ሀትሪክ የ15ኛ ሳምንት የሊጉ እይታ (ክፍል አንድ)

👉👉የመጀመሪያውን ዙር በድል የደመደመው ሀድያ

👉👉ልምምድ ሳያደርግ ተጋጣሚውን ያስጨነቀው ጠንካራው ጅማ አባጅፋር

👉👉አርቢትርን ለመደብደብ ያቃጣው ቡርኪናፋሷዊው አጥቂ

👉👉ጉዳት ያስተናገዱት የመሀል አርቢትር ተፈሪ አለባቸው

👉👉 ግብ አግብቶ ደስታውን በእንባ የገለፀው ተከላካይ

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ ትላንት ፍፃሜውን ሲያገኝ በሳምንቱ የተመለከትናቸውን ቅልብ ሳቢ እና ክንዋኔዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

የመጀመሪያውን ዙር በድል የደመደመው ሀድያ

በ 8ኛው ሳምንት ከሜዳው ውጭ ወልዋሎ አዲግራትን 1-0 ካሸነፉ በኋላ፤ ለተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ያለ ስኬት የተጓዙት ሀድያዎች በስተመጨረሻም ነፍስ የዘሩበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ በ15ኛ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር በድል ጨርሰው ከሌሎች ክለቦች ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችለዋል። በጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕና የእዮብ በቃታ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ታድጋቸዋለች።

ልምምድ ሳያደርግ ተጋጣሚውን ያስጨነቀው ጠንካራው ጅማ አባጅፋር

በ14ኛ ሳምንት ድሬዳዋን ካሸነፉ በኋላ በደሞዝ ችግር ምክንያት ልምምድ ሳይሰሩ በጨዋታው ቀን ወደ ወደ ሀዋሳ አምርተው ሀድያን ገጥመው ቢሸነፉም ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ግን በፍፁም በላይነት የፀጋየ ኪዳነማርያምን ሀድያ ሆሳዕና አስጨንቀው ወጥተዋል። ያገኙትን አጋጣሚዎች አለመጠቀም እንጂ ጅማ አባጅፋሮች አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበት አጋጣሚም ነበር።

አርቢትሩን ለመደብደብ ያቃጣው ቡርኪናፋሷዊው አጥቂ

በዚህ ሳምንት ከተመለከትናቸው ግርምትን ከሚፈጥሩ ትዕይንቶች መካከል የሰበታ ከተማው ባኑ ዲያዋራ ተቀይሮ ቢገባም ከ21 ደቂቃዎች በኋላ በፌደራል አርቢትር ተፈሪ አለባቸው ሆን ብለህ እያጠፋህ ነው በማለት በሁለት ቢጫ ካርዶች ቀይ ካርድ ተመልክቶ ከጨዋታው ተሰናብቷል። ተጫዋቹ የተሰጠኝ የቀይ ካርድ ተገቢ አይደለም በማለት አርቢትሩን ለመምታት ያቃጣበት መንገድ የስፖርት ቤተሰቡን ያስቆጣ ጉዳይ ነበር። ይህም አላስፈላጊ ድርጊት ሊታረም የሚገባው አስነዋሪ ተግባር ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነገሩን ለማርገብ የሄዱበት መንገድ በሌሎች አሰልጣኞችም ሊበረታታ የሚገባው ነው።

ጉዳት ያስተናገዱት የመሀል አርቢትር ተፈሪ አለባቸው

ሲዳማ ቡናን ከ ሰበታ በበርካታ ውዝግቦች አጅበው የመሩት ፌደራል አርቢትር ተፈሪ አለባቸው በጨዋታው መጨረሻ በተጨማሪ አምስት ደቂቃዎች እግራቸው ላይ በደረሰባቸው መጠነኛ ጉዳት ጨዋታውን በማቆም በሲዳማ ቡና የህክምና ባለሞያ አበባው በለጠ እርዳታ ተደርጎላቸው ጨዋታውን አስቀጥለዋል። ይህም በስታዲዮሙ ለታደሙ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ፈገግ ያስባለ አጋጣሚ ነበር።

ግብ አግብቶ ደስታውን በእንባ የገለፀው ተከላካይ

ሀድያ ሆሳዕናዎች ከተከታታይ ስድሰት ጨዋታ ነጥብ መጣል በኋላ በ15ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ሲያሽንፍ ተከላካዩ እዮብ በቃታ በቅጣት ምት ድንቅ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን በእንባ የገለፀበት መንገድ የብዙ ደጋፊዎች ልብ የነካ ነበር።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor