ለ2023 የኮት ዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በደርሶ መልስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚገጥመው የጊኒ ብሐራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካባ ዲያዋራ በሞሮኮ የሚደረጉትን ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ሙሉ ስድስት ነጥብ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
ማርች 24 እና ማርች 27 በሞሮኮ ከተሞች የሚደረጉትን ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አስመልክተው ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ዲያዋራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በሚገባ እናውቀዋለን በምናውቃቸው መጠንም ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
አሰልጣኙ ተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድንን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ
« የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዘጠና በመቶ በላይ በሃገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ልጆች የተገነባ ብሔራዊ ቡድን ነው፤ የባለፈው የቻን ውድድር በደንብ እንድናያቸው ዕድል ፈጥሮልናል፣ ኳስ ይዘው መጫወት ይፈልጋሉ፣ ብዙ ይሮጣሉ፣ ሶስቱንም ጨዋታዎቻቸውን ተመልክተን ለነሱ የሚሆን ታክቲክ አዘጋጅተናል፤ ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፈን ስድስት ነጥብ ከኢትዮጵያ ላይ ወስደን ወደኮት ዲቯር እናቀናለን፡፡»
- ማሰታውቂያ -
የሁለቱ ሃገራት ጨዋታዎች በማርች 24 በካዛብላንካ መሃመድ አምስተኛ እንዲሁም የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ማርች 27 በራባት ከተማ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይደረጋሉ፡፡
ከሜዳቸው ውጪ መጫወታቸው በውጤቱ ላይ ልዩነት ይፈጥር እንደሆነ የተጠየቁት አሰልጣኙ ሲመልሱ
« ሞሮኮን የመረጡት ሁለቱም ፌዴሬሽኖች በስምምነት ነው፤ ወቅቱ የራማዳን ጾም ወቅት በመሆኑ ለኛም በመሃል ጉዞ ሳናደርግ መጫወታችን ይጠቅመናል የትራንስፖርት ወጪም ይቀንሳል፤ በርካታ ጊኔያውያን በሞሮኮ እንደሞኖራቸው በኛ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራል ብዬ አላስብም ዋናው ነገር በርካታ ጊኒያውያውያን በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን እንዲመለከቱ መጋበዙ ላይ ነው፡፡»