ዋሊያዎቹ ከጊኒ ጋር ላለባቸው ጨዋታ
ዛሬ ምሽት ወደ ራባት ያቀናሉ
“ከጊኒ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ከተሳካ 6 ነጥብ ካልሆነ ግን 4 ነጥብ ለማግኘት እንጥራለን”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
“የሆኑ ፕሮግራሞች ብሄራዊ ቡድኑን ለመሳደብ የተዘጋጁ ይመስላል ስብስባቸውም አሰልጣኙን፣ ቡድኑንና ፌዴሬሽኑን ለመተቸት የተዘጋጁ መሆኑ መቆም አለበት”
አቶ ባህሩ ጥላሁን
/የፌዴ.ዋና ስራ አስፈጻሚ/
- ማሰታውቂያ -
ዋሊያዎቹ ከጊኒ አቻቸው ጋር ባለባቸው የደርሶ መልስ ጨዋታ ከተሳካ 6 ነጥብ ካልሆነ ግን 4 ነጥብ ለማግኘት እንደሚጥሩ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስታወቁ።
አሰልጣኙ ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ ከጠራናቸው 23 ተጨዋቾች መሃል በጉዳት በተለዩን ተጨዋቾች ምትክ ሌሎቹን አካተን ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ከጊኒ ጋር የሚኖረን ጨዋታ ወሳኝ ነው እኛ ደርሶ መልስ ስንጫወት በምድባችን የሚገኙት ግብጽና ማዳጋስካር ስለሚጫወቱ የሚያልፉትን ከመወሰን አንጻር ወሳኝ ስለሆነ ከጊኒ ጋር ስንጫወት ጠንክረን የምንፋለም ይሆናል ከተሳካ 6 ነጥብ ካልሆነ ግን 4 ነጥብ ለመያዝ እንጥራለን” ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ እንደተናገሩት” ከድሬዳዋ የሊጉ የጨዋታ መቆራረጥ አንጻር ብሄራዊ ቡድኑ ተጎድቷል። ሚስቶቻችን ስጥ ሲያሰጡ ዝናብ መጣ ይግባ አይግባ እንደሚሉት የድሬዳዋ ሜዳም በዝናብ በመጨቅየቱ የተነሳ ጨዋታው ይካሄድ አይካሄድ መባባል መጀመሩ ሲታይ 23 ተጨዋች ለማግኘት መቻል እድለኝነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ፌዴሬሽኑ የተመረጡ ተጨዋቾችን ይፋ ለማድረግ ከያዘው ሰአት በ2 ሰአት መዘግየቱ አሰልጣኙ ጌታነህን እንዲያስገቡ ሙከራ እየተደረገ ስለነበር ነው በሚል ለወጣው መረጃ አሰልጣኝ ውበቱ በሰጡት ምላሽ “የዋሊያዎቹን ዋና አሰልጣኝነት ከያዝኩ 2 አመት ከ6 ወር አልፎኛል በተጨዋቾች ምርጫ ላይ የፌዴሬሽኑ አመራሮች አንድም ቀን ጣልቃ ገብተው አያውቁም.. መጥቶም ያናገረኝ ሰው የለም” ሲሉ አስተባብለዋል።በመግለጫው ላይ የተገኙት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው “በቻን ማጣሪያ ከአንድም ሁለቴ ታንዛኒያ ሄደናል የመጀመሪያ ምርጫችንም ታንዛኒያ ነበረች ። ነገር ግን ከወጪና ከጉዞ አንጻር ድካምና ጉዳት እንዳያስከትል ከጊኒ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባደረግነው ውይይት ሞሮኮን ስለመረጡ እኛም ተስማምተናል። በርግጥ በሰሜን አፍሪካ መጓዝ ከባድ ነው ሞሮኮ ተጫውተን ወደ ታንዛኒያ ከመመለስ እዛው መጨረስ በሚለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተስማሙ ሲሆን ሞሮኮን ለመምረጥ ከአየር ሁኔታ ጋርና ከአሰልጣኙ ፍላጎት ጋር ተነጋግረን ወደ ውሳኔ ገብተናል። ወደ 70 ሺህ ዶላር የሚጠጋው ወጪ በሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚቻል ሲሆን በቆይታችንም ባለሜዳ በምንሆንበት ጊዜ ወደ 8 ሺህ ዶላር ገቢ እናገኛለን ። እንደ ሀገር ግን ሜዳ አለመኖሩ ጎድቶናል ጊኒና ሞዛምፒክ ከቅጣት መልስ ሜዳዎቻቸውን አዘጋጅተው በሀገራቸው ለማድረግ ከጫፍ ደርሰዋል እኛ ጋር ግን የለም ዋና ተጎጂም እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ነው ‘ ሲሉ አስረድተዋል።
በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሚሰጡ መግለጫዎች ላይ ሀሳቦችን ትቆርጣላችሁ ይሄ ለምን ሆነ የግድ መደገፍ አለባችሁ..? ወይ የተባሉት አቶ ባህሩ “የተጠየቁ ጥያቄዎችን የምንፈራበትና የምንቆርጥበት ምክንያት የለም በተለያዩ ሚዲያዎች የተገለጹና ህዝቡ የሰማው በመሆኑ ለመቁረጥ አንነሳም የነበሩትን ጥያቄዎችና ምላሾችንም አልቆረጥንም እንዲቆረጥም ከፌዴሬሽን የተሰጠ መመሪያ የለም ክፍተት ካለ ለማስተካከል እንጥራለን። እንደ አጠቃላይ የሚያስወድሰንም ሆነ የሚጠላን ሚዲያ አለ ነገር ግን የሚያሞግሰንን ብቻ የምንይዝበት መንገድ የለም ሚዲያ ሆነው ያለመረጃ የሚያወሩ በድፍረት የሚተቹ አሉ በስም ማጥፋት ህግ የያዘው ጉዳይም አለ” ሲሉ ተናግረዋል።
“እንደ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት አለን እኔም አለው ለመረጃ በራችን ክፍት ነው መደወል ይችሉ ነበር ነገር ግን የፈለጉትን አጀንዳ ለማስተላለፍ የዘገቡ አሉ ይሄ ትክክል አይደለም 8 ሰአት ተብሎ 10 የሆነው በቴክኒክ ችግር ነው ነገር ግን ይህን ክፍተት ተንተርሶ የማይሆን ዘገባዎች ወጥተዋል የተሳሳቱ መረጃዎች በሚዲያ አጀንዳ ሆነው ሶስት ቀን ሙሉ መወራቱ ገርሞናል ሙሉ መረጃው ግን ውሸት ነው” ያሉት አቶ ባህሩ ” የሆኑ ፕሮግራሞች ብሄራዊ ቡድኑን ለመሳደብ የተዘጋጁ ይመስላል ስብስባቸውም አሰልጣኙን ቡድኑን ፌዴሬሽኑን ለመተቸት የተዘጋጁ መሆኑን መቆም አለበት የሆነ ቴሌቪዥን ደግሞ ፌዴሬሽኑን ዋና ጸሃፊውን ሲተቹ ይታያል ማይክ ስለያዙ ብቻ ማውራት ልክ አይደለም ከመተቸት መነጋገር ቢቀድም የተሻለ ነው እናንተም የጋዜጠኝነት ስነምጎባር በጠበቀ መልኩ እንድትዘግቡ ጥሪ አቀርባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።የጊኒ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካባ ዲያዋራ ደግሞ “ኢትዮጵያን በደርሶ መልሱ ጨዋታ አሸንፈን ስድስት ነጥብ እንወስዳለን” ማለታቸው የተሰማ ሲሆን በቻን ውድድር ስላወቅናቸው ለነሱ በሚገባ ተዘጋጅተናል” ሲሉ ዝተዋል።
ዋሊያዎቹ የፊታችን ዓርብ ካዛብላንካ በሚገኘው የመሀመድ አምስተኛ ስታዲየም ከሶስት ቀናት በኋላ የዛሬ ሳምንት ሰኞ ራባት በሚገኘው ሙላይ አብዱላይ ስታዲየም ከጊኒ አቻቸው ጋር ላለባቸው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ ራባት ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።