ሀትሪክ የ15ኛ ሳምንት የሊጉ እይታ (ክፍል ሁለት)

👉👉ተቃውሞ ያስተናገዱት የሊጉ አሰልጣኞች

👉👉የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማህበር መዋጮ

👉👉በድሮ ክለባቸው የተወደሱት ክፍሌ ቦልተና

👉👉የማስጠንቀቂያ ወረቀቱ ያበረታታው ዳኛቸው በቀለ

👉👉ባልተለመደው ቦታ የተሰለፈው ፍርዳወቅ ሲሳይ

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ ትላንት ፍፃሜውን ሲያገኝ በሳምንቱ የተመለከትናቸውን ቀልብ ሳቢ እና ክንዋኔዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

👉👉ተቃውሞ ያስተናገዱት የሊጉ አሰልጣኞች

በዚህ ሳምንት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ሲዳማ ቡናን ገጥሞ 1-0 የተሸነፈው የውበቱ አባተው ሰበታ ከተማ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኙ ከደጋፊያቸው ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እስጣ ገባ ውስጥ ገብተው እስከ መደባደብ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ችግሮች ቢኖሩም በፀጥታ ሀይሎች ርብርብ ጉዳዩ በርዶ ከቡድን አባሎቻቸው ወደ ማረፊያ ሆቴላቸው አምርተዋል። በተመሳሳይ ሀዋሳ ላይ የተደረገውን የሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሀይቆች ሁለት ግብ ማስተናገዳቸውን ተከትሎ የቡድኑ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ከደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው የፕላስቲክ ኮዳዎች ቢወረወሩባቸውም የመልካም ስብእና ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው አሰልጣኙ ወደ ደጋፊው በመዞር ኮፍያቸውን በማውለቅ ለደጋፊዎች ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።

👉👉የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማህበር መዋጮ

ባለፈው ሳምንት ሲዳማ ቡና ወደ ወልቂጤ አምርተው በይገዙ ቦጋለ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተፈጠረው የደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ከተመልካቹ በደጋፊዎች ማህበር አማካኝነት ለህክምና የሚውል ብር አሰባስበዋል። ይህም ሊበረታታ የሚገባው መልካም ተግባር በስፖርቱ እክል ለሚገጥማቸው የስፖርት አፍቃሪያን ተመሳሳይ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል።

በድሮ ክለባቸው የተወደሱት ክፍሌ ቦልተና

በዚህ ሳምንት ተቃውሞ እንዳስተናገዱት አሰልጣኞች ሁሉ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በሀዋሳ ስታዲዮም ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሲወደሱ የነበሩበት መንገድ ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነበር። ሰበታ ከተማ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ። የሰበታ ከተማ ደጋፊዎች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጋቸውን የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ስም በመጥራት ያላቸውን አድናቆት እና ክብር የገለፁ ሲሆን በአንፃሩ የአሁኑ አሰልጣኛቸውን ተቃውመዋል።

 

የማስጠንቀቂያ ወረቀቱ ያበረታታው ዳኛቸው በቀለ

ድሬዳዋ ከተማ የሚጠበቅብህን አገልግሎት እየሰጠህ አይደለም በሚል ምክንያት የማስጠንቀቂያ ወረቀት የደረሰው ተጫዋቹ እራሱን በማሻሻል ማንነቱን ገልጿል። ድሬዳዋ ከተማ ከአስከፊ ጉዞ በኋላ የመጀመሪያው ዙር በጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ዳኛቸው በቀለ ባስቆጠረው ግብ የዋንጫ ተፎካካሪው መቐለ 70 እንደርታን አሸንፎ በድል እንዲወጣ አስችሎታል።

ባልተለመደው ቦታ የተሰለፈው ፍርዳወቅ ሲሳይ

ሰበታ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሲዳማ ቡና 1-0 መሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በጨዋታው በጉዳት ተጫዋቾቻውን ያጡት ውበቱ አባተ የግራ መስመር አጥቂያቸውን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደኋላ በመመለስ የግራ ተከላካይ አድርገው ሲጠቀሙበት ተስተውሏል። ተጫዋቹ በተሰለፈበት ቦታ ሰበታዎች ጫና ሲበዛባቸው የተስተዋሉ ሲሆን ይህም ተጫዋቹ ነቅሎ በሚውጣት ስአት የኋላ መስመሩ በተደጋጋሚ ክፍት ይሆን ነበር። በተጨማሪም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ፍርዳወቅ ሲሳይ ነቅሎ ከወጣ በኋላ ወደ ቦታው ተመልሶ የመሸፈን ችግር  የታየበት  ሲሆን አሰልጣኙ በተደጋጋሚ እየጠሩ ስህተቶቹን እንዲያርም ያደርጉት ነበር።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor