“ሆቴሎቼን ያወደሙ ሶስት ዕዳ አለባቸው የኃይሌ ላብ፣ የኃይሌ ደምና የኃይሌ እንባ” ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ

መንግስት ሊከፍለኝ ይገባል፤… ሆቴሎቼን የገነባሁት ላቤንና ደሜን አፍስሼ ነው”

“ሆቴሎቼን ያወደሙ ሶስት ዕዳ አለባቸው የኃይሌ ላብ፣ የኃይሌ ደምና የኃይሌ እንባ”
ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ

እርግጥም ሰውዬው ቀደም ሲል እንደተሠራለት “ፅናት” (Endurance) እንደሚ ባለው የግል ታሪኩን እንደሚ ያጠነጥነው ፊልም በጥንካሬው ፀንቶ የቆመ ሰው ነው፤ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞበትም ፊቱ ላይ የመረበሽ ስሜት አለማየቴ በጥንካሬው የስኬቱን ቁልፍ የጨበጠው ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ስላሴን የማደንቅበት ቃላት አጥቻለሁ፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ ብቅ የሚለው ቁጭቱ ከውስጡ እየተብሰለሰለ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ ቢያጭርብኝም ከእሱ ይልቅ የተበተኑት ሠራተኞቹና የቤተሰቦቻቸው ህይወት በጣም ያሳስበኛል ማለቱ እንዳከብረው አድርጎኛል፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ ሁለት ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴሎች ላይ ጉዳት የደረሰበት አትሌትና ከፍተኛ የቢዝነስ ሰው የሆነው ኃይሌ ገ/ስላሴ ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም ውስጡም ባልተረጋጋበት ሁኔታ ጊዜውን ተሻምቶ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ደርሶብህ እንደሰው ቆመህ እየሄድክ ነው? በደረሰብህ ነገርስ በመማረር ምነው ከዚህ ሁሉ ይሄን ሀገር ጥዬ ልብረርስ አላሰኘህም? ሲል ውጤታማውን ግን ደግሞ በጣም ጠንካራውን ሰው በደረሰበት ጉዳት ዙሪያ አናግሮት እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ሀትሪክ፡- ኃይሌ በመጀመሪያ በአንተም በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ንብረት ላይ በደረሰው ውድመትና ጉዳት እንዲሁም ህልፈተ ህይወት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ እወዳለሁ…

ኃይሌ፡- …. በጣም አመሰግናለሁ…

ሀትሪክ፡- በሁለቱም ሆቴሎችህ ላይ የደረሰው ውድመት ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ እስቲ በሻሸመኔና በዝዋይ ባሉት ሆቴሎች ላይ የደረሰውን ከአንተ አንደበት ልስማው?

ኃይሌ፡-ምን ከእኔ ትሰማለህ ተብሎ… ተብሎ አልቋል፤ ሻሸመኔና ዝዋይ በሚገኙ ሁለት ባለ ሶስት ኮኮብ ሆቴሎች ላይ ነው ውድመት የደረሰው፤ በተለይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ያደረኩበት የሻሸመኔው ሆቴል ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ ከዚህ በኋላ የሻሸመኔው ሆቴል ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ እሱ ከዚህ በኋላ ወደ ሆቴልነት አይመለስም፤ ሆቴል አናደርገውም፤ የዝዋዩም ቢሆን የሻሸመኔውን ያህል አይሁን እንጂ ጉዳት ደርሶበታል፤ የመሰባበር፣ የዕቃ ዝርፊያ በተለይ ተካሄዶበታል፤ ምናልባት ትንሽም ቢሆን ተስፋ ያለው እሱ ነው ከአንድ አመት በኋላ ወደ ስራ እንመልሰዋለን ብለን እናስባለን፡፡

ሀትሪክ፡-ይሄ ሁሉ የንብረት ውድመት በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል ብር ይሆናል?

ኃይሌ፡-…እንግዲህ ወደፊት በደንብ ሲገመት ሂሣቡ ከፍ አልያም ዝቅ ሊል ይችላል፤ እስካአሁን ባለው ግመታ ግን ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ውድመት ደርሶብናል፡፡
ሀትሪክ፡- 290 ሚሊዮን?

ኃይሌ፡- ምነው… አነሰብህ?

ሀትሪክ፡- ምን ያንሳብኛል በጣም በዝቶብኝ ነው እንጂ፡፡
ኃይሌ፡-እንግዲህ በደንብ በባለሙያ ሲታይ ከዚህም ሊበልጥ ይችል ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡-ኃይሌ 290 ሚሊዮን ብር በጣም ብዙ ነው፤ ይሄን ያህል ውድመት የደረሰበት ሰው መንገድ ላይ ብቻውን እያወራ ቢሄድ ጨርቁን ጥሎ ሊታመም ሊያብድ የሚችልበት አጋጣሚ ሁሉ አለ፤ ኃይሌስ የ290 ሚሊዮን ብር ውድመት ደርሶበት ቆሞ እየሄደ ነው? እንደ ሰውስ ይስቃል ይጫወታል?

ኃይሌ፡-(በጣም ሳቅ)… ምን ይሆናል ብለህ ጠብቀህ ነበር? አሁን ደውለህ የምታወራኝ እኮ እንደሰው ቆሜ ስለምሄድ፣ ብቻዬን ስላማላወራና ስላልታመምኩ ይመስለኛል፤ በዚህ ግርግር ከእኔ ሆቴል በላይ ገንዘብ የማይገዛው የወገኖቻችን ህይወት እኮ ተነጥቋል፤ ጥረው ግረው ያፈሩት ሆቴልና ንብረት በአንድ ሌሊት ዶጋ አመድ ሆኖ ጎዳና ወጥተው የሚያለቅሱ እኮ ብዙ ናቸው፡፡ ይሄንን ስታይ የእኔን እረሣዋለሁ፤ በእርግጥ እኔንም አበሳጭቶኛል ዘርፌ ሳይሆን ላቤን አፍስሼ እግሬ ደምቶና ነፍሮ ባመጣሁት ገንዘብ ንብረቴ ሲወድም ሳይ ያማል፤ ግን ከእኔም የከፋ እንዳለ ሳስብ ሀዘኔን እረሣዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የሆቴሎቹ በዚህ ደረጃ መውደም ብዙ ነገር እንድታጣ በማድረጉ በኩልስ ምን ትላለህ?

ኃይሌ፡- … አትሳሳት የሆቴሉ ወረቀት ነው እንጂ የእኔ ሆቴሉ የእኔ አይደም፤ ብል ይቀለኛል፣ ከእኔ ይልቅ ሀገር እንደሀገር ዜጋ እንደ ዜጋ ተጠቃሚ ናቸው፤ አንድ እወነት ልንገርህ በሁለቱም ሆቴሎች ከ400 ያላነሱ ሠራተኞች አሉ በእነሱ ስር የሚተዳደሩ ከሶስትና ከአራት የበለጡ ቤተሰቦች አሉ ልብ በል እንግዲህ ይሄ ውደሙት በዋናነት የሚጎዳው እነዚህን ወገኖቼን ነው፤ የኃይሌ ቢወድም ሌላ ቦታ ሄደው ይቀጠራሉ እንዳትል ሻሸመኔም ዝዋይም ያሉት ሆቴሎች በሙሉ ወድመዋል፡፡ ውድመቱ መንግሥት የሚያገኘውን ከፍተኛ ታክስ እንዲሁም ሠራተኞቹ ቤተሰቦቻቸው የሚያስተዳድሩበትን ጥቅም ነው ያጡት፡፡ እኔን በተመለከተ እንግዲህ የሻሸመኔውም ከተመሠረተ ወደ 10 አመቱ አካባቢ ይመስለኛል፤ አንድም ሣንቲም ወደ ኪሴ አልከተትኩም እንደውም አሁን ኮሮና በመጣ ጊዜ ደሞዝ ሁሉ ከዚህ ነው የምልከው ኃይሌ በሆቴሉ ተጠቀመ ካልከኝ አንድ ቀን ሻሸመኔ ባድር ወይም ዝዋይ ላይ አንድ ቀን ሻይ ጠጥቼ የምመለሰው ነው፤ የወደፊቱን ብለን ካልተፅናናን በስተቀር ከዚህ ውጪ ያገኘሁት ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ኃይሌ አንተ ለሀገር የማይዘነጋ ብዙ ውለታ የዋልክ ሰው ነህ፤ በሀገርህ ልትከበር የተለየ ቦታ ሊሰጥህ ንብረትህ ሊጠበቅ ሲገባ ስድስት ጊዜ ተመላልሰው ሲያወድሙብህ ምን ተሰማህ? ሀገሬን አስከብርኩ ወይስ ሀገሬን በደልኩ የሚል ምሬት በውስጥህ አልተፈጠረም?

ኃይሌ፡- የእኔ ስሜ እንደ ሸክላ በቀላሉ የሚሰባበር አይደለም ጥቂት ሰዎች በእኩይና በሰይጣናዊ ሥራ ተነሳስተው ያደረጉትን ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ አድርጌ የማስብ ትንሽ አዕምሮ ያለኝ ሰው አይደለሁም፤ ደግሞም በኢትዮጵያዊን በህዝቤ አንዳችም ጥርጣሬው ስለሌለኝ በዚህ ደረጃ አላስብም፡፡ ደግሞም ይሄ ድርጊት እኮ የተፈፀመው በተልዕኮ ነው፤ የተፈፀመው ነገር እኮ የኢትዮጵያዊያን ባህሪ አይደለም፤ በእርግጥ ድርጊቱን የፈፀሙት ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ኢትዮጵያዊያ መልክ ነው ያላቸው፤ እነሱን የላኩብን ያሰማሩብን ግን ኢትዮጵያዊ እኮ አይደሉም፡፡ ከኋላ ያሉት ኢትዮጵያዊ ቢሆኑ የኢትዮጵያ ደም ቢኖራቸውማ ኖሮ ሆቴሉን እንዴት አድርጌ እንደገነባሁት በላቤና በደሜ የተገነባ እንደሆነ ስለሚያውቁ ይሄን አያደርጉም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-ከንግግርህ ስረዳ ከጀርባ ሌላ አካል አለ የምትል ይመስላል?

ኃይሌ፡- … ምን ጥያቄ አለው… አዎን አለ? እያደግን መምጣታችን አባይን በራሳችን አቅም መገደባችን ሠላማቸውን እንቅልፋቸውን ያሳጣቸው የውጪ ሀገራት አሉ፤ የራሣቸውን ቅጥረኞች ምንም የሚያውቁ ሰዎችን መልምለው በማሰማራት ሀገራችን ስትታመስ ማየት የሚናፍቁ ወገኖች ያደረጉት ነገር ነው፡፡ እኔ ዝዋይን ያቃጠሉት የዝዋይ ሰዎች ናቸው አልልም፡፡ ሻሸመኔን በአንድ ሌሊት ያወደሙት የሻሸመኔ ሰዎች አይደሉም፡፡ ምናልባት ሻሸመኔ ላይ የሚጠቁሙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የእከሌን አንድዱ የእከሌን ተው የሚሉ? ከዚህ ውጪ በአይሱዙ ተጭነው መጥተው አይደለም እንዴ እሳት ሲያርከፍክፉና ሲያነዱ የነበሩት ከእነዚህ ሰዎች ጀርባ የውጪ ኃይሎችና እነሱ የቀጠሯቸው ቅጥረኞች አሉ፡፡

ሀትሪክ፡- .. የሆነውን ነገር ስታይ ውስጥህ ምን አለ?

ኃይሌ፡- በነገራችን ላይ ጉዳዩን የአንድ የኃይሌ ጉዳይ አድርገህ ብቻ አትውሰደው፤ ይሄ የሀገር ጉዳይ ነው፡፡ የኃይሌ ንብረት ሣይሆን የሀገር ንብረት ነው የወደመው፤ ማውራት ካለብን እንደ ሀገር ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊት የሚፈፅሙ አንድ ማወቅ ያለባቸው ነገር እኔ ዘርፌ አይደለም ሆቴል የገነባሁት ላቤን አንጠፍጥፌ ደምቼ ነው የገነባሁት፤ ደም የገበርኩበት ስራ ነው፡፡ ሁሌም ላቤን ደሜን አፍስሼ የገነባሁትን ንብርት ያለሀጢአቱ ሲያወድሙት ሣይ በድርጊታቸው አዝኜ አንብቻለሁ፡፡ እኔ እኮ አንድ ማራቶን ሮጬ ስጨርስ ጫማዬ በደም ተጥለቅልቆ እግሬ ነፍሮ ነው የምጨርሰው፡፡ አንድ ማራቶን ከሮጥኩ በኋላ ለስምንት ቀን ጫማ ማድረግ እያቃተኝ እየተሰቃየሁ ነው የምኖረው፤ እኔ እኮ ያኔ ስሮጥ የነበረው ለኬንያ ወይም ለግብፅ አይደለም፡፡ የግብፅን ባንዲራ ይዤ አይደለም ስሮጥ የነበረው፡፡ የሀገሬን ነው ግብፅን እኔ አላውቃትም የማውቃት በህዳሴ ግድብ እንቅፋትነቷ ነው፡፡ ደሜን አፍስሼ ላቤን ዘርቼ የሠራሁት ሀብት ሲወድም ከልቤ አልቅሻለሁ፡፡ ይሄንን ላደረጉት አካላት አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ምን…..?

ኃይሌ፡- … ተልኮ የሰጡት ተልዕኮ ያስፈፀሙትም የሶስት ነገር እዳ አለባቸው የኃይሌ ላብ፣ የኃይሌ ደምና የኃይሌ እንባ አለባቸው፤ የሆነውን ሁሉ ፈጣሪ ይመለከታል፤ እዚህ ምድር ላይ ተሽሎክሉከው ከፍርድ የሚያመልጡ ሊመስላቸው ይችላል፤ መቼም ቢሆን ግን ከፈጣሪ ዋጋቸውን ከማግኘት አያመልጡም፤ እንዳልኩህ ሶስቱ ነገሮች እረፍት ይነሷቸዋል የኃይሌ ላብ፣ የኃይሌ ደምና የኃይሌ እንባ፤ በኃይሌ ላይና በወገኑ ላይ ይሄ ሁሉ ውድመት ደርሶ አምላክ ዝም የሚል ይመስልሃል? የኃይሌ ደምስ አይጮህም?

ሀትሪክ፡-ኃይሌ የአለም ህያው አትሌት በመሆንህ በርካቶች ዜጋቸው እንድትሆን ሲያግባቡህ ሲለምኑህ እንደነበር ከድሮ ጀምሮ አውቃለሁ፤ የሆላንድ የክብር ዜግነት እንዳለህም እንደዚሁ አውቃለሁ፤ እንደውም ነገሮች በአንተ ላይ በተደጋጋሚ ከመድረሳቸው አንፃር በመማረር ከዚህ ሁሉ ለምን ሀገሬን ጥዬ የሠላም ኑሮዬን አልኖርም በማለት ሀገር ጥለህ የመሄድ ሃሣብ ለሰከንድም ቢሆን በአዕምሮህ መጥቶ አያውቅም?

ኃይሌ፡- …በፍፁም … ከዚህ በላይ በሞት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈልም ዝግጁ ነኝ እንጂ ሀገር ጥዬ ስለመሄድ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ስለመሄድ ለሰከንድም ያሰብኩበት ጊዜ የለም፡፡ እኔ ሀገሬን የምወድ ሰው ነኝ፤ ኢትዮጵያ ለምትባለው ሀገር ክብርና ዝና ነው ላቤንና ደሜን ሳፈስ የነበረው፡፡ ከዚህ በላይም ቢመጣ በፍፁም እዚሁ ሀገሬ እሞታለሁ እንጂ ሀገሬን ጥሎ ስለመሄድ አዕምሮዬ ለሰከንድም ቢሆን አስቦ አያውቅም፤ ብፈልግ ኖሮ ከወዲሁም አለኝ 24 አመት ሙሉም እዚህ ውስጥ ነበርኩኝ፤ ግን ከዚህ በላይ መከራና ፈተና ቢመጣም አላደርገውም፡፡

ሀትሪክ፡-በደረሰው ነገር የቤተሰቦችህ ስሜትስ?

ኃይሌ፡-… እነሱም ሰዎች ናቸው፤ እንኳን በራሳቸው ሰውና ንብረት ቀርቶ በሌላውም ላይ ሲደረስ በጣም የሚያዝን ልብ አላቸው፡፡ ከዚህ በመነሣት እነሱም እንደማንኛውም ሰው አዝነዋል፣ ተበሰጭተዋል በጣም የሚገርምህ ግን ባለቤቴም ልጆቼም በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ ከወደመው ንብረት በላይ የሚያስቡትና የሚጨነቁት ለእኔ ነው፡፡ የምንፈልገው አንተን ነ በማለት የሚያስቡት ለእኔ ነው፤ ስለዚህ እኔም እነሱን መረበሽና ማስጨነቅ ስለማልፈልግ ብስጭቴንም ንዴቴንም ውጪ ጥዬ ነው የምገባው፡፡ ምክንያቱም እኔ ተስፋ ከቆረጥኩ እነሱም ተስፋ ይቆርጣሉ፤ እኔ ኬክ ከቆረጥኩ ደግሞ እነሱም ኬክ ስለሚቆርጡ በዚህ መንገድ መሄድን ነው የምመርጠው፡፡

image © walta tv

ሀትሪክ፡- በኦሮሚያ ነው በቢዝነሶችህ ላይ አደጋ የደረሰውና ከደረሰብህ ነገር በመነሣት በብስጭት ወደዛ ክልል ሄጄ ኢንቨስት አላደርግም በሚል ከራስህ ጋር ያወራህበት አጋጣሚስ ነበር?

ኃይሌ፡-… እኔ የምጠላው ይሄንን ነው ወደዚህ ክልል ወደዛ ክልል የሚባል ነገር የለም፤ ታውቃለህ እኔ እኮ የተገኘሁት ከኦሮሚያ ክልል ከአርሲ ክፍለ ሀገር ነው፤ የዚህ ክልል ተወላጅ ነኝ በቋንቋ በኩል አማርኛ ልናገር እችላለሁ፤ ሌላው ኦሮምኛ፣ ትግሪኛና ጉራጊኛ ልናገር ይችላል ቋንቋ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም አንድ ቁርጥ ያለ ነገር ልንገርህ ይሄን ድርጊት የሚያደርጉ ተስፋ ይቁረጡ እንጂ እኔ በፍፁም ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ኦሮሚያ ላይ ንብረት ስለተቃጠለ ኦሮሚያ አቃጠለ ብዬ የማስብ ሰው አይደለሁም፡፡ እንደውም በዚህ አጋጣሚ አንድ ትልቅ ነገር ልንገርህ አዳማ ላይ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ሆቴል ሰሞኑን ወደ ስራ ይገባል፤ አሁንም ለአንተ አልነግርህም እንጂ ሌላም ትልቅ ፕሮጀክት ኦሮሚያ ውስጥ አለኝ እሱንም አስቀጥላለሁ እንጂ አላቆምም፤ እንዳልኩህ ይሄን የሚያደርጉ ተስፋ ይቁረጡ እንጂ እኔ ተስፋ አልቆርጥም፡፡

ሀትሪክ፡- ኃይሌ አንተ ካለህ ታዋቂነትና አለም አቀፍ ዝና ከደረሰብህ ነገር በመነሣት ደውለው የተሰማቸው ስሜት የገለፁልህ ታላላቅ የባህር ማዶ ሰዎች የሉም? ሚዲያዎችስ አላሳደዱህም?

ኃይሌ፡- ፤.. ኡው… በጣም ብዙ ናቸው የማልጠብቃቸውና የማልገምታቸው ሰዎች ናቸው የደወሉልኝ እነሱ እንደውም የሀገር ጉዳይ መሆኑን ትተው ወደ እኔ በማዞር “ኃይሌ ኃይሌ” ማለቱን ነው የመረጡት፤ እኔ ግን በሀገር የመጣ በውጭ ሀገሮች ረዣዥም የጥፋት እጆች የተቀነባበረ ሴራ ነው ብዙም አትጨነቁ ስላቸው አንዳንዳቹ እንደውም አታይም እንዴ እንኳን ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ሰለጠነች በተባለችው ሀገር አሜሪካ በአንድ ሰው በፍሎይድ ሞት የደረሰውን ውድመትና የተቀጣጠለውን ተቋውሞ አላየህም ብለው መልሰው ሊያፅናኑኝ ሞክረዋል፤ እንደ እውነት ከሆነ ብዙዎች ትላልቅ የውጪ ሰዎች ደነግጠው ደውለውልኛል፡፡

ሀትሪክ፡-ሚዲያዎችስ?

ኃይሌ፡- ይሄው አንተን ጨምሮ ደውላችሁልኝ አይደል፤ ከውጪ ብዙ ሚዲያዎች ጠይቀውኛል፤ ጉዳዩን የኃይሌ ብቻ አታድርጉ በሚል ለቃለ ምልልስ ፍቃደኛ አለመሆኔን ገልጬ በር ዘግቻለሁ እንጂ ብዙዎች ሞክረዋል፡፡ ግን እንዳልኩህ ምንም ቢደርስብኝ ምንም ብትሆን ሀገሬ ስለሆነች በር ዘግቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚህ በኋላ ከመንግሥትም ይሁን ከሚመለከታቸው አካላት ምን ትጠብቃለህ?

ኃይሌ፡- መንግሥት ዜጎቹ ነን፤ የሚጠበቅብኝን ታክስ ስከፍል ኖሪያለሁ፤ ለመንግሥት ማድረግ ያለብኝን ሣደረግም እንደዚሁ፤ አሁን መንግሥት በተራው ለእኔ ሊደርስ ይገባል፤ መንግሥት ሊከፍለኝ ይገባል ያኔ ነው የህመሜ መጠን ጋብ የሚለው፤ ነገ ዛሬ ሳይባል ይሄ ተግባራዊ ሆኖ የበተናቸውን ሠራተኞች ሰብስበን ወደ ሥራ ልንገባ ይገባል፡፡ መንግሥት አልጠበቀንም፣ ይጠብቀናል ብለን አምነናቸው የተኛን ሰዎች አይተው ደርሰው ሊያድኑን አልቻሉም፤ ጭራሽ አንዳንዶቹ የተባባሪ ያህል ቆመው እያዩ ነው ንብረታችን የወደመውና መንግሥት ለእነሱ ከያዘው በጀትም ቢሆን ቀንሶ ሊከፍለኝ ይገባል፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.