን አድርገን ዋንጫውን ለማንሳት እንጥራለን።

ስለ ኮሮና ቫይረስ ለህዝባችን እምታስተላልፈው መልእክት

ስለ ቫይረሱ የኛ ህዝብ ብዙ ግንዛቤ አለው ብየ አላስብም። መንግስት ደግሞ ህዝቡን ለማስተማር ከፍተኛ ጥሩት እያደረገ ነው እሚገኘው። እኛም ደግሞ ከአውሮፓ ሀገራት መማር አለብን። እኔ ለሀገራችን ህዝቦች ማስተላልፈው ጥንቃቄ አድርጉ፣በስነስርአት እጃቹህን በሳሙና ታጠቡ ውድ ያገሬ ህዝብ ሆይ በጣም እወዳቹሀለው በተለይ ከ40 አመት በላይ ያላቹህ ሰዎች ተጠንቀቁ ምክንያቱም በእናንተ ምክር እና ፀሎት ነው ሀገር የምትኖረው አብዛታቹህ ፀልዩ ጥንቃቄን አትዘንጉ።

በስተመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገው ካለ እድሉን ልስጥህ

በመጀመሪያ እዚህ ላደረሰኝ እግዚአብሄርን አመሰግናለው ከዛ በመቀጠል ወላጆቼን እና እዚህ እንድደርስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉልኝ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ማመስገን እፈልጋለው።