“ህጋዊ ተጨዋች መሆንን እፈልጋለው፤ አዲሱ ክለቤንም የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት አሳውቃለው”ይሁን እንዳሻው

ይሁን እንዳሻው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኮትዲቯር አቻውን በተፋለመበት እና ድል ባደረገበት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ የዋልያዎቹን የመሃል ሜዳ ክፍል በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ከፍተኛ ተደናቂነትን ማትረፉ ይታወሳል፤ የሀዲያ ሆሳህናው ይሁን እንዳሻው በሜዳ ላይ ያለውን ጥሩ የኳስ ብቃት ተከትሎና የአሁን ሰዓት ላይም ከክለቡ ጋር የነበረውን የውል ጊዜ ማጠናቀቁን ተንተርሶም በበርካታ ክለቦች እየተፈለገ ቢሆንም፤ በአንድአንዶችም ዘንድ ወደዚህ ክለብ ሊያመራ ነው ተብሎም ሊነገር ቢችልም የተጨዋቹ አንደበት ግን ይህንን ሊያስደምጠን ችሏል “የአሁን ሰዓት ላይ ብዙ ክለቦች እኔን የራሳቸው ንብረት ሊያደርጉኝ እያናገሩኝ ይገኛል፤ ያም ሆኖ ግን የእኔ መልስ የዝውውር መስኮቱ እስካሁን ድረስ ስላልተከፈተና ህጋዊ ተጨዋች ሆኜም መጫወትን ስለምፈልግ ለእነዚህ ለጠየቁኝ ክለቦች ምላሽን አልሰጠዋቸውም፤ ወደየትም ክለብ ስለማምራት አሁን ላይ እያሰብኩኝም አይደለውም” ካለ በኋላ “የዝውውር መስኮቱ መስከረም 2 ቀን ስለሚከፈት ያኔ ፊርማዬን የማኖርበትን ክለቤን አሳውቃለው” ሲል ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ጥሩ እንቅስቃሴን በሜዳ ላይ በማሳየት የሚታወቀው እና ከጅማ አባጅፋርም ጋር በነበረው የተጨዋችነት ዘመን ተሳትፎው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የቻለው ይሁን እንዳሻው ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን በማድረግ ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አብዛኛው ክለቦች ተፈላጊ ተጨዋች ሆንሃል፤ አሁን ላይ ወደየትኛው ክለብ ልታመራ ተዘጋጅተሃል?

ይሁን፡- እስካሁን ወደየትኛውም ክለብ ስለማምራት እያሰብኩም ሆነ እየተዘጋጀው አይደለም፤ እኔን ለመውሰድ የፈለጉ ብዙ ቡድኖች ግን አሉ፤ ያ ስለሆነም መጨረሻ ላይ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት አንዱ ቡድን ጠብቆ ይወስደኛል፡፡

ሀትሪክ፡- አንተን የሚወስድህ ቡድን ማን ይሆን?

ይሁን፡- አሁን ላይ አላውቅም፤ ያም ሆኖ ግን ከላይ እንደገለፅኩትም የዝውውር መስኮቱ መስከረም 2 ቀን ሲከፈት ብቻ ነው አዲሱን ቡድኔን የማውቀው፡፡

ሀትሪክ፡- ያ የአንተ ምርጫ የሚሆነው ክለብ በምን ደረጃ ላይስ የሚገለፅ ነው?

ይሁን፡- ክለቡ እኔን በተጨዋችነት የሚፈትነኝ ትልቅ ክለብ ነው፤ ያን ስል ግን እስከዛሬ የተጫወትኩባቸው ክለቦች ትልቅ አይደሉም ለማለት ፈልጌ አይደለም፤ ትላልቅ ተጨዋቾች ያሉበት፤ ልፎካከራቸው የምችላቸው ተጨዋቾች ያሉበት ቡድን ውስጥ ነው ራሴንም መፈተን ስለምፈልግ ወደዛ ቡድን ለማምራት የምፈልገውና እንደ ፈጣሪ ፈቃድ አሁን ላይ ደግሜም መናገር እፈልጋለው ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ ልጫወት ወደምችልበት ቡድን መግባትን እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- በአሁን ሰዓት ለየትኛውም ቡድን አለመፈረምህን ተከትሎም ይሁን ወደ አንድ ቡድን ለማምራት እና ፊርማውንም ለማኖር ዘግይቷል የሚሉም አሉ?

ይሁን፡- በፍፁም አልዘገየውም፤ መች የዝውውር መስኮቱ ተከፈተና ነው የምዘገየው፤ ምክንያቱም እኔ ለአንድ ቡድን ስፈርም በጣም እርግጠኛ መሆን እፈልጋለሁ፤ የእኔ እርግጠኝነት የሚረጋገጠው ደግሞ የዝውውር መስኮቱ ተከፍቶ ፌዴሬሽን ሄጄ ስፈርም ነውና ያን ጊዜ እየጠበቅኩኝ ነው የምገኘው፡፡ አሁን ላይ ግን ብዙ ተጨዋቾች ለአንድ ክለብ ፈረሙ ከተባለ በኋላ በቀናት ልዩነቶች መልሰው ለሌላ ክለብ ሲፈርሙ እየተመለከትን እንገኛለን፤ በዚህ መልኩ ለመፈረም መቻልስ ምን ዋስትና አለ፤ አንተን እዚህ ወቅት ላይ ካስፈረመ በኋላ መልሶ ደግሞ በአንተ ላይ ሌላ ተጨዋች አምጥቶ አልፈልግህም ቢልህስ፤ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች በጣም ደስ አይሉምና ለዛም ነው እስካሁን ድረስ ለየቱም ክለብ ፊርማዬን ለማኖር ያልቻልኩትና ሕጋዊ ተጨዋች ሆኜ ነው መፈረምን የምፈልገው፡፡ መስከረም 2 ቀን ደግሞ ብዙም ሩቅ አይደለም፤ ምንም የሚፈጠርም ነገር የለም ክለቦችም ወደ ዝግጅት አይገቡምና ለዛም ነው በመፈረሙ ላይ እንዳልዘገየው አፌን ሞልቼም መናገርን የፈለግኩት፡፡

ሀትሪክ፡- በዘንድሮ የሀድያ ሆሳዕና የተጨዋችነት ቆይታህ መልካምና ጥሩ የሚባል የጨዋታ ጊዜን አሳልፈሃል ማለት ይቻላል?

ይሁን፡- በአብዛኛው አዎን፤ ለዛ ፈጣሪንም ይመስገን እላለው፤ በእዚህ ክለብ ውስጥ የነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ምንም እንኳን ለ6 ወራት ብቻ የዘለቀ ቢሆንም ጥሩ ጊዜን ነው ከቡድኑ ጋር ያሳለፍኩት፤ እንደዛም ሆኖ ግን የተከፋሁበት ሁኔታም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በሀድያ ሆሳዕና የተጨዋችነት ቆይታ አንተን ያስከፋ ወይንም ደግሞ ለአንተ ጥሩ ያልነበረው ሁኔታ ምን ነበር?

ይሁን፡- ይሄ እኔን ብቻ አይደለም አብዛኛዎቹንም የቡድናችንን ተጨዋቾች ያስከፋ ነው፤ ይሄም ምንድን ነው? ክለባችን ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የአራት ወር ያህል ደመወዛችንን ሊከፍለን አለመቻሉ ደስ እንድንሰኝ አላደረገንምና፤ ያ መሆን መቻሉ አስከፍቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ከእዚህ በፊት ተጫውተህ ባሳለፍክባቸው ክለቦች ውስጥ በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግህን ተከትሎ በችሎታህ ጥሩ ስምና ዝናን አትርፋሃል፤ ዘንድሮ አንተ የተጫወትክበት ሀድያ ሆሳዕና ግን የእዚህ አመት ላይ ውድድሩ በኮቪድ 19 ተሰረዘ እንጂ በወራጅ ቀጠና ላይ ይገኝ ነበር፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር አለህ?

ይሁን፡- አዎን፤ ሀድያ ሆሳዕና በዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በወጣቶች የተገነባን ጥሩ ቡድን ይዞ ቢቀርብም ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በክለቡ ውስጥ ለማከተት አለመቻሉ ያ ክፍተትን ፈጥሮበታል፤ ለዛም ነው በወራጅ ቀጠናው ላይ ለመገኘት አንዱ ምክንያት ሊሆነው የቻለው፤ ከዛ ውጪም በክለቡ ውስጥ ላለነው ተጨዋቾች የቡድኑ አመራሮች ደመወዝ ካለመስጠት ጋር ተያይዞም የቡድናችንን ተጨዋቾች ኳስ የመጫወት ፍላጎትን ስላሳጣ ያ ሌላው ምክንያት ሆኗል፤ ተጨዋች ጥቅም ሲቀርበት ከእሱ የምትፈልገውን ነገር አታገኝም፤ ያ ማለት ልክ መኪና ነዳጅን ካጣ እንደማይነቀሳቀሰው ማለት ነውና ስፖርተኛውም የሚያስተዳድረው ቤተሰብ ስላለው ከእሱ የምትጠበቀውን ነገር ላታገኝ ትችላለህና ይሄ ነው ቡድናችንን ውጤቶች ያሳጣው፡፡

ሀትሪክ፡- የሀድያ ሆሳዕና የውል ጊዜህ እንደተጠናቀቀ እነሱ ከክለቡ ጋር ዳግም እንድትቀጥል አላነጋገሩህም?

ይሁን፡- እነሱማ እንድቀጥል አውርተውኝ ነበር፤ ግን ያልከፈላችሁኝን ደመወዝ በቅድሚያ ስጡኝና ከዛ በኋላ በቡድኑ ስለምቀጥልበት ጉዳይ እንነገጋራለን፤ ከተስማማንም እቀጥላለው፤ ካልተስማማን ደግሞ ወደ ሌላ ክለብ ፊቴን አዞራለው ብዬ ነግሬያቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ቀሪ እና ውዝፍ እዳ እያለባቸው መፈራረሙ ለእኔ አልታየኝምና፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

ይሁን፡-ሁሉም ሰው ከእዚህ አስከፊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ራሱን ይጠበቅ ነው የምለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website