ሀትሪክ የ15ኛ ሳምንት የሊጉ እይታ (ክፍል ሶስት)

👉👉ስሜታዊው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

👉👉ለመገናኛ ብዙሀን የሚገባውን ክብር የነፈጉት ፌደራል አርቢትር

👉👉አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡት አዲሴ ካሳ

👉👉በ34 ደቂቃ አምስት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ

👉👉የፋሲል ከተማ የመሀል ሜዳ ላይ ጥምረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ ትላንት (ሰኞ የካቲት 16/2012) ፍፃሜውን ሲያገኝ በሳምንቱ የተመለከትናቸውን ቀልብ ሳቢ እና ዋነኛ ክንዋኔዎች እንደሚከተለው አቅርበንላቹሀል።

ስሜታዊው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

የሀድያ ሆሳዕናን እና ጅማ አባጅፋርን ጨዋታውን ለመምራት የተቸገሩት ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ በተደጋጋሚ ሲያደርጓቸው የነበሩትን ስህተቶች አሰልጣኙን ወደ ስሜታዊነት እና ውሳኔውን መቃወም እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ሮጠው ያልጠገቡ ወጣት ተጫዋቾች የቡድን ስብስብ እንዳላቸው በተደጋጋሚ የሚናገሩት አሰልጣኙ በወጣቶች አምነን ማሰለፋችን ሊበረታታ ሲገባው አንዳንዴ ዳኞች ጥፋት ሲሰሩ ተጫዋቾቼ ስሜታዊ ቢሆኑም አልፈርድባቸውም ሲሉ በተደጋጋሚ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሚሰጧቸው አስተያየት ላይ ይደመጣሉ። የተሻለ ቡድን ያሸንፍ ከዛ ውጭ ዳኞች ለባለሜዳ ብቻ መደገፍ የለባቸውም ሲሉ ይደመጣል።

ለመገናኛ ብዙሀን የሚገባውን ክብር የነፈጉት ፌደራል አርቢትር

እግር ኳስ ምንም በቢሊየን የሚቆጠር አንጡራ ሀብት ብታፈስበት ሚዲያ ካልታከለበት አንድ እርምጃ እንኳን መራመድ አይችልም። ወደ ስታዲዮም ቅጥር ለመግባት የሚከለከለው የሚዲያ አካል ወይስ ደጋፊ ጥቃት አድራሽ ወይስ መረጃ አድራሽ። በየጊዜው ህጋቸውን የሚለዋውጡት ዳኞች ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከተማ በነበረው የ15ኛ ሳምንት መርሀግብር በእለቱ አራተኛ ረዳት ዳኛ ተመድበው የነበሩት አዳነ ወርቁ መገናኛ ብዙሀን ከተመልካች ጋር ሆነው እንጂ ሜዳ ውስጥ ገብተው ጨዋታውን ለህብረተሰብ ማድረስ አይችሉም በማለት በደጋፊ ፊት ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ያደረጉት እሰጣ ገባ ሊደገም የማይገባው እና መታረም ያለበት አፀያፊ ተግባር ነው።

አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡት አዲሴ ካሳ

ከፕሪምየር ሊጉ ጅማሮ አንስቶ እሰከ 14ኛ ሳምንት ቡድናቸው ቢሸነፍም ቢያሸንፍም በጨዋታው ሊተገብሩ የፈለጉትን እና የተገበሩትን አጨዋወት ትህትና በተሞላበት መንገድ ለመገናኛ ብዙሀን ከጨዋታ በኋላ ገለፃቸውን የሚሰጡት አሰልጣኙ በዚህ ሳምንት ግን ቡድናቸው በጥሩ ብቃት ተጋጣሚውን 3-2 ቢያሸንፍም አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል። ምናልባትም ቡድኑ ውስጥ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ሀሳባቸውን እንዳይሰጡ ምክንያት እንደሆነ ሲገመት በሌላ በኩም ከደረሰባቸው ተቃውሞ አንፃር በክለቡ ያላቸውን የወደፊት ቆይታ ምን ይመስላል የሚል ጥያቄ እንዳይሰነዘርባቸው ከመፍራት የተነሳ ነው በማለትም ሀሳባቸውን የሚገልፁ አሉ።

በ34 ደቂቃ አምስት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ

በዘንድሮው አመት እስከ 34ኛው ደቂቃ 5 ግቦች የተቆጠረበት የሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ የዚህ ሳምንት ምርጡ ብሎም አዝናኙ ጨዋታ ተብሎም በድፍረት መናገር ይቻላል። በዚህ ጨዋታ አፄዎቹ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ በመቀየር ተሳክቶላቸው ሁለት ግቦች አስቆጥረው ጨዋታውን በቀላሉ ድል አድርገው የሚወጡ ቢመስሉም ሀይቆች ተስፋ ሳይቆርጡ ያደረጉት ተጋድሎ ግን ከእንግዳዎቹ ሙሉ ሶስት ነጥብ ከመንጋጋቸው ፈልቅቀው እንዲወስዱ አስችሏቸዋል። በዚህ ጨዋታ የስፖርቱ ታዳሚ ተዝናንቶ መውጣት የቻለበት የዚህ ሳምንት አስደናቂ ጨዋታ ነበር።

የፋሲል ከተማ የመሀል ሜዳ ላይ ጥምረት

አማካዮቹ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሀብታሙ ተከስተ እና በዛብህ መለዮ በሁለተኛው ግማሽ ያደረጉትን ድንቅ ጥምረት ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ በመክተት በርከት ያሉ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በተለይ የተከላካዮቹ ላውረንስ ላርቴ እና መሳይ ጳውሎስ ድንቅ ብቃት ግቦችን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor