ለሐዋሳ ከተማ ፊርማዬን አኑሬያለው፤ አለአግባብ የጠፋውን ስሜንም ዳግም አድሰዋለሁ” ኤፍሬም ዘካሪያስ /ሀዋሳ ከተማ/

በወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ የነበረውን የዘንድሮው የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውን በማጠናቀቅ ትናንት ለሐዋሳ ከተማ ፊርማውን ያኖረው ኤፍሬም ዘካሪያስ በአዲሱ የውድድር ዘመን በጣም ምርጥ የሆነ ብቃቱን በሜዳ ላይ ለማሳየትና ሐዋሳ ከተማንም ለድል ለማብቃት መዘጋጀቱን እየተናገረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ተሳትፎው ላይ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው እና አበረታች የሚባል እንቅስቃሴንም በሜዳ ላይ ለማሳየት የቻለው ይኸው ተጨዋች የውል ዘመኑን ካጠናቀቀበት ከወልቂጤ ከተማ ወደ ሐዋሳ ከተማ ሊዘዋወር ስለቻለበት እና ከራሴ የኳስ ህይወት ጋር በተያያዘ አናግረነው ምላሹን ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡


ስለ ትውልድ ሀገሩ መተሐራ

“መተሐራ እንደ አንድ ቤተሰብ የምትገለፅ እና የፍቅር ሀገር ናት፤ ሰዎች ተሳስበው እና ተዋደውም የሚኖሩባት ምርጥ ሀገርም ናትና ለእዚህች እኔን ላፈራች ከተማ ልዩ አክብሮት እና ምስጋና ነው ያለኝ”፡፡

ስለ ልጅነት ጓደኛው

“የልጅነት ጓደኞቼ አብረውኝ በሰፈር ደረጃ ኳስን የተጫወቱ እና አብረውኝም ያደጉ ናቸው፤ ከእነዛም መካከል ስንታየሁ አያሌው እና ካሳዬ በቀለ የሚባሉ አሉ፤ ወደ ክለብ ማለትም ወደ መተሐራ ስኳር ቢ ቡድን ከገባው በኋላ ደግሞ የእኔ ጓደኛ የነበረው ብሩክ ቃልቦሬ ነው፤ ከእሱ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም እንኳን እኔ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ባመራሁበት ሰዓት እና እሱ ወደ ወላይታ ድቻ ሲገባ ብንለያይም መልሰን በአዳማ ከተማ ቡድን ውስጥ ጓደኛምነታችን ቀጥሎ አሁንም ድረስ አብሮ እንዳለ ነው፤ በተለይ ከብሩክ ጋር በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ የነበረን ቆይታ የማይረሳ ነው”፡፡
በተማሪነት ዘመኑ ስለሚከብደው እና ስለሚቀለው ትምህርት
“ከትምህርት የሚከብደኝ ፊዚክስ ነበር፤ ሊከብደኝ የቻለበት ዋናው ምክንያትም ያኔ ለኳስ እንጂ ለትምህርቴ ብዙም ትኩረትን የምሰጥ አይነት ሰው ስላልነበርኩኝ ነው፤ የሚቀለኝ ትምህርት ደግሞ የራሳችን ቋንቋ አይደል አማርኛ ነው”፡፡

ስለ ትምህርት ጉዞው

“የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ ትምህርቴን ተምሬ ያጠናቀቅኩት በቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት ነው፤ በእዚህ የሙያ ቆይታዬም በጄኔራል ሜካኒክ ልመረቅም በቅቻለሁ”፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ

“በጄኔራል ሜካኒክነት ሙያ ተምሬ እና ተመርቄ አይደል፤ ስለዚህም በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ግቢ ውስጥ የድርጅቱ ሜካኒክ ሰራተኛ ሆኜ እሰራ ነበር”፡፡

በተማሪነት ዘመንህ ስላጋጠመህ ቁጡ መምህር

“በኤለመንተሪ ደረጃ ስማር ቲቸር መካሻ ነበሩ፤ ሀይስኩል ስገባ ደግሞ የስፖርት አስተማሪያችን የነበሩትና ብዙ ጊዜም ከአዳማ ስታድየም የማይጠፉት አቶ አለማየሁ ናቸው ቁጡ፤ እሳቸው በተለይ ተማሪው ሁሉ ጥሩ እንዲሆን ስለሚፈልጉ ነበር ይቆጡን ጭምር የነበሩትና ሲያባርሩንም እንሯሯጥም የነበርነውና ያኔ ሁሉም ይፈራቸውም ነበር”፡፡

በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላው ለውጥን ስለማድረጉ

“የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ ለመተሐራ ስኳር፣ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለሐዋሳ ከተማ፣ ለአዳማ ከተማ እና ለወልቂጤ ከተማ ቡድኖች ለመጫወት ችያለሁ፤ በእነዚህ ቡድኖች ቆይታዬም ለቡና ለአራት ዓመታት በመጫወት የረጅም ጊዜ ቆይታንና የተረጋጋ ጥሩ የኳስ ጊዜንም አሳልፌያለው፤ በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥም ጥሩ የኳስ ጊዜው ነበረኝ፤ በእንደዚህ መልኩ የኳስ ተጨዋችነት ጉዞዬን ከክለብ ወደ ክለብ ላደርግ ብችልም በእዚህ መንገድ የሄድኩበት ዋናው ምክንያት የተለየ ጥቅምን ላገኝ ስለቻልኩኝ ነው”፡፡

ለወልቂጤ ከተማ ውልህን ካራዘምክ በኋላ በአሁን ሰዓት ወደ ሐዋሳ ከተማ ያመራኸውስ በጥቅም ነው…?

“አይደለም፤ የወልቂጤ ከተማ ክለብ ውስጥ የነበረኝ የእዚህ ዓመት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ጥሩ የሚባል ነው፤ የቡድኑ ሰዎችም እኔን ከክለቡ ጋር እንድቀጥል በመፈለግ አናግረውኝ ውሌን አራዝሜም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የቀድሞ ክለቤ ሐዋሳ ከተማ እኔን በጥብቅ የፈለገኝ ሁኔታ በመፈጠሩና ለቡድኑም ለመጫወት ብችል ለእኔ ነገሮች ሁሉ ጥሩ ይሆኑልኛል ብዬ ስላሰብኩ ነው፤ ወደ ሐዋሳ ከተማ ያመራሁት፤ ወልቂጤን ከጥቅም ጋር በተያያዘ አለቀቅኩም፤ ቡድኑ ጥሩ ወቅትን ያሳለፍኩበት ቡድን ነው፤ አመራሮቹን በተለይ ደግሞ በክለቡ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ አቶ አበባውን በጣሙን ላመሰግናቸውም እወዳለውኝ፤ ስለዚህም ወደ ሐዋሳ ከተማ ለማምራቴ ምክንያት የሆነኝ ነገር ከላይ የተቀስኩትና የሐዋሳ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትም የእኔን በሜዳ ላይ ያለኝን ችሎታ እና አቅምን በሚገባ የሚያውቅ በመሆኑና በእሱም መሰልጠንን ስለፈለግኩ ከዚህ ቀደም ደግሞ በቡድኑ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እኛና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ባደረግነው ጨዋታ ላይ እኔ በግጥሚያው ባልተሰለፍኩበት ሁኔታ ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በአንድአንድ ሰዎች አለህበት ተብዬ አለአግባብ ስሜ ጠፍቶ ስለነበርና በኋላ ላይ ደግሞ ነፃ መሆኔም ተረጋግጦልኝ በሁሉም ዘንድ በመረጋገጡ ይሄ ቡድን ጥሪውን ሲያቀርብልኝ አይኔን ሳላሽ ነው የተቀበልኩት፤ ምክንያቱም የሐዋሳ ከተማ አመራራሮችም ሆኑ ህዝቡ እንደዚሁም ደግሞ ኮቺንግ ስታፉም የእኔን ንፁ ተጨዋች መሆኔን አረጋግጠው ወደ ቡድኑ እንድመጣ ስላደረጉኝም በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ስለዚህም በዚህ ቡድን የቀጣይ ጊዜ ቆይታዬ ከእዚህ በፊት ስሜ ጠፍቶ ስለነበር ያ አለአግባብ የጠፋውን ስሜም ዳግም በመመለስ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ”፡፡

በእግር ኳስ ህይወቱ ደስተኛ ስለመሆኑ

“አዎን፤ የምፈልገው ደረጃ እና ቦታ ላይ ባልደርስም እስካሁን ደስተኛ ነኝ፤ በኳሱ ምንአልባት ተከፍቻለው ብዬ የማስበው በሐዋሳ ከተማ ቆይታዬ ከላይ እንደገለፅኩትም ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር አለአግባብ ስሜ እንዲጠፋ የተደረገበትን ጊዜ ብቻ ነውና ፈጣሪ ግን እውነቱን አውጥቶ እኔን ነፃ ስላደረገኝ ለእሱ ከፍተኛ ክብርና ምስጋናን አቀርብለታለው፤ በኳስ ዘመኔ ሌላው የተከፋሁበት ወቅት ቢኖር የምጫወትበትን ቡድን ሽንፈት ሲያጋጥመው ብዙ ጊዜ ይከፋኛል፤ ስሜቴም ወዲያው ይለዋወጣል”፡፡

በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ መድረስ ስለሚፈልግበት ቦታ

“ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወት ነው የቅድሚያ ፍላጎቴ፤ ይሄን እስካሁን አለማሳካቴ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹንም ይቆጫቸዋል፤ በተለይ የእኔን ችሎታ እና አቅም የሚያውቁ አሰልጥነውኝ ያለፉ ባለሙያተኞች እና ጓደኞቼም አሁንም ድረስ በምንም ነገር ተስፋ እንዳትቆርጥ ጠንክረህ ስራም ስለሚሉኝ ያን ዕድል ለማግኘት ጥረትን እያደረግኩኝ ነው”፡፡

የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ተምሳሌቱ ስላደረገው ተጨዋች

“በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ የእኔ አርአያ ወይንም ደግሞ ሞዴሌ የሆነው ተጨዋች ሰለሞን ገብረ መድህን ነው፤ እሱ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የመተሐራ ከተማ እግር ኳስ ተጨዋቾችም ምልክት የሆነ ተጨዋች ነው፤ አጨዋወቱ ሁሌም ያዝናናል፤ የእሱን የአጨዋወት ስታይልም ለመውረስ የሚፈልጉም ነበሩና በአጠቃላይ እሱ ለሀገሩ ባህል የሆነ አይነት ተጨዋች ነው”፡፡

በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ስላሳካው ትልቅ ድል

“በትልቅነቱ የምጠቅሰው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያገኘሁትን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ድልን ነው፤ ከዛ ውጪ ከቡና ጋር እና ከአዳማ ከተማ ጋር ሆኜ ሊጉን በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ ያጠናቀቅኩበት ወቅት አለና እነዚህ የማይረሱ ናቸው”፡፡

የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ስለመቻል

ይሄን ዋንጫ እስካሁን ስላላነሳሁት በጣም ናፍቆኛል፤ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ልታነሳ የምትችልበት ሁኔታ ደግሞ ያለህ ቡድን ይወስነዋል፤ ዋንጫውን ለማግኘት ጥሩ ሜንታሊቲ ያላቸው ተጨዋቾች ያስፈልጉሃል፤ ስለዚህ ፈጣሪ ካለ በድጋሚ ከተቀላቀልኩበት እንደዚሁም ደግሞ ጠንካራ እና ወጣት የሆኑ ተጨዋቾችንም ከያዘው ሐዋሳ ከተማ ጋር ይህን እልሜን ለማሳካት የምጥር ይሆናል፤ አንድ ቀንም ይህ የድል እልሜ ይሳካል”፡፡

የእሱ ምርጥ ተጨዋች

“ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያው ከመተሐራ ስኳር ወጣት ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ድረስ አብሬው በማደግ የተጫወትኩት ብሩክ ቃልቦሬ ሲሆን ሌላው ደግሞ እንደ ብሩክ ሁሉ ከጎኑ በኢትዮጵያ ቡና ቡድን የተጨዋችነት ዘመኔ አብሬው የተጫወትኩት እና አሁንም ጓደኛዬ የሆነው ዳዊት እስጢፋኖስ ነው

ከባህር ማዶ ስለሚያደንቀው እግር ኳስ ተጨዋች እና ስለሚደግፈው ቡድን

“የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፤ ዋይኒ ሩኒን ደግሞ ከተጨዋቾች በጣም አደንቀዋለውኝ”፡፡

የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ብትሆንም ስለ ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት መቻል

“ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው በፊት ቢሆን ኖሮ ከጓደኞቼ ጋር እበሻሸቅ ስለነበር በጣም እናደድ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ከድጋፍ የወጣው እና ኳስንም በጥልቀት የምመለከት አይነት ተጨዋች ስለሆንኩኝ የሊቨርፑል ድል የሚገባው ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ የሊቨርፑልን ጨዋታ በደንብ ተከታትዬዋለው፤ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጥሩ እና ጠንካራ ቡድን ነው የሰራውና የሚመች አይነትን ጨዋታም ነው ልመለከት የቻልኩት”፡፡

ኮቪድ 19 እና ወቅቱን በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ

“ኮቪድ እጅግ አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑን አሁንም ቀጥሏል፤ ለእዚህ በምንም መልኩ ሳንዘናጋ ጥንቃቄያችንን አጠናክረን ልንቀጥልበት ይገባናል፤ ይህን ካልኩ እኔ ኮቪድ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ወቅት እያሳለፍኩ ያለሁት ፈጣሪ በጣም ከምወዳት ባለቤቴ አንድ ልጅ በቅርቡ ስለሰጠኝ ከእሷ እና ከልጄ ኤማሪያ ጋር ሆኜ በቤት ውስጥ ነው፤ ከዛ ሌላም በሞባይሌ አፕሊኬሽን ላይ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን የሚገልፁ ልምምዶች ስላሉም እነሱንም እየሰራሁኝ ነው”፡፡

ስለ ባለቤቱ እና ስለ ትዳር ህይወቱ

“የትዳር ህይወቴ በጣም ጥሩ ነው፤ ምርጥ ሚስትም አለችኝ፤ እሷ ማለት በእግር ኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ በብዙ ነገሮች ያገዘችኝ እና ሁሌም ቢሆን ከጎኔ ያለችም ናት፤ ያለ እሷ እዚህ ደረጃ ላይ አልደርስም ነበርና በእዚሁ አጋጣሚ ጠንካራዋን ባለቤቴን ሊዲያ ገዛኺን ለማመስገን እፈልጋለሁ፤ ባለቤቴን ሌላ የምገልፅበት ሁኔታ እሷ ማለት በቃ የህይወቴ የላይኛው ምዕራፍም ናት”፡፡

ለሐዋሳ ከተማ ፊርማህን አኑረሃል፤ ከዚህ በኋላስ ወደ ሌላ ቡድን ታመራ ይሆን?

“በፍፁም አላደርገውም፤ ይሄ የመጨረሻዬ ውሳኔ ነው፤ የቀድሞ ክለቤ እኔን እንድጫወትለት ፈልጎ ወስዶኛል፤ አሰልጣኙም በእሱ ስር እንድሰለጥን ከፍተኛ ፍላጎቱ ስለሆነ ጥሪውን ሲያቀርብልኝ ወዲያው ነው የራሴን ችሎታ አሳይቼ ውጤታማ ተጨዋች መሆንን ስለምፈልግ በወጣቶች ለተገነባው እና ጠንካራም ለሆነው ለሐዋሳ ከተማ ዳግም ለመጫወት ፍላጎትን ያሳደርኩት”፡፡

በመጨረሻ

‘”የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ላይ ከእኔ ጎን የነበሩትን ሁሉ አመሰግናለው፤ ይህን ካልኩ አሁን ላይ ለዓለምም ሆነ ለአገራችን ከፍተኛ ስጋት የሆነብንን ኮሮና ቫይረስን ፈጣሪ አጥፍቶልን ወደምንደው ኳስችን እንድንመለስ ምኞቴ ነው፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team