“ሃዲያ ሆሳዕና በሊግ ኮሚቴ ውሳኔ ተጠቃሚ ቢሆንም ባይሆንም ውሳኔው ተገቢ ነው ብለን ግን እናምናለን” ጸጋዬ ኪዳነማሪያም /የሃዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ/

መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የሚመራው የሊግ ኮሚቴ በሰጠው ውሳኔ በ2012 አሸናፊ፣ወራጅና ኃላፊ ክለብ የለም ሲል መወሰኑ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ክለቦች መኖራቸው አልቀረም፡፡ በ17 ጨዋታ 14 ነጥብና 13 የግብ እዳ ያለበት ሀድያ ሆሳዕና ከወራጅነት ስጋት ከተረፉ ክለቦች መሀል ይጠቀሳል፡፡ ይህን ተከትሎ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር ያደረገው አጠር ያለ ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- የሊግ ካምፓኒው በወሰነው ውሳኔ ሃዲያ ሆሳዕና ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ምን ተሰማችሁ?
ፀጋዬ፡-በእርግጥ በውሳኔው ደስተኛ ነን፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ የወሰነው ውሳኔ ተገቢ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ደረጃ ውስጥ ለመግባት ነበር ወደ ውድድሩ የገባነው… ግን እስከ 17ኛ ሳምንት ድረስ ያለው ውጤታችን ጥሩ አልነበረም፡፡ በ1ኛና 2ኛ ዙር መሀል ላይ ድክመታችንን ለማስተካከል ሰርተን ወደ 4 ተጨዋቾችን አስፈርመን 2ኛው ዙር አንድ ጨዋታ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ቀሪ 13 ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤት እናስመዘግባለን ብለን አስበን የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሣ ጨዋታው በመቋረጡ ተጠቃሚ ሆነናል….. ባለፉት 2 አመታት በወሰድነው ትምህርት የተሻለ ለመሆን ጠንክረን እንመጣለን፡፡
ሀትሪክ፡-በአፍሪካ መድረክስ አለመሳተፋችን አገራችንን አይጎዳም?
ፀጋዬ፡- በሀገር ደረጃ በሻምፒዮንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን ካፕ አለመሳተፋችን ቅር ያሰኛል፡፡ ብንሳተፍ በሀገር ደረጃ ጥሩ ይሆን ነበር ግን አልሆነም……ዋናው መታሰብ ያለበት የሊጉ ኮሚቴ ደግሞ ሊያየው ይችላል ውሳኔው ቢፀናም ግን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ለውሳኔው ተቸግረውም ሊሆን ስለሚችል ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለንም፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን በተሰጠው ውሳኔ ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ እየተቃወሙ ነው በተቃራኒ ሁለቱ ቢወከሉ የሚቃወሙ ክለቦች አይኖሩም?
ፀጋዬ፡-ባህሪያችን ይታወቃልኮ በእያንዳንዱ ውሣኔ ላይ ተቃውሞ መቅረቡ አይቀርም…. በኮከብ ተጨዋችና በኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ላይም ተቃውሞ ሲቀርብ አይተናል፡፡ አሁንም ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ ይሂዱ ቢባል ሶስተኛውና አራተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ክለቦች ቅርብ ነበርን በጥሎ ማለፍ መለየት ነበረብን ብለው መቃወማቸው አይቀርም የትኛውም ውሳኔ ሁሉንም ሊያስደስት አይችልም ብዬ አምናለሁ…. በአመራር ደረጃ ላይ ያሉት ግን የመወሰን መብታቸውን መጠቀማቸው ተገቢ ነው ብዬ አምናለው፡፡ የትኛውም ውሳኔ አንዱን አስደስቶ ሌላውን ሊያስከፋ ይችላል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ደስተኛ የሆናችሁት ውሳኔው ክለባችሁን ተጠቃሚ ስላደረገ አይመስልም?
ፀጋዬ፡- አይደለም…. ሃዲያ ሆሳዕና በሊግ ኮሚቴ ውሳኔ ተጠቃሚ ቢሆንም ባይሆንም ውሳኔው ተገቢ ነው ብለን ግን እናምናለን፡፡ ውሳኔዎች ሁሉንም ወገን ማስደሰት ስለማይችል የአወዳዳሪ አካሉን ውሣኔ ግን ማክበር መልመድ አለብን፡፡
ሀትሪክ፡-ከኮሮና ቫይረስ መከላከል ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ የተዘናጋ አይመስልም?
ፀጋዬ፡-ይሄ ነገር ቀላል ይመስላል እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ እኛኮ በተለመደው መንገድ እየኖርን ነው፡፡ ቫይረሱ ግን በየክልሉና በየከተማው እየገባ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን ሰምተን በመተግበር ጥንቃቄያችንን ልንቀጥል ይገባል፡፡ አገራችንን በጋራ በመጠበቅ ቫይረሱን መፋለም ይናርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-አመሰግናለሁ…

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport